Sunday, February 25, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የማበረታቻ ያለህ የሚለው የመድን ኢንዱስትሪ

ተዛማጅ ፅሁፎች

አቶ የወንድወሰን ኢተፋ፣ በኢትዮጵያ የመጀመርያ በሆነው የኢትዮጵያ ጠለፋ መድን ኩባንያ አክሲዮን ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው፡፡ ከ30 ዓመታት በፊት በቢዝነስ ማኔጅመንት በዲግሪ ተመርቀው ሥራ የጀመሩት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ውስጥ ነበር፡፡ ብሔራዊ ባንክ ከገቡ በኋላ የኢንሹራንስ ሱፐርቪዥን ዲቪዥን ክፍልን የተቀላቀሉት አቶ የወንድወሰን፣ በወቅቱ የነበረውን ብቸኛውን የኢትዮጵያ መድን ድርጅትን መቆጣጠር የሥራ ድርሻቸው ነበር፡፡ የዚሁ ክፍል ኃላፊም ሆነው አገልግለዋል፡፡ በ2009 ዓ.ም. የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆን ለሰባት ዓመታት ካገለገሉ በኋላ፣ ከካቻምና ጀምሮ የጠለፋ መድን ኩባንያን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት እየመሩ ይገኛሉ፡፡ በኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪና በኢትዮጵያ የጠለፋ መድን ሰጪ ኩባንያ እንቅስቃሴ ዙሪያ ዳዊት ታዬ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የአገሪቱን የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በሚቆጣጠረው የብሔራዊ  ባንክ ክፍል ውስጥ እንደመሥራትዎ ስለፈቃድ አሰጣጥና ቁጥጥሩ ቢነገሩን? የአገሪቱ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ታሪካዊ ዳራ እንዴት ይገለጻል?

አቶ የወንድወሰን፡- እኔ ብሔራዊ ባንክን በተቀላቀልኩበት ወቅት የነበረው ተቋም የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ብቻ ነበር፡፡ እኔ የነበርኩበት ዲቪዥን ይቆጣጠር የነበረውም ይህንኑ ተቋም ነው፡፡ የዓረቦን አተማመኑ የካሳ አከፋፈሉ የመሳሰሉትን እንቆጣጠር ነበር፡፡ 1983 ዓ.ም. በኋላ ግን በአዲሱ የመድን ሥራ አዋጅ መሠረት የግል የኢንሹራንስ ኩባንያዎች መቋቋም ጀመሩ፡፡ ለብሔራዊ ባንክ በተሰጠው ሥልጣን አግባብ ለኩባንያዎች ፈቃድ መስጠትና በአዋጁ መሠረት እየሠሩ መሆናቸውን እንከታተል ነበር፡፡ አዲሱ የመድን ሥራ አዋጅ እንደወጣ የግል የኢንሹራንስ ኩባንያ ለማቋቋም የመጀመርያውን 001 የፈቃድ ቁጥር በማግኘት የኢንሹራንስ ሥራ ፈቃድ የወሰደው ዩኒቨርሳል ኢንሹራንስ የሚባል ኩባንያ ነበር፡፡ ፈቃዱን ከወሰደ በኋላ ግን ወዲያው በባለአክሲዮኖች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት በፍርድ ቤት ታገደ፡፡ የፍርድ ቤት ጉዳዩን ከፈታ በኋላ ወደ ሥራ ቢገባም መቀጠል ግን አልቻለም፡፡ ከዚያም ናይስ ኢንሹራንስ ኩባንያ ፈቃድ በመውሰድ ወደ ሥራ ገባ፡፡ ከዚህ በኋላ የመድን ሥራ ቁጥጥር በጥልቀትም በስፋትም እየጨመረ በመምጣቱ፣ የኢንሹራንስ ሱፐርቪዥን ዲቪዥን፣ ከዚያም የኢንሹራንስ ሱፐርቪዥን ዲፓርትመንት ተቋቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪን ቀደም ያለ ታሪክ ስንመለከት፣ የኢንሹራንስ ሥራ ኢትዮጵያ ውስጥ የተጀመረው ከ1905 ዓ.ም. ጀምሮ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በወቅቱ የነበረው የኢንሹራንስ አገልግሎት በዚያን ወቅት ከነበረው የሐበሻ ባንክ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የኢንሹራንስ ዘርፉ ለባህር ላይ ጉዞና ለእሳት አደጋዎች ዋስትና ይሰጥ ነበር፡፡ ጠላት ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ ሥራው በመቀዛቀዙ ተቋርጦ ነበር፡፡ ከ1933 ዓ.ም. በኋላ ግን በአዲስ አበባ የተሽከርካሪዎች ቁጥር እየጨመረ መሄዱ፣ የውጭና የአገር ውስጥ የንግድ እንቅስቃሴ ከፍ እያለ መምጣቱ የመድን ሥራ እንዲስፋፋ ምክንያት ሆኗል፡፡ በዚያን ጊዜ በአብዛኛው ሥራውን የሚሠሩት የውጭ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ነበሩ፡፡ በአዲስ አበባ የነበሩት ኩባንያዎች የሌሎች አገሮች ትላልቅ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ቅርንጫፍ ሆነው ነበር የሚያገለግሉት፡፡ እነዚህ ተቋማት የውጭ ቅርንጫፎች በመሆናቸው፣ መንግሥት የመድን ገቢዎችን የመጠበቅ ኃላፊነት አለበት ወደሚል እሳቤ ተገባ፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ኩባንያዎች ዓረቦን ሰብስበው ምንም ካሳ ሳይከፍሉ ሊሸሹ ስለሚችሉ፣ ኩባንያዎቹ ወደ ሥራ ሲገቡም በቂ ካፒታልና በቂ የሰው ኃይል ሳይኖራቸው ሊሆን ስለሚችል ይህ ሊፈጥር የሚችለው ችግር ታስቦ፣ በ1962 ዓ.ም. የመጀመርያው የኢንሹራንስ አዋጅ ወጣ፡፡

ሪፖርተር፡- አዋጁ ምን ዓይነት ይዘት ነበረው?

አቶ የወንድወሰን፡- የመድን ንግድ ሥራ አዋጅ የሚል መጠሪያ የነበረው ይህ አዋጅ፣ ዓላማው ኢትዮጵያ ውስጥ በቅርንጫፍነት የሚሠሩ የውጭ ኩባንያዎች በአገሪቱ ሕግ መሠረት እንዲቋቋሙ ማድረግ ነበር፡፡ ኩባንያዎቹ በሕግ የተወሰነ ካፒታል እንዲኖራቸው የሚያስገድድ ሕግ ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ በውጭ ሰዎችና በኢትዮጵያውያን መካከል ባለቤትነት እንዲኖር፣ ኢትዮጵያውያን የተወሰነ ድርሻ እንዲኖራቸው የሚያስችልና ይህንኑ በትክክል ያስቀመጠ አዋጅ ነበር፡፡ እንዲሁም በንግድ ሚኒስቴር ሥር የመድን ሥራን የሚቆጣጠር ክፍል እንዲኖር ያደረገ አዋጅ ነበር፡፡ ይህ አዋጅ በወጣበት ጊዜ ከ33 እስከ 40 የሚጠጉ የኢንሹራንስ ኩባንያ ወኪሎች ኢትዮጵያ ውስጥ ይሠሩ ነበር፡፡ ሆኖም በአዋጁ የተቀመጡትን መሥፈርቶች ማሟላት ስላልቻሉ አብዛኞቹ ቅርንጫፎቻቸውን ዘግተው ወጥተዋል፡፡ በአንፃሩ በኢትዮጵያ ሕግ በኢትዮጵያውያን የተቋቋመው የመጀመርያው የኢንሹራንስ ኩባንያ ኢምፔሪያል ኢንሹራንስ ወደ ሥራ ገባ፡፡ ከዚያም ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን የተቋቋመው ብሉናይል ኢንሹራንስ ኩባንያን ጨምሮ 15 ኩባንያዎች መሥፈርቱን  አሟልተው ሥራ ጀመሩ፡፡ ደርግ ወደ ሥልጣን መጣና በወቅቱ ከነበሩት ውስጥ 13 የኢንሹራንስ ኩባንያዎችን ወርሶና በአንድ ጨፍልቆ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት እንዲቋቋም አደረገ፡፡ ነገር ግን አንድ የኢንሹራንስ ኩባንያ ብቻ መኖሩ ኢንዱስትሪው ላይ ተፅዕኖ ማሳረፉ አልቀረም፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ዓይነት ተፅዕኖ?

አቶ የወንድወሰን፡- ብቻውን መሆኑ ያለተወዳዳሪ እንዲሠራ አደረገው፡፡ ውድድር ሲኖር ፈጠራ ይኖራል፡፡ አዳዲስ የመድን ሽፋን ፖሊሲዎች የመፍጠርና በጣም ተፈላጊ የሆኑ የመድን ሽፋኖች ወደ ሕዝቡ ለማቅረብ የሚያስችል ምንም ዓይነት ማበረታቻ አለመኖሩ አንዱ ተፅዕኖ ነው፡፡ እስካሁን ድረስ የምንጠቀምባቸው በ1940ዎቹና 50ቹ ውስጥ  ከእንግሊዝ በቀጥታ የወሰድናቸውን የኢንሹራንስ ፖሊሲዎች ናቸው፡፡ አሁንም ድረስ ቃላቶቹ ሳይቀየሩ የምንጠቀምባቸው እነዚህን የመድን ውለታዎች ናቸው፡፡ የመድን ሥራ እንደማንኛውም የንግድ ሥራ ነው፡፡ ሕዝቡና ኢኮኖሚው የሚፈልገውን የመድን ፖሊሲዎች እያጠና ተስማሚና አዳዲስ የመድን ሽፋን የሚሰጥባቸው ፖሊሲዎች ማውጣት ይጠይቃል፡፡

ሪፖርተር፡- በኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ውስጥ የሚቀርበው የመድን ሽፋን ዓይነ ምርጫ የሚሰጥ አይደለም፡፡ ኢንዱስትሪው የተንጠለጠለው በአብዛኛው በሞተር ኢንሹራንስ ላይ ነው፡፡ አዳዲስ ነገሮች አይታዩም፡፡ እንዲህ የሆነበት ምክንያት ምንድነው ይላሉ?

አቶ የወንድወሰን፡- በአሁኑ ወቅት 17 የኢንሹራንስ ኩባንያዎች አሉ፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች በተለያየ ደረጃም ቢሆን ገቢ አላቸው፡፡ ትርፍ ያገኛሉ፡፡ አዳዲስ ነገሮች ብዙም የማይታዩት፣ ባለው ገበያ የረካን ስለሚመስል ነው፡፡ ባለን ረክተን ከዚያ ውጭ ማሰብ የቻልን አይመስልም፡፡ አብዛኛው የአገራችን ሕዝብ ነዋሪነቱ በገ ነው፡፡ አብዛኛው በእርሻ ሥራ ላይ የተሠማራ ነው፡፡ ለዚህ ሕዝብ የአደጋ ሥጋቱን ሊያሸጋግርለት የሚችል አሠራር መኖር አለበት፡፡ ይህንን ሰፊ ክፍል መድረስ የሚቻልበት ነገር መሠራት አለበት፡፡ ነገር ግን ይህንን ዘርፍ ለመድረስ አስቸጋሪ የሚያደርገው የኢንሹራንስ ፖሊሲውና አገልግሎቱ በጣም ወጪ የሚጠይቅ መሆኑ ነው፡፡ ተቋማቱ  ይህንን ወጪ የሚያወጡት ከሚቀበሉት ዓረቦን ነው፡፡ ስለዚህ አንዱ ችግር የአስተዳደር ወጪ ነው፡፡ ሁለተኛው ሥጋቱን ለመሸፈን የሚያስከፍሉት ክፍያና የሚያገኙት ትርፍም ታሳቢ የሚደረግበት አሠራር ነው፡፡ ነገር ግን ብዙኃኑን የኢንሹራንስ ተጠቃሚ ለማድረግ ኩባንያዎ ብዙ መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡ ለዚህ የየኩባንያዎቹ ጥረት ወሳኝ ቢሆንም ይህንን ሥራቸውን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ ግን ትልቅ ማበረታቻ ያስፈልጋቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ብዙኃኑን ለመድረስና የመድን ሽፋኖችን ወይም ፖሊሲዎችን ለማስፋት መደረግ አለበት የሚሉት ማበረታቻ ምንድነው?

አቶ የወንድወሰን፡- በበለፀጉ አገሮች የኢንሹራንስ ሕግ ሲወጣ ሌላው ቀርቶ፣ በኢንሹራንስ ጉዳዮች ፍርድ ቤት የሚሄዱ ነገሮች በምን አኳኋን መፈታት እንዳለባቸው የመሳሰሉት ላይ በመቀስቀስ በኩል የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ትልቅ ሚና ነበራቸው፡፡ በቢዝነስና በሕግ ሥርዓት ላይ ይህንን ዘርፍ ለማሳደግ ምን ይደረግ በሚለው ላይ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በንቃት ይሳተፉበት ነበር፡፡ አሁን ቀረ እንጂ ለምሳሌ አንድ ሰው የሕይወት ኢንሹራንስ ሲገዛ መንግሥትን እየደገፈ በመሆኑ መበረታታት ይኖርበታል፡፡ መንግሥት የዜጎቹን ሕይወት መጠበቅ አለበት፡፡ እነዚህ ዜጎች ባልተጠበቀ ሁኔታ ቢሞቱ፣ ቤተሰቦቻቸው ያለምንም ዋስትና ይቀራሉ፡፡ ይህ ደግሞ ኋላ ላይ ልጆቻቸው እንዳይማሩና ተገቢው ደረጃ ላይ እንዳይደርሱ ጫና ያደርጋል፡፡ ይህ ክስተት እንደ ቀውስ የሚቆጠር ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሰዎች የሕይወት ዋስትና መግዛታቸው በራሱ የመንግሥትን ኃላፊነት በከፊልም ቢሆን መወጣት እንደሆነ በማመን ለዚህ የሚከፈለው ዓረቦን ከታክስ ነፃ ይደረጋል፡፡ ከዚህ ቀደም ሰው ገንዘብ ተበድሮ ቤት ሲሠራ፣ የሕይወት ኢንሹራንስ ይገባ ነበር፡፡ ገንዘብ ተበድሮ ቤት የሠራ ሰው ለራሱ መጠለያ እያበጀ ነው፡፡ መንግሥት ለዜጎች መጠለያ የመስጠት ኃላፊነት አለበት፡፡ ነገር ግን ይህንን ቤት ሰውዬው ራሱ ስለሠራ፣ ለዚህ ኢንሹራንስ ከገባ ለኢንሹራንሱ የሚከፈለው ዓረቦን ከታክስ ነፃ ይደረጋል፡፡ ሌሎችም አስገዳጅና ዝቅተኛ ኢንሹራንሶችን ሰዎች ሲገዙ፣ ከታክስ ነፃ ማድረግ እንደ አማራጭ ይወሰዳል፡፡ እንዲህ ያሉ ማበረታቻዎች ያስፈልጋሉ፡፡ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ ከታሰበ እንዲህ ዓይነት ነገሮች መደረግ ይኖርባቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አሠራር ከታክስ ነፃ የሚሆንበት መንገድ የለም?

አቶ የወንድወሰን፡- በእኛ አገር ከታክስ ነፃ የሚባል ነገር የለም፡፡ ለምሳሌ የጡረታ ሲቆረጥበት ከታክስ ነፃ ነው፡፡ ጡረታ ሲቆረጥበት ሰውዬው እየቆጠበ ነው፡፡ የወደፊት ዋስትናውን እያመቻቸ ነው፡፡ ስለዚህ መንግሥት ዕውቅና ሰጥቶ ለዚህ ሰውዬ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ከሆነ፣ በተመሳሳዩ በተለይ የሕይወት ኢንሹራንስ ሲገዛም ከታክስ ነፃ ሊደረግ ይገባዋል፡፡ ከንጉሡ ጊዜ ጀምሮ ኢንሹራንስ የሚከፍል ሰው የሚከፍላት ዓረቦን ነፃ ነበረች፡፡ ምንም ዓይነት ታክስ የለባትም፡፡ እንዲህ ማድረጉ ሰዎች ወደ ኢንሹራንስ እንዲሳቡ ይጋብዛል፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ አንዱ አከራካሪ ነገር፣ ኩባንያዎች የመድን ሽፋን ውል በእንግሊዝኛ ቋንቋ ማድረጋቸው ብቻ ሳይሆን፣  የተማረውም እንኳ የማይረዳቸው ውስብስብ ይዘቶችን ማስቀመጣቸው ነው፡፡ ይህ ብዙዎችን እያደናገረ ስለሚገኝ ለምንድነው ተጠቃሚዎች በቀላሉ በሚረዱት ቋንቋ የማይቀርብላቸው?

አቶ የወንድወሰን፡- ይህ ትልቅ ችግር ነው፡፡ በእንግሊዝ እንኳ የኢንሹራንስ አገልግሎት የሚቀርብበት የእንግሊዝኛ ቋንቋ ብዙ ሲያሟግት የቆየ ነው፡፡ ለምሳሌ የማሪን ኢንሹራንስ ከ400 ዓመታት በፊት የተጻፈ ነው፡፡  አሁንም እንዳለ ነው፡፡ በእንግሊዝም ሳይቀር በቀላል እንግሊዝኛ ይቅረብ የሚል ቅሬታ እስከማስነሳት ደርሶ ነበር፡፡ በዚያ ምክንያት የመድን ሰጪዎች ማኅበርና ተቆጣጣሪው አካል አንድ ላይ በመሆን፣ አንድ ውለታ ምንድነው የሚሸፍነው? የካሳ ጥያቄ ለማቅረብ ምን ያስፈልጋል? ምን መደረግ አለበት? ምንድነው የማይሸፈነው? የሚለውን የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በሙሉ ለደንበኛው በሚገባውና በቀላል የእንግሊዝኛ ቋንቋ እንዲሰጡ ትልቅ ሥራ ሠርተዋል፡፡ ይህ ከእኛ አገር አንፃር ሲታይ፣ ብዙ ጊዜ የሚቀርበው ምክንያት ኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ ከጠለፋ መድን ሰጪዎች ጋር በተያያዘ የሚያነሱት ነው፡፡ ስለዚህ እዚህ ከተቀየረ የጠለፋ መድኑንም መቀየር አለብን የሚል ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች ብዙውን ጊዜ ላለመግባባት የሚያጋልጡ ናቸው፡፡ በመድን ፖሊሲው ትርጉም ምክንያት ከጠለፋ መድን ውለታ ጋር ተቃርኖ ቢኖር፣ በመድን ሰጪዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል፡፡ ሌላው ቀርቶ የጠለፋ መድን ሰጪዎች ሊያገኙት የሚችሉትን ካሳ ጭምር ሊያስቀር ይችላል የሚል ሥጋት አለ፡፡ ነገር ግን ይህ በመድን ሰጪዎች ብቻ ሳይሆን፣ ውለታው የሕግም ጉዳይ ስላለው የሕጉ አባል መድን ሰጪዎች እንዲሁም ሸማቾች እነዚህ ነገሮች በቀላሉ በሚገባን ቋንቋ ተጽፈው ማግኘት አለብን ብለው መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡ ለምሳሌ እንደ ኬንያ ያሉ አገሮች፣ በቀላሉ በርካታ የኢንሹራንስ ተጠቃሚዎችን አፍርተዋል፡፡ ለገበሬው ኪሱን የማይነካ፣ በራሱ አቅም ሊገዛቸው የሚችላቸውና በቴክኖሎጂ የተደገፉ፣ አደጋ ቢደርስ በመድን ሽፋን የሚጠቀሙትን ፕሮጀክቶች ዲዛይን አድርገው ትልቅ የፕሮሞሽን ሥራ በመሥራት፣ የመድን ሽፋን ገበሬው ጋር እንዲደርስ አድርገዋል፡፡ በገጠር የጤና ኢንሹራንሳቸው ብዙ ሰው አዳርሷል፡፡ የሚቀበሉትም ፕሪሚየም በጣም ትንሽ ነው፡፡ ኬንያ ውስጥ በጤናና በሕይወት ረገድ ትልቅ ሥራ ተሠርቷል፡፡ ተጠቃሚው በሞባይል ስልኩ ሁሉንም ነገር ይጨርሳል፡፡ ስለዚህ ገጠር ድረስ በመግባት የሠሩት ሥራ የሕይወት መድን ሽፋኑ ብልጫ እንዲይዝ አስችሏቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የሕይወት መድን ከተነሳ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የመድን ሽፋን ከሌሎች አገሮች አንፃር ሲታይ እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ዘርፍ መራመድ አልቻለችም፡፡ ከጠቅላላው የመድን ሽፋን ውስጥ የሕይወት መድን ሽፋን ከአምስት በመቶ በታች ነው፡፡ በሌላው አገር ግን ብልጫ የሚይዘው የሕይወት ኢንሹራንስ ነው፡፡ ይህ ለምን ሆነ? ችግሩስ ምንድነው?

አቶ የወንድወሰን፡በእኛ አገር ሁኔታ በሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ ያሉት ፕሮጀክቶች ምንድናቸው? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ አንዳንዶቹ የቁጠባ ይዘትም አላቸው፡፡ አንድ ሰው ለምሳሌ ከአሥር ዓመት በኋላ እንዲከፈለው ኢንሹራንስ ይገባና በዚያ አሥር ዓመት ውስጥ ያስቀመጠው ገንዘብ ይከፈለዋል፡፡ በመካከሉ ቢሞት ገንዘቡ ለቤተሰቡ ይከፈላል፡፡ ይኼ የቁጠባ ጠባይ ያለው አሠራር ነው፡፡ ነገር ግን ይህ የቁጠባ ይዘት ድሮ በጣም በተረጋጋ ወይም በዝቅተኛ መጠን የዋጋ ግሽበት በሚታይበት ኢኮኖሚ ውስጥ የነበረ ነው፡፡ ዛሬ ላይ የ100 ሺሕ ብር መድን ቢገባ፣ የዛሬ አሥር ዓመት 100 ሺሕ ብር ታገኛለህ ቢባል ወይም በዛ መካከል ቢሞት ይህንን ነገር ቤተሰቦቹ የሚወስዱት ከሆነ፣ ከአሥር ዓመት በኋላ አነስተኛ የዋጋ ግሽበት በመኖሩ ምክንያት የሚገኘውን ገንዘብ እኔም የምቀበለው ይሆናል፡፡ ነገር ግን አሁን 100 ሺሕ ብር ገብቼ ምናልባት በአሥር በመቶ የዋጋ ግሽበት፣ የዛሬ አሥር ዓመት 100 ሺሕ ብር ብቀበል፣ ከገንዘብ የመግዛት አቅም መቀነስ አንፃር የተቀበልኩት ዋጋ ዜሮ ነው ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም በአሥር ዓመት ውስጥ የአሥር በመቶ የዋጋ ግሽበት ገንዘቡን ስለሚበላው ነው፡፡ በ1960 እና 70ዎቹ ውስጥ በተለይ በአውሮፓና በአሜሪካ ገበያዎች ውስጥ ፖሊሲው ወይም የመድን ዓይነቱ ሲቀርብ፣ የግሽበት መጠኑን ታሳቢ በማድረግ ነበር፡፡ ለምሳሌ ግሽበቱ አሥር በመቶ ከሆነ፣ ፖሊሲውም በየዓመቱ አሥር በመቶ እየጨመረ ይመጣል፡፡ ቅድም በነገርኩህ ምሳሌ ላይ፣ አሁን 100 ሺሕ ብር የገባሁበት የመድን ዋስትና ከአሥር ዓመት በኋላ 200 ሺሕ ብር ይሆንልኛል፡፡ ይኼ ትልቅ ማበረታቻ ነው፡፡ በብዙ አገሮች ተሞክሮ የሕይወት ኢንሹራንስ ማለት የሞት ሥጋት ሽፋን ብቻ ሳይሆን፣ የኢንቨስትመንት ሞተርም ነው፡፡ እንደውም ከሚከፈለው ፕሪምየም ውስጥ የሞት ሪስክ ሽፋንዋ ለብቻዋ ወጥታ ሌላውን ኢንቨስት የሚያደርጉበት ዕድልም አላቸው፡፡ ይኼ ከዋጋ ግሽበት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በሌላ በኩል መቶ ብር ብከፍልና 50 ብሩ የሞት ሪስኩን ቢሸፍን፣ ቀሪውን 50 ብር የቁጠባ አካል ላደርገው እችላለሁ፡፡ ስለዚህ የቁጠባ አካል የሆነውን 50 ብሩን በምን ዓይነት ኢንቨስትመንት መስክ ላይ ላውልልህ በማለት የኢንሹራንስ ኩባንያው እንደ ኢንቨስትመንት አማካሪ ሆኖ ደንበኛውን  ይጠይቃል፡፡ ደንበኛው በበኩሉ 50 ብሩን የመንግሥት ቦንድ ግዛልኝ፣ ይህ ቦንድ ግዥ አስተተማማኝ ስለሆነ፣ ትርፉ  አነስተኛ ቢሆንም እንኳ ግዛልኝ ሊል ይችላል፡፡ የኩባንያ አክሲዮን ግዛልኝ ወይም ሌላ ኢንቨስትመንት ላይ አውልልኝ ሊለው ይችላል፡፡ በዚህ መሠረት የተገበያየው ፖሊሲ ከአሥር ዓመት በኋላ ሲያልቅ፣ ኢንቨስትመንቱ ያመጣውን የትርፍ ድርሻ  መጀመርያ መድን የገባሁበትንም ዋጋ ጨምሮ ይከፍላል ማለት ነው፡፡ ይኼ ማለት ኢንሹራንስ ኩባንያዎች የኢንቨስትመንት አማካሪነት አገልግሎትም  ይሰጣሉ ማለት ነው፡፡ በእኛም አገር የሕይወት ኢንሹራንስ የዛሬ 60 እና 70 የነበረ ነው፡፡ ይሁንና በሌላ በኩል ሲታይ፣ ብዙዎቻችን መንገዳችንን ለፈጣሪ መስጠትን እንመርጣለን፡፡ ፈጣሪ ይህንን ያስብበት እንጂ፣ እኛ እንዴት ስለሞት እናስባለን? ከሞትን በኋላ የምንጨነቀው ለምንድነው? የሚለው አሉታዊ ተፅዕኖ አለው፡፡ መሠረታዊው ነገር ግን ኢንዱስትሪው በራሱ በኩል ፍላጎትን ሊያሟሉ የሚችሉ የመድን ሽፋን ዓይነቶች በእጁ አሉት ወይ? የሚለው ነጥብ ነው፡፡ ለምሳሌ ተጠቃሚዎች ከባንክ ይልቅ ገንዘባቸውን ኢንሹራንስ ላይ ቢያውሉ ጠቀሜታው የሚልቅበት ሁኔታ አለ፡፡ ለመድን ሽፋን የሚከፍሉት ገንዘብ የሞት ሥጋትንም ይሸፍናል፡፡ ባንክ ቤት ገንዘብ ባስቀምጥ መጨረሻ ላይ የሚሰጠኝ ትርፍ ገንዘብ ወለድ ነው፡፡ ለኢንሹራንስ ሽፋን የምታውለው ገንዘብ ግን ሞትንም ሸፍኖ እንደገና እንደ ኢንቨስትመንት ካፒታል የሚውልበት ብዙ አማራጮች ስላሉ፣ እንዲህ ያሉ አዳዲስ አሠራሮችን ፈትሾ ለገበያ ማቅረብ ይገባ ነበር፡፡ ነገር ግን ኢንዱስትሪው በራሱ በኩል ያሉትን ነገሮች በዚህ ረገድ ትርጉም ባለውና ለውጥ ሊያመጣ በሚችል መንገድ የሠራበት አይመስልም፡፡

ሪፖርተር፡- በብሔራዊ ባንክ ውስጥ የኢንሹራንስ ዘርፉን ሲከታተሉ ነበር፡፡ ከዚያም የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ሥራ አስፈጻሚም ስለነበሩ፣ ኢንዱስትሪው በገለጹት ዓይነት ቅርፅ አዳዲስ አሠራሮችን እንዲያተዋውቅ እርስዎ ምን ያደረጉት ነገር አለ?

አቶ የወንድወሰን፡- ኢንዱስትሪው ስል እኛም የኢንዱስትሪው አካል ነን፡፡ ሁላችንም በዚህ ረገድ በየጊዜው በቡድን የጀመርናቸው ሥራዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ ፕሮጀክቶችን ተደራሽ በሆነ ዋጋ ለተጠቃሚው የማቅረብ ሥራዎች ስንሠራ ነበር፡፡ እኔም ሁልጊዜ በምንጽፋቸው ጽሑፎች ውስጥ በተለይ የሕይወት ዘርፍ መቀጨጭ እጅግ እንደሚፀፅት ስጽንፍ ቆይተናል፡፡ ኢንሹራንስ በማክሮ ኢኮኖሚው ውስጥ ትርጉም ያለው ሚና የሚጫወተው፣ የሕይወት ዘርፍ በከፍተኛ ደረጃ ሲያድግ ነው፡፡ የሕይወት ኢንሹራንስ ድርሻ ሕይወት ነክ ካልሆነው በአንፃራዊነት ሲጨምር፣ ዘርፉ በኢኮኖሚው ውስጥ የሚጫወተው ሚና እየሰፋ ይሄዳል፡፡ ምክንያቱም አንድ ሰው የሕይወት ኢንሹራንስ ሲገዛና ዛሬ ላይ ክፍያውን ሲፈጽም፣ ገንዘቡን የሚጠይቀው ግን የዛሬ አሥር ዓመት ነው፡፡ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ይህንን ገንዘብ ዝም ብለው ይዘው አይቀመጡም፡፡ በተለያዩ የኢንቨስትመንቶች ውስጥ ይሳተፉበታል፡፡ በኢኮኖሚ ውስጥ ትርጉም ያለው ሚና እንዲጫወቱ ያስችላቸዋል፡፡ በአንዳንድ አገሮች ትልልቅ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ራሳቸው ፋይናንስ አድርገው ይሠራሉ፡፡ ለምሳሌ የፍጥነት መንገድ በተወሰነ ጊዜ ተስማምተው ሠርተው ገንዘባቸውን ከፍለው የሚወጡበት ሁኔታ አለ፡፡ በሌሎች ትላልቅ አገራዊ ፕሮጀክቶች ላይም ይሳተፋሉ፡፡ ይህንን ማድረግ የሚያስችላቸው ብዙ ጊዜ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የሚያሰባስቡት ገንዘብ ነው፡፡ ኩባንያዎቹ ባንክ ውስጥ ያላቸው ገንዘብ ይህንን ያህል ነው ይባላል፡፡ ይህ በአደራ የተያዘ ገንዘብ ነው፡፡ የሕዝብ ገንዘብ ነው፡፡ ይህንን ገንዘብ ካሳ የሚጠይቀው አካል ባስፈለገው ጊዜ እንዲከፈለው ሊጠይቅ ይችላል፡፡ ስለዚህ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች በጥንቃቄ ማስቀመጥ አለባቸው፡፡ የመድን ኩባንያው በባንክ ያለውን የአደራ ገንዘብ የፍጥነት መንገድ ሠርቶበት ከሆነና በተጠየቀ ጊዜ መክፈል ካልቻለ ግን ኩባንያው ከስሯል ማለት ነው፡፡ የሕይወት ዘርፍ መድን ግን የረዥም ጊዜ መድን ነው የሚባለው፡፡ አብዛኞቹ ኩባንያዎች ለ30 ዓመታትና ከዚያም በላይ ገንዘብ ይይዛሉ፡፡ ይህ ገንዘብ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ሊያስገኙ በሚችሉ ኢንቨስትመንቶች ላይ ይውላል፡፡ ይህንን ነገር ስንመለከተው በግምት በዓመት አንድ ቢሊዮን ብር ሊያመጣ የሚችል ቢዝነስ ነው፡፡ ሰፊ የገበያ ዕድል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ገበያው ሰፊ የገበያ ዕድል እንዳው ግልጽ ነው፡፡ ጥያቄው ግን ለምን መጠቀም አልተቻለም? ነው፡፡ የሕይወት ኢንሹራንስ ማደግ ያለበትን ያህል ለምን አላደገም?

አቶ የወንድወሰን፡-  አልተጠቀምንበትም፡፡ አንዱ ችግር የፈጠራ ነው፡፡ ኢንዱስትሪዎች እንዲጠቀሙበት የሚያስችሉ በፈጠራ ላይ የተመሠረቱ የመድን ምርቶች አልዳበሩም፡፡ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ለዚህ ነገር ትኩረት ሰጥተን አለመሥራታችን ሌላኛው ችግር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ አዲስ የሆነውን የጠለፋ መድን ሰጪ ኩባንያ እየመሩ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም አገሪቱ በጠለፋ ዋስትና የምትጠቀመው በምን አግባብ ነበር? የመጀመርያው የጠለፋ ዋስትና ኩባንያ እንዲቋቋም ሲደረግ ዋነኛ ዓላማው የውጭ ምንዛሪን መቀነስ ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር ምን እየሠራችሁ ነው? አጀማመራችሁስ የታሰበውን ነገር እያመጣ ነው?

አቶ የወንድወሰን፡- ጠለፋ ኢንሹራንስ በአጭሩ ሲገለጽ አንድ መድን ሰጪ ከመድን ገዥዎች የተቀበለውን የአደጋ ሥጋት ለሌላ መድን ሰጪ የሚያሳልፍበት አሠራር ነው፡፡ በዚህ ረገድ የጠለፋ መድንን የሚለየው፣ በመድን ገቢውና በመድን ሰጪው መካከል የተደረጉ ውለታዎችን በጠለፋ ዋስትናነት መያዙ ነው፡፡ እንደ አንድ ጠለፋ መድን ኩባንያ እኛ በቀጥታ የመድን ገበያውን አንቆጣጠርም፡፡ በመድን ገበያው የሚያመጣውን እኛ እንቀበላለን፡፡ ሆኖም መድን ገበያ ውስጥ የተፈጠሩ ነገሮች የጠለፋ መድኑንም ይመለከቱታል፡፡ እኛ እንደ አገር በ1970ዎቹ አካባቢ ብዙዎቹ በኢኮኖሚ ወደ ኋላ የቀሩ አገሮች በስንት መከራ ያገኙትን የውጭ ምንዛሪ ለመድን ሽፋን ብለው እንደገና ወደ ውጭ የሚያስኬዱበት አኳኋን ተገቢ አይደለምና የራሳቸው የሆነ የጠለፋ መድን ኩባንያ ያስፈልጋቸዋል ተብሎ በከፍተኛ ደረጃ ሲተዋወቅ ነበር፡፡ ግብፅና ጋና የራሳቸውን የጠለፋ መድን ኩባንያ አቋቁመው ነበር፡፡ የአገር ውስጥ ኩባንያዎች በሙሉ ያንን ሪስክ ለአንድ ብሔራዊ ለሆነ ኩባንያ ሲሰጡ በትክክልም ወደ ውጭ የሚወጣውን ገንዘብ ያስቀራሉ፡፡ በሌላ አንፃር ስናየው ደግሞ፣ የአደጋ ሥጋቱ በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል፡፡ ወደ ውጭ ከሚላከው ገንዘብ ምን ያህል አስቀርቻለሁ? የአደጋ ሥጋቱንስ? ከፍተኛ የአደጋ ሥጋት ቢኖር ምን ያህሉን ልሸፍን እችላለሁ? የሚለውን መመልከት ያስፈልጋል፡፡ ብዙውን ጊዜ የውጭ ምንዛሪ እጥረት በከፍተኛ ደረጃ ተፅዕኖ ስለሚያሳድርብን ሁላችንንም የውጭ ምንዛሪ ጉዳይ ያሳስበናል፡፡ በተለይ ለጠለፋ ዋስትና ተብሎ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ለማስቀረት ነው የምንነሳው፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ በአንድ ዓመት ውስጥ ይህንን ተልዕኮ ከማሳካት አኳያ እስካሁን ምን አደረጋችሁ? የጠለፋ መድኑ እዚህ በመቋቋሙ ምን ያህል የውጭ ምንዛሪ አስቀርተናል ትላላችሁ?

አቶ የወንድወሰን፡- የጠለፋ መድን ኩባንያው ሲቋቋም በወጣው ሕግ መሠረት ሁሉም የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ለውጭ ጠለፋ ዋስትና ሊያውሉ ከሚችሉት 25 በመቶውን በቀጥታ ለእኛ ይሰጣሉ፡፡ ከዚህም ሌላ ከእያንዳንዱ የኢንሹራንስ ውላቸው አምስት በመቶ ለእኛ መስጠት አለባቸው፡፡ ይህ አስገዳጅ ነው፡፡ ከኢንሹራንስ ኩባንያው አቅም በላይ ሲሆን ደግሞ ተጨማሪ የጠለፋ ዋስትናዎችን እንወስዳለን፡፡ ስለዚህ እንዲህ ባለው አሠራር ቢያንስ የአገር ውስጥ መድን ድርጅቶች ለውጭ ኩባንያዎች ይሰጡ የነበረውን 25 በመቶ የውጭ ምንዛሪ አስቀርተናል ማለት ይቻላል፡፡ ይህ ግን በቂ አይደለም፡፡ ፍላጎታችን ብዙ ድርሻ ይዘን ወደ ውጭ የሚወጣውን ገንዘብ ማስቀረት ቢሆንም፣ በእነዚህ መካከል ግን ሁልጊዜ ሚዛናዊ መሆን ያስፈልጋል፡፡ ብዙውን አስቀርተን፣ የውጭ ምንዛሪውን ቀንሰን ነገር ግን አንድ ያልተጠበቀ ነገር ቢከሰት፣ አንድ ያልተጠበቀ ነገር ቢመጣ ሁሉንም ነገር ጠራርጎ ከሚወስድብን ይልቅ በሁለቱም በኩል የምናደርጋቸው ጥረቶች ተመጣጣኝ መሆናቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ እንደ መጀመርያ ዓመት እንቅስቃሴያችን ብዙ የሚያስኬድ አይደለም፡፡ ባለፈው ዓመት የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ከሰበሰበው 7.1 ቢሊዮን ብር ውስጥ ለጠለፋ ዋስትና ኩባንያው በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት፣ የ25 በመቶን  በመውሰዳችን፣ ከዚሁ ጋር ተመጣጣኝ የውጭ ምንዛሪ ወጪ አስቀርተናል ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በገንዘብ የምን ያህል ይሆናል?

አቶ የወንድወሰን፡- የሰጠነውን የሽፋን መጠን በእርግጠኝነት መናገር አልችልም፡፡

ሪፖርተር፡- በአሠራራችሁ መሠረት የጠለፋ ዋስትና የሚገባላቸውና የማይገባላቸው ዘርፎች አሉ፡፡ ዓመታዊ ሪፖርታችሁ የሚያሳየውም አብዛኛው የጠለፋ ዋስትና የተገባለት የተሽከርካሪ ዘርፍ ነው፡፡ አሠራሩን ቢገልጹልኝ?

አቶ የወንድወሰን፡- አንድ የኢንሹራንስ ኩባንያ በተወሰነ ቀመር፣ ባለኝ ካፒታል፣ ባለኝ  ፖሊሲ፣ ከአንድ የአደጋ ሥጋት ለምሳሌ ከሞተር ላይ ለራሴ ማስቀረት የምፈልገው ሁለት ሚሊዮን ብር ነው ሊል ይችላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከአምስት እስከ ሰባት የሚሊዮን ብር የሚያወጡ ተሽከርካሪዎች አሉ፡፡ ይህ የኢንሹራንስ ኩባንያ የሰባት ሚሊዮን ብር ተሽከርካሪ መድን እንዲሰጥ ቢቀርብለት፣ የሁለት ሚሊዮን ብር ብቻ ካልሆነ አልቀበልም አይልም፡፡ የሰባት ሚሊዮን ብሩን ሽፋን ይወስድና በራሱ መንገድ ይጽፍና ሁለት ሚሊዮን ብሩን ይወስዳል፡፡ የቀረውን አምስት ሚሊዮን ብር ለጠለፋ መድን ኩባንያው ይሰጠዋል፡፡ ይህ ማለት አደጋው ቢደርስ ሁለት ሚሊዮን ብሩን የኢንሹራንስ ኩባንያው፣ አምስት ሚሊዮን ብሩን ደግሞ የጠለፋ መድን ኩባንያው ይከፍላሉ ማለት ነው፡፡ ይህ በዋጋ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በሚደርሰው ጉዳት ልክ የጠለፋ ዋስትና ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ ለወሰዳችሁት የመድን ሽፋን ዓረቦኑን (ፕሪሚየም) ትከፍላላችሁ ማለት ነው?

አቶ የወንድወሰን፡- አዎን፡፡ እንደተሸፈነው መድን፣ የተከፈለውን ዓረቦን ኩባንያውና እኛ እንካፈላለን ማለት ነው፡፡ ሌሎችም ብዙ ዓይነት አሠራሮች አሉት፡፡ በዚያ አሠራር መሠረት ኩባንያዎች ከጠለፋ መድን ሰጪው ኩባንያ ጋር ይሠራሉ፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ የተቋቋመው የጠለፋ መድን ኩባንያ ባለአክሲዮኖች፣ ባንኮችና የኢንሹራንስ ተቋማት ናቸው፡፡ ይህ ለምን ሆነ? እነዚህን በዋና ባለቤትነት ይዞ መቋቋሙ ከሌሎች አገሮች አደረጃጀት አኳያ ልዩነት አለው?

አቶ የወንድወሰን፡- አንድ ጽሑፍ እያየሁ ነበር፡፡ እንደ ጠለፋ መድን ኩባንያ መጀመርያ ስለመቋቋሙ የሚነገርለት ‹‹ኮለኝ ሪ ኢንሹራንስ›› የተባለው ኩባንያ ነው፡፡ ይህ ኩባንያ የተቋቋመው በኢንሹራንስና በባንኮች ነው፡፡ በእኛ አገር ሁኔታ ስናየው፣ ኢንሹራንስ ኩባንያ በራሱ እንደ ቢዝነስ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እንጂ ለአብዛኞቹ ገንዘብ ላላቸው ባለሀብቶች ይህን ያህል የሚስብ የቢዝነስ ዘርፍ አይደለም፡፡ ነገር ግን ኢንሹራንስና ባንክ ተመጋጋቢ አሠራሮች ያሏቸው ናቸው፡፡ ባንኮች ለሚያበድሩት ገንዘብ በሙሉ በመያዣነት የሚቀበሉት ንብረት ኢንሹራንስ ያልተገባለት ከሆነ፣ ብድር አይሰጡም፡፡ ስለዚህ ባንክና ኢንሹራንስ ዘርፉን ስለሚያውቁት፣ የኢትዮጵያ የጠለፋ መድን ኩባንያ አደረጃጀትም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ስለዚህ የጠለፋ መድን ኩባንያው የቢዝነስ ምንጭ የሆኑት አካላት ባንኮችና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ሲሆኑ፣ የጠለፋ መድን ሰጪው ኩባንያ ባለቤቶችም ናቸው፡፡ ጉዳዩን ጠንቅቀው የሚያውቁ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ዓመታዊ ሪፖርቶች ስናቀርብ ኪሳራ መመዝገቡን ገልጸናል፡፡ የኩባንያው ባለአክሲዮኖች ከኢንሹራንስ ቢዝነሱ ብዙ የራቁ ቢሆኑ ኖሮ፣ ጩኸት ሊፈጥር ይችል ነበር፡፡ ነገር ግን በተመሳሳይ ሥራ ላይ ያሉ ተቋማትን በባለቤትነት በመያዛችን ኪሳራ የተዘገበበትን ምክንያት በቀላሉ ተገንዝበውታል፡፡ ይህም ለኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ድጋፍ ይሰጣል፡፡ መንግሥት ይህንን ኩባንያ እንዲያቋቁሙ ሲያደርግ አገራዊ ራዕይ ይዞ ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው የጠለፋ መድን ሰጪው ኩባንያ በእነዚህ ኩባንያዎች ባለድርሻነት መመሥረቱ ጠቃሚ ወሳኝ መሆኑን ነው፡፡ የጠለፋ መድን ኩባንያ በእግሩ እስኪቆም ድረስ እገዛ እንደሚያስፈልገው ነው እንጂ ብዙም መነሻ ቢዝነስ ኖሮት አልተቋቋመም፡፡ ምክንያቱም በአስገዳጅ ሁኔታው ለጠለፋ መድን ሰጪው የሚገባ ገቢ አለ፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ የጠለፋ መድን ኩባንያ ሲቋቋም ታሳቢ የተደረገው የውጭ ገበያ ጭምር ነው፡፡ ነገር ግን እስካሁን ከውጭ ያገኛችሁት ገበያ የለም፡፡ ይህ ለምን ሆነ? ከዚህስ በኋላ ምንድን ነው የምታደርጉት?

አቶ የወንድወሰን፡- ይህንን ከተለያዩ አቅጣጫዎች ማየት አለብን፡፡ ለውጭ ገበያ ምን ያስፈልጋል ለሚለው አስፈላጊ ነው፡፡ የመጀመርያውና ትኩረት ሰጥተን መሥራት የሚኖርብን የገንዘብ አቅማችንን የሚለኩ ኩባንያዎች ደረጃ እንዲወጡልን ማድረጉ ላይ ነው፡፡ ያለንበትን ደረጃ መዝነው የብቃት ማረጋገጫ የሚሰጡ፣ የማበደርና የመበደር ብቃታችንን የሚመዝኑና የምዘና ውጤት የሚሰጡ (ኢንተርናሽናል ሬቲንግ) ተቋማት አሉ፡፡ የጠለፋ ዋስትና የምናስገባቸው ኩባንያዎች እንዲህ ያለውን የማረጋገጫ ሰነድ መመልከት አለባቸው፡፡ ማረጋገጫ የሰጠውን አካል ማወቅ ስለሚኖርባቸው ሬቲንጉን ማግኘት ግድ ይለናል፡፡ በስትራቴጂ ዕቅዳችን መሠረት፣ በሦስት ዓመት ውስጥ ይህንን ሬቲንግ ማግኘት አለብን ብለን አስቀምጠናል፡፡ ይህንን ሥራ ስትሠራ ያለህን አቅምና ብቃት የሚያረጋግጥልህን ሠርተፊኬት መያዝ አለብህ፡፡ ይህንን ለማግኘት ትመዘናለህ፡፡ ይህንን የምዘና ማረጋገጫ ካገኘን በኋላ የውጭው ገበያ ውስጥም እንገባለን፡፡

ሪፖርተር፡- ስለጠለፋ መድን ሥራ ሲነሳ በአፍሪካ ትልቁ የጠለፋ መድን ኩባንያ አፍሪካ (የአፍሪካ ጠለፋ መድን ኩባንያ) ነው፡፡ እዚህ ተቋም ውስጥ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ባለአክሲዮን ነው?

አቶ የወንድወሰን፡- የአፍሪካ የጠለፋ መድን ሰጪ ኩባንያን (አፍሪካ-ሪ) ያቋቋሙት የአፍሪካ መንግሥታት ናቸው፡፡ 43 አገሮች ሲያቋቁሙት ኢትዮጵያም አንዷ ነች፡፡ የኢትዮጵያ መድን ድርጅትም የኢትዮጵያን መንግሥትን ወክሏል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች