Wednesday, December 6, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክየመተማመኛ ድምፅ መስጠትና መንፈግ ሕጋዊነትን ለማስፈን

የመተማመኛ ድምፅ መስጠትና መንፈግ ሕጋዊነትን ለማስፈን

ቀን:

በውብሸት ሙላት

ገዥው ፓርቲ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከሁለት ሳምንታት በላይ የፈጀ ስብሰባ በማድረግ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ በዚህም መሠረት ፓርቲው ራሱ በተለይም ሥራ አስፈጻሚው የፈጸማቸውን ስህተቶች አምኖ ምን ማድረግ እንዳለበትም በተከታታይ በመግለጽ ላይ ይገኛል፡፡

ኢሕአዴግ ገዥ ፓርቲ ስለሆነ መንግሥትንም ይመራል፡፡ በድክመትና በችግር መልክ የተገለጹት አድራጎቶች በፓርቲው ውስጥ ታጥረው የቀሩ ሳይሆኑ በአጠቃላይ በአገሪቱና በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ላይ የተፈጸሙ መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ችግሮች በሚከሰቱበት ወቅት፣ ሕገ መንግሥቱና ሌሎች ሕግጋት ላይ የተቀመጡ የመፍትሔ ሐሳቦች ምን እንደሆኑ በመለየት ሊወሰድ ይገባ የነበሩትን ዕርምጃዎች እንመለከታለን፡፡

አስቀድመን ኢሕአዴግ ገዥ ፓርቲ የገለጻቸውን ችግሮች በሚከሰቱበት ወቅት ከሕግ አንፃር ምን መደረግ እንደሚገባው በአጭሩ ይቀርባል፡፡ በመቀጠልም ፓርቲው በራሱ እንደ ፈጸማቸው ያመናቸውን ስህተቶች የተወሰኑትን ተቀንጭበው ይቀርባሉ፡፡ በመቀጠል ገዥው ፓርቲ እንደ መንግሥት እንዲህ ዓይነት ስህተት ሲፈጽም በሕግ አውጭው አካል ያለው ሚና ምን እንደሆነ እንመለከታለን፡፡ የበለጠ ትኩረት የምንሰጠው ደግሞ የመተማመኛ ድምፅ መስጠት ወይም መንፈግን ነው፡፡ ቢያንስ ለወደፊቱ ትምህርት እንዲሆን በመመኘት፡፡

ፓርላሜንታዊ  አሠራርን በሚከተሉ አገሮች እንደሚደረገው ሁሉ በኢትዮጵም ቢሆን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡ ጥቅል መርሆችን ሥራ ላይ ለማዋል የሚረዱ ሕጎችን ያፀድቃሉ፡፡ ፖሊሲዎችን ያወጣሉ፡፡ በጀት ያፀድቃሉ፡፡ የሕግ አስፈጻሚውም ምክር ቤቱ ባወጣቸው ሕግጋትና ፖሊሲዎች መሠረት ሕገ መንግሥታዊ ግዴታውን እየተወጣ ስለመሆኑ ክትትልና ቁጥጥር ያደርጋሉ፡፡ በትክክል ስለመፈጸማቸው ክትትል ማድረግ የዘወትር ግዴታቸው ኃላፊነታቸውም ተግባራቸው ነው፡፡ ሕግ አስፈጻሚው በበኩሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚያወጣቸውን ሕግና ፖሊሲ መከተል አለበት፡፡

ሕግ አውጭው አስፈጻሚው ላይ ክትትልና ቁጥጥር የሚመነጨው ያወጣቸው ሕጎች ያፀደቃቸው ፖሊሲዎች በትክክል ሥራ ላይ መዋላቸውን ለማረጋገጥ ካለበት ኃላፊነት ነው፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት እንዲሾሙ ጥያቄ ቀርቦ ይሁንታ ሲቸራቸውና ቃለ መሐላ ሲያስገባቸው ታሳቢ የሚደረገው ባለሥልጣናቱ ሕግ አውጪው ባስቀመጠው የአሠራር ሥርዓት ያልሠራን ሚኒስትር ወይም የካቢኔ አባል የማባረር ሥልጣን ስላለው ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 55 ንዑስ ቁጥር 18 ላይ የተገለጸውም ይኼው ነው፡፡ ይህ ድንጋጌ እንደሚለው ፓርላማው ለአስፈጻሚው የተሰጠውን ሥልጣን በተመለከተ ተወያይቶ ተገቢ የመሰለውን ውሳኔ የማሳለፍ ሥልጣን አለው፡፡ ይህ አንቀጽ አስፈጻሚው ላይ የመተማመኛ ድምፅ እንዲሰጥ የሚቀርብን ጥያቄም ሊይዝ ይችላል፡፡

እንዲህ ዓይነት ሥልጣንን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መስጠቱ፣ የዴሞክራሲ ሥርዓትን የሚፈታተን ተግባር በዋናነት የሚመነጨው ከአስፈጻሚው በመሆኑና እሱን ለማረቅ ሲባል መሆኑ የታመነ ነው፡፡፡ ይህንን ባህሪውን በማረቅ ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የሚያስገድዱ ተቋማትን ማቋቋምና ሥርዓትን ማስፈን ደግሞ ከሕግ አውጭው የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡

ይሁን እንጂ የሕግ አውጭው ቁጥጥርን ውጤታማነት የሚገዳደሩ በርካታ ሁኔታዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡ ከእነዚህ ውስጥም የመጀመርያውና ዋነኛው የተጠናከረ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት መጥፋት ነው፡፡ በአጠቃላይ እንደ አገርም ሆነ በፓርላማው መድበለ ፓርቲያዊ ሥርዓት በመጥፋቱ ቁጥጥሩ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ ግልጽ ነው፡፡ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ውሳኔም ይኼንኑ ከግምት በማስገባት ይመስላል ስለ መድብለ ፓርቲ ሥርዓት አለመገንባትና የዴሞክራሲ ተቋማት የሚጠበቅባቸውን ተግባር እንዲወጡ አለመመቻቸቱን እንደችግር ዕውቅና የሰጠው፡፡

በሕገ መንግሥቱ ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው ፓርላማው በተለያዩ ዘዴዎች አስፈጻሚውን ሊቆጣጠር ይችላል፡፡ የፓርላማው በሚያቋቁማቸው ቋሚና ጊዜያዊ  ኮሚቴ አማካይነት ቁጥጥር ማድረግ አንዱ ነው፡፡ የተለያዩ ቋሚና ጊዜያዊ ኮሚቴዎችን በማቋቋም የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችንና የሌሎች ተቋማትን ሥራ በመከታተል፣ ሪፖርት እንዲያቀርቡ በማድረግና ዕርምጃ መውሰድ አንደኛው ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ፓርላማው እንደ ተቋም ጠቅላይ ሚኒስትሩንም ሆነ ሌላ ባለሥልጣንን በመጥራት ለምክር ቤቱ ሪፖርት እንዲያደርጉ፣ ማብራሪያ እንዲሰጥ ወዘተ. በማድረግ ነው፡፡ ይህ በመደበኛ የሪፖርት ወቅት ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ጊዜያትም በመጥራትም ይከናወናል፡፡ ሌላው የቁጥጥር ሥልት ደግሞ ተቆጣጣሪ ተቋማትን በማቋቋም አስፈጻሚውን በተጨማሪነት መቆጣጠርና መከታተል ነው፡፡ ለዚህ ተግባር እንዲያገለግሉ ሲባል ከሚቋቋሙት ውስጥ ለአብነት ኦዲተር ጄኔራል፣ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የእንባ ጠባቂና የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ተቋማትን ማንሳት ይቻላል፡፡ ለእነዚህ ተቋማት አፈጣጠር ምክንያቱ አስፈጻሚው አካል በሕገ መንግሥቱና በሌሎች ሕግጋት የተቀመጡለትን አሠራር ተክትሎ  ስለመሥራቱ በመቆጣጠር  ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ለማድረግ ሲባል ነው፡፡ ይሁን እንጂ፣ እነዚህ ተቋማት አገሪቱ አስቸጋሪ የመልካም አስተዳደርና ሌሎች ችግሮች ውስጥ በምትገኝበት ወቅት እንኳን  የተነሳውን ችግር ከመቅረፍ አኳ እምብዛም የጎላ ድርሻ ነበራቸው ማለት ያስቸግራል፡፡ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ መግለጫም የሚያረጋግጠው ይኼንኑ ነው፡፡ ከላይ የተገለጹት እንደተጠበቁ ሆነው የአስፈጻሚውን አሠራር የሚያርቁ፣ ሥልጣንና ኃላፊነታቸውን የሚገልጹና የሚገድቡ ሕጎችን ማውጣት ደግሞ ሌላው የመቆጣጠሪያ ሥልት ነው፡፡

እነዚህ የመቆጣጠሪያና የመከታተያ ዘዴዎች ቢኖሩም፣ ፓርላማው ከሕግ አስፈጻሚው የበላይ እንደሆነ ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 50(3) ላይ የተገለጸ ቢሆንም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩንና ሌሎች የካቢኔ አባላትን እየተቆጣጡ አገሪቱን ሉዓላዊነት የሕዝቡን አንድነት፣ ሰላምና ልማት፣ ዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብት ወዘተ. ማስጠበቅ እንዳለበት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ኃላፊነቱን ቢጥልበትም በተግባር ግን ሁሉ ነገር እየተፈጸመ ያለው ኢሕአዴግ እንደ ፓርቲ በሚወስዳቸው ዕርምጃዎች እንጂ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኩል አይደለም፡፡

ከመግለጫው የተጨረፉ የኢሕአዴግ ስህተቶች

ጠቅለል ተደርጎ ሲታይ፣ ሥራ አስፈጻሚው እንደገለጸውም ፓርቲው በፈጸማቸው ስህተቶችና ከታየው ዕድገት ጋር ተያይዘው በተከሰቱ አዳዲስ ለውጦችና ፍላጎቶች ምክንያት አገሪቱ በአሳሳቢ ወቅታዊ ችግሮች ውስጥ ገብታለች፡፡ የተለያዩ ስኬቶችን ቢያስመዘግብም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተከሰቱ ባሉ እንደ ሥራ አስፈጻሚው አገላለጽ ጊዜያዊ ቢሆኑም እንኳን ሁሉንም ማኅበረሰብ  ሥጋት ሆኗል፡፡

 

ከላይ በጥቅል አገላለጽ የተቀመጡት የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኑዛዜዎች የሚያሳዩት አስፈጻሚው አካል የተጣለበትን ሕገ መንግሥታዊም ሕጋዊ ኃላፊነት ከመወጣት አንፃር ችግር እንደነበረበት ነው፡፡ ይህ የፓርቲው የሥራ አስፈጻሚው ገለጻ በፓርቲው ላይ ተቀንብቦ የቀረበ ችግርን ሳይሆን የገለጸው እንደመንግሥት በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው የሕግ አስፈጻሚው አካል ያጋጠሙትን ችግሮችም የሚመለከት ነው፡፡ በመሆኑም በሕገ መንግሥቱ ላይ በሕግ አስፈጻሚው የተጣሉበትን ተግባርና ኃላፊነት በአግባቡ አለመወጣቱን ያሳያል፡፡

ሌላው የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ራሱ እንዳመነው በየደረጃው ባሉ የአመራር እርከኖች ሳይወሰን በከፍተኛው አመራር ደረጃም ጭምር የውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲ ዕጦት ሥር እየሰደደ መምጣቱን ያሳያል፡፡ እንደ ፓርቲ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 38 ላይ እንደተገለጸው ውስጣዊ ዴሞክራሲን ማክበር ይጠበቅበታል፡፡ እንደ መንግሥት ደግሞ ፓርቲው ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ማድረግ አለበት፡፡ ምክያቱም ሕገ መንግሥቱን የማክበርም የማስከበርም ግዴታ አለበትና ነው፡፡

ፓርቲው የልማታዊ መንግሥትን ባህሪያት በመላበስ በጠንካራ ዲስፒሊንና የሐሳብና የተግባር አንድነትን በማሰናሰል ለሕዝብ ቃል በገባው መሠረት መፈጸም ሲገባው በተቃራኒው ተገቢ ባልሆኑ ጥቅሞች ላይ የተመሠረቱ የቡድን ትስስሮች በመፈጠራቸው ልማታዊ መንግሥቱና ድርጅቱ ተልዕኳቸውን በብቃት አለመፈጸሙን አምኗል፡፡ በፖሊሲው መሠረት በትክክል ሥራውን መፈጸሙን ሊከታተልና ሊቆጣጠር ይገባው የነበረው አካል ባይቆጣጠረውም፣ ባለው ሥልጣን መሠረትም ዕርምጃ ባይወስድም ራሱ አስፈጻሚው ግን ድክመቱን ለሕዝብ ይፋ አድርጓል፡፡ ፓርላማው አስፈጻሚው አካል ይፋ ያደረጋቸውን ፖሊሲዎች ጠንቅቆ እየፈጸመ መሆኑን ግን መከታተል ነበረባቸው፡፡

ፓርቲው የራሱን የድርጅቱን እንዲሁም የመንግሥት ቋሚ መመርያዎች አክብሮ መፈጸም ሲገባው ባለመቻሉ በየቀኑ መሰጠት የነበረባቸውን ውሳኔዎች ሳይሰጡ በመቅረታቸው በበርካታ የመንግሥት ተቋማት ሕዝብ የሚጠብቃቸው አገልግሎቶች በተገቢው ሁኔታ መስጠት ሳይቻል መቅረቱን መግለጫው ያሳያል፡፡ ፓርላማውና ሌሎች ተቋማት እንዲህ ዓይነት ችግሮችን በማጥናት አስፈጻሚው ዕርምጃ እንዲወስድ ማድረግ ይጠበቅባቸው ነበር፡፡

ፓርላማውም ይሁን ሌሎች ተቋማት ከላይ ኢሕአዴግ ያመናቸውን ችግሮች በመንቀስ ቁጥጥርና ክትትል ለማድረግ የሚችሉት የተለያዩ ድምጾችን የሚወክሉ ተቋማት ሲኖሩ የሐሳብ ብዙኃነት ሲከበር ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከመግለጫው መረዳት እንደሚቻለው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ዕውቅና የተሰጣቸው ጥቅሞች፣ ፍላጎቶች፣ ልዩነቶች በዴሞክራሲያዊ፣ ሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ እንዲስተናገዱ በቂና አስተማማኝ ዕድል ቢያመቻም ቅሉ የፓርቲው አመራር ግን ዴሞክራሲውን የማስፋት ግዴታውን ባለመወጣቱ በአገሪቱ ውስጥ የሚስተዋሉትን እንዲህ ዓይነት ልዩነቶች ሰላማዊ ከሆነው ይልቅ በግጭት መንገድ የሚፈቱበት ሁኔታ እንዲፈጠር አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ይህ ደግሞ አገሪቱ ውስጥ ለተከሰቱት ግጭቶች በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ  የፓርቲው አመራር ችግር ነው፡፡

ሥራ አስፈጻሚው በርከት ባሉ የአገራችን አካባቢዎች ሰላምና መረጋጋት እየደፈረሰ ሁከት የተዘወተረ ክስተት እየሆነ መምጣቱን ከተለያዩ አገሪቱ ክፍሎች በተለያዩ ሰበቦች በሚፈጠረው ግጭት የዜጎች ሕይወት ተቀጭቷል፣ ከሚኖሩበት ተፈናቅለዋል፣ ከፍተኛ የንብረት ውድመትና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ከባድ ችግር አስከትሏል፡፡ ኅብረተሰቡንም ከፍተኛ የሆነ ሥጋትና ጭንቀት ውስጥ ከቷታል፡፡ 

ኢሕአዴግ እንደ ገዥ ፓርቲነት የፈጸማቸው ስህተቶች በዚህ ሳያበቁ የመድበለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እንዳይፈጠርም ራሱ እክል ሆኗል፡፡ የአስተሳሰብ ብዝኃነት በአግባቡ እንዲሰፍን የሚያደርግ ተጨባጭ ሁኔታ አለመፍጠሩ፣ እንዲሁም ችግሩን በጊዜና በአግባቡ ተገንዝቦ ማስተካከል አለመቻሉ የሚዲያና ፕሬስ በሚገባው ደረጃ ነፃነታቸው ተጠብቆ ለሕዝብ ዓይነተኛውን ግልጋሎታቸውን አለማበርከታቸው ላይ የፓርቲው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጿል፡፡

በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ዙሪያ ብሔራዊ መግባባት መፍጠር ሲገባው የሲቪል ማኅበራት እንዲጠናከሩ አለማድረጉ እንዲሁም የዴሞክራቲክ ተቋማት ግንባታና የሕዝብ የተደራጀ ተሳትፎ አለመጎልበቱ፣ በመልካም ሁኔታ ለሕዝብ አገልግሎት ከመስጠት አንፃርም የአመራር ድክመት እንደነበር አምኗል፡፡ እነዚህ ችግሮች ደግሞ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ፣ የግልጽነትና የተጠያቂነት አሠራርን ለመዘርጋት ብሎም  ውጤታማና ቀልጣፋ አስተዳደር ከመገንባት ረገድ የነበረውን ድክመት በጥቅሉ አስቀምጧል፡፡ አገሪቱን በተለያዩ መስኮች ተወዳዳሪ ሊያደርጉ ይችሉ የነበሩ የሕዝብን ተጠቃሚነት ከፍ ሊያደርጉ የሚችሉ ፕሮጀክቶች መጠናቀቅ በሚገባቸው ጊዜ ባለማለቃቸው ዋጋቸውም በመናሩ የአገር ሀብትም ለብክነት ተዳርጓል፡፡

ከላይ የተገለጹት ችግሮች አገሪቱን ለአደጋ ማጋለጥ የጀመሩት በዋነኛነት በኢሕአዴግ ከፍተኛ አመራር በተለይም የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው የድርጅትና የመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎች በተናጠልና በጋራ የሚጠበቅባቸውን ተግባርና ኃላፊነት ባለመወጣት ተገቢ የሆነ አመራር መስጠት ባለመቻላቸው የተፈጠረ ችግር እንደሆኑ ይፋ አድርጓል፡፡ ፓርላማው ሊኖረው ይችል የነበረውን ሚና ከላይ እንደተገለጸው ከሆነ ገዥው ፓርቲ ደግሞ በዚህ ደረጃ የገዘፉ ችግሮች ሲፈጠሩ ቢያንስ የመተማመኛ ድምፅ እንዲሰጥ ጥያቄ መቅረብ ይገባ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ፓርላው የተሞላው በአንድ ፓርቲ አባላት ብቻ በመሆኑ ይህ የሚጠበቅ አልሆነም፡፡

የመተማመኛ ድምፅ መስጠትና መንፈግ

የመተማመኛ ድምፅ መስጠት ወይም መንፈግ አንድ በኃላፊነት ቦታ ላይ ያለን ሥልጣን የያዘን ሰው ኃላፊ እንደሆነ እንዲቀጥል ወይም እንዲለቅ በሚመለከታቸው ሰዎች የሚሰጥ ውሳኔ ነው፡፡ ኃላፊ ወይም ባለሥልጣን የሆነ ሰው በቅድሚያ መኖር አለበት፡፡ ከዚያም በሥራ ላይ እያለ የተሰጠውን ተግባርና ኃላፊነት አልተወጣም በሚባልበት ጊዜ ለውይይት ቀርቦ ድምፅ ይሰጥበታል፡፡ በኃላፊነቱ እንዲቀጥል የሚፈልገው ወገን የሚሰጠው ድምፁ ከሌላው ከፍ ያለ ከሆነ ደጋፊ የመተማመኛ ድምፅ  (Constructive Vote of Confidence) አግኝቷል ማለት ነው፡፡ እንዳይቀጥል የሚፈለገው ድምፅ ከበዛ ደግሞ የመተማመኛ ድምፅ (Vote of no Confidence) ተነፈገው ማለት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አሠራር በበርካታ አገሮች ዘንድ የፖለቲካ ሥልጣን ከያዘው በዘለለም በተለያዩ ተቋማት ውስጥም የተለመደ ነው፡፡

የመተማመኛ ድምፅ የማግኘት ወይም የመንፈግ ጉዳይ የሚነሳው ኃላፊነት ላይ ያለው ሰው ወይም ቡድን የተሰጠውን ተግባር በአግባቡ አልተወጣም፣ እየተወጣ አይደለም፣ አጓድሏልና ጎድቷል ወዘተ. በሚባልበት ጊዜ ነው፡፡ ፓርላሜንታዊ ሥርዓትን የሚከተሉ አገሮች የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ርዕሰ መስተዳድሩና ካቢኔው (ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከነሚኒስትሮቹ) ላይ አመኔታ ባጣበት ጊዜ እንዲህ ዓይነት ድምፅ ሊሰጡ ይችላሉ፡፡ የተለመደም ነው፡፡ የመተማመኛ ድምፅ ከተነፈገ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከነካቢኔው ይፈርሳል ማለት ነው፡፡

ከመተማመኛ ድምፅ ጋር የሚመሳልና አንድ ወይም የተወሰኑ ሚኒስትሮች ብቻ በተመለከተም ፓርላማው ድምፅ ሊሰጥ ይችላል፡፡ ፓርላማው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያዋቀረውንና ያፀደቀውን መልሶ እንዳረመው ወይም ደግሞ ሳንሱር እንዳደረገው ስለሚቆጠር የሳንሱር የውሳኔ ሐሳብ (Censure Motion) በመባል ይታወቃል፡፡ የአንድ ወይም የተወሰኑ ሚኒስትሮች ቢለቁም አስፈጻሚው አካል በተነሱት ምትክ ሌሎችን ይተካል እንጂ ካቢኔው አይፈርስም፡፡ የእኛም ሕገ መንግሥት ካቢኔው ሳይፈርስ ፓርላማው የመሰለውን ውሳኔ እንዲያስላልፍ ዕድል ይሰጣል፡፡

አንዳንድ ጊዜ የመተማመኛ ድምፅ መንፈግ የሚያስችል ድምፅ መስጠት እንደማይቻል ቢታወቅም፣ አጀንዳው መቅረቡ ለቀረበበት ሚኒስቴርም ይሁን አስፈጻሚውን አካል የሚያሳፍር ስለሚሆንና ተግቶ እንዲሠራም አመኔታ እንዳይጣልበትም ለማድረግ ስለሚረዳ ሲቀርብ ይስተዋላል፡፡ ይሁን እንጂ በአንድ ፓርቲ ብቻ በተያዘ ፓርላማ በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት በሚመራ ድርጅት የሚጠበቅ አይደለም፡፡ በእርግጥ ይህን ዓይነቱን የፓርቲ አሠራር ከሕገ መንግሥቱ ከአንቀጽ 38 መንፈስ ጋር የሚስማማ አይደለም፡፡ ለአገርም አይጠቅምም፡፡ ኢሕዴግም ይኼንኑ ያመነና የተረዳ ይመስላል፡፡ ፓርቲው በራሱ አባላትም ጭምር የመተማመኛ ድምፅ መንፈግን ወይም መስጠትን የሚፈቅድ አሠራር ቢተገብር የሚጎዳው አይሆንም፡፡ ዞሮ ዞሮ በፓርቲ ውሳኔ ኃላፊዎች መነሳታቸው ካልቀረ የፓርቲ አሠራርን በሕጋዊ ሥርዓት መተካት ተገቢነት አለው፡፡

የመተማመኛ ድምፅ ለመንፈግ የሚቀርብ አጀንዳ በብዛት የሚተገበረው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡ ይሁን እንጂ በሁለቱም ምክር ቤቶች በአንድነት የሚታይባቸውም አገሮች አሉ፡፡ አጀንዳውን ከአንዱ ምክር ቤት ሊነሳ ይችላል፡፡ ውሳኔው ግን በጣምራ ነው፡፡ በመሆኑም የሚቀርብባቸውም ምክር ቤቶች ይሁኑ በምን ያህል አባላት መደገፍ እንዳለበት እንደየአገሮቹ ይለያያል፡፡ አጀንዳው በምን ያህል አባላት ሲደገፍ ለውይይት እንደሚቀርብም እንደ አገሮቹ ሕግና የፓርላማው ቁጥር  ይለያያል፡፡

ከፌደራሉ መንግሥት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተጨማሪ በየክልል ፓርላማዎች እንዲህ ዓይነቱ አሠራር ማስፈን ይገባል፡፡ የድምፅ አሰጣጥ ሥርዓትና የፓርቲ ተጠሪ/ጠርናፊ መኖር የመተማመኛ ድምፅ መንፈግ ላይ የራሱ ተፅዕኖ አለው፡፡ የፓርቲ አባላት በተጠሪያቸው በኩል ስለሚሰጡት ድምፅ ቁጥጥር የሚደረግ ከሆነ እንዲሁም በፓርላማው ውስጥ የአንድ የፓርቲ የበላይነት ካለ የመተማመኛ ድምፅ መንፈግ ውጤታማ የመሆኑ ዕድሉ ዝቅተኛ ነው፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመተማመኛ ድምፅ በመስጠትም ሆነ በመንፈግ ረገድ ጥቅል የሚባል እንጂ ዝርዝር ሕግ እስካሁን የለውም፡፡ ነገር ግን በሕገ መንግሥቱ የተጣለበትን ኃላፊነት ይወጣ ዘንድ አሠራሩን ማዳበር ይጠበቅበታል፡፡

በክልሎችም ይሁን በፌደራል ደረጃ የገዥ ፓርቲን ከመንግሥት ለመለየት የሚያስችል በጥቂት የፓርቲ አመራሮች ውሳኔ ሳይሆን በታወቀና ዜጎች የሚገምቱት አኳኋን መስፈን አለበት፡፡ ለአብነትም እስረኞችን በምሕረት ወይም በይቅርታ እንዲፈቱ መወሰን እንደ ማዕከላዊ የምርመራ ተቋም ዓይነቱን መዝጋት ወዘተ. የፓርቲ ሥራ ሳይሆን የመንግሥት ነው፡፡ ወንጀል የፈጸሙ ሰዎች ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረግ የመንግሥት ተግባር ነው፡፡ አንድን የክልል ርዕሰ መስተዳድር ከሥልጣኑ ለማንሳትና በወንጀል ተጠያቂ እንዲሆን ማድረግ (ያለመከሰስ መብቱን በማንሳት) የመንግሥት ተግባር ነው፡፡  እንደዚሁ ሁሉ የገዥው ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ወይም ከፍተኛ አመራር፣ ልክ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ እንደገለጸው፣ በሚያጋጥምበት ወቅት የተለያዩ ኃላፊዎች ከሥልጣናቸው የሚነሱበት ተጠያቂ የሚሆኑበትን ሥርዓት ማስፈን ይገባል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...