ዳግማዊት እመቤቷ፣ ‹‹ባገኛችሁት ትምህርት ራሳችሁንና ማኅበረሰባችሁን እንደምትለውጡ አምናለሁ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ከመጣሁባቸው ምክንያቶች አንዱም ይህንን ላረጋግጥላችሁ ነው፤›› በማለት ለተመራቂዎቹ ንግግር አድርገዋል፡፡ ሴቶች በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የሚያደርጉት ተሳትፎ ማደግ እንዳለበትና በአንድ አገር ዕድገት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ገልጸዋል፡፡ ‹‹ሴቶች ትምህርት ማግኘትና መሆን የሚፈልጉትን ዓይነት ሰው የመሆን ዕድል ሊፈጠርላቸው ግድ ይላል፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በዛው ዕለት ምሽት ላይ ዶ/ር ጂል ተመሳሳይ ንግግር በአሜሪካ ኤምባሲ ውስጥም አሰምተዋል፡፡ በተለያየ የሥራ ዘርፍ የተሰማሩ ሴቶች በተገኙበት መርሐ ግብር፣ ‹‹ሴቶች ለአገራቸው ዕድገት የሚያበረክቱት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እውቅና ሊሰጠው ይገባል፡፡ ማንኛውም ዓይነት ጾታዊ ጥቃት ሊደርስባቸውም አይገባም፡፡ አንድ አገር ሴቶች ሙሉ አቅማቸውን ካልተጠቀሙ ሙሉ በሙሉ አያድግም፤›› ብለዋል፡፡