Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርትናንትን ስናስብ ነገን እናጣለን

ትናንትን ስናስብ ነገን እናጣለን

ቀን:

በጌታቸው አስፋው 

ለነገ የሚጠቅም ትናንት አለ፡፡ ለነገ የማይጠቅም ትናንትም አለ፡፡ ወደ ነገ ስለሚያራምደው ትናንት ዛሬ ማሰብ ጥቅም እንጂ ጉዳት የለውም፡፡ ለዛሬና ለነገ የማይጠቅመው ትናትን እንደ ታሪክነቱ መጠናት፣ መጻፍና መታወቅ ቢኖርበትም የትናንትን እያወራን በትናንቱ ዛሬ ከኖርንበት ከተጨቃጨቅንበት፣ ለነገ ሳንሠራ በከንቱ ካሳለፍነው ጊዜ ቆሞ አይጠብቀንምና የሚጠቅመውን ነገን እናጣለን፡፡ ‹‹የገደለው ባልሽ የሞተው ወንድምሽ ሐዘንሽ ቅጥ አጣ ከቤትሽ አልወጣ›› ሆነች የዚህ ዘመን ኢትዮጵያ፣ ከጭቅጭቅም አልፈን መሣሪያ ተማዘናል፡፡ የፖለቲካ ሰዎች ‘ጎበና እንዲህ አደረገ፣ ምኒልክ እንዲህ አደረገ፣ ጦና እንዲህ አደረገ፣ ኃይለ ሥላሴ እንዲህ አደረገ…’ እያሉ እርስ በርስ ይጎነታተላሉ፡፡ ሞሶሎኒ ሰው ስላልገደለባቸው ሳይሆን ዛሬ የሞሶሎኒ ልጆች መሬታቸውንና ሥልጣን ስለማይጋሯቸው፣ የሞሶሎኒን ስም በዓመት አንዴ የድል በዓልን ለማክበር ካልሆነ በክፉ አያነሱም፡፡ ወይም ጣሊያን የቆቃ ግድብን ለደም ካሳ ገድባ የሙት ስም በከንቱ እንዳይነሳ አደረገች፡፡ ከመቶ ዓመት በፊት የሞተን ሰው ስም እያነሱ ለራሳቸው የዛሬን ሥልጣን ለማመቻቸት ሰውና ሰውን በማጋጨት በፖለቲካ የሚነግዱ ሰዎች፣ ዛሬ ለሕዝብ ጥቅም መሥራት የሚገባቸውን አልሠሩምና ነገ የእነሱ አይደለም፡፡ ከዚህ በላይ የቀረበው መንደርደሪያ ሐሳብ ፖለቲካዊ ንድፈ ሐሳብን ከኢኮኖሚያዊ ቁሳዊ ሕይወት ውጪ በመመልከት፣ ለግል ሥልጣን ሲሉ ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት የሚመር የፀብ መርዝ የሚረጩ ሐሳባውያን ፖለቲከኞች ራሳቸው ተጎድተው ሕዝብንም እንዳይጎዱ የማሳሰቢያ ጽሑፍ መግቢያ እንዲሆነኝ ነው፡፡ አገር በቀል ሐሳባዊ ፖለቲካ በአገር ውስጥ የሚገኙ ሐሳባውያን ፖለቲከኞች በሚናገሩትና በሚጽፉት የፖለቲካ ወሬና መርዘኛ የፀብ ሐሳብ፣ ለዛሬና ለነገ የሚጠቅምና ዛሬና ነገን የሚገልጽ የኢኮኖሚ ጉዳይ ወይም የቁሳዊ ሕይወት መነሻ አጣሁበት፡፡ ሕዝቡን በሚቀልቡት በአዕምሯቸው ውስጥ በተፈጠረ ሐሳባዊ ፖለቲካ ወሬ ሲሻቸው የግል አርነትን ይሰብካሉ፣ ሲሻቸው በቡድን ይጠይቃሉ፣ ሲሻቸው የዛሬውን ፖለቲካ ትተው የትናንቱን ታሪክ መዝዘው ይጨቃጨቃሉ፡፡ ‘እኔ የአክስቱ ልጅ እያለሁ ለምን ባዕድ ያስተዳድረዋል?’ በሚል ጠባብ ፍልስፍናቸው ኢኮኖሚውን ትተው ስለፖለቲካው ብቻ እያወሩ፣ ለሕዝቡ ዳቦ የሚያስገኝ የኢኮኖሚ ኑሮ ብልኃት ይቅርና ቂጣ እንኳ መጋገር የማያስችል የኢኮኖሚ ዕውቀትና ብልኃት እንደሌላቸው ይጋለጣሉ፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አያት ቅድመ አያቶቻቸው በመርዝ ጭስ ያለቁባቸው አይሁዶችና ጀርመኖች በደላቸውን ረስተው በኢኮኖሚ ጥቅም ተሳስረው አብረው ይኖራሉ፡፡ በአንደኛውና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በመርዝ ጭስ የተጨራረሱ አውሮፓውያን አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ፈጥረዋል፡፡ ጃፓን የሂሮሺማና የናጋሳኪን የኃይድሮጂን ቦምብ ዕልቂት ረስታ ከአሜሪካ ጋር ጥብቅ ወዳጅ ሆናለች፡፡ ምዕራብ አፍሪካውያን ከቀድሞ ቅኝ ገዥዎቻቸው ፈረንሣዮች ጋር የጠበቀ ግንኙነት አላቸው፡፡ ምሥራቅ አፍሪካውያንም ከእንግሊዝ ጋር እንደዚሁ፡፡ የአፍሪካ ደም ያላቸው ባራክ ኦባማ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነዋል፡፡ ቁስላቸውን የጠገኑት በደም መላሽነት መልሰው በማቁሰል ወይም ሕዝብ ከሕዝብ ጋር ተጋጭቶ የትናንቱን በደል በዛሬ በቀል በማወራረድ ሳይሆን፣ ሠልጥነው ይቅር ለእግዚአብሔር ብለው በመተው ከፀብ ይልቅ ፍቅር እንደሚያሸንፍ ተረድተው ያመኑትን በመተግበር ነው፡፡ ከመቶ ዓመት በፊት ከሞተ ሰው ጋር ታግለው ለራሳቸው የዛሬን ሥልጣንና የነገን በታሪክ ታሳቢነት እየተመኙ ሰውና ሰውን በማጋጨት በፖለቲካ የሚነግዱ ሰዎች፣ ዛሬ ለሕዝብ ጥቅም መሥራት የሚገባቸውን አልሠሩምና ሥልጣንም አያገኙም፣ ነገም በታሪክ አይታወሱም፡፡ ከትናንት ወላጆቻቸው፣ ከዛሬ ቲፎዞዎቻቸው፣ ከነገ ልጆቻቸው በቀር ማንም አያውቃቸውም፡፡ ወንዝ ተሻጋሪ ሐሳባዊ ፖለቲካ ሌሎች ደግሞ አሉ፡፡ ከፈረንጆች ጋር አብረው ኖረው የፈረንጆቹን ሥልጣኔ ከእግር እስከ ራሱ የሚያውቁ ፖለቲከኞች እነሱ በኢንዱስትሪ ብልፅግና ከመሬትና ከተፈጥሮ ጥገኝነት ወደተላቀቁት አውሮፓውያን እንጀራ ፍለጋ ፈልሰው፣ በዘርም በቀለምም በማይመስሏቸው ነጮች አገር ይኖራሉ፡፡ የፈረንጆቹን ሥልጣኔ የአዕምሮ ብስለትና ትዕግሥተኛነት እንዳልሰሙ፣ እንዳላዩ፣ እንዳላወቁ ሆነው አያቶቻችን ተገዳድለዋል በሚል መርዛዊ የበቀል ቡድንተኝነት ተሰባስበው ሕዝብን ከሕዝብ ያጋጫሉ፡፡ እነሱ የፈረንጅ አገር የዜግነት ፓስፖርት ይዘው በነፃነት ሠርተው እየኖሩና በሰላም ወጥተው እየገቡ፣ እኛ በመንደር እንድንከፋፈል በቀበሌ መታወቂያ ላይ በሚጻፍ ብሔር ስም እንድንታወቅ ይሰብካሉ፡፡ ሰውና መሬት እንደ ወንድና ሴት ናቸው፡፡ እንደ ባልና ሚስት ካልተጋቡ ፍሬ አያፈሩም፡፡ እነሱ በፈረንጆች አገር የፈረንጆች መሬት አግብተው ለፈረንጅ አፈር ግጠው ላባቸውን አንጠፍጥፈው ጉልበታውን ሸጠው ፍሬ ያፈራሉ፡፡ ፈረንጆቹም ካፒታላቸውን እኛ አገር ይዘው መጥተው የእኛን መሬት አግብተው መኖር እየጀመሩ ነው፡፡ ሐሳባውያን ፖለቲከኞች ግን የደቡብም ሆነ የሰሜኑ ኢትዮጵያውያን ሰዎችና መሬት የሚያለማና የሚለማ አጥተው ፍሬ ሳያፈሩ መካን እንዲሆኑ ወንድማማቾች በጦርነት እንዲፋጁ ይሻሉ፡፡ የትናንቱን ታሪክ እየኮረኮሩ ሕዝባችን ስለሳይንስና ስለኢኮኖሚ አስቦ የትናንቱን ቁስል ረስቶ ወደ ነገ እንዳይራመድ ያደናቅፋሉ፡፡ አባ ሲመልና አመለካከታቸው እነ ዶክተር ፕሮፌሰር ማንትሴ የዚህ ዘመን ፖለቲከኞች ከሃምሳ ዓመት በፊት አርጅተው ከሞቱት ማንበብና መጻፍ ካልተማሩት፣ በሰብዕናቸው ግን የመንደር ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ ሰው መሆን ከሚችሉት አባ ሲመል ስላነሱብኝ ነው ይህን ፖለቲካ መሳይ የሰላ ትችት ጽሑፍ ላቀርብ የተገደድኩት፡፡ ዛሬ ያለውን ቁሳዊ ሕይወት የትግላቸው መነሻ ሳያደርጉ ከመቶ ዓመት በፊት የተፈጸመን ድርጊት የትግላቸው መነሻ ቢያደርጉ፣ የትግላቸው መድረሻ መቶ ዓመት ወደኋላ ይሆናል፡፡ በዛሬው ቁሳዊ ሕይወታቸው የሆዳቸውን ልክና የኑሮ ደረጃቸውን የዓለም ባንክ ሳይነግራቸው ራሳቸው ለክተው የትግላቸው መነሻ ካላደረጉ፣ መነሻና መድረሻ ያለው ትግል አይኖራቸውም፡፡ የትግላቸው መነሻም መድረሻም ከመቶ ዓመት በፊት ተፈጽሟል አብቅቷል ያለፈ ታሪክ ሆኗል፡፡ እናትና ልጅ ባለ ሁለት ውሻ ውስኪ ‹‹ከን ሰሬ ለማ›› ሙሉ ጠርሙሱን አሥር ብር በማይሞላ ዋጋ ማውረድ ያልቻሉ እነ አባ ሲመል፣ አዋቂዎችና የጅማ ከተማ ልጆች ‹‹ለማ ሰዲ›› በምንልበት በሃያ አምስት ሳንቲም ሦስት ብርሌ ንፁህ የማር ጠጅ በምንጠጣበት ጠጅ ቤት ነበር የምንገናኘው፡፡ ሕፃን አዋቂ ጥቁር ነጭ ደቡብ ሰሜን ተባብሎ መከፋፈል አልነበረም፡፡ ‘ኢሳ ጢሲ ዳዲ ቡሲ’ ይሉ ነበር አባ ሲመል እንደ ዛሬዎቹ ፖለቲከኞች ጠጅ ሊቀዳ በመጣ ቁጥር የፖለቲካ ወሬ ጣል ማድረግ የማይሰለቸው ጠጅ ቀጂ የፖለቲካ ወሬ እያበዛ ሲያላዝንባቸው፡፡ አባ ሲመል ፖለቲካ የማይገባቸው ሰው ሆነው አይደለም፡፡ የእሳቸው ፖለቲካ ማን ከየት መጣ ሳይሆን ሰው በሰላም ሠርቶ ኑሮውን በፈለገው መልክ መርቶ የመኖር ነፃነት አለው ወይ ብቻ ነው፡፡ እንደ አባ ሲመል የማር ጠጅ እየጠጣን ያደግን የጅማ ልጆችም አብሮ በመኖር አስተሳሰባችን ከዛሬ ዶክተር ፕሮፌሰር ፖለቲከኞች እንሻል ነበር፡፡ ዕድገቴ ማንነቴ ነው ወደ አያት ቅድመ አያት ሳልረማመድ በእናትና አባቴ ብቻ የሦስት ብሔረሰቦች ተወላጅ አባል መሆኔን በኢሕአዴግ ዘመን ባውቅም፣ ትውልዴና ዕድገቴ ከመላው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የተውጣጡትን ወልዳ ባሳደገችው ጅማ ከተማ ውስጥ ስለሆነ፣ እስከዛሬም ድረስ የምታወቀው የጅማ ልጅ በመባል ነው፡፡ በስምንት ዓመት ዕድሜዬ በጅማ ዙሪያ ወረዳ ትውልድ መንደሬ ቀይ አፈሯ ዲቱ ከተማ አጠገብ ላንጂቦ ድፍርስ ወራጅ ወንዝ ውስጥ ስንዋኝ፣ ከደራሽ ውኃ ያተረፈኝን ዛሬ በሕይወት የሌለውን የልጅነት ጓደኛዬን ቡልጉ አባ ጎጃምንና ጅማን እንዴት እረሳለሁ? ከዚህም የተነሳ በብሔር ብሔረሰብ ስም መጥራትና መጠራትን ነፍሴ ስለማትፈልግ፣ ይህን ለሐሳባውያን ፖለቲከኞች ማሳሰቢያ ጽሑፌን የማቀርበው ሰሜን ደቡብ በሚል የቦታ መጠሪያ ነው፡፡ የዚያን ዘመን ልጆች ስለከተሞቻችን ውበት ማውራትና ከተማን ከከተማ ማወዳደር በጣም እንወድ ነበር፡፡ በተለይ ደግሞ በዚያን ዘመን የከተማ አንበሳ አውቶቡስና በርካታ ዘመናዊ አውቶሞቢል ታክሲዎች የሚሽከረከሩባት ጅማ፣ በውበት ከኢትዮጵያ ከተሞች አራተኛዋ መሆኗን ለመስማትና ለማውራት በጣም ደስ ይለን ነበር፡፡ ጅማ ከአዲስ አበባ፣ ከአስመራ፣ ከድሬዳዋ ቀጥላ አራተኛዋ ውብ ከተማ መሆኗን መስማት እህል ከመብላት በላይ ያስደስተናል፡፡ ጅማ የውበት ከተማ እያልንም ዘምረናል፡፡ ዛሬማ ያኔ ጋቢ ከለበሰ በቀር ከተሜ ሰው አይታይባቸው የነበሩ እነ ሽሬ፣ መቀሌ፣ ጎንደር፣ ባህር ዳር፣ ደብረ ብርሃን፣ ሐዋሳ ቅልጥ ያሉ ከተሞች ሲሆኑ የኔዋ ጅማ ከነበረበችበት አንሳ የገጠር ከተማ መስላለች፡፡ ዛሬ የከተሞች ደረጃ ቢወጣ አርባኛ ደረጃም አታገኝም፡፡ ከአንድ ትውልድ በኋላ ደግሞ በከተማነት ደረጃ አራት መቶኛ ሆናለች፡፡ አባ ሲመል ሞቱ እንጂ በሕይወት ቢኖሩ ኖሮ በቀጭን ትዕዛዛቸው እንደ ጠጅ ቀጂው ‘ኢሳ ጢሲ ዳዲ ቡሲ’ ብለው ለትናንት ወሬ እንጂ ለነገ ሥራ ያልተፈጠረ ምላሳቸው፣ ከእጃቸው የረዘመ ፖለቲከኞችን ልክ ልካቸውን ይነግሯቸው ነበር፡፡ አባ ጂፋርና ፍልስፍናቸው ለጅማ ካለኝ ፍቅር እኩል እስከ ዛሬም ድረስ በኩራት የማስታውሰው ነገር የፈላስፋው አባ ጂፋር ታላቅነት ነው፡፡ ‘ሰሜኖች መሬታችንን ገዝተው ጨረሱብን’ ብለው ደቡቦች አቤቱታ ቢያቀርቡላቸው፣ ‘ምንቸገራችሁ ያልሙላችሁ ነቅለው ይዘውት አይሄዱ’ ብለው መለሱላቸው፡፡ እንዳሉትም የራስ መስፍን ስለሺ የነበረ አርባ ጋሻ የለማ የቡና መሬት ዛሬ የደቡብ ልጆች ንብረት ሆኗል፡፡ በአባ ጂፋር ፍልስፍና ሰው ተፈጥሮን (መሬትን) ያለማል እንጂ የመሬት ዕዳ ሆኖ አያውቅም፡፡ አራጋቢ ጠፍቶ አልተራገበላቸውም እንጂ የተናገሩትን ዘመን ተሻጋሪ ፍልስፍናዊ ንግግር ለዓለም ጆሮ የሚያደርስ ቢኖር ኖሮ፣ ከማንዴላ በፊት ሰዎች ዘር ቀለም ሳይለዩ ተስማምተው ቢኖሩ እንደሚጠቅማቸው የተናገሩት የእኛው አባ ጂፋር ናቸው፡፡ ኔልሰን ማንዴላ ነጮችና ጥቁሮች ሀብት አፍርተው በአንድነት እንዲኖሩ አድርግው የተደነቁበትን ሐሳብ የእኛው አባ ጂፋር ከመቶ ዓመት በፊት ተናግረዋል፡፡ የአያት ቅድመ አያቶቻችንን ጠቃሚ የፍልስፍና እሴቶች ለዓለም ጆሮ ማድረስ አልቻልንም፡፡ የተሰረቀው የቀድሞ ተማሪዎች ትግል ከእነዚያ ደረታቸውን ለጥይት ለመስጠት ካልፈሩ የንጉሠ ነገሥቱን ዙፋን ከገረሰሱ የ1960ዎቹ ወጣቶች ጀግና ትውልድ ውስጥ፣ ብዙዎች የአፍላ ዕድሜ ሐሳባቸውንና የትግል ሥልታቸውን ትክክለኛነትና ስህተት ሊገነዘቡ የሚያበቃ ዕድሜ አላገኙም፡ ቢሆንም ግን የቀድሞ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ ከጫፍ እስከ ጫፍ በኅብረት የተደረገ በመሆኑ ኢኮኖሚን ከፖለቲካ ቁሳዊ ሕይወትን ከንድፈ ሐሳብ በማጣመሩ ውጤቱ ባያምርም ግቡን መቷል፡፡ የመሬት ለአራሹ መፈክር በደርግም ቢሆን ተግባራዊ ተደርጓል፡፡ ከትግራዩ መለስ ተክሌ እስከ ወላይታው ሰለሞን ዋዳ፣ ከራያና አዘቦ የፊውዳል ዘሩ ጥላሁን ግዛው እስከ የበረንዳ እህል ነጋዴው የደሴ ልጅ ዋለልኝ መኮንን፣ ከኃይሌ ፊዳ የወለጋ ልጅ እስከ ግርማቸው ለማ የሰሜን ሸዋው፣ ሰሜኑ ከደቡብ ሁሉም በአንድነት አብረው ሲጮሁ አይተናል፡፡ የትግላችን መነሻ በመሬት ለአራሹ መፈክር ሥር ነቀል የሥርዓት ለውጥ ማድረግ፣ መድረሻችንም ለሕዝቡ ዘውዳዊና ባላባታዊ ሥርዓቱን ገርስሶ የቁሳዊ ሕይወት ለውጥ ያለው ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ መገንባት ነበር፡፡ ነገር ግን ከውስጣችን የመደብ ትግሉን በጠባብ የብሔር ትግል፣ ኢኮኖሚያዊ ትግሉን በፖለቲካዊ ትግል ሊቀይሩና አገር ሊገነጣጥሉ የከጀሉ ውስጥ ውስጡን የሚያሴሩ በቅለው ትግሉ ግቡን መቶ ሥርዓቱ ቢገረሰስም ፍሬ ሳያፈራ አመከኑት፡፡ ብዙዎችም ይህን የዓላማ ቅልበሳ ሳያዩ ሕይወታቸው አለፈች፡፡ ከጥላሁን ግዛው በቀር ሌሎቹን ሁሉ በአካል አውቃቸዋለሁ፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከመግባቴ ከሁለት ዓመት በፊት በትግል የተገደለውን ጥላሁን ግዛውንም ቢሆን ጅማ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሆኜ ለወራት ትምህርት አቁመን ሰላማዊ ሠልፍና ትዕይንትን በማድረግ፣ እንደ ዛሬው በጥይት ሳይሆን በአርጩሜ እየተገረፍን ሐዘናችንና አንድነታችንን ገልጸናል፡፡ የግርማቸው ለማንና የመለስ ተክሌን ዲስኩር በዩኒቨርሲቲው ቆይታዬ እንደ ውኃ ጠጥቼአለሁ፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ስሙን ከወረሱለት መለስ ተክሌ ጋር ከሰባ ደረጃ በላይ ናዝሬት የልጃገረዶች ትምህርት ቤት አጠገብ በሃምሳ ሳንቲም ዋጋ በባልትና ባለሙያ በጥንቃቄ ተዘጋጅቶ ለሞጃ የሚቀርብ የዶሮና የሥጋ አልጫና ቀይ ወጥ የሆቴል ምግብ ለወራት በአንድነትም ተመግበናል፡፡ ከትግሉ ጋር በተያያዘ በዩኒቨርሲቲው መረበሽ ምክንያት ትምህርቴን ለአንድ ዓመት አቋርጬ ቦሌ ጉምሩክ ስሠራ፣ ዋለልኝ መኰንን የአውሮፕላን ጠለፋ አድርጐ የተገደለ ዕለት አውሮፕላን ሲሳፈር የሰውነት ፍተሻ አድርጌ አሰናብቼዋለሁ፡፡ ተባብረሃልም በሚል በጊዜው ኮሎኔል ሰለሞን ከድር በሚመሩት ሰሜን ማዕከላዊ ምርመራ በሃያ ዓመት ዕድሜዬ ለሃያ ቀን ያህል ታስሬም ነበር፡፡ በጊዜው እንደ ፈላስፋ ይቆጠር የነበረውና ተከታዮቹ ከደቡብ ጫፍ እስከ ሰሜን ጫፍ፣ ከምሥራቅ ጫፍ እስከ ምዕራብ ጫፍ በሙሉ በእሱ ስም ፊዲስቶች ተብለው የሚጠሩበትን በስመ ገናናነቱ የማደንቀውን ኃይሌ ፊዳም በአካል አይቼዋለሁ፡፡ እነኚህ ከላይ የጠራኋቸው ጀግኖች በሙሉ ታግለው አልፈዋል፡፡ እኔ በእግዚአብሔር ፀጋ በሕይወት ቆሜ ስማቸውንና ሥራቸውን በአንዳንድ አጋጣሚዎች ይኸው ለማንሳት በቃሁ፡፡ ዛሬ ግን አንድነቱና ኅብረቱ ጠፍቶ ደቡቡ ሲመታ ሰሜኑ ይስቃል፣ ሰሜኑ ሲመታም ደቡቡ ይስቃል፡፡ የ1960ዎቹን ጀግኖች ትግል ያሸነፈው የዛሬው ጥፋት ተልዕኮ ክፉ መንፈስ የዚያው ዘመን መሰሪ ርዝራዦች ቡድንና ውላጁ ናቸው፡፡ ርዝራዦቹና ውላጆቹ ዛሬም የኢትዮጵያ ሕዝብ በዛሬው ቁሳዊ ሕይወት ዙሪያ ተሰባስቦ እንዳይታገል፣ በትናንቱ ፀብ እያላዘኑ ትርጉም የሌለው የቁራ ጩኸት ይጮሃሉ፡፡ ምላሳቸው እየረዘመ እጃቸው የሚያጥር ዶክተር ፕሮፌሰር ፖለቲከኞች በትናንቱ የእርስ በርስ ግጭት ነገር እያኘኩ ይኖራሉ፡፡ ሳይተዋወቁ እኔን የሚባባሉ ሰዎችን አጣሏቸው እንቅፋት የመታው ሰው ሲያጋጥም ከደቡብ ይሁን ከሰሜን፣ ከምዕራብ ይሁን ከምሥራቅ ሳይለዩ እኔን የሚባባሉ ሰዎችን ተማርን ያሉ ዶክተር ፕሮፌሰር ከፋፋዮች ሊለያዩዋቸው ፈልገው ብዕራቸውን አሾሉ፡፡ በአንተ ወይም በአንቺ ምትክ እኔን እንቅፋት ይምታኝ መባባል ቀላል የፍቅር ማሳያ አይደለም፡፡ በማኅበረሰባችን የሚታወቁ ሌሎችም ፍቅርና አዘኔታ የሚገለጽባቸው ቃላት አሉ፡፡ እኔን አፈር ይብላኝ ይባባላሉ በተለይም ሴቶች ለማያውቁት የተጎዳ መንገደኛ ሐዘኔታቸውን ሲገልጹ፡፡ በኦሮሚኛ ‘ደቼ አና ሀኛቱ’ በወላይትኛም ‘ታና ቢታ ሞ’ ይባባላሉ ሰሜኖችና ደቡቦች ለሰው በሰውነቱ ሲተዛዘኑ፡፡ በትግርኛም ‘ቅድመኸ ይስጠኸኒ’ ይላሉ ለክፉ ነገር ከአንተ በፊት ያድርገኝ ለማለት ሲፈልጉ፡፡ ሕዝብን በብሔር ከፋፍሎ አንዱ ለሌላው በተፈጥሮ ባህርይው መጥፎ እንደሆነ ጭራቅ አድርገው የሚስሉ ፖለቲከኞች፣ በእጅጉ ታሪክን ያጣምማሉ በማቀራረብ ፋንታ ያራርቃሉ፡፡ ክፉን እንጂ ደግ ደጉን ለመናገር ያልታደሉ ከፋፋይ ፖለቲከኞች በገሀድ በዓይን የሚታዩትን የዘመናት የሕዝብ ወንድማማችነት ሀቆችን ክደው እርስ በርስ ለማጋጨት የሚያደርጉት ግፊት ወደ ነገ ለመራመድ የሚደረገውን ጉዞ ያጓትታል፣ የሰውን ነፍስ ይቀጥፋል እንጂ ለማንም አይበጅም፡፡ ሐሳባዊ መርዝን በቁሳዊ መድኃኒት ማርከስ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በየዓመቱ በየካቲት ወር አዘውትሮ የሚያሳየው አንድ የ1960ዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴ አለ፡፡ ራሴን በምሥሉ ውስጥ ባላይም በጊዜው በቦታው እንደነበርኩ በዓይነ ልቦናዬ አያለሁ፡፡ እኔን ብቻ ሳይሆን ከዘመኑ መሪዎቻችንም አንዳንዶቹን አያቸዋለሁ፡፡ ፖሊስ እንዳይገባበት ሉዓላዊ በሆነው ዩኒቨርሲቲያችን በአራት ኪሎ ግቢ ውስጥና አጥር ላይ ተንጠላጥለን እንዘምር የነበረውና የዕለቱ መፈክራችንም ‘ጉልቻ ቢለዋወጥ ወጥ አያጣፍጥም’ ነበር፡፡ ንጉሡ ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድን ከጠቅላይ ሚኒስትርነት አውርደው የትራንስፖርትና መገናኛ ሚኒስትር የነበሩትንና በዕድሜያቸው ገና ጎልማሳ የነበሩትን ልጅ እንዳልካቸው መኰንንን ስለሾሙ፣ ስደተኛው መድኃኔዓለምን ለመሳለም ከቤተ መንግሥት ወደ ስድስት ኪሎ በአራት ኪሎ በኩል ሲያልፉ እንዲሰሙን ነበር በመፈክሩ የጮህንባቸው፡፡ ሁለቱም ጠቅላይ ሚኒስትሮች የሰሜን ሸዋ ሰዎች ቢሆኑም እኛ በብሔርና በዘር ሳንከፋፈል በሥርዓት ጉድለት ሁለቱንም አልፈለግንም፡፡ በዘራቸው ሳይሆን በሚያገለግሉት ሥርዓት ማንነታቸው ነበር ያልፈለግናቸው፡፡ ሁለቱም ሰዎች እጅግ የተማሩና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተመሰከረላቸው አዋቂዎች ነበሩ፡፡ ልጅ እንዳልካቸው ለተመድ ዋና ጸሐፊነት ዕጩ ተወዳዳሪ ሆነውም ነበር፡፡ ጥቂት ጉልቻዎች ይውረዱ ብለን የሹመት ንግግራቸውን በሙስናና በኪራይ ሰብሳቢነት ዲስኩር የሚያሟሹ ብዙ ሺሕ ጉልቻዎችን ፈጠርን፡፡ የቀድሞ ሚኒስትሮች ከአገር ማገልገል ወደ አኅጉር፣ ከአኅጉር አገልግሎት ወደ ዓለም አቀፍ አገልግሎት ነበር የሚጠሩት፡፡ ብር አምላኪ የዘንድሮ ሚኒስትሮች ከአገር አገልግሎት ወደ ቀበሌ ሊቀመንበርነት ወይም የክፍለ ከተማ መሬት አስተዳደር ሹምነት ሆነው የሚጠሩትና የሚያድጉት፡፡ ኃይለ ሥላሴን የጣለው የጭሰኛው ሥርዓት ቁሳዊ ኑሮ ሁኔታ ጫፍ ደርሶና የሕዝቡ ንቃተ ህሊናም በዚያው ልክ ሆኖ ነው፡፡ ደርግንም የጣለው የሶሻሊዝም መፍረክረክ ቁሳዊ ሕይወት ሁኔታ ጫፍ ደርሶ ነው፡፡ ኢሕአዴግንም የሚጥለው የኑሮ ውድነት፣ ሥራ አጥነት፣ ድህነትና የሀብት ክፍፍል መዛባት ቁሳዊ ሁኔታዎች ጫፍ ደርሰው እነዚህን ተረድቶ ለመተርጐም የሚያስችል በቁሳዊ ሕይወት ሁኔታ ላይ የተመሠረተ የኢኮኖሚ ንድፈ ሐሳብ ሲፀነስና ሕዝብም ተቀብሎ ሲታገልለት ነው፡፡ የግብርና ኢኮኖሚን መምራት ያቃተው፣ ያልተማሩ ሰዎችን መምራት ያቃተው፣ በጥቂቱ የሚረኩ ሰዎችን መምራት ያቃተው፣ ኋላቀር ኢኮኖሚን መምራት ያቃተው፣ ኢንዱስትሪውን፣ የተማሩ ሰዎችን፣ ብዙ የሚፈልጉ ሰዎችን፣ ዘመናዊ ኢኮኖሚን መምራት ይሳነዋል፡፡ ያኔ ሳይገፈትሩትም ‘የእናቴ ቀሚስ አደናቀፈኝ’ ብሎ ራሱ ይወድቃል፡፡ ሐሳባውያን እርም በሉ፡፡ እኔ እንደ ኢኮኖሚስት ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ሆኜ የምነግራችሁ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ለውጥ የሚመጣው ሕዝቡ ቁሳዊ ሕይወቱ ጎድሎ በኢኮኖሚው ሁኔታ ተማሮ አሻፈረኝ ሲል እንጂ፣ በእናንተ መርዝ ያዘለ በዘር ክፍፍል የተመሠረተ የሰከረ የፖለቲካ ሽኩቻ አይደለም፡፡ ሥርዓትን በጋራ መታገያ ጦሩ የኢኮኖሚውን ሁኔታ ለሕዝብ ማስረዳት እንጂ፣ ደጋግሞ የጎበናንና የምኒልክን የጦናንና የኃይለ ሥላሴን ስም መጥራት አይደለም፡፡ በእነ ምኒልክ ጭንቅላት ውስጥ ገብተን ትናንትን በትካዜ ስናስብ ነገን እናጣለን፣ ለሕዝቡም የነገውን ብርሃን እናጨልማለን፡፡ ሰላማዊ ፍልሰት ከደቡብ ወደ ሰሜን ከሰሜን ወደ ደቡብ ትምህርቴን ጨርሼ ከውጭ ከመጣሁበት ከ1977 ዓ.ም. ጀምሮ የኢትዮጵያ ጦር ልቅም ብሎ ወጥቶ ሻዕቢያ ኤርትራን ከተቆጣጠረ በኋላ ስድስት ወራት ያህል የጥይት ባሩድ የሌለበት አየር እየተነፈስኩ አስመራ ቆይቼአለሁ፡፡ ባንዲራ ወርዶ ሌላ ባንዲራ ሲሰቀል በዓይኔ ሳይሆን በልቤ አልቅሼና እርሜን አውጥቼ፣ በዓሉ ግርማ ኦሮማይን ከጻፈበት መኖሪያ ቤቴ ወጥቼ ከተከበሩ የመቶ አለቃ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ጋር ጠዋት ጠዋት የዕርምጃ ስፖርት የሠራንባቸውን የአስመራን ጎዳናዎች ለቅቄ በኅዳር ወር 1984 ዓ.ም. ነው ወደ አዲስ አበባ የመጣሁት፡፡ በኤርትራ ቆይታዬ እንደሰማሁት የኤርትራን ትግል የወለደው እድሪስ ዓወተ፣ ከብቶቹ ሱዳን ድንበር የሰው ማሳ ገብተው በአፈላማ ተይዘውበት ለአስመራ ሹማምንት እንዲያስለቅቁ ቢያመለክት የሚሰማው ሰው አጥቶ አንድ ጥይት ተኩሶ ወደ ሽፍትነት መግባቱ ነው፡፡ ቆይታ ቆይታ ይህች አንዲት ጥይት ብዙ ሺሕ የኢትዮጵያና የኤርትራ ልጆችን ሕይወት ከቀጠፈች በኋላ በኤርትራ ከኢትዮጵያ መገንጠል ተደመደመች፡፡ አያት ቅድመ አያቶቻችን ‘ቁጭ ብለው የሰቀሉት ቆሞ ማውረድ ያስቸግራል’ የሚሉት እንዲህ ለመሳሰለው ነገር ነው፡፡ ሐሳባውያን ፖለቲከኞች ቁጭ ብላችሁ የሰቀላችሁት ቆሞ ለማውረድ እንዳያስቸግራችሁ ተጠንቀቁ፡፡ ሃያ አምስት ዓመታት የዘለቀው የአባትህን መሬት አርሰህ ብላ የኢሕአዴግ የግብርና ፖሊሲ ሰዎች ለኑሮአቸው ከመሬት ጥገኝነት እንዳይላቀቁ አደረገ፡፡ የእናት የአባትህ ርስት ወዳልሆነ ያለ ክልልህ መጣህ ተባብለውም ሰዎች እንደ ጠላት ተያዩ፡፡ የመሬት አልሚ ሳይሆን የመሬት ዕዳ ሆነው ተቆጠሩ፡፡ አንድ የደብረ ማርቆስ ጓደኛዬ ሲያጫውተኝ አንድ ብዙ መሬት የነበራቸው የከተማዋ አዛውንት፣ መሬት ሳትበዪኝ ልብላሽ ብለው ሸጠው ቅርጥፍ አድርገው በልተው ቀልባቸውን አስደስተው ቀናቸው ደርሶ ሞት መጣና መሬት በተራዋ በላቻቸው ብሎ ነገረኝ፡፡ እሳቸው የመሬቷን አገልግሎት ሸጠው በሉ እንጂ መሬቷን ለሚቀጥለው ትውልድ እንዳትጠቅም ይዘዋት አልሄዱም፡፡ ሰው መሬትን ያለማል እንጂ መሬትን ነቅሎ ይዞ አይሄድም፡፡ የደቡብ መሬታችሁን ሰሜኖች ተሻሟችሁ ወይም የሰሜን መሬታችሁን ደቡቦች ተሻሟችሁ ብለው ጥላቻና ፀብን የሚሰብኩ ፖለቲከኞች በአሳሳች ፍልስፍናቸው፣ ደቡቦች መሬትን ከነፍሬዋ ሳይበሏት በመሬት እያስበሏቸው ነው፡፡ ለማያውቁት ቅድመ አያቶቻቸው እያለቀሱ የሚወዷቸውን ልጆቻቸውን እንዲቀብሩ አደረጓቸው፡፡ መርዘኛው የሐሳባውያን ፖለቲከኞች ጠባብ አስተሳሰብ የሚረክሰው በቁሳዊ ሕይወት ለውጥ ትግል መድኃኒትነት ነው፡፡ መታገል ለቁሳዊ ሕይወት ለውጥ እንደ የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ሰው ለመኖር በመጠየቅ ሲሆን፣ ይህም የሚሆበት ጊዜ የራሱ ሒደት አለው፡፡ እኛ ከሞትን በኋላ ቢሆን ሥልጣንና ስምን በታሪክ ማጻፍ እናጣ ይሆናል ብለው እንደፈሩት ወደ ነገ የሚሸጋገርም ሳይሆን ጊዜው ዛሬም ሊሆን ይችላል፡፡ በቴክኖሎጂ ዕድገት ሰዎች መሬትን ለእርሻ ሥራ ብቻ መፈለጋቸው ቀርቶ፣ ለኑሮ በመሬት ላይ ያለው ጥገኝነት ሲቀንስና ለእርሻ የማይጠቅመው ድንጋያማ የሰሜን መሬት ለኮንስትራክሽንና ለኢንዱስትሪ ተፈላጊ ማዕድን ሲሆን፣ ሰሜኖች ወደ ደቡብ ብቻ ሳይሆን ደቡቦች ወደ ሰሜንም ሰላማዊ ፍልሰት ያደርጋሉ፡፡ የአርሶ አደር መደብ በወዛደር መደብ ይተካል፡፡ የሕዝብ ንቃተ ህሊናም በዚያው መልክ ይለወጣል፡፡ ከመቶ ዓመት በፊት የነበረው በጦርነት የታጀበ የሀብት ፍለጋ ፍልሰት በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የፋብሪካ ሥራ ፍለጋ ሆኗል፡፡ ኢሕአዴግ ግብርና ግብርና እያለ ባያጓትተው ኖሮ በዚህ ሰላማዊ እንጀራ ፍለጋ ፍልሰት ሕዝባዊ ቅልቅሉና የወንድማማችነት ስሜቱ ዛሬ ወይም ከዛሬ ቀደም ብሎ በተፈጠረና በዘር ላይ የተንተራሰ የእርስ በርስ መጠላላቱ በቀረ ነበር፡፡ አንድ የፋብሪካ ባለቤትና ከልዩ ልዩ ብሔረሰቦች የተውጣጡ ሺሕ ወዛደሮች አብረው ሲሠሩ ሺዎቹን የሚያፋቅር፣ የሚያስተሳስርና በጋራ የሚያታግላቸው ዓላማ ይፈጠራል፡፡ ይህ ዓላማም ከኢኮኖሚያዊ ጭቆናና ከብዝበዛ ቀንበር ነፃ መውጣት ነው፡፡ በኢኮኖሚም በፖለቲካም ለውጥ እንዳይመጣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነቀርሳ ሆኖ አላፈናፍን ያለው የፖለቲከኞች ፍልስፍና ከደቡብ ወደ ሰሜንና ከሰሜን ወደ ደቡብ በሚደረግ ሰላማዊ ፍልሰት ሲረክስ፣ ያኔ በኢትዮጵያ ውስጥ የቁሳዊ ሕይወት ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ሕዝባዊ አመፅ ተቀስቅሶ የጭቆናና የብዝበዛ ሥርዓት ተወግዶ የሥርዓት ለውጥ ይመጣል፡፡ በቅርብ ጊዜ መካከለኛ ገቢ ውስጥ የመግባት ህልም እየከሸፈ ነው፣ ወሬው ከጠፋ ሰነባበተ፡፡ እንደ አቡነ ዘበሰማያት ጠዋት ማታ ይደገም የነበረው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ከተረሳ ከራረመ፡፡ የጋዜጦች ትኩስ ወሬ ክስረትና ጉድለት ሆኗል፡፡ የሴክተር መሥሪያ ቤቶች ለፓርላማው በሚያቀርቡት ሪፖርቶች ጭቅጭቅ ነጋ ጠባ ሆነ፡፡ የውጭና የአገር ውስጥ ኢንቬስተሮች አቤቱታ ፓርላማ ደርሷል፡፡ ኢሕአዴግ ብዙ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማርሽ ቀያየረ ከግብርና ወደ ጥቃቅን ከጥቃቅን ወደ የውጭ ኢንቨስተር ከውጭ ኢንቨስተር ወደአገር ውስጥ ኢንቨስተር ማርሽ መለዋወጡ ብዙም አልሠራም፡፡ እሳት የማጥፋት ማርሽ ስለሆነ እሳቱ በአንድ በኩል ሲጠፋ በሌላ በኩል ይቀጣጠላል፡፡ ምንም እንኳ በዚህ ዝቅተኛ የምርት ደረጃ ላይ ሆኖ የማምረት አቅም ጣሪያ ላይ ተደርሷል ለማለት ባይቻልም፣ የኢኮኖሚ ፖሊሲው ሊያሠራ ከሚችለው የማምረት ጣሪያ ጠርዝ ላይ ተደርሷል ሊባል የሚችልበት ሁኔታ ግን አለ፡፡ ሁለቱም የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶች ውስጥ የሚታየው ሀቅ መንግሥት የአገር ሀብት አስተዳዳሪ መሆኑንና ለግል ባለሀብቶች እየቆነጠረ እንደሚሰጥ ነው፡፡ የመሥሪያ ቦታ የሚሰጠው መንግሥት ነው፡፡ የመሸጫ ቦታ የሚሰጠው መንግሥት ነው፡፡ የባንክ ወለድን ጣሪያና ወለል የሚወስነውም መንግሥት ነው፡፡ ብድር የሚያመቻቸው መንግሥት ነው፡፡ የገበያ ትስስር የሚፈጥረው መንግሥት ነው፡፡ ይህ ሁሉ የሶሻሊዝም መርህ በካፒታሊዝም ውስጥ አልሠራ ማለት ሁኔታዎች ለለውጥ መብሰላቸውን የሚያመለክት ነው፡፡ ያልታገልንለትና ሕዝቡን በኢኮኖሚያዊ ኑሮው ዙሪያ ንቃተ ህሊናውን ሳናሳድግ በፊት ጊዜው ከፍቷል፡፡ የአገራችን ወቅታዊ ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ ሆኗል፡፡ የኢኮኖሚ አርነት ይቅደም ወይስ የጥንቱን የሚያስታውስ የፖለቲካ ሽኩቻ? ፖለቲከኞች የማንኛችሁም አካሄድ ፈሩን ሳይለቅ በፊት ሳይመሽ ሕዝብ እርስ በርስ በፀብና በክፉ ሳይፈላለግ በፊት ወስኑ፡፡ አቋማችሁን ግልጽ አድርጋችሁ ለሕዝብ አሳውቁ፡፡ በ1966 ዓ.ም. ጮኸን ተጯጩኸን ንጉሡን ስናወርድ ተረካቢ መኖር አለመኖሩን አላየንም ነበር፡፡ ትግላችንን ለወታደራዊ መንግሥት አስረክበን አረፍነው፡፡ በኢሕአፓና በመኢሶን አባልነት ተከፋፍለንም እርስ በርሳችን በቀይ ሽብርና በነጭ ሽብር ተላለቅን፡፡ ዛሬም ተመሳሳይ ሁኔታ ይታያል፡፡ የአሁኑ ከበፊቱም ይብሳል፡፡ የቀድሞ አንድነትና ኅብረት የለም፡፡ በብዙ ነገሮች ተከፋፍለናል፡፡ ጠንቀቅ እንበል፡፡ ልናደርገው ስለማንችለው ስላለፈው ትናንት እያሰብን ነገን እንዳናጣ፡፡ ቁጭ ብለው የሰቀሉትን ቆሞ ለማውረድ ያዳግታል፡፡ ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...