የአማራ ክልል በቱሪዝምና ባህል ዘርፍ ሁሉን አሟልቶ ከሰጣቸው አገሪቱ አካባቢዎች አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ ክልሉ በተጥሮ ሀብት፣ በታሪክና በቅርስ፣ በባህልና ትሁፊት፣ በሃይማኖታዊ ሀብቶች እንዲሁም በማኅበራዊ መስክ ለዓለም ያበረከታቸው የቱሪዝም ሀብቶች ትልቅ ቦታ አላቸው፡፡
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በመጪው ዓመት በድጋሚ ለማካሔድ ያቀደውን የሆቴሎች የደረጃ ምደባ በማመልከት ታኅሳስ 21 ቀን 2010 ዓ.ም. በባህር ዳር ከተማ ከተካሔደው ስብሰባ ጎን፣ የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ከአገሪቱ ለተውጣጡ የዘርፉ ተዋናዮች፣ የፓርላማ አባላትና መንግሥታዊ አካላት በጣና ሐይቅ ከሚገኙ ደሴቶች ውስጥ የዘጌ ገዳምንና በውስጡ የሚገኙ ሁለት ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናትን አስጎብኝቷል፡፡
የክልሉ መንግሥት ካሉት ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ ሀብቶች ውስጥ ባህር ዳርን የሪዞርት ከተማ ለማድረግ፣ በአፍሪካ ሻርም ኤልሼክን ከመሳሰሉት የግብፅ የሪዞርት ከተሞች አንዷ እንድትሆን ማሰብ ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ ይህን ውጥን ተግባራዊ ማድረጉ የትዬ ለሌ የሚቀረው ቢሆንም ቅሉ፣ ባህር ዳር ግን የሪዞርት ከተማ ለመሆን ተፈጥሯዊ ገጽታዋ ይፈቅድላታል፡፡ ከተማዋን የከበበው ጣና ሐይቅ አንዱና ዋናው ምክንያት ነው፡፡
የጣና ሐይቅ ከኢትዮጵያ ታላቁና ሰፊው መሆኑ፣ በውስጡ ከያዘው ሰፊ ሥነ ምህዳራዊ ሀብት፣ ካለው አኅጉራዊ ፋይዳ (የዓባይ ወይም የናይል ወንዝ 60 በመቶ የውኃ መገኛ መሆኑና ያለው ሥነ ምህዳራዊ በዓለም ከሚገኙ 250 ታላላቅ ሐይቆች አንዱ ለመሆን መብቃቱን ጸሐፍት ይናገራሉ) ብቻም ሳይሆን በውስጡ የሚገኙ ደሴቶች፣ በደሴቶቹ የሚገኙ ጥንታውያን ገዳማትና በውስጣቸው የሚገኙ የጽሑፍ፣ የሥነ ሥዕልና የሕንፃ ሀብቶች ሐይቁን ከአገሪቱ ልዩ ቅርሶች አንዱ ያደርጉታል፡፡ በጣና ሐይቅ በብዛት ከሚጎበኙት እንደ ክብራን ኪዳነ ምኅረት ገዳም፣ አባ እንጦንስ ገዳም፣ ዘጌ በሚባለው ደሴት ውስጥ የሚገኙትና በ13ኛውና በ14ኛው ክፍለ ዘመን እንደተገነቡ የሚነርላቸውን የእነ ኡራ ኪዳነ ምኅረት፣ የመንበረ ብርሃን አዝዋ ቅድስት ማርያምንና ሌሎችም በርካታ ገዳማትም የቱሪስቶች መስህቦች ናቸው፡፡
የጣና ሐይቅ ብቻም ሳይሆን፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የአፄ ፋሲለደስ ግንብ፣ የሰሜን ተራሮችና በውስጣቸው የሚገኙ (ብርቅዬዎቹን ጨምሮ) የዱር እንስሳት፣ አዕዋፍትና ዕፅዋት፣ ቤተ መንግሥቶች፣ እንደ ጥምቀት፣ አስተርዕዎ ማርያም፣ የቅዱስ ላሊበላ ገና ያሉ ሃይማኖታዊ በዓላትን ጨምሮ ሌሎችም በርካታ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ባለቤት የሆነው የአማራ ክልል፣ ከክልሉ ባሻገር ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያገኙ ሀብቶች የሚገኙበት፣ በአገሪቱ ከሚታየው የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ቱሪስቶች ፍሰት ከፍተኛውን ቁጥር የሚያስተናግድ አካባቢ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡
በእነዚህ ሀብቶች ላይ የሕዝቡ እንግዳ ተቀባይነት በተለይም ለውጭ ጎብኝዎች የሚያሳየው አክብሮት ለቱሪዝም ዘርፉ ትልቅ ድርሻ እንደሚያበርክት ለሪፖርተር የገለጹት፣ በአማራ ክልል የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ልዑል ዮሐንስ ናቸው፡፡ ‹‹ቱሪስቶች ወደ ክልሉ ሲመጡ ተከፍተው አይመለሱም፤›› ያሉት አቶ ልዑል፣ በሌላው ዓለም ሊገኙም ሊተኩም የማይችሉ እንደ ላሊበላ ያሉት ቅርሶች በክልሉ መኖራቸው፣ በቱሪዝም ዘርፍ የሚደረግ ማንኛውንም ኢንቨስትመንትን አክሳሪ አያደርገውም ሲሉ ይገልጻሉ፡፡
የቱሪዝም ዘርፍ የሚፈልጋቸው መሠረተ ልማቶች በተለይ መንገድ፣ ውኃ፣ የኤሌክትሪክ ኃይልና የቴሌኮም አቅርቦቶች እየተስፋፉ ስለመምጣታቸውም አቶ ልዑል አብራርተዋል፡፡ የክልሉም የፌደራል መንግሥትም በቱሪዝም መስክ ለሚሠማሩ ኢንቨስተሮች የሚሰጡት የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎችና ድጋፎች ሲታከሉበት፣ ኢንዱስትሪውን ቁልፍ የኢኮኖሚው ክፍል እንደሚያደርጉት ያብራራሉ፡፡
ፖለቲካ አረምና የክብካቤ እጦት የጋረጡት ፈተና
ምንም እንኳ በቱሪዝም ዘርፍ የዳበረ ሀብት የታቀፈም ቢሆን፣ የአማራ ክልል የቱሪዝም መስህቦች ከሚፈተኑባቸው መካከል የፖለቲካ ትኩሳት፣ የጣና ሐይቅ ህልውናን የሚፈታተነው እምቦጭ አረም እንዲሁም ለታሪካዊና ሃይማኖታዊ ቅርጾች የተነፈገው ክብካቤ ከፍተኛ ሥጋት ደግነዋል፡፡
ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ አገሪቱ የምትገኝበት የፖለቲካ ቀውስ በዜጎች ህልውና ላይ እያደረሱ ከሚገኘው ጉዳት በተጨማሪ፣ በቱሪዝም መስክም ኪሳራ ማስከተሉ ይታመናል፡፡ አስጎብኝዎችና ሆቴሎች የፖለቲካ ቀውሱን ተከትሎ የውጭ ጎብኝዎች ቁጥር መመናመኑን ሲገልጹ ሰንብተዋል፡፡ ባለፈው ዓመት በተለይ ይህ ችግር ከፍተኛ እንደነበር መንግሥትም ያምናል፡፡ እንደ አቶ ልዑል ማብራሪያ ግን ዘንድሮ የፖለቲካ ቀውሱ እየተባባሰ ቢገኝም፣ እንደ አቶ ልዑል አባባል ከሆነ ግን የተገላቢጦሹ እየታየ ነው፡፡
‹‹አንድ መታወቅ ያለበት እውነታ ከዚህ በፊትም በአገር ደረጃ በነበረውም ሆነ በክልሉ በነበረው አለመረጋጋት ሳቢያ በቱሪስቶች ላይ የደረሰ ጉዳት የለም፡፡ መንገድ በተዘጋ ጊዜ ለቱሪስቶች መንገዱን ከፍቶ ያለ ችግር ሲያደርሳቸው ነበር፡፡ በተፈጠረው ችግር አንድም ሻንጣ አልጠፋም፡፡ አንድም ሰው ከጉዞው አልተስተጓጎለም፡፡ በዚህም አብዛኛው ቱሪስት በጣም ጥሩ ሕዝብ አላችሁ እያለ የምስጋና መልዕክት ይጽፍልናል፡፡››
በመሆኑም የፖለቲካ ቀውስ በተንሰራፋበት፣ ዜጎች በሚገደሉበትም ወቅት ቢሆን የቱሪዝም ዘርፉ ከሁለት ዓመት በፊት ከተመዘገበውም በላይ በዚህ ዓመት ትልቅ ውጤት እንደታየበት ዋቢ የሚያደርጉት የዘንድሮውን የመጀመሪያው ሩብ ዓመት የዘርፉን እንቅስቃሴ ነው፡፡ ከክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የተገኘው ስታቲስቲካዊ መረጃ እንደሚያሳየው፣ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ብቻ ከ3.5 ሚሊዮን በላይ ጎብኝዎች ክልሉን ጎብኝተዋል፡፡ ይህም ሆኖ ከዚህ አኃዝ ውስጥ የውጭ ጎብኝዎች ቁጥር ግን ከ26,213 አይበልጥም፡፡ በገቢ ረገድ ሲታይም፣ ከአገር ውስጥና ከውጭ ጎብኝዎች የተገኘው ከ397 ሚሊዮን ብር በላይ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ ከውጭ ጎብኝዎች የተገኘው ግን 96 ሚሊዮን ብር ገደማ ነው (ትክክለኛው አኃዝ 95,036,942 ብር ነው)፡፡ ባለፈው ዓመት በነበረው ፖለቲካው ውጥረት ሳቢያ ክልሉ ካቀደው የቱሪዝም ገቢ የ53 በመቶ ቅናሽ፣ በገቢ ረገድም ከዚህ ያነሰውን ውጤት ለማስተናገድ መገደዱን አቶ ልዑል አስታውሰዋል፡፡ ነገር ግን ቅናሹ አጭር ቆይታ እንደነበረው፣ የክልሉ መንግሥት በወሰዳቸው አፈጣኝ ዕርምጃዎች መስተካከሉን አቶ ልዑል ገልጸዋል፡፡
ከፖለቲካው ባሻገር፣ በክልሉ አንገብጋቢ እየሆነ የመጣው የቅርሶች ጥበቃ፣ ዕድሳትና ክብካቤ ችግር አንዱ ነው፡፡ ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ፤›› እንደሚባለው፣ የጣና ሐይቅን እየወረረ የሚገኘው የእንቦጭ አረም ለክልሉ ብቻም ሳይሆን ለኢትዮጵያ፣ አልፎም ለጎረቤት አገሮች ትልቅ ሥጋት እየሆነ መጥቷል፡፡ ምሁራን እንደሚገልጹት፣ ከ50 ሺሕ ሔክታር መሬት በላይ የሐይቁ ውኃማ ክፍል በእንቦጭ አረም ተወሯል፡፡
በየዓመቱ ወደ ሐይቁ የሚገባው ደለል አፈር፣ የቆሻሻ ዝቃጭና የውኃ ትነት ተደማምረው የሐይቁን የውኃ መጠን ብቻም ሳይሆን፣ በውስጡ የሚገኙ ሀብቶችን እያራቆቱ እንደሚገኙ ተረጋግጧል፡፡ ሐይቁ ከነበረው የዓሳ ሀብት 75 በመቶ በላይ እንደጠፋ አጥኝዎች እየገለጹ ነው፡፡ በዚህ አያያዙ ሐይቁ እንደ ሐሮማያና ሌሎችም ሐይቆች የመጥፋት ዕድሉ እየተፋጠነ መምጣቱ እየተገለጸ ነው፡፡ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የክልሉ ነዋሪዎችና ከሌሎችም የአገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ ዜጎች በደቦ እየወጡ አረሙን ቢነቅሉም ከመስፋፋት አልገቱትም፡፡
ዩኒቨርሲቲዎች አረሙን ለመከላከል የሚረዱ ሥራዎችን ቢሠሩም እዚህም እዚያም የሚሠሩትን ሥራዎች አስተባብሮ ውጤታማ የማድረግ ችግር እንደሚታይ በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም፣ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ በመሆን በቅርቡ የተሾሙት፣ አቶ አብርሃም አሰፋ በግላቸው መታዘባቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ‹‹የሀብት አሰባሰብ ኮሚቴ መቋቋሙን አይቻለሁ፡፡ ይህ ነገር ግን የተደራጀና የተቀናጀ ነው ማለት ያስቸግራል፡፡ ሰው ይጮሃል፡፡ ሚዲያውም እንዲሁ፡፡ ለመፍትሔ የቀረበ ግን አይደለም፡፡ አረሙ አደገኛ እንደሆነ ግን ምሁራን፣ ተመራማሪዎችና አርሶ አደሩም እንደሚናገሩ ታዝቤያለሁ፤›› ያሉት አቶ አብርሃም፣ ሥጋቱ የሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡
ሌላኛው የሕዝብ ሥጋት፣ እንደ ላሊበላ ባሉት ጥንታዊ ሥነ ሕንፃዊ፣ ሥዕላዊና መሰል ቅርሶች ላይ የተጋረጠው አደጋ ነው፡፡ ሰፊ መነጋገሪያ የሆነው የላሊበላ ጉዳይ ነው፡፡ የላሊበላ ሕንፃን በዝናብና በፀሐይ ምክንያት ከሚደርስበት ጉዳት ለመከላከል ተብሎ የተከለለለት ዳስ ለአምስት ዓመት እንዲቆይ ታስቦ ቢሠራም፣ በአሁኑ ወቅት ግን ወደ አሥር ዓመት እየተጠጋ በመምጣቱ ዳሱ ሕንፃውን እንዳይንደው አሥግቷል፡፡ የአካባቢው ሕዝብም ይህንን ሥጋት ሲያስተጋባ ይደመጣል፡፡ የሕንፃው ስንጥቃት እየተባባሰ መምጣቱ ይነገራል፡፡
ስለዚህ ጉዳይ አቶ ልዑል ከሪፖርተር ተጠይቀው እንዳብራሩት፣ ዳሱን ማንሳቱም ከባድ ፈተና ጋርጧል፡፡ ሕንፃው ላይ አንድም ጉዳት ሳይደርስ ማንሳት ስለሚቻልበት መንገድ ማረጋገጫ መስጠት አስቸጋሪ መሆኑን፣ ዳሱን ለማንሳት የሚፈለገው ገንዘብም ከፍተኛ መሆኑን አቶ ልዑል አብራርተው፣ ክልሉም የፌደራል መንግሥት ባደረጉት ጥናት ላሊበላ ለአደጋ መጋለጡ በመረጋገጡ፣ የዳሱ አነሳስ ላይ አደጋውንና ሥጋቱን በመውሰድ ሊያነሳ የሚችል አካል ለማግኘት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡ በላሊበላ ዙሪያ እንዲነሱ የተደረጉ ነዋሪዎችን መልሶ ማቋቋሙም ከሕንፃው ጋር አብሮ የሚነሳ የበጀት ችግር ነው ቢሉም፣ በክልሉ ተነሳሽነት የቱሪዝም ልማትና የቅርስ ጥበቃ ፈንድ የተባለ ጽሕፈት ቤት እየተቋቋመ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡ ይህ ጽሕፈት ቤት ከመንግሥት በጀት ውጭ ሊገኙ የሚችሉ የፋይናንስ ምንጮችን በማፈላለግና በማሰባሰብ ለሚፈለገው ሥራ እንዲያውል የሚጠበቅ ነው፡፡ የገና በዓል ማግሥት ጀምሮ ጽሕፈት ቤቱን በማቋቋም ወደ ሥራ ለማስገባት እንደሚሠራ አብራርተዋል፡፡
በባህር ዳር ጉዞ ከተሳተፉት መካከል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ይገኙበታል፡፡ በፓርላማው የባህል፣ ቱሪዝምና መገናኛ ብዙኃን ቋሚ ጉዳዮች ሰብሰባቢ አምባሳደር መስፍን እሸቱ፣ የላሊባላን ቅርስ በተመለከተ በዚህ ዓመት ከአንዴም ሁለት ጊዜ ወደ አካባቢው በመጓዝ የመንግሥት ኃላፊዎችና ሕዝቡን ማነጋገራቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ እንደ ሕግ አውጭው አካል፣ ለቅርሱ የሚገባውን ክብካቤና ዕድሳት ማድረግ የሚቻልባቸውን አፋጣኝ ዕርምጃዎች በመንግሥት ስለመወሰዳቸው ክትትል እንደሚደረግ አምባሳደር መስፍን ጠቅሰው፣ ችግሮች መኖራቸውም አመላክተዋል፡፡ ‹‹ቅርሶችን በወቅቱ የመጠገን ችግር እንዳለ ታይቷል፡፡ ለምሳሌ ብናነሳ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያን መጠለያ እንዲሆን ከዓለም ባንክ በተገኝ ብድር የተሠራው መጠለያ ሳይነሳ ጊዜ አልፎበታል የሚለው በሕዝቡም የሚነሳ ቅሬታ ነው፤›› ያሉት አምባሳደር መስፍን፣ መንግሥት ለአገሪቱ ቅርሶች ጥበቃ እንዲደረግ እየሠራም ቢሆን በጥራት መሥራትና መተግበር ላይ የሚታዩ ችግሮች እንደማይጠፉ አመላክተዋል፡፡ ለላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ጥበቃ ብሎም ለጥገና የሚሆን ገንዘብ በመገኘቱ በቅርቡም ሥራው እንደሚጀመር፣ ቅርሱን የተመለከቱ የክትትል ሥራዎች እንደሚጠናከሩ ገልጸዋል፡፡
700 ዓመታትና ከዚያም በላይ ዕድሜ ያስቆጠሩ ጥንታውያን የብራና ጽሑፎች፣ ከዕፅዋት በተቀመመ ቀለም የተሳሉ ቅዱሳት ሥዕሎች፣ ቤተ መቅደሶችና አብያተ ክርስቲያኖች ቅርሶች ለደጋ መጋለጣቸው በጣና ሐይቅ የሚገኙ ደሴቶችን የጎበኘ የሚገነዘበው እውነታ ነው፡፡ የቅርስ ጥበቃና ክብካቤ ሥራ ኋላ ቀር መሆኑ የአገሪቱ መሠረታዊ ችግር እንደሆነ መገለጫዎቹ እንዲህ ያሉት ዕድሜ ጠገብ ቅርሶች የሚገኙበት ሁኔታ ሲታይ ነው፡፡