Thursday, September 21, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየፓርላማ አባላትን በቁጭት ያንገበገበው የኦሮሚያና የሶማሌ ግጭት ሪፖርት

የፓርላማ አባላትን በቁጭት ያንገበገበው የኦሮሚያና የሶማሌ ግጭት ሪፖርት

ቀን:

‹‹የደረሰብንን በደልና ግፍ ሳታሰሙ በሕዝብ ወንበር ላይ መቀመጥ ለምን ያስፈልጋል?››

ተፈናቃዮች

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኦሮሚያና የሶማሌ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎችን ግጭት እንዲያጣራ የተዋቀረው የሱፐርቪዥን ቡድን ሪፖርቱን ያቀረበው ሐሙስ ታኅሳስ 26 ቀን 2010 ዓ.ም. ነበር፡፡ በሁለቱ ክልሎች የተሰማራው የሱፐርቪዥን ቡድን በአካል ተገኝቶ እስከ ኅዳር 2010 ዓ.ም. ድረስ ከተፈናቃዮችና ከአካባቢ አመራሮች የሰበሰበውን መረጃ በዝርዝር አቅርቧል፡፡ ተፈናቃዮች በግጭቱ ወቅት በደረሱባቸው ጉዳትና እንግልት፣ የንብረት ዘረፋና የተለያዩ ጥቃቶች ለጤናና ለሥነ አዕምሮ ቀውስ መዳረጋቸው ተገልጿል፡፡ መንግሥት ግጭቱን ለማስቆም ካለመቻሉም በላይ ችግሩ ከተፈጠረ በኋላ ፈጥኖ ዕርምጃ ባለመወስዱ፣ እንዲሁም የመንግሥት አመራሮች ለግጭቱ መፍትሔ ባለመስጠታቸው ተስፋ መቁረጣቸው ተመልክቷል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትም ከሕገ መንግሥቱ በተፃራሪ ግፍና በደል ሲደርስ ድምፃቸውን ባለማሰማታቸው ተወቅሰዋል፡፡ ዝርዝር ሪፖርቱ ከቀረበ በኋላ የፓርላማ አባላት በቁጭት በመንገብገብ ጥያቄዎች አቅርበዋል፡፡ ለዚህ ሁሉ በደልና ግፍ ከፍተኛ አመራሮች ሳይቀሩ ተጠያቂ መሆን አለባቸው ያሉም አሉ፡፡ ደረሰ የተባለውን ግፍ በዝርዝር ለፓርላማው ማቅረብ አለማስፈለጉም ተገልጿል፡፡ በምሥሉ ላይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሪፖርቱ ሲቀርብ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ መሰንበቻውን በይፋ ሥራ የጀመሩት አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳና የሱፐርቪዥኑ አስተባባሪ አቶ ጫኔ ሽመካ ይታያሉ፡፡ 

ሐሙስ ታኅሳስ 26 ቀን 2010 ዓ.ም. በፓርላማ የተዋቀረው ሱፐርቪዥን ቡድን በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች በግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ነዋሪዎችን ሁኔታ፣ እንዲሁም በግጭቱ እንዴት እንደተፈናቀሉ በመስክ ተገኝቶ ከተፈናቃዮችና ከአካባቢ አመራሮች የሰበሰበውን መረጃ አሰባስቦ ሪፖርት አቅርቧል፡፡ በሪፖርቱ እስከ ኅዳር ወር 2010 ዓ.ም. ድረስ ብቻ የነበረውን ክስተት የቃኘ ሲሆን፣ የሱፐርቪዥን ቡድኑ ከአካባቢው ከወጣ በኋላ ውጥረት መንገሡን አረጋግጦ የነበረ ቢሆንም፣ ነገር ግን በሪፖርቱ ዝርዝሩ አልተካተተም፡፡ የሱፐርቪዥኑ ሪፖርትና የፓርላማው ውይይት እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

በሁለት ወንድማማች ሕዝቦች መካከል በተወሰኑ አካባቢዎች በተፈጠረው ግጭት በተለያዩ ጊዜያት ዜጎች ቀዬአቸውን እየለቀቁ ተፈናቅለዋል፡፡ በ2009 ዓ.ም. ታኅሳስ ወር በባሌና ጉጂ ዞኖች ከሶማሌ ክልልና ከኦሮሚያ አዋሳኝ ቀበሌዎች ወደኋላ ያፈገፈጉ ወይም የተፈናቀሉ የኦሮሚያ ተወላጆች ነበሩ፡፡ ለእነዚህ ወገኖች መፍትሔ ሳይሰጥ መኖሪያ ቀዬአቸውን ለቀው በየመጠለያ ጣቢያ እያሉ፣ በተጨማሪ ደግሞ ሰፊ አካባቢን የሸፈነ በርካታ ቁጥር ያላቸው ወገኖች በ2009 ዓ.ም. ነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ መፈናቀላቸውን ይገልጻሉ፡፡

በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የኦሮሞ ተፈናቃዮች የመጡበት ወይም የነበሩበት ሁኔታ ሲታይ አንደኛ በሶማሌ ክልል ውስጥ ይኖሩ የነበሩ፣ ሁለተኛ በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ ቀበሌዎች ይኖሩ የነበሩ ግን በተፈጠረው ግጭት መኖሪያ ቀበሌያቸውን ለቀው ወደኋላ ያፈገፈጉ፣ ሦስተኛ ከሶማሌላንድ ተፈናቅለው የመጡ ናቸው፡፡ የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ተወላጆች ደግሞ ይኖሩበት ከነበረው ኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉ ናቸው፡፡

በተፈናቃዮች ውስጥ በተለያየ ሙያ ዘርፍ ተሰማርተው ይሠሩ የነበሩ ከተማ ነዋሪዎች፣ አርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደሮች ይገኛሉ፡፡ የከተማ ነዋሪዎችን በተመለከተ ትልልቅ የንግድ ሥራ ያከናውኑ የነበሩ የንግድ ድርጅት ባለቤቶች፣ አነስተኛ የንግድ ሥራና የጉልበት ሥራ የሚሠሩ ዜጎች፣ በመንግሥት ሥራ ተቀጥረው አገራቸውንና ሕዝባቸውን ሲያገለግሉ የነበሩ መምህራን፣ የሕግ ባለሙያዎች፣ የልማት ጣቢያ ሠራተኞችና የባንክ ሠራተኞች ይገኙበታል፡፡

በፓርላማ የተቋቋመው የሱፐርቪዥን ቡድን በተመለከታቸው መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ተፈናቃዮች መረጃ ያሰባሰበ ሲሆን፣ በአጠቃላይ የሱፐርቪዥን ቡድኑ ያልደረሰባቸውን አካባቢዎች ጨምሮ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በየመጠለያ ጣቢያዎች ይገኛሉ፡፡

ተፈናቃዮች በደረሰው ግጭት የደረሰባቸውን ጉዳት የገለጹበት ሁኔታ

በሁሉም መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ የኦሮሚያ ክልል ተፈናቃዮች ዘግናኝ የሆነ ጉዳትና እንግልት አድርሶ እንድንፈናቀል ያደረገንና በወገኖቻችን ላይ በደል የፈጸመው የሶማሌ ክልል ልዩ የፀጥታ ኃይል፣ የየአካባቢው ፖሊስና ሚሊሺያ ነው፡፡ አብረነው በሰላም እንኖር የነበረው የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ሕዝብ አይደለም በሚል በተመሳሳይ ሁኔታ ይገልጻሉ፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ይህንን ሕገወጥና ኢሕገ መንግሥት ድርጊት የመሩትን የፀጥታ አካላትንና የየአካባቢው አስተዳደር አካላትን በስም ጭምር በመጥራት የነበረውን ሁኔታ ይገልጻሉ፡፡

ዝርዝር የደረሰውን ጉዳት አስመልክተውም ባልጠበቅነውና ባላሰብነው ጊዜ ኦሮሞ በመሆናችን ብቻ እየተለየን አሰቃቂ የሆነ ግድያ ተፈጽሟል፡፡ በዚህም ቤተሰቦቻችንን ከሕፃን እስከ አዋቂ አጥተናል፡፡ በዚህ ዘመን ሊፈጸም የማይገባ ከፍተኛ የሆነ የአካል ጉዳት ደርሶብናል፡፡ በሴት እህቶቻችን ላይ ለመግለጽ የሚዘገንን ኢሰብዓዊ የሆነ የፆታ ጥቃት በማድረስ ለከፍተኛ የጤናና የሥነ አዕምሮ ቀውስ ተዳርገዋል በማለት ገልጸዋል፡፡ በቀጥታ ጉዳቱ የደረሰባቸው ወገኖችም ለሴት የሱፐርቪዥን ቡድን አባላት የደረሰባቸውን በደል ራሳቸው ገልጸውላቸዋል፡፡

በሰላም ስንኖር በነበርንበት በርካታ ዓመታት ያፈራነውን ሀብት ንብረት ምንም ነገር ሳንይዝ ባዶ እጃችንን ወጥተናል በማለት የተዘረፉትን ንብረት ይዘረዝራሉ፡፡ ትልልቅ የንግድ ድርጅት ቤቶች፣ መኖሪያ ቤቶች፣ ተሽከርካሪዎች፣ የቤት ቁሳቁስ፣ ጥሬ ገንዘብና አርብቶ አደር አካባቢ ደግሞ እንስሳት፣ እህልና የቤት ቁሳቁስ ጥለው እንደወጡና ለእንግልት እንደተዳረጉ ይገልጻሉ፡፡

አንድ ቤተሰብ ለሁለት የተለያዩበትና ባል ወይም ሚስት ተፈናቅሎ ወጥቶ አንደኛው የቀረበት፣ ልጆች የተለያዩበት፣ የተወሰኑት መጥተው የተወሰኑት የቀሩበት፣ አንዳንዶቹም ይኑሩ ወይም ይሙቱ የማይታወቁ ያሉበትና ቤተሰቦቻቸው ተገድለውባቸው በሥርዓት ዕርማቸውን ሳያወጡ ተደብቀው ቁጭ ያሉና እባካችሁ አውጡን እያሉ የሚደውሉላቸው የተጎጂ ቤተሰቦች እንዳሉም ተገልጿል፡፡

የመንግሥት ሠራተኛ ተፈናቃዮች በሚሰጣቸው የዕርዳታ እህል ቤተሰቦቻቸውን ለማኖር ጥረት እያደረጉ ቢሆንም፣ አገራችንንና ሕዝባችንን ለረዥም ዓመት አገልግለን ከቦታችን ተፈናቅለን ያለ ሥራና ደመወዝ ችግር ውስጥ በመውደቃችንና መፍትሔ ባለመሰጠቱ በእጅጉ አዝነናል ይላሉ፡፡

የደረሰውን በደል ከላይ በተገለጸው መንገድ ከገለጹ በኋላ የፌዴራል መንግሥት ጉዳዩን ተከታትሎ በአጭር ጊዜ መፍትሔ መስጠት ባለመቻሉ፣ ተስፋ በቆረጠ ስሜት በፌዴራል መንግሥት፣ በአስፈጻሚው፣ በፓርላማና በመከላከያ ኃይሉ ላይ የሚከተለውን አስተያየት ይሰጣሉ፡፡

በሰላም በምንኖር ሕዝቦች ላይ ዓይተነው የማናውቅ ግፍ ሲፈጸምብን መንግሥት ፈጥኖ ዕርምጃ መውሰድ ሲገባው ዝም ብሎ ተመልክቶናል፣ ዘግይቶም ቢሆን ያለንበትን ሁኔታ የተመለከቱ አመራሮች መፍትሔ አልሰጡንም፡፡ ይህ በመሆኑ በፌዴራል መንግሥት በእጅጉ አዝነናል፣ ተስፋም ቆርጠናል፡፡ የሌሎች አገሮች ሰላምን ለማስከበር የሚያደርገውን ጥረትና በተለያዩ ጉዳዮች በእኛ ዜጎች ላይ የሚደርስን ጉዳት አስከትሎ የሚሰጠውን የሐዘን መግለጫ በእኛ ላይ በደረሰ ጉዳት ሲያደርገው አልተመለከትንም፡፡ በኢትዮ ቴሌኮም ዕርዳታ ለማሰባሰብ የተጀመረው እንቅስቃሴ እንዲቆም የተደረገበትን ምክንያትም አላወቅነውም፣ መቆምም አልነበረበትም፡፡ በአጠቃላይ መንግሥት ችግራችንን በአግባቡ ተረድቶ ፈጥኖ ምላሽ አልሰጠንም ማለታቸው ተገልጿል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትም ሕገ መንግሥቱን በመፃረር በደልና ግፍ ሲደርስብን ድምፃችሁን አላሰማችሁም፣ ይህን የምታደርጉ ከሆነ ሕዝብ በሰጣችሁ ወንበር ላይ መቀመጥ ለምን ያስፈልጋል በማለት ተቋሙ ችግሩ መፍትሔ እንዲያገኝ ሥራውን ባለመሥራቱ የተሰማቸውን ቅሬታ በምሬት ይገልጻሉ፡፡

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊትን በተመለከተ አንዳንዶች በነበረው ሁኔታ መከላከያ ኃይል ባይደርስ ኖሮ የመውጣት ዕድል ሳናገኝ ይጨርሱን ነበር፡፡ የተረፍነው በመከላከያ ሠራዊት ብርታት ነው ብለው ይገልጻሉ፡፡ የተወሰኑት ደግሞ የመከላከያ ሠራዊት ሰፊ ጉዳት እንዳይደርስ መከላከል እየቻለ ዝም ብሎ የተመለከተበት አካባቢ አለ፡፡ ግጭቱን ባለበት ሁኔታ ማስቆም ሲገባም በራሱ መኪኖች እየጫነ ማውጣቱ ተመራጭ አልነበረም በማለት ይገልጻሉ፡፡ አርብቶ አደሩ አካባቢም በሁለቱ ወገኖች መሀል ላይ የሰፈረው መከላከያ ያመጣውን አንፃራዊ ሰላም ገልጸው፣ አልፎ አልፎ እንስሳት ሲወሰዱና የመተናኮስ ሙከራ ሊደረግ ሲል ፈጥነው ዕርምጃ አይወስዱም በማለት ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡

የሶማሌ ክልል ተፈናቃዮችም በተመሳሳይ እንዲፈናቀሉ ያደረጋቸውና በደሉን ያደረሰባቸውን አብረውት ይኖሩ የነበሩት የኦሮሞ ሕዝብ ሳይሆን በዋነኛነት የአካባቢው አመራሮች፣ የፀጥታ አካላትና የተወሰኑ ወጣቶች መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡ እነዚህ አካላት ወገኖቻችንን ገድለዋል፣ ሴት እህቶቻችንን ደፍረዋል፣ ሀብት ንብረታችንንም ዘርፈዋል ይላሉ፡፡ እነዚህን አካላት መንግሥት ለሕግ ሊያቀርባቸው ይገባል ሲሉም ይገልጻሉ፡፡ ለረዥም ጊዜ ከኖርንበት አካባቢ ተፈናቅለን በመጠለያ ካምፕ ከዚህ በላይ መቆየት ስለማንፈልግ ወደ ነበርንበት ቦታ መንግሥት ይመልሰን፡፡ ይህ የማይቻል ከሆነ ከዚህ ካምፕ ወጥተን ኑሯችንን እንድንመራ የተዘረፍነው ሀብትና ንብረታችን ተመልሶልን እንድንቋቋም ሊደረግ ይገባል ብለው አስተያየታቸውን ይሰጣሉ፡፡

በአጠቃላይ የሁለቱም ክልል ተፈናቃዮች ችግሩ ከመከሰቱ በፊት የሁለቱን ክልሎች ወሰን ሪፈረንደሙን ተከትሎ ማካለሉ ረዥም ጊዜ የወሰደ ቢሆንም፣ አለመቋጨቱንና ግጭቱ ከተፈጠረ በኋላም ፈጥኖ በአጥፊዎች ላይ ዕርምጃ ወስዶ ለተፈናቃዮች መፍትሔ ባለመስጠቱ በፌዴራል መንግሥት ላይ ያላቸው አመኔታ በእጅጉ እንደተሸረሸረ ይገልጻሉ፡፡

ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች (መጠለያ፣ ልብስና የምግብ ማብሰያ አቅርቦት)

የኦሮሚያ ክልል ተፈናቃዮች ባልጠበቁት ሁኔታና ጊዜ ለዘመናት ያፈሩትን ሀብትና ንብረት ጥለው ባዶ እጃቸውን ሲወጡ፣ በቅድሚያ በየደረሱበት አካባቢ የሚጠጉበት ቦታና ልብስ በመስጠት የደረሰላቸው የአካባቢው ሕዝብ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በመንግሥትና ረጂ ድርጅቶችም የዘገየና ለሁሉም ተፈናቃይ በበቂ ሁኔታ ባይደርስም መጠለያ፣ አልባሳትና የምግብ ማብሰያ ቁሳቁስ ለማቅረብ ጥረት መደረጉን ተፈናቃዮች ይገልጻሉ፡፡ በከተማ አካባቢ ተፈናቃዮች በአዳራሾችና በትምህርት ቤቶች በጋራ እንዲጠለሉ ሲደረግ፣ አርብቶ አደር አካባቢም አፈግፍገው በተቀመጡበት ቦታ የየራሳቸውን መጠለያ ቀልሰው ለማረፍ እንዲችሉ ፕላስቲክ ወይም ሸራ እንደተሰጣቸው ሪፖርት ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም ብርድ ልብስ፣ የሴቶች ልብስ፣ የምግብ ማብሰያ ብረት ድስት፣ የውኃ መቅጂያ ጀሪካንና አጎበር የተሰራጨባቸው ቦታዎችን መመልከቱን የሱፐርቪዥን ቡድኑ አስታውቋል፡፡

የሶማሌ ክልል ተፈናቃዮች በተመሳሳይ ሁኔታ ተፈናቅለው ወደ ክልላቸው ሲመለሱ፣ የአካባቢው ሕዝብና የክልሉ መንግሥት በጥሩ ሁኔታ እንደተቀበላቸውና ሴቶችና ሕፃናት ለብቻቸው የተለየ ቦታ እንደተሰጣቸው፣ በተጨማሪም ቤተሰቦቻቸውን በሞት ላጡ ወገኖች የፍርድ ቤት ማስረጃ እንዲያቀርቡ ተደርጎ ለ21 ሰዎች የመቋቋሚያ ገንዘብ መስጠቱ ተገልጿል፡፡

ከላይ የተገለጸው እንደተጠበቀ ሆኖ ከመጠለያና ከቁሳቁስ አቅርቦት ጋር ተያይዞ በርካታ ችግሮች ይነሳሉ፡፡ በአዳራሽና በትምህርት ቤቶች እንዲጠለሉ የተደረጉ የኦሮሚያ ተፈናቃዮች ቦታው ከተፈናቃዮች ቁጥር ጋር የማይጣጣም ከፍተኛ መጨናነቅና መተፋፈግ ያለበት ወንዶች፣ ነፍሰ ጡር እናቶች፣ ወላድ ሴቶችና ሕፃናት በአንድ ላይ ተፋፍገን የምንኖርበት በመሆኑ የጤና ችግር እያስከተለ ነው በማለት ፈጥነው የሚወጡበት ሁኔታ እንዲመቻችላቸው አጥብቀው ይጠይቃሉ፡፡ በተለይም የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ተፈናቃዮች በችግራችን ላይ ሌላ ችግር እየጨመርን ነው በማለት በምሬት ይገልጻሉ፡፡ ዘመዶቻቸው ወደየአሉበት አካባቢ እንዲሄዱ የተደረጉ ተፈናቃዮች ደግሞ በየከተማው ተበታትነው የሚኖሩ በመሆኑ ምቹ ባልሆነ ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ፣ አንዳንዶች በረንዳና ፖሊስ ጣቢያ አካባቢ ተጠግተው እንዳሉ መገለጹ ተመልክቷል፡፡ እነዚህ ተፈናቃዮች መፍትሔ እስኪያገኙ ድረስ ሳይበተኑ አንድ አካባቢ እንዲሰፍሩ ቦታ ይሰጠን የሚል ጥያቄ አላቸው፡፡

አርብቶ አደር ተፈናቃዮች አፈግፍገው በሰፈሩበት አካባቢ መጠለያ ቀልሰው ለመኖር እየሞከሩ ሲሆን ፕላስቲክ፣ ሸራ፣ ብርድ ልብስና ቁሳቁስ እንዳልደረሳቸው የሚገልጹ አሉ፡፡ የሠሩት መጠለያም በተለይ በ2009 ዓ.ም. ታኅሳስ ወር የተፈናቀሉ ፀሐይና ዝናብ ሲፈራረቅበት ተቀዳዶ እንደ አዲስ ጥያቄ እያቀረቡ መሆኑን ተመልክቷል፡፡ በአጠቃላይ በሁሉም አካባቢዎች ከተፈናቃዮች ቁጥር መብዛትና መረጃው ከተሰበሰበ በኋላ ዘግይተው የሚንቀሳቀሱ በመኖራቸው ምክያት የመጠለያ፣ የአልባሳትና የቁሳቁስ አገልግሎት አላገኘንም የሚለው ሰው ቁጥር ቀላል አለመሆኑም ተገልጿል፡፡

የምግብ እህልና የአልሚ ምግብ አቅርቦት

በሁሉም ቦታዎች የሱፐርቪዥን ቡድኑ ያነጋገራቸው የኦሮሚያ ክልል ተፈናቃዮች ቀድሞ የደረሰላቸውን የአካባቢያቸውን ሕዝብ የበሰለ ምግብና የሚጠጣ ውኃ በማቅረብ፣ መንግሥትና ሌላው አካል እስኪደርስልን ድረስ ሕይወታችንን ታድጓል በማለት ከከፍተኛ ምሥጋና ጋር የተደረገላቸውን ነገር ይገልጻሉ፡፡ አንዳንድ የአካባቢው አስተዳደር አካላትም የወረዳቸውን ሕዝብና ከጎረቤት ወረዳም ጭምር በማስተባበር እህል አሰባስበው ለማሰራጨት ጥረት ማድረጋቸው ተጠቁሟል፡፡

በመቀጠልም መንግሥትና ረጂ ድርጅቶች በቆሎ፣ ስንዴ፣ ሩዝና ዱቄት በተፈናቃዮች የቤተሰብ ብዛት መጠን እያከፋፈሉ ይገኛሉ፡፡ አልሚ ምግብ ለእናቶችና ሕፃናት፣ እንዲሁም የምግብ ማጣፈጫ ሥርጭቱ ሁሉንም ያዳረሰ ባይሆንም ለማቅረብ ተሞክሯል፡፡ ከተለያዩ አካላት በዕርዳታ የተለገሰ ገንዘብንም ለተፈናቃዮች ለማከፋፈል የተሞከረባቸውን ዞኖች ለመመልከት መቻሉ ተገልጿል፡፡ በከተማ አካባቢ አንድ ላይ በሰፈሩባቸው መጠለያ ቦታዎች ጥሬ የምግብ እህል ከማከፋፈል ይልቅ፣ በተሻለ ሁኔታ ምግብ በጋራ አንድ ቦታ ላይ እንዲበስል በማድረግ ለማከፋፈል ጥረት መደረጉ ተጠቁሟል፡፡

የሶማሌ ክልል ተፈናቃዮች ያሉባቸው መጠለያ ጣቢያዎች ላይ ተፈናቃዮች በምግብ አቅርቦቱና አጠቃላይ አያያዛቸው ብዙ ችግር እንደሌለባቸው፣ ለሕፃናትና ለወለዱ እናቶች አልሚ ምግብ እንደሚቀርብላቸውና ምግብ አንድ ቦታ ተዘጋጅቶ እንደሚቀርብላቸው በምሥጋና አስተያየታቸውን የሰጡ መኖራቸውም ተገልጿል፡፡

ከላይ የተገለጹ ጥንካሬዎች ያሉ ቢሆንም ተፈናቃዮች ከምግብ አቅርቦት ጋር ተያይዞ እንዲስተካከሉ የሚያነሷቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ በመንግሥት በኩል የቀረበው ዕርዳታ ከተፈናቀሉ ከ45 ቀናት በኋላ የመጣና የዘገየ መሆኑን፣ አንዳንድ ቦታዎች ላይም በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ዕርዳታውን በጊዜው ለማድረስ ባለመቻሉ የኦሮሚያ ተፈናቃዮች ባሌ ዞን ጉራዳ ሞሌ ወረዳ ሁከልቱና ሀብሮና ቀበሌዎች፣ ቦረና ዞን አሬሮ ወረዳ ካራ ጉማታ ቀበሌ፣ የሶማሌ ክልል ተፈናቃዮች ደግሞ ዳዋ ዞን ሞያሌ ወረዳ ውስጥ በተገቢው መንገድ ዕርዳታውን እያገኙ አለመሆናቸውን መረዳቱን ቡድኑ አመልክቷል፡፡

የዕርዳታ እህሉ እየደረሰ ባለበት አካባቢም ዕርዳታው የሚራገፍበት ቦታና ተፈናቃዩ ያለበት ቦታ ርቀት ያለውና ሄዶ ለመረከብ እስከ 40 ኪሎ ሜትር ድረስ ለመጓዝ እንደሚገደዱና እንደተቸገሩ ተገልጿል፡፡ የባሌና የቦረና ዞን ቆላማ አካባቢዎች ላለፉት ተከታታይ ሦስት ዓመታት የዝናብ እጥረት ወይም ድርቅ ተከስቶ በዕርዳታ ላይ የነበሩ አካባቢዎች ሲሆኑ፣ ግጭቱ ተጨምሮበት ከፍተኛ የምግብ እህል እጥረት ያለበት አካባቢ ነው፡፡ ይህ ባለበት ሁኔታ ሁለኛው ዙር ዕርዳታ በእህል መሆን ሲገባው በገንዘብ መላኩ በአካባቢው ችግሩን ሊያባብስና ተፈናቃዩ በቀላሉ እህል ገዝቶ መጠቀም ስለማይችል ገንዘቡ ቀርቶ እህል እንዲቀርብላቸው ይጠይቃሉ፡፡

በመጠለያ ጣቢያው ውስጥ ለወለዱ እናቶች፣ ሕፃናትና ነፍሰ ጡር እናቶች የአልሚ ምግብ አቅርቦት በቂ አለመሆኑንና በአንዳንድ መጠለያ ጣቢያዎች የሌለ መሆኑ ተገልጿል፡፡ በተለይም የወለዱ እናቶች ጡታቸው ባዶ ሆኖ ሕፃናትን ማጥባት እንደተቸገሩ በምሬት ያወሳሉ፡፡ የሱፐርቪዥን ቡድን አባላትም ይህን መመልከታቸውን አረጋግጠዋል፡፡ እየቀረበ ያለው እህል ያለማጣፈጫ የሚሰጣቸው መሆኑና ለማስፈጨትም ባለመቻላቸው ብዙውን ቀቅለው በንፍሮ መልክ እየተመገቡ እንደሆነም በመግለጽ፣ የማጣፈጫና አልሚ ምግብ እንዲቀርብላቸው ይጠይቃሉ፡፡ ምግብ በጋራ ለማብሰል፣ ለተፈናቃዩ የሚቀርብበት ቦታ ድጋፍ ጥረቱ ጥሩ ሆኖ አልፎ አልፎ የበሰለው ምግብ ለሁሉም ሳይደርስ አለቀ የሚባልበት ጊዜ እንዳለና እንደሚቸገሩ የገለጹ ተፈናቃዮችም አሉ፡፡ የሶማሌ ክልል ተፈናቃዮች ከላይ በተገለጸው መንገድ የተሻለ አያያዝና አቅርቦት ያለ ቢሆንም፣ የእናቶችና የሕፃናት የአልሚ ምግብ አቅርቦት እጥረት እንዳለ ገልጸዋል፡፡

የንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት

የኦሮሚያ ተፈናቃዮች የቅርብ ዘመዶቻቸው ባሉበት አካባቢ ሄደው እዚያው ድጋፍ እንዲደረግላቸው በመደረጉና የሚኖሩት ከኅብረተሰቡ ጋር ተቀላቅለው በመሆኑ፣ ኅብረተሰቡ ከሚጠቀመው ውኃ ይጠቀማሉ፡፡ በአንድ ላይ የሰፈሩት ደግሞ የውኃ ቦቴ ተሽከርካዎችን በመጠቀም ውኃ በታንከሮች እየተሰባሰበ ይሠራጫል፡፡ አርብቶ አደር ተፈናቃይ ባለበት አካባቢ ደግሞ ከዝናብ የሚገኘውን ኩሬ ውኃ ሲጠቀሙ ታይቷል፡፡ አንዳንድ የአርብቶ አደር መጠለያ ጣቢያዎች ላይም የውኃ ቦቴ ተሽከርካሪዎችን በመጠቀም ውኃ ለማድረስ ጥረት ተደርጓል፡፡ በተመሳሳይ የሶማሌ ክልል ተፈናቃዮች ከተማ ያሉት ኅብረተሰቡ ከሚጠቀመው ውኃ የሚጠቀሙ ሲሆን፣ በአንድ መጠለያ ለሰፈሩት ደግሞ በውኃ ማመላለሻ መኪኖች ውኃ እየቀረበ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ይህ ጥረት እንደተጠበቀ ሆኖ ከምግብ አቅርቦት ጋር ተያይዞ እንደተገለጸው በኦሮሚያ ክልል ቆላማ አካባቢዎች መጀመርያም ከፍተኛ የውኃ እጥረት የነበረና ላለፉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት ድርቅ የነበረ መሆኑ፣ የውኃ እጥረቱ እጅግ ከፍተኛና አሳሳቢ መሆኑ ተመልክቷል፡፡ የዝናብ ውኃውን በኩሬ በማጠራቀም ለመጠቀም የሚሞክሩ አካባቢዎችም ይህን ውኃ የሚያገኙት በጣም ረዥም ርቀት ተጉዘውና የኩሬውን ውኃ በውኃ አጋር ወይም በሌላ ኬሚካል ሳይታከም የሚጠቀሙ በመሆኑ፣ ለጤና ችግር የተጋለጡ መሆናቸው ሪፖርት ተደርጓል፡፡ ከችግሩ ስፋት ጋር የሚመጣጠን የውኃ ማመላለሻ ቦቴ መኪኖች አቅርቦት እጥረት ያለበትና ለሚሠሩ መኪኖች የሥራ ማስኬጃ ገንዘብና የጥገና አገልግሎት ችግር እንዳለም የየአካባቢው አስተዳደር አካላት ገልጸዋል፡፡

የሶማሌ ክልል ተፈናቃዮች በዳዋ ዞን ሞያሌ ከተማ ከኦሮሚያ ነዋሪዎች ጋር በጋራ እንጠቀምበት የነበረ የውኃ መስመር ስለተቆረጠብን ከሁለት ወራት በላይ ችግር ላይ ወድቀናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ለውኃ ቦቴ ተሽከርካሪዎች በተመሳሳይ የሥራ ማስኬጃ ገንዘብ ችግር እንዳለ የኢትዮጵያ ሶማሌ አካባቢ አስተዳደር አካላት ገልጸዋል፡፡

የጤና አገልግሎት

የኦሮሚያ ክልል ተፈናቃዮች ባሉባቸው መጠለያ ጣቢያዎች በተወሰኑት ብቻ ጊዜያዊ የጤና ተቋም ወይም ማዕከል በመክፈት ሙያተኛና መድኃኒት በማቅረብ የጤና አገልግሎት ለመስጠት ጥረት ተደርጓል፡፡ ሌሎች ደግሞ በአቅራቢያቸው በሚገኝ ጤና ተቋም እየሄዱ አገልግሎቱን እንዲያኙ ሲያደርጉ ተመላላሽ ሙያተኛ በመመደብም የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት ጥረት ተደርጓል፡፡ በጡሎና ሚኤሶ ጣቢያ ከፍተኛ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ተፈናቃዮች በአቅራቢያው ባለ ሆስፒታል የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል ተብሏል፡፡ ተላላፊ በሽታዎች በወረርሽኝ መልክ እንዳይከሰቱ የአጎበር ዕደላና እንደ አተት ላሉ ተላላፊ በሽታዎች ደግሞ መጠባበቂያ መድኃኒት በዞን ደረጃ ለመያዝ ጥረት አድርገዋል፡፡ የንፅህና መጠበቂያ ሳሙናና ሌሎች ቁሳቁሶችም በተወሰኑ ጣቢያዎች እንደተሠራጨ ለማረጋገጥ መቻሉ ተገልጿል፡፡ ይህ በመሆኑ አልፎ አልፎ አንዳንድ ምልክቶች የታዩ ቢሆንም በወረርሽኝ መልክ የተከሰተ የጤና ችግር የለም ተብሏል፡፡

የሶማሌ ክልል ተፈናቃዮች የግልና የአካባቢያቸው ንፅህና እንዲጠበቁ የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች የቀረቡላቸው መሆኑንና መፀዳጃ ቤቶችም ምቹ መሆናቸውን ተፈናቃዮች ይገልጻሉ፡፡ በመጠለያ ጣቢያዎች አካባቢም የጤና ተቋም ወይም ማዕከል ተከፍቶ የባለሙያና የመድኃኒት አቅርቦትም መኖሩን የሱፐርቪዥን ቡድኑ አረጋግጧል፡፡

ከላይ የተገለጸው የጤና እንክብካቤና አገልግሎት እንደተጠበቀ ሆኖ ከመጠለያው ምቹ አለመሆኑንና ተፋፍገው የሚኖሩ በመሆኑ፣ በኦሮሚያ ተፈናቃዮች በኩል በአብዛኛው መጠለያ ጊዜያዊ የጤና ተቋም ወይም ማዕከል ባለመከፈቱ አገልግሎቱን እያገኙ አለመሆኑንና የመድኃኒት አቅርቦት ችግርም የጎላ መሆኑ ተገልጿል፡፡ በአቅራቢያ ካለ ጤና ተቋም ሄዶ ለመረዳትም በበጀትና ባለሙያ እጥረት የነፃ ሕክምና አገልግሎቱን ለሁሉም ተፈናቃዮች መሰጠት እንዳልቻሉ የሚገልጹ የአካባቢ አስተዳደር አካላትም አሉ፡፡

በአዳራሾችና ትምህርት ቤቶች የተጠለሉ ተፈናቃዮች በከፍተኛ መተፋፈግ የሚኖሩ በመሆኑ፣ ከፍተኛ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ለተጨማሪ የጤና ችግር የተጋለጡና የተቸገሩ መሆኑ ሪፖርት ቀርቧል፡፡ መፀዳጃ ቤቶች በጋራ የሚጠቀሙበት አካባቢ ሞልተው ለመጠቀም የማያስችሉና ለጤና ችግርም መንስዔ እየሆኑ ሲሆን፣ በብዙ አካባቢዎች ደግሞ የጋራ መፀዳጃ ቤት እንዲያዘጋጁ ስላልተደረገ በአካባቢው በሽታ በወረርሽኝ መልክ ሊከሰት ይችላል የሚል ሥጋት አለ፡፡ በተጨማሪም የሴቶች የግል ንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ያላገኙ በርካታ ተፈናቃዮች መኖራቸውን፣ በፀጥታ ችግር ምክንያትም የአምቡላንስ አገልግሎት ከምሽቱ 12 ሰዓት በኋላ የማይሰጥበት አካባቢ በተለይም ወላዶች የሕክምና አገልግሎት ሳያገኙ ባልተመቻቸ ሁኔታ እንደሚገላገሉ ለመረዳት መቻሉ ተገልጿል፡፡

የትምህርት አገልግሎት

የኦሮሚያ ክልል ተፈናቃዮች በተጠለሉበት አካባቢ ባለው መደበኛ ትምህርት ቤት ልጆቻቸውን በመላክ ለማስተማር ጥረት ያደረጉበት አካባቢ መኖሩ ተመልክቷል፡፡ የአካባቢው አስተዳደር አካላትና ረጂ ድርጅቶች ለተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ በማቅረብ ድጋፍ ለማድረግ ሙከራ ማድረጋቸው ተጠቁሟል፡፡ ጉጂ ዞን በተፈጠረው ችግር ተቋማቸውን ዘግተው ከተፈናቃዩ ጋር ወደ ኋላ ላፈገፈጉ መምህራንና ለሌሎችም ተፈናቃዮች ጊዜያዊ ምደባ ሰጥቶ ሥራ ላይ እንዲሰማሩ መደረጉ ተገልጿል፡፡ ድሬዳዋ መጠለያ ጣቢያ ከቤተሰቦቻቸው ጋር አብረው የተፈናቀሉ የኦሮሚያ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ወደ ተመደቡበት ዩኒቨርሲቲ እንዲሄዱ የገንዘብ ድጋፍ እንደተደረገላቸውም ተወስቷል፡፡

የሶማሌ ክልል ተፈናቃዮች ጅግጅጋ ማኔጅመንት መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ትምህርታቸውን ላቋረጡ ሕፃናት የክልሉ ትምህርት ቢሮ ዩኒፎርምና ሌሎች የትምህርት ቁሳቁስስ በማሟላት፣ ትምህርታቸውን አቅራቢያ ባለ የትምህርት ተቋም እንዲጀምሩ መደረጉ ተገልጿል፡፡

ሆኖም በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አዋሳኝ አካባቢ የነበሩ ነዋሪዎች ተፈናቅለው ወደኋላ በማፈግፈጋቸው ቁጥራቸው ቀላል ያልሆኑ የትምህርት ተቋማት ተዘግተዋል፡፡ ይህ በመሆኑ በርካታ ሕፃናት ትምህርታቸውን አቋርጠው በአንዳንድ አካባቢ ሳተላይት የትምህርት ጣቢያዎችን በመክፈት በበጎ ፈቃድ የአሥረኛ ክፍል የጨረሱ ተማሪዎች ለማስተማር ቢሞከርም፣ ልጆቹ ሥራ ፈላጊና ማስታወቂያ ሲወጣ የሚንቀሳቀሱ በመሆናቸው ሙከራው ውጤታማ አልሆነም ተብሏል፡፡ በአቅራቢያው ወዳለ ተቋም የማይሄደው ተማሪ ቁጥርም ከፍተኛ ነው፡፡ በቦረና ዞን ሞያሌ ከተማ ባለው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በተፈጠረው የፀጥታ ችግርና ውጥረት፣ ቡድኑ በተሰማራበት ጊዜ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ተማሪዎች 40 በመቶ ያህል ብቻ ነበሩ፡፡ በአጠቃላይ በትምህርት ሥራው ላይ  ግጭቱ ትልቅ ተፅዕኖ አሳድሯል ተብሏል፡፡

የተፈናቃይ እንስሳት ያሉበት ሁኔታ

በግጭቱ ወቅት እንስሶቻቸውን ይዘው ለመውጣት ዕድል ያገኙ የኦሮሚያ ክልል ተፈናቃይ አርብቶ አደሮች ወቅቱ የዝናብ በመሆኑ፣ በግጦሽና በውኃ በኩል እስካሁን ሰፊ ችግር እንዳልደረሰባቸው ይገልጻሉ፡፡ ከእንስሳት ጤና አኳያም መሠረታዊ የሆነ የእንስሳት በሽታ አለመከሰቱ ተገልጿል፡፡ ነገር ግን ብዙ ተፈናቃዮች በርካታ እንስሶቻቸውን ማለትም የቀንድ ከብት፣ ፍየል፣ ግመልና አህዮችን ጥለው እንደወጡና አሁን በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ እንደማያውቁ ወይም እንደተዘረፉ ይገልጻሉ፡፡ እንስሳትን ይዘው የወጡት ደግሞ የሰፈሩበት አካባቢ ጫካና ከቅርብ ርቀት የሶማሌ ክልል ታጣቂዎችና ነዋሪዎች ስላሉ፣ እንስሳቱ ወደለመዱት የድሮ ቦታቸው ሲሄዱባቸው መመለስ እንደማይችሉ ከሞከሩም ለግጭት መንስዔ መሆኑን ያወሳሉ፡፡ አርብቶ አደሮች ሕይወታቸው ከእንስሶቻቸው ጋር የተቆራኘ በመሆኑ በተለይ ለልጆቻቸው ምግብ ለማቅረብ ከዚህ በፊት ከእንስሳቱ የሚያገኙትን ተዋጽኦ (ወተት) በማጣታቸው መቸገራቸውን እናቶች ይገልጻሉ፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ችግሩ የከፋ ባይሆንም የዝናብ ጊዜው ካለፈ እንስሳቱም ለከፋ የውኃና የግጦሽ ችግር የሚጋለጡባቸው መሆኑን በውይይት ወቅት መረዳት መቻሉ ተገልጿል፡፡

የሶማሌ ክልል ተፈናቃይ አርብቶ አደሮችም እንስሶቻቸውን እንደተዘረፉና ላልተወሰዱባቸው እንስሳት ደግሞ በቂ የሆነ የውኃ፣ የመኖና የጤና አገልግሎት እንደሌለ ይገልጻሉ፡፡

የተፈናቃዮች መጠለያ ቦታና የአካባቢው የፀጥታ ሁኔታ

በሁለቱም ክልሎች ግጭቱ በተከሰተባቸው አዋሳኝ ቦታዎች ላይ ተጨማሪ ግጭት እንዳይፈጠር መንግሥት በሰጠው ትዕዛዝ መሠረት፣ የመከላከያ ሠራዊት አልፎ አልፎ መሀል ላይ እንዲሰፍርና ቁጥጥር እንዲያደርግ በመደረጉ አንፃራዊ ፀጥታ እንዲሰፍን አስተዋጽኣ ያደረገ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ተፈናቃዮች ያለቡትን መጠለያ ቦታ ፀጥታ ለማስከበር በራሳቸውና በአካባቢው ያሉ የፀጥታ ኃይሎች አማካይነት ቁጥጥር ለማድረግም ጥረት እንደሚያደርጉ ይገልጻሉ፡፡ በኦሮሚያና በሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች ዳግመኛ ግጭት ሊፈጥር የሚችል የፀጥታ ሥጋትና ውጥረት መኖሩ ተጠቁሟል፡፡

ሆኖም ችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ባለማግኘቱና በሁለቱም በኩል ተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ቁጭ ብለው የሕዝብና የመንግሥት እጅ የሚጠባበቁበት ሁኔታ ከመፈጠሩ ጋር ተያይዞ፣ በአካባቢው ከፍተኛ የፀጥታ ሥጋትና ቀጣይ ቀውስ ሊፈጠር ይችላል በሚል ስሜት ከፍተኛ ውጥረት ይታያል ተብሏል፡፡

አሁንም እንስሳትን ጠፍተተው ሲሄዱ መመለስ አንችልም፣ ስንሞክርም ለግጭት መንስዔ ይሆናሉ፣ በዚህ ምክንያትም አንዳንድ ቦታዎች ላይ የሰው ሕይወት እንደ ጠፋ፣ እንስሳት እስከ ጠባቂዎቻቸው ተወስደው ጠባቂዎች ከሁለትና ከሦስት ቀናት በኋላ እንደሚለቀቁ ይገልጻሉ፡፡ ምንም እንኳ የሁለቱም ክልል ታጣቂዎች ከሚዋሰኑት ቦት ሊቀመጡበት የሚገባበት ርቀት በመንግሥት የተወሰነ ቢሆንም፣ የሚዋሰኑት መሬት ሰፊ በመሆኑና ሁሉንም በመከላከያ ሠራዊት መሸፈን ስለማይቻል የሶማሌ ክልል ታጣቂዎች ገብተው ያጠቁናል በሚል ሥጋት መጠለያ ጣቢያቸውን ለቀው ጫካ ውስጥ እንደሚያድሩ እናቶች ይገልጻሉ፡፡

በአጠቃላይ የፀጥታ ሁኔታው እጅግ አሥጊ፣ ውጥረቱ በከፍተኛ ሁኔታ የነገሠበትና የሱፐርቪዥን ቡድኑ ሥራ ላይ ባለበት ጊዜም ሆነ ከወጣ በኋላ ግጭቶች እየተከሰቱ በሁለቱም ወገን የዜጎቻችን ሕይወት እየጠፋ፣ ሌላው ሰውም ከዛሬ ነገ ምን ሊፈጠር ይችላል በሚል ሥጋትና ውጥረት ውስጥ እንደሚገኝ ተፈናቃዮችም ሆነ የአካባቢው አስተዳደር አካላት ገልጸዋል፡፡

ማጠቃለያ

ለዘመናት ተከባብሮ፣ ተፋቅሮ ተዛምዶና ተዋልዶ በኖረው በሁለቱ አጎራባች ሕዝብ መካከል በተፈጠረው ግጭት በበርካታ ዜጎች ላይ የሕይወት፣ የአካል መጉደልና የንብረት መውደም ደርሷል፡፡ ይህ ግጭት መነሻው በሕዝቦች መካከል የተፈጠረ አለመሆኑን ከተፈናቀለው ሕዝብ በሚሰጥ አስተያየት መረዳት ተችሏል፡፡ ጉዳቱ እንዳይሰፋ የተከላከሉ፣ በመፈናቀል ላይም አብሮነትን የመረጡና አንድ ላይ ቀዬአቸውን ለቀው የወጡ የተለያዩ የብሔር ጥንዶች እንዳሉ ተረጋግጧል፡፡ ስለዚህ መንስዔው የኪራይ ሰብሳቢው (ጥገኛው) ፍላጎት፣ ሕዝቡን ሳይሆን መሬትን መሠረት ያደረገ ስግብግብ አጀንዳ መሆኑ አሻሚ አይደለም ተብሏል፡፡

ስለዚህ ፌዴራል መንግሥት በተደጋጋሚ እየሰጠ ባለው መግለጫ መሠረት አጥፊዎችን በቁጥጥር ሥር በማዋል በሕግ እንዲጠየቁና ዳግም ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር አስተማሪ ሕጋዊ ዕርምጃ ጊዜ ሳይሰጥ ሊወሰድ እንደሚገባ ተመልክቷል፡፡ የተፈናቀሉ ዜጎችም ወደ ቀዬአቸው ተመልሰው ከነበሩበት አካባቢ ኅብረተሰብ ጋር ዘላቂ ሰላምና እርቅ እንዲፈጥሩ የተጠናከረ የሰላም ኮንፈረንስ ማካሄድ ያስፈልጋል ተብሏል፡፡ በመጨረሻም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ በቀረበው ሪፖርት ላይ ውይይት አድርጎ ውሳኔ እንዲያስተላልፍ የሱፐርቪዥን ቡድኑ አስተያየቱን አቅርቧል፡፡

የሱፐርቪዥን ቡድኑ አስባባሪ አቶ ጫኔ ሽመካ ሪፖርቱን ካቀረቡ በኋላ የፓርላማ አባላት በቁጭት እየተንገበገቡ ጥያቄዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡ ጥያቄውን ካቀረቡት የምክር ቤት አባላት መካከል አቶ ተስፋዬ ሮቤላ አንዱ ሲሆኑ ‹‹ከአሥር ሺሕ በላይ በሞቱበትና ሰብዓዊ ኪሳራ በደረሰበት ግጭት የቀረበልን የዘገየ ሪፖርት ዕርዳታ ላይ ያተኮረ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ለግጭቱ ተጠያቂ ናቸው የተባሉት ኪራይ ሰብሳቢዎችና ኮንትሮባንዲስቶች ናቸው በመባሉ የተበሳጩ የሚመስሉት የፓርላማ አባሉ አቶ ተስፋዬ፣ ‹‹ኪራይ ሰብሳቢ ማነው? የታለ? ለምን አይያዝም? ወይስ ኪራይ ሰብሳቢ ማለት ጭራቅ ነው?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ታሪካዊ ግፍ እንደተፈጸመ የተናገሩት ደግሞ የሕወሓት ተወካይ የሆኑት ወ/ሮ ሙሉ ገብረ እግዚአብሔር ናቸው፡፡ ‹‹እነዚህን በደለኞች ሕዝብ ማወቅ አለበት፡፡ መጠየቅ አለባቸው፡፡ ከፍተኛ አመራሮችም ጭምር ሳይቀሩ መጠየቅ ስንችል ነው ደማቸውን መካስ የምንችለው፤›› ብለዋል፡፡

ሌላ የፓርላማ አባል (ኦሕዴድ) አቶ ሆርዶፋ በቀለ፣ ‹‹በዚህ ውይይት ብቻ የምናበቃ ከሆነ ምን ይዘን ነው ወደ ሕዝብ የምንወርደው? ዜጎች እንዴት ነው በመንግሥት ላይ እምነት ሊኖራቸው የሚችለው?›› ብለዋል፡፡ ‹‹ይህንን ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ማነው የሚያዘው? ለምንድነው የራሳችንን ሕዝብ መጠበቅ ያቃተን?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ወ/ሮ ሙንተሃ ኢብራሒም የተባሉ የምክር ቤት አባል በበኩላቸው እናቶች ተፈናቅለው ሜዳ ላይ እየወለዱ ሪፖርቱ ለቃላት ተጨንቋል ሲሉ ወቅሰዋል፡፡ ‹‹ዜጎቻችን ናቸው ዘግናኝ ችግር የደረሰባቸው፡፡ ከችግሩ ልንወጣ የምንፈልግ ከሆነ ለቃላት መጨነቅ የለብንም፤›› ሲሉ አሳስበዋል፡፡

ለቀረቡት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የሱፐርቪዥን ቡድኑ አስተባባሪ ምላሽ የሰጡ ሲሆን፣ ሪፖርቱ የዘገየው ምላሽ መስጠት የነበረባቸው የሥራ አስፈጻሚ አካላት በሥራ ምክንያት መገኘት ባለመቻላቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ሪፖርቱ ለምን ለቃላት ተጨነቀ የሚለውን በተመለከተ በሰጡት ምላሽም፣ ‹‹ያደመጥናቸውን ዘግናኝ ግፎች ሁሉ ለምክር ቤቱ ማቅረብ ተገቢ ነው ብለን አላመንበትም፤›› ብለዋል፡፡

በምክር ቤቱ ከተገኙት አመራሮች መካከል የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር አሰፋ በዩ በግጭት የተሳተፉ ተጠርጣሪዎችን ፖሊስ በቁጥጥር ሥር እየዋለ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ተጠያቂነትን በተመለከተ ምንም ድርድር አያስፈልግም፤›› ያሉት ኮሚሽነሩ፣ በእስካሁኑ ጥረት 98 ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን ተናግረዋል፡፡

እነዚህ ተጠርጣሪዎች በቀጥታ የወንጀል ድርጊት ላይ የተሳተፉ መሆናቸውን የጠቆሙት ኮሚሽነር አሰፋ፣ የፖለቲካ አመራሩን በተመለከተ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርት ከቀረበ በኋላ በመንግሥት የሚወሰን እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡

ሪፖርቱን ያዳመጠው ምክር ቤቱ ውይይት ካካሄደ በኋላ የውሳኔ ሐሳቦችን አስተላልፏል፡፡ መፈናቀሉ የጀመረው በታኅሳስ ወር 2009 ዓ.ም. ቢሆንም መፍትሔ ሳይሰጥ ችግሩ ችግር እየወለደ አሁን የደረሰበት ደረጃ መድረሱን፣ አሁንም ውጥረቱና ሥጋቱ ከፍተኛ በመሆኑ መንግሥት ለችግሩ እልባት መስጠትን ቀዳሚ ሥራ በማድረግ በየቀኑ የሚሰማውን ግጭትና የዜጎች ሕይወት መጥፋት ማስቆም አለበት ብሏል፡፡

አጥፊ የሆኑ በየትኛውም የአስተዳደር እርከን ላይ የሚገኙ አመራሮች፣ የፀጥታ ኃይሎችና ግለሰቦች ተለይተው በሕግ ሲጠየቁ ብቻ ነው ከዚህ ችግር መማር የሚቻለው ሲል ፓርላማው ወስኗል፡፡ አጥፊዎችን ለሕግ የማቅረብ ሥራ ጊዜ ሳይሰጠው መፈጸም እንዳለበትም ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...