Tuesday, April 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምቱርክ በመፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራ ማግሥት

ቱርክ በመፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራ ማግሥት

ቀን:

በመፈንቅለ መንግሥቱ ማግሥት ቱርክ 6,000 ሰዎችን አስራለች፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 2,840 የሚሆኑት የጦር ሠራዊት አባላት ሲሆኑ፣ 2,745 ደግሞ ዳኞች መሆናቸው ተገልጿል፡፡ ወደ እስልምናው ሥርዓት እየተጠጋ ነው የሚባለው የኤርዶጋን መንግሥት ባልተሳካው መፈንቅለ መንግሥት ማግሥት አምስት የዜና ድረ ገጾችን መዝጋቱን የታይም ዘገባ ያመለክታል፡፡ የአገሪቱ ፍትሕ ሚኒስትር እንዳረጋገጡት አይኤስን ለመደብደብ አሜሪካ እየተጠቀመችበት ያለ የአየር ኃይል ጣቢያ ይመሩ የነበሩ ጄኔራሎች ከታሰሩት መካከል ናቸው፡፡ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራውን ተከትሎ በመንግሥት እየተወሰደ ያለውን ዕርምጃ ያጤኑ ተንታኞች ተቃዋሚዎቻቸውን በመምታት፣ የመገናኛ ብዙኃንን ነፃነት በመገደብ ኤርዶጋን አጋጣሚውን መንበራቸውን ለማጠንከር መጠቀም መጀመራቸውን እየገለጹ ነው፡፡ እየተወሰደ ያለው ዕርምጃ አገሪቱን ወደ አለመረጋጋት ሊመራት ይችላል እየተባለ ሲሆን፣ ይህ ደግሞ እየታመሰ ባለው የመካከለኛው ምሥራቅ የቱርክ አጋር የሆነችውን አሜሪካን ያሳስባታል፡፡ በዋሽንግተን የቅርብ ምሥራቅ ፖሊሲ ኢንስቲትዩት የቱርክ ምርምር ዳይሬክተር ሶነር ካጋብቲ ‹‹የተፈጠረው ነገር የሚያሳየው በቱርክ ጦር ኃይል ውስጥ ያለውን መፍረክረክ ነው፤›› ብለዋል፡፡ የኤርዶጋን ብርቱ እጅ መሆኑ ይነገርለት በነበረው፣ በውስጥም በውጭም ትልቅ ግምት በሚሰጠው በጦር ኃይሉ የተወሰደው ዕርምጃ አንድምታ ከባድ ነውም እየተባለ ነው፡፡ ይህ የጦር ኃይል በሰሜን አሜሪካ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ውስጥ በትልቅነቱ ሁለተኛው ነው፡፡ ከኢራን፣ ከኢራቅና ሩሲያ የሚዋሰን የጦር ኃይል ነው፡፡ ‹‹ስለዚህም በኔቶ ውስጥ ትልቅ ተፅዕኖ ባለው የጦር ኃይል ውስጥ መፍረክረክ መፈጠሩን አሜሪካ ፈጽሞ የማትፈልገው ነው፤›› ይላሉ ካጋብቲ፡፡ አሜሪካ ምንም ትፈልግ ምንም ግን በተሞከረው መፈንቅለ መንግሥት በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ እጇ አለበት በማለት ቱርክ አሜሪካ ላይ ጣቷን ቀስራለች፡፡ የዘ ኢኮኖሚስት ዘገባ እንደሚያመለክተው ከ1960ዎቹ ጀምሮ በቱርክ ጀነራሎች ሥልጣን ላይ በወጡ ቁጥር ቱርክ አሜሪካ ላይ ጣቷን የመቀሰር ልማድ አላት፡፡ የአሁኑም ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ የቱርክ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ሱሌማን ሶይሉ ፕሬዚዳንት ኤርዶጋንን ከሥልጣን ለማውረድ ከተደረገው ሙከራ ጀርባ አሜሪካ አለች ብለዋል፡፡ ባለፈው ዓርብ የተካሄደውን የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ተከትሎ ፕሬዚዳንት ኤርዶጋን እየወሰዱ ያለው ዕርምጃ አገሪቱ ከአሜሪካ ጋር ላላት ግንኙነት እንደ ማንቂያ ደወል እየሆነ ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱ በበኩላቸው ከመፈንቅለ መንግሥቱ ጀርባ አሉ ያሏቸውና በአሜሪካ ፔንሲልቫኒያ የሚገኙት የእስልምና ምሁሩን ፌቱላህ ጉለንን አሜሪካ አሳልፋ እንድትሰጣቸው ጠንከር ብለው ጠይቀዋል፡፡ ወንጀለኛን አሳልፎ የመስጠት ስምምነት በሁለቱ አገሮች መካከል በመኖሩ፣ አሜሪካም ይህን ታሳቢ አድርጋ ጉለንን ለቱርክ መስጠት ይኖርባታልም ይላሉ ኤርዶጋን፡፡ በቱርክ ለቀረበባት ወቀሳ አሜሪካ የሰጠችው ምላሽ መረር ያለ ይመስላል፡፡ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ አሜሪካ ከመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው ጀርባ አለች የሚባለው ነገር ሙሉ በሙሉ ሐሰት እንደሆነ፣ ለአገሮቹ የሁለትዮሽ ግንኙነትም መጥፎ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ጆን ኬሪ ከዚህ አልፈውም ኤርዶጋን አጋጣሚውን ተቃዋሚዎቻቸውን ለመጉዳት እንዳይጠቀሙበት አስጠንቅቀዋል፡፡ ‹‹ኤርዶጋን ይህን የሚያደርጉ ከሆነ ግን ከአውሮፓ፣ ከኔቶና ከሁላችንም ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት ችግር ውስጥ ይወድቃል፤›› ብለዋል ጆን ኬሪ፡፡ አሜሪካ በአውሮፓና በመካከለኛው ምሥራቅ መካከል ከምትገኘው ቱርክ ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት ለዓመታት ተግታለች፡፡ ቱርክ ደግሞ ለአሜሪካ ወሳኝ አጋር ነች፡፡ አይኤስ ላይ በተከፈተው ዘመቻ ከሶሪያ የስደተኞች ቀውስ ጋር በተያያዘ በኔቶ ጠንካራ አባልነትም ቱርክ ትልቅ ግምት የሚሰጣት አገር ነች፡፡ አሁን ግን ይህ ከቱርክ ጋር ያለ ትብብርና የአሜሪካ ፍላጐትም አብሮ ሊያከትምለት ነው ተብሎ እየተፈራ ነው፡፡ አንዳንድ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት የታሰሩት ሰዎች 7,000 የደረሰ ሲሆን፣ የመንግሥት ሠራተኞችንም ይጨምራል፡፡ 20 ሺሕ ያህል ሰዎችም ከሥራ መባረራቸው ይነገራል፡፡ ከተቃዋሚዎች ጋር ግንኙነት ያላቸው 11 የዜና ድረ ገጾችም በመፈንቅለ መንግሥቱ ማግሥት ተዘግተዋል፡፡ ነገር ግን በአሜሪካና በቱርክ መካከል ትልቅ ጉዳይ የሆነው ሚስጥራዊ የሙስሊም ቡድን ይመራሉ የሚባሉት የጉለን ጉዳይ ነው፡፡ ቱርክ ሰውዬው የመፈንቅለ መንግሥቱ ጠንሳሽ ናቸው ስትል፣ አሜሪካ ደግሞ ይህ በማስረጃ ይደገፍና የሰውዬው ተላልፎ ይሰጠኝ ጥያቄ ይቅረብ እያለች ነው፡፡ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራውን ተከትሎ የተፈጠሩት ነገሮች ሁለቱን አገሮች ፍጥጫ ውስጥ ቢከትታቸውም፣ አሜሪካ የኤርዶጋን አምባገነን የመሆን አዝማሚያ ቀድሞም እያሳሰባት ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፍትሕ ተቋማት፣ በመገናኛ ብዙኃን፣ በፖለቲካ ተቃዋሚዎችና በምሁራን ላይ የኤርዶጋን እጅ መክበድ ለአሜሪካ አሳሳቢ ነበር፡፡ ኤርዶጋን የሚያደርጉት ሁሉ ሥልጣናቸውን አንድ የስቴት ዲፓርትመንት ባለሥልጣን ለማጠናከር ነው በማለት፣ መንግሥታቸው ዴሞክራሲያዊ ያለመሆን ገጽታ ማሳየት ከጀመረ ውሎ ማደሩን ይናገራሉ፡፡ ከዚህ በላይ ኤርዶጋን በጀመሩት የአምባገነንነት ጐዳና እንዳይጓዙ አሜሪካና የአውሮፓ ባለሥልጣናት እያስጠነቀቁ ነው፡፡ ማስጠንቀቂያውን ካልሰሙ ግን ከኔቶ መታገድን ጨምሮ ሌሎች ቅጣቶችን እንደሚቀምሱ እየገለጹ ነው፡፡ ኤርዶጋን የሚወስዱት ዕርምጃ በቱርክና በአሜሪካ ግንኙነት ላይ አዲስ መስመር ሊያሰምር፣ አልያም እ.ኤ.አ. በ2017 የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የቤት ሥራ ይሆን ዘንድ በመካከለኛው ምሥራቅ ሌላ ራስ ምታት እንደሚፈጠር ተንታኞች እየገለጹ ነው፡፡ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው ታሪክ ሆኖ የሚቀር ሲሆን፣ ኤርዶጋን ለተፈጠረው ነገር የሚሰጡት ምላሽና ከዚህ በኋላ አገሪቱን መውሰድ የሚፈልጉት ወዴት ነው? የሚለው ቱርክ በቀጣይ ከአሜሪካና ከአውሮፓ ጋር የሚኖራትን ግንኙነት እንደሚወስን እየተገለጸ ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱ የሚደርሱበት ውሳኔ በተለይም ከወታደራዊ ትብብር አንፃር አንድምታው ቀላል እንደማይሆን እየተነገረ ነው፡፡ ሁለት የአሜሪካ መከላከያ ባለሥልጣናት ለሲኤንኤን እንደገለጹት፣ የአሜሪካና የቱርክ ወታደራዊ ትብብር ተወደደም ተጠላ እንደ አዲስ መቃኘት ይኖርበታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...