ሁለተኛው ‹‹ንባብ ለሕይወት›› የመጻሕፍት ዐውደ ርዕይ ከሐምሌ 14 እስከ ሐምሌ 17 ቀን 2008 ዓ.ም. በኤግዚቢሽን ማዕከል ይካሄዳል፡፡ በዐውደ ርዕዩ ከ123 በላይ ተሳታፊዎች የሚገኙ ሲሆን፣ አብላጫውን ቁጥር የሚይዙት አሳታሚ ድርጅቶች እንደሆኑ አዘጋጁ የንባብ ለሕይወት ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ቢንያም ከበደ ለሪፖርተር ገልጿል፡፡ በዐውደ ርዕዩ ለሽያጭ በሚቀርቡ መጻሕፍት ዋጋ ላይ ከ15 በመቶ እስከ 80 በመቶ ቅናሽ ተደርጓል፡፡ እንደ ቡክ ወርልድ ያሉ የመጻሕፍት መደብሮች የሚያቀርቧቸው በእንግሊዝኛ የተጻፉ ልብ ወለድ፣ ራስ አገዝና የሥነ ልቦና መጻሕፍት በ80 በመቶ ቅናሽ ይሸጣሉ፡፡ አዘጋጁ ‹‹አላማችን ብዙ ሰው ዐውደ ርዕዩን እንዲታደም ማድረግ ስለሆነ የመጻሕፍት ዋጋ ቅናሽ ላይ አትኩረን ሠርተናል፤›› ብሏል፡፡ በዐውደ ርዕዩ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ መጻሕፍት በሶፍት ኮፒ የሚቀርቡ ሲሆን፣ 40 ኮምፒዩተሮች ለአገልግሎቱ ተዘጋጅተዋል፡፡ ከመጻሕፍቱ መካከል ከኢትዮጵያ የእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ማኅበር የተሰጡ መጻሕፍት የሚገኙ ሲሆን፣ አብዛኞቹ የትምህርት ማጣቀሻ ናቸው፡፡ ቢንያም እንደገለጸው፣ መጻሕፍት አምና በሶፍት ኮፒ የሚወስዱ ሰዎችና የኮምፒውተር ቁጥር ባለመመጣጠኑ መጨናነቅ ተፈጥሮ ነበር፡፡ ‹‹በዚህ ዓመት የኮምፒውተር ቁጥር ከመጨመራችን በተጨማሪ በጎ ፈቃደኛ የኮምፒውር ሳይንስ ምሁራን ጥሩ ዳታቤዝ እንዲሠሩልን አድርገናል፡፡ ሰዎች በብዛት በሚመጡበት ሰዓት፣ አንድ ኮምፒውተር ላይ የተወሰነ ደቂቃ ብቻ እንዲጠቀሙ በማድረግ ለሁሉም እናዳርሳለን፤›› ብሏል፡፡ በዐውደ ርዕዩ እንደ ሊደርሺፕ ኢንስቲትዩትና ቅድስተ ማርያም ዩኒቨርሲቲ ያሉ የትምህርት ተቋሞች ይሳተፋሉ፡፡ በተጨማሪም በየቀኑ አዳዲስ መጻሕፍት ይመረቃሉ፡፡ የዶ/ር ተስፋዬ ሞላ የሥነ ልቦና መጽሐፍ ከሚመረቁት አንዱ ነው፡፡ ቅዳሜና እሁድ ጠዋት ልጆች ላይ ያተኮረ መርሐ ግብር ይካሄዳል፡፡ ወላጆች የልጆቻቸውን የንባብ ባህል ለማዳበር ምን ማድረግ አለባቸው በሚለው ጉዳይ በባለሙያዎች የሚመራ ውይይት ይካሄዳል፡፡ ልጆች ላይ ያተኮሩ ልዩ ልዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶችም ይቀርባሉ፡፡ በዐውደ ርዕዩ ለኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጉ ባለሙያዎች የሚዘከሩበት መርሐ ግብርም ይኖራል፡፡ ዮፍታሔ ንጉሴና አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ ስለ ሥራዎቻቸው ከሚነገርላቸው አንጋፎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ውይይት ከሚደርግባቸው ነጥቦች ውስጥ ጥሩ አንባቢ የሚገለጽባቸው መንገዶች፣ መጻሕፍቶች እንደየይዘታቸው የሚሰጡት ጠቀሜታ፣ የዕምነት ተቋሞችና የንባብ ባህል የተሰኙት ይጠቀሳሉ፡፡ ከተለያዩ የሃይማኖት ተቋሞች የተውጣጡ ምሁራን የዕምነት ተቋሞች የንባብ ባህልን በማጎልበት ረገድ ስላላቸው ሚና ንግግር ያደርጋሉ፡፡ ከኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ዶ/ር አባ ዳንኤል አሰፋ፣ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መጋቤ ሀዲስ እሸቱ አለማየሁና ሌሎችም እንደሚገኙ አዘጋጁ ተናግሯል፡፡ ከጀርመን ባህል ማዕከል (ጎተ) ጋር በመተባበር የሥነ ግጥም፣ የወግና ሌሎችም ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች ዐውደ ርዕዩ በሚካሄድበት ቦታ አመሻሽ ላይ ይቀርባሉ፡፡ በአምናው ዐውደ ርዕይ የንባብ አምባሳደሮች በዝግጅት ክፍሉ ተሾመው ነበር፡፡ ግለሰቦቹ ዘንድሮ ከትምህርት ሚኒስቴርና ከትምህርት ቢሮ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ይፈራረማሉ፡፡ ቢንያም፣ ‹‹በ2008 ዓ.ም. በየትምህርት ቤቱ በመዘዋወር የማነቃቂያ ንግግር በማድረግና በሌላም መንገድ ንባብ ተኮር እንቅስቃሴ ያደረጉት የንባብ አምባሳደሮች፣ ዘንድሮ ካደረጉት በበለጠ እንዲሠሩ ስምምነቱን ያደርጋሉ፤›› ሲል ገልጿል፡፡ የንባብ አምባሳደሮቹ አምና እንደ ክበበ ፀሐይ ላሉ የሕፃናት ማሳደጊያዎች የመጻሕፍት ድጎማ በማድረግና በመገናኛ ብዙኃን ንባብ ተኮር ዝግጅቶች ላይ በመሳተፍ ያደረጉት እንቅስቃሴ በ2009 ዓ.ም. ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግሯል፡፡