Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያና የኡጋንዳ መፋጠጫ እየሆነች ነው

ደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያና የኡጋንዳ መፋጠጫ እየሆነች ነው

ቀን:

ከሁለት ሳምንት በፊት ዳግም በደቡብ ሱዳን ያገረሸውን ግጭትና አሳሳቢ ብጥብጥ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ኃይል በመጠቀምም ቢሆን ለመፍታት በወቅቱ የኢጋድ ሊቀመንበር ኢትዮጵያ አማካይነት የቀረቡት አማራጮች፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ በአፍሪካ ኅብረትና በአሜሪካ ጭምር ተቀባይነትን ቢያገኝም ኡጋንዳና የደቡብ ሱዳን መንግሥታት ግን ተቃርነውታል፡፡ ባለፈው ሳምንት ሐምሌ 5 ቀን 2008 ዓ.ም. የተሰበሰበው የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (IGAD) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም መሪነት ተሰብስቦ ካቀረባቸው የውሳኔ ሐሳቦች መካከል፣ በደቡብ ሱዳን የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ሰላም አስከባሪ ኃይል ሰላም መፍጠር የሚያስችለው ተዋጊ ኃይል በሥሩ እንዲያካትት እንዲፈቀድለት መጠየቁ አንዱ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት በደቡብ ሱዳን ጉዳይ የኢትዮጵያን አቋም እንዲያብራሩ ሪፖርተር ጥያቄ ያቀረበላቸው የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹የደቡብ ሱዳን ጉዳይ አሳሳቢ ሆኗል፣ ዳፋውም ለኢትዮጵያ ሰፊ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ደቡብ ሱዳን ‹‹ወደ ለየለት መተራረድ›› ውስጥ እየገቡ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ጌታቸው፣ ኢትዮጵያ እንደ ወቅቱ የኢጋድ ሊቀመንበርነቷ ብሎም በደቡብ ሱዳን የሚገኘው የተመድ ሰላም አስከባሪ ኃይል ዋና አዛዥ እንደመሆኗ በአሁኑ ወቅት የተፈጠረውን ቀውስ ጠንከር ያለ ዕርምጃ በመውሰድ መፍታት እንደሚያስፈልግ አቋም መያዟን አስረድተዋል፡፡ ይህንንም መሠረት በማድረግ ከኢጋድ አባል አገሮች ጋር ውይይት ተደርጐበት መስማማት ላይ እንደተደረሰና የተመድ የፀጥታው ምክር ቤትም ኢትዮጵያ፣ ኬንያና ሩዋንዳ ተጨማሪ ኃይል ለመላክ እንዲዘጋጁ ማሳወቁን ገልጸዋል፡፡ ይህንን መሠረት በማድረግ ኢትዮጵያ አስፈላጊውን ዕርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆኗን አስታውቀዋል፡፡ ባለፈው ሐምሌ 9 እና 10 ቀን 2008 ዓ.ም. የአፍሪካ ኅብረት 27ኛ መደበኛ ጉባዔውን በሩዋንዳ ዋና ከተማ ኪጋሊ ባደረገበት ወቅት ሌሎች ጉዳዮችን ሰርዘው በጉባዔው እንደተገኙ የተናገሩት የተመድ ዋና ጸሐፊ ባንኪ ሙን፣ የደቡብ ሱዳን መሪዎችን ወቅሰዋል፡፡ ባንኪ ሙን በሩዋንዳ ቆይታቸው ለአፍሪካ መሪዎች ባደረጉት ንግግር፣ የደቡብ ሱዳን መሪዎችና ከአገሪቱ ጦር ኃይል ኤታ ማዦር ሹም እስከ ታችኛው ሰንሰለት ያሉ ወታደራዊ መኮንኖች ለድርጊታቸው ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸው አስታውቀዋል፡፡ በይፋ ካደረጉት ንግግር በተጨማሪ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር የተወያዩ መሆኑን፣ የዋና ጸሐፊው ቃል አቀባይ በትዊተር ገጻቸው አረጋግጠዋል፡፡ የአገሪቱ የጦር ኃይሎች ዋና አዛዥ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ ኃይል መጠቀምን አስመልክቶ ያቀረቡትን አማራጭ ሙሉ ለሙሉ መቀበላቸውን ቃል አቀባዩ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሁለቱ አመራሮች በደቡብ ሱዳን ላይ የጦር መሣሪያ ማዕቀብ መጣል እንዳለበት፣ በደቡብ ሱዳን በተቀሰቀሰው ብጥብጥ ዋነኛ ተዋናይ የሆኑት አካላት ላይም ማዕቀብ መጣል፣ እንዲሁም በደቡብ ሱዳን የሚገኘውን ሰላም አስከባሪ ኃይል ማጠናከር እንደሚገባና ይህንንም ለፀጥታው ምክር ቤት በምክረ ሐሳብነት ማቅረባቸውን ጠቁመዋል፡፡ የተመድ ዋና ጸሐፊ ባንኪ ሙን በመቀጠል ከኡጋንዳ ፕሬዚዳንት ዮዌሪ ሙሴቬኒ ጋር የተናጠል ውይይት ማድረጋቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በዚህ ውይይታቸው ወቅትም ባንኪ ሙን ግልጽ አድርገው የተናገሩት ተመድ በደቡብ ሱዳን ላይ የጦር መሣሪያ ማዕቀብ እንደሚጥል፣ የግጭቱ ተሳታፊዎችን በመለየት ማዕቀብ መጣል፣ የደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ ጁባን ከጦር መሣሪያ ማፅዳትና ትጥቅ ማስፈታት ይገኝበታል፡፡ ከውይይቱ በኋላ የኡጋንዳን አቋም በተመለከተ የፕሬዚዳንት ሙሴቬኒ ጽሕፈት ቤት መግለጫ አውጥቷል፡፡ መግለጫው እንደሚጠቁመው ኡጋንዳ የታቀደውን የጦር መሣሪያ ማዕቀብ ፈጽሞ የማትቀበለው መሆኑን ነው፡፡ ‹‹የጦር መሣሪያ ማዕቀብ መጣል ማለት የአገሪቱን መከላከያ ኃይል ማፍረስ ነው፤›› በማለት ፕሬዚዳንቱ ተቃውማቸውን ገልጸዋል፡፡ በኪጋሊ በተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ስብሰባ ላይ ያልተሳተፉት የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ከጁባ ባወጡት መግለጫ፣ በኢጋድም ሆነ በተመድ ዋና ጸሐፊ የቀረበውን በደቡብ ሱዳን የተሰማራውን የሰላም አስከባሪ ኃይል ለማጠናከር ተጨማሪ ኃይል የማሰማራት ዕቅድን ፈጽሞ እንደማይቀበሉት በመግለጽ ላይ ይገኛሉ፡፡ በደቡብ ሱዳን የሚገኘው 12,000 የተመድ ሰላም አስከባሪ ኃይል በቂ መሆኑንም ይገልጻሉ፡፡ ይህ ንግግራቸውም በሌላ መንገድ ከኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ጋር አንድ ያደርጋቸዋል፡፡ የኡጋንዳ ፕሬዚዳንት ለአገሪቱ ጋዜጦች በሰጡት መግለጫ፣ የደቡብ ሱዳን መንግሥት ሰላም የማስከበር ዕርዳታ ከኡጋንዳ ከጠየቀ የአገራቸው ጦር እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ የኡጋንዳ ልዩ ፍላጐትን የመጋፈጥ ፈተና በግጭት ጉዳዮች ላይ ሰፊ ትንታኔዎችንና ምክረ ሐሳቦችን በመስጠት የሚታወቀው ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ፣ የኡጋንዳን ፍላጐት ፖለቲካዊም ኢኮኖሚያዊም ነው በማለት ይገልጸዋል፡፡ የኡጋንዳ ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ከሱዳን አቻቸው ፕሬዚዳንት ሐሰን ኦማር አል በሽር ጋር የቆየ ቁርሾ እንዳላቸው ይነገራል፡፡ የዚህ መነሻም ፕሬዚዳንት አል በሽር የኡጋንዳ አማፂ የሆነው ሎርድ ሬዚዝስታንስ አርሚን ከማስጠለል ባለፈ ትደግፋለች በሚል ነው፡፡ ለዚህ ምላሽም ኡጋንዳ የደቡብ ሱዳን ነፃ አውጪ ጦርን ስትደግፍ ቆይታለች፡፡ ይህ የቆየ ግጭት አሁንም ድረስ በመዝለቅ ሁለቱም ፕሬዚዳንቶች እያንዳንዱን የአዲሲቷን ደቡብ ሱዳን ውሳኔ መከታተልና ተፅዕኖ መፍጠር ይፈልጋሉ፡፡ ፕሬዚዳንት አል በሽር የደቡብ ሱዳን የወቅቱን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንትንና የሳልቫ ኪር ተቀናቃኝ ዶ/ር ሪክ ማቻር ፓርቲ የሆነውን ከደቡብ ሱዳን ነፃ አውጪ ጦር የተገነጠለውን ተቃዋሚ ቡድን በጦር መሣሪያ እንደሚረዱ፣ ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ በትንታኔው ገልጾታል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2013 የመጀመሪያው ግጭት በደቡብ ሱዳን ሲከሰትም ከየትኛውም የጐረቤት አገር ጦሯን ቀድማ በመላክ በደቡብ ሱዳን ዋና ጁባ ከተማ ያሠፈረችው ኡጋንዳ ነች፡፡ ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ በኢትዮጵያ ከዓመት በፊት ይፋዊ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት በጉዳዩ ላይ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ በደቡብ ሱዳን መጨራረስ እንዳይከሰትና የኡጋንዳን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ጦራቸውን መላካቸውን ገልጸዋል፡፡ በዚሁ የኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ወቅትም በደቡብ ሱዳን የሚገኘው የኡጋንዳ ጦር ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ጦርም እንደሚገኝ ለመጀመሪያ ጊዜ መግለጻቸውን ሪፖርተር በወቅቱ መዘገቡ ይታወሳል፡፡ ፕሬዚዳንት ሙሴቬኒ በወቅቱ እንደተናገሩት ከኢጋድ አባል አገሮች የሚውጣጣው ሰላም አስከባሪ ጦር ወደ ደቡብ ሱዳን ሲደርስ፣ የኡጋንዳ ጦር እንደሚወጣ ጠቁመው ነበር፡፡ ፕሬዚዳንቱ የተናገሩትን እ.ኤ.አ. በ2015 መጀመሪያ ላይ ተግባራዊ ቢያደርጉም፣ በቅርቡ በድጋሚ የኡጋንዳ ጦር ድንበር አቋርጦ ደቡብ ሱዳን በድንገት ተገኝቷል፡፡ ይህ የኡጋንዳ ድርጊት በኢትዮጵያ ከሚመራው የሰላም አስከባሪ ጦር ትዕዛዝ ውጪ ከመሆኑም በላይ፣ ዓላማው ምን እንደነበር በግልጽ እንደማይታወቅ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቲክ ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ይህም በኢትዮጵያ መንግሥት መሪነትና በኢጋድ አባል አገሮች በተለይም በኬንያና በሩዋንዳ ተሳትፎ የሚደረገውን ሰላም የማስከበርና የሰላም ስምምነቱን የመተግበር ኃላፊነት የሚያስተጓጉል መሆኑን ምንጮች ይገልጻሉ፡፡ የደቡብ ሱዳን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሪክ ማቻር ፓርቲ (SPLM/IO) የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኮአት ጋቱት ለሪፖርተር በላኩት መግለጫ፣ የኡጋንዳ ጦር ከፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ታማኝ ወታደሮች ጋር በመሆን የፓርቲያቸውን ወታደሮች እየወጉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ የኡጋንዳና የደቡብ ሱዳን ድንበር በሆነችው ኒሙል ሙሉ በሙሉ የኡጋንዳ ጦር መቆጣጠሩን፣ እንዲሁም በጁባ የኡጋንዳ ጦር መስፈሩን መግለጫው ያስረዳል፡፡ የኡጋንዳ ፕሬዚዳንት ግን ጦራቸው ወደ ደቡብ ሱዳን የገባው በደቡብ ሱዳን የሚገኙ በርካታ የአገሪቱ ዜጐች የግጭቱ ሰለባ እንዳይሆኑ ለማስወጣት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ኡጋንዳ በደቡብ ሱዳን ያላት ሌላ ፍላጐት ኢኮኖሚያዊ መሆኑን የሚያሳየውም ይኼ ነው፡፡ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ነጋዴዎች በደቡብ ሱዳን የሚንቀሳቀሱ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በኡጋንዳ ታዋቂ የሆነው ዘ ሞኒተር ጋዜጣ ሰሞኑን እንደዘገበው፣ በደቡብ ሱዳን በተከሰተው ግጭት ኡጋንዳ በየቀኑ 3.3 ቢሊዮን የዩጋንዳ ሽልንግ ወይም አንድ ሚሊዮን ዶላር እያጣች ነው፡፡ ኡጋንዳ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሟን ለማስከበር በደቡብ ሱዳን የረዘመ እጇን በሰደደችበት በአሁኑ ወቅት፣ በአካባቢው ሰላም ማስፈንን ዋነኛ ተልዕኮና ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ፍልሰት የመቀነስ ድርብ ዓላማ ያደረገችው ኢትዮጵያ በሶማሊያ፣ በሱዳን፣ በሱዳንና በደቡብ ሱዳን አዋሳኝ በሆነችው አቢዬ የተጣለባት የሰላም የማስከበር ኃላፊነት አለባት፡፡ በተጨማሪም በኤርትራ በኩል ካለባት የደኅንነት ሥጋት በተጨማሪ በደቡብ ሱዳን ሌላ ፈተና ከኡጋንዳ ጋር ገጥሟታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...