Saturday, July 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

ፖለቲካውንም፣ ኢኮኖሚውንም፣ መዝናኛውንም፣ ምክሩንም፣ ‹‹ቫካንሲውንም›› አጣምሮ የሚያቃምሰኝን ሳምንታዊውን ሪፖርተር ጋዜጣ ሰኞ ከሰዓት በኃላ፣ አራት ኪሎ ፕሬስ ድርጅት ጎን ያለው የሕዝብ መናፈሻ ውስጥ የጀበና ቡናዬን ይዤ ካነበብኩና ከኮመኮምኩ በኋላ፣ በእግሬ በሺሕ ሰማንያ በኩል ወደ ቤቴ ማዝገም ልምዴ ነው፡፡ ታዲያ በአንዱ ቀን ታኅሳስ 09 ቀን 2010 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትራችን ሠፈራችንን ባፀዱልን ሳምንት መሆኑ ነው ቀስ እያልኩኝ ቀኜን ይዤ ስጓዝ፣ የግንፍሌን ድልድይ እንዳቋረጥኩ ‹‹ከርቩ›› ላይ በጋሪ የሚያስጎመጁ ሙዞችን የያዘ አንድ ወጣት ነጋዴ አጋጠመኝ፡፡ በጣም ከመጓጓቴ የተነሳ ጠጋ ብዬ ዋጋ ከተደራደርኩ በኃላ አንድ ኪሎ ተኩል ያህል ገዝቼ ግማሹን ኪሎ እዚያው በላሁና ልጣጩን በፌስታል ለነጋዴው መልሼ ሰጠሁ፡፡

ቀልጣፋው ወጣት በፌስታል ያቀበልኩትን የሙዝ ልጣጭ አጠገቡ በሚገኘው የመንገድ ላይ የብረት ጋርቤጅ ውስጥ ዓይኔ እያየ ሲከተው በማየቴ፣ በሥልጠኑ ወጣት ተደስቼ የቀረኝን አንድ ኪሎ ሙዝ ለልጆቼ አንጠልጥዬ ወደ ቤቴ ጉዞ ጀመርኩኝ፡፡ ጥቂት ሜትሮች እንደ ተጓዝኩ በርከት ያሉ ትራፊኮች ቆመው ከፍጥነት በላይ የሚያሽከረክሩ፣ ከልክ በላይ የጫኑ አሽከርካሪዎችን በማስቆም ታርጋቸውን እየፈቱ ወደ ቅጣት ሊያስላልፏቸው አየሁና ሕግና ሥርዓት በመከበሩ እሰየው በማለት ጉዞዬን ቀጠልኩ፡፡

መቼም እኔ በእግሬ መጓዝ ስለማበዛ ጫማ አይበረክትልኝም፡፡ ራስ አምባ ሆቴል ፊት ለፊት ስደርስ አንዲት ዲኤክስ ታክሲ ዳሯን ይዛ ቆማለች፡፡ በአጠገቧ እያለፍኩ ሳለሁ አንድ ነገር ቀልቤን ሳበው፡፡ በመኪናዋ ጎማ ሥር አስፋልቱ ላይ በርከት ያለ የጫት ገረባና የተጣሉ የወተት ፕላስቲኮች አየሁ፡፡ ገረመኝና ወረድ ብዬ የጥላ ዛፍ ሥር ቆሜ ወደ ታክሲዋ ውስጥ ሳማትር፣ አምስት ያህል ወጣቶች ከፊትና ከኋላዋ ተቀምጠው ይኼንን ጫት እያመነዠጉ ሲጫወቱ አስተዋልኩኝ፡፡ በርከት ያለ ጫትም የመኪናው መሪ አጠገብ ተከምሮ ይታየኛል፡፡

መኪናቸው ውስጥ ጫት መቃማቸው አልደነቀኝም፡፡ የገረመኝ ነገር ቢኖር ሁሉም ቃሚዎች የጫቱን ገረባ በመስኮት እዚያው መኪናዋ ጎማ ሥር ያለምንም ከልካይ ሲያራግፉት ማየቴ ነው ያሳዘነኝ፡፡ አጠገባቸው እኮ ጋርቤጅ ይታያል፡፡ እስቲ ምናለበት ሰብሰብ አድርገው እዚያው የእግረኛ መንገዶች ላይ ወደ ተደረደሩት ጋርቤጆች ጠጋ ብለው ቢወረውሩት? አይ የእኛ ነገር፡፡

አሁንም በአግራሞት መንገዴን ቀጥያለሁ፡፡ ቤልኤር መታጠፊያ ወደ አቧሬ የሚወስደው መንገድ ጋ ስደርስ ዓይኖቼ ሌሎች ወጣቶችን አየ፡፡ አንድ ከባድ መኪና አንገቱን አጎንብሶ በወጣቶቹ እየተጎረጎረ ይመስላል፡፡ ግማሾቹ (ሁለቱ) ቱታ ለብሰው መፍቻዎችን ይዘው ይታያሉ፡፡ ሁለቱ ቆም ብለው ያወራሉ፡፡ ታዲያ ይኼ ምን ያስገርማል ትሉኝ ይሆናል፡፡ ነገሩ ወዲህ ነው፡፡ አራቱም ወጣቶች አጠገባቸው አንድ የሽምብራ እሸት በባሬላ የሚያዞር ልጅ ቆሞ እሸጠላቸው ነው፡፡

ያንን የሽንብራ እሸት እየጠረጠሩና እየተጫወቱ ይበላሉ፡፡ ገለባውንም አስፋልቱ ላይ ይረጫሉ፣ ይበትናሉ፡፡ አጠገባቸው ያለው ጋርቤጅ ባዶውን አፉን ከፍቶ ከአሁን አሁን ቆሻሻውን ይወረውሩልኝ? ያጎርሱኝ ይሆን? እያለ በጉጉት የሚታዘባቸው ይመስላል፡፡ እነሱ ግን ‹‹ወይ ፍንክች ያባ ቢላዋ ልጅ››፡፡ ያንን በእናቶቻችንና በእህቶቻችን ተጠርጎ ፀድቶ የዋለውን አስፋልት እንደ ጉድ እያራገፉበት ነው፡፡ ወይ ጉድ አልኩኝ፡፡

በአንድ ወቅት የአዲስ አበባ ቀለበት መንገድ ይሠሩ የነበሩት ቻይናዎች መንገዱ ላይ ያስቀምጡት የነበረው ብረት እየተነቃቀለ በመወሰዱ፣ ‹‹እነዚህ ሰዎች (እኛን ማለታቸው ነው) ሌላ አገር አላቸው እንዴ?›› አሉ የተባለው ነገር ትዝ አለኝና አሁንም ቁልቁል ትዝብቴን እያማተርኩ ወደ አቧሬ መንገዴን ቀጠልኩ፡፡ ህንድ ኤምባሲ አካባቢን አለፍ እንዳልኩ ከአንድ የሕንፃ መሣሪያ መደብር አጠገብ ቆም አልኩኝና ሳስተውል፣ መንገዱ ላይ የተዘረገፉ በርካታ ቁርጥራጭ ካርቶኖች፣ ፌስታሎችና ወረቀቶች ተዝረክርከዋል፡፡ ያለጥርጥር ቆሻሻዎቹ ከመደብሩ እንደወጡ ያስታውቃል፡፡ ባለቤቶቹ ግን ምንም አልመሰላቸውም፡፡ ይገርማል፡፡ ቁልቁል አቧሬ አደባባይ ጋ ስደርስ መታጠፊያው ላይ አንድ ጋራዥና የመኪና መሸጫ ቤት አለ፡፡ አጥሩ ሥር ቁጭ ያሉ ሰዎች ይኼንን ሸንኮራ እየቀረደዱ፣ እየሸረከቱ የሸንኮራውን ጭማቂ ወደ ሆዳቸው እያስገቡ ገለባውን አስፋልቱ ላይ እንደ ሠርግ አበባ ይበትኑልኛል፡፡

ከዚህም ወይ ጉድ አልኩኝና የአቧሬ አደባባይን አልፌ የተደረደሩት የካዛንቺስ – አቧሬ ሚኒባስ ታክሲዎች አጠገብ ሳልፍ አንዱ ባለታክሲ ሚኒባሱ ላይ የሆነ  ማስታወቂያ በትልቁ ከኋላ ይለጥፋል፡፡ ከዚህ የማስታወቂያ ‹‹ስቲከር› ተልጦ የቀረውን አላስፈላጊ ወረቀት እዚያው አስፋልቱ ላይ እየጣለ ጨረቃ አስመስሎታል፡፡ ሌሎች ቆሻሻዎችም እንዲሁ በጎማዎቹ ሥር ይታያሉ፡፡ እነዚያን የማይፈለጉ ወረቀቶች ሰብሰብ አድርጎ ወደ ጋርቤጅ ወይም ወደ ጥግ ማድረግ ምን ይከብዳል?

ጠዋት እህቶቻችንና እናቶቻችን የሚጠርጉት አስፋልት የማን ነው? ዕውነት ሌላ አገር አለን እንዴ? ኧረ ጎበዝ እየተስተዋለ፡፡ በግዴለሽነትና በማናለብኝነት በየመንገዱ ላይ የምንበትነውን የቆሻሻ ክምር በተገቢው ቦታ እናስቀምጥ፡፡ ይህንን እየታዘብኩ ከየንግድ ቤቶች በዘፈቀደ ዝም ብለው አስፋልት ላይ የሚወረወሩትን ቆሻሻዎች እያስተዋልኩ እየረገጥኩ በሠፈራችን አቅራቢያ የሚገኘውንና ከሳምንት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መጥረጊያ ይዘው አስፋልቱን እየጠረጉ ፅዳት ያስተማሩበትን ቦታ ‹‹የኢትዮጵያ ሴቶች አደባባይን›› እየገረመምኩ፣ ወደ ግራ ታጥፌ ቁልቁል ወደ ዓደዋ ድልድይ ወደ ሠፈሬ ደረስኩ፡፡ በዚህ ልሰናበት፡፡ ሁሉም አካባቢውን ማፅዳት የሥልጣኔ ምልክት ነው ቢሉኝ፣ ሥልጡኖች ወዲያ ደናቁርት ወዲህ ታዩኝ!!! ስለዚህ ሁላችንም ኃላፊነትና ግዴታ አለብንና እንሠልጥን እባካችሁ!!!

(ተክልዬ ጀማነህ፣ ከአዲስ አበባ)            

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...