– የግል አየር መንገዶች በነዳጅ እጥረት ተቸግረናል ይላሉ
– ሕገወጥ ደላሎችና ዕቃ ጫኞች በኤርፖርት ውስጥ ማስቸገራቸው ተገለጸ
የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ከሚያስተዳድራቸው ልዩ ልዩ የመንገደኞች አገልግሎት መስጫ ተቋማት መካከል የሚጠቀሱት የንግድ ሱቆችን በጨረታ ማስተላለፍ ቢጀምርም፣ ለወራት ያሸነፏቸውን ሱቆች መረከብ ያልቻሉ ተከራዮች ቅሬታቸውን ገለጹ፡፡ የኤርፖርቶች ድርጅት በጨረታ የሚያከራያቸው ሱቆች ላይ ቅሬታ የተነሳው አሸናፊዎች በተገባላቸው ቃል መሠረት ሱቆቻቸውን ሊረከቡ ካለመቻላቸውም በላይ ጥያቄ ሲቀርብም ቀድመው በሌሎች ተይዘው የነበሩ ሱቆችን ማስለቀቅ ባለመቻሉ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል፡፡ የአገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመንና ለደንበኞችም እርካታ የሚሰጥ አገልግሎት ለማቅረብ በማለት ማክሰኞ ሐምሌ 12 ቀን 2008 ዓ.ም. ድርጅቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በዋናው መሥሪያ ቤት በተካሄደ ስብሰባ ወቅት እንደተነሳው፣ ተከራዮች ያሸነፉባቸውን ቤቶች በጊዜ ለመረከብ ባለመቻላቸው ምክንያት ላልተገባ ወጪና የባንክ ዕዳ ተዳርገዋል፡፡ ከተከራዮች መካከል ሕወይት ለማ ትሬዲንግ የተባለው ኩባንያ ያነሳው ቅሬታ ይጠቀሳል፡፡ ኩባንያው ኤርፖርቶች ድርጅት ከዚህ በፊት ለሱቅ ኪራይ ባወጣው ጨረታ ተሳትፎ፣ ውል ፈርሞና ገንዘብ አስይዞ ከግንቦት ወር ጀምሮ ለመረከብ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡ ይሁንና በጨረታ ያሸነፈበትን የንግድ ቤት እስከ ሰኔ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. ኤርፖርቶች ድርጅት መፍትሔ እንደሚሰጠው አስታውቆት እንደነበር፣ ነገር ግን እስካሁን ማቅረብ እንዳልቻለ አስታውቋል፡፡ ኤርፖርቶች ድርጅት ቦታውን የያዙት አካላት ሊወጡለት እንዳልቻሉ እንደገለጸለት የንግድ ድርጅቱ ጠቅሶ፣ ቤቱን ተረክቦ ሥራ ሊጀምር ባለመቻሉ የባንክ ዕዳና ሌሎችም ወጪዎች እየተከማቹበት እንደሚገኙ አስረድቷል፡፡ የኤርፖርቶች ድርጅት የኤርፖርት ፋሲሊቲዎች ዳይሬክቶሬት በሰጠው ምላሽ፣ ሕይወት ለማ ትሬዲንግ ያነሳውን ዓይነት ጥያቄ ያላቸው የንግድ ድርጅቶች በጨረታ ያሸነፏቸውን ቤቶች ለመረከብ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ አስረድቷል፡፡ ከኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅት ጋር ያለው የፍርድ ቤት ክርክር አንዱ ምክንያት መሆኑን አስታውቋል፡፡ በኤርፖርቶች ድርጅት የገበያ ልማት ዳይሬክተር አቶ ፀጋዬ ብርሃነ በበኩላቸው፣ በጨረታ ሒደት ተሸንፈው አንወጣም ያሉ በርካታ ተከራዮች ማስቸገራቸውንና ሕግ ማስከበር እንዳልተቻለ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ሦስት አራት ቦታ የያዙ ሰዎች በጨረታ ሲሸነፉ ፍርድ ቤት ሔደው በመክሰስ እያደናቀፉ ነው፡፡ በተለያየ ሽፋን ተጠቅመው የዕድሜ ልክ ርስት ይመስል ላለመልቀቅ የሚያስፈራሩ፣ የሚሳደቡ ተከራዮች አስቸግረዋል፤›› ያሉት አቶ ፀጋዬ፣ ጨረታ ተጭበርብሯል የሚሉ ካሉ ወይም ደግሞ በአድልዎ የሚሠሩ ባለሙያዎች ካሉ እንዲጠየቁ ማደረግ እየተቻለ ያላግባብ ጫና ለመፍጠር በሚራወጡ ነጋዴዎች ላይ መፍትሔ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡ ይህ በዚህ እንዳለ የግል አየር መንገድ ኩባንያዎች በኤርፖርቶች አካባቢ የነዳጅ አቅርቦት እንደ ልብ ለማግኘት እንዳልቻሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡ ናሽናል ኤርዌይስና አቢሲንያ የበረራ አገልግሎትና የአቪዬሽን አካዳሚ ተወካዮች እንደገለጹት፣ ነዳጅ ለመሙላት ተቸግረዋል፡፡ የቻርተር አገልግሎት እየሰጡ ቢሆንም ደንበኞቻቸው የሚስተናገዱት በመደበኛው የተጓዦች ማስተናጋጃ በኩል ተሠልፈው መሆኑ በቻርተር አውሮፕላኖች የሚስተናገዱ ተሳፋሪዎች ላይ ቅሬታ አሳድሯል ብለዋል፡፡ በዴዴሳ ኤርፖርት የተከማቹ፣ ከዓረብ አገር ተመላሾች የተወረሱና ሌሎችም በርካታ ቁሳቁሶችም እክል እየፈጠሩ ከሚገኙ የጄኔራል አቪዬሽን ጋር የተያያዙ የአገልግሎት ጥያቄዎች ሆነዋል፡፡ የኤርፖርቶች ድርጅት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ሕይወት ሞሲሳና ባልደረቦቻቸው በሰጡት ምላሽ፣ በተለይ በዴዴሳ ኤርፖርት የተከማቸውን ዕቃ በሚመለከት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጉዳዩን በመከታተል ላይ እንደሚገኝና በቅርቡ መፍትሔ እንደሚሰጠው አስታውቀዋል፡፡ በነዳጅ አቅርቦት መስክም ያሉት ችግሮች እንደሚፈቱ፣ ለግል አየር መንገዶች ደንበኞች የተለየ መግቢያ በርና የአውሮፕላኖች መንደርደሪያ እንዲዘጋጅ ሲቀርቡ የነበሩ ጥያቄዎችም ምላሽ እንደሚያገኙ ጠቁመው፡፡ የቢጫ ታክሲዎች ማኅበር ተወካዮች ደጋግመው ካሰሟቸው ቅሬታዎች መካከል፣ በአዲስ አበባ ቦሌ ኤርፖርት የሚታየው በሕገወጥ ደላሎችና ዕቃ ተሸካሚዎች በተሳፋሪዎች ላይ የሚደርሰው ዝርፊያና ወከባ ይጠቀሳል፡፡ የቢጫ ታክሲዎች ማኅበራት ሰማያዊ ታክሲዎች ወደ ኤርፖርት እንዲገቡ የሚፈቀድላቸው ጭነው እንዲወጡ ሳይሆን ጭነው ያመጧቸውን ተሳፋሪዎች አራግፈው እንዲወጡ ቢሆንም፣ ዓመቱን ሙሉ ግን በኤርፖርት ውስጥ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ስላሉ እንዲወጡ ይደረግልን በማለት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ የተባባሰው ዝርፊያ በተለይ ከዓረብ አገር ተመላሾች ላይ ያነጣጠረና በሞባይል ስልኮች የታገዘ ማታለልና ማጭበርበርን እንደሚያካትት በመግለጽ መፍትሔ እንዲሰጥበት ተጠይቋል፡፡ ኤርፖርቶች ድርጅት በበኩሉ እንዲህ ያሉ ስሞታዎች በማስረጃ ተደግፈው፣ የሰሌዳ ቁጥሮች ጭምር እንዲሰጡት ጠይቆ በዚህ መሠረትም መፍትሔ እንደሚሰጥ አስታውቋል፡፡ ሆኖም ቢጫዎቹ ታክሲዎች በአሁኑ ወቅት የዋጋ ተመን አውጥተው እየሠሩ እንደሚገኙ፣ በቅርቡም ወደተለያዩ አካባቢዎች ለሚያሳፍሯቸው ተገልጋዮች በዲጂታል የዋጋ መግለጫ መረጃዎችን ማሠራጨት እንደሚጀምሩ አስታውቀዋል፡፡ በሌላ በኩል ኤርፖርቶች በዚህ ዓመት 8.5 ሚሊዮን መንገደኞችን በማስተናገድ ያሳየውን ውጤት በመጪው ዓመት በማሻሻል ከአሥር ሚሊዮን ያላነሱ መንገደኞችን ለማስተናገድ መዘጋጀቱን ወ/ሮ ሕይወት ተናግረዋል፡፡ የመንገደኞች ማስተናገጃ ተርሚናል የማስፋፊያ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ከ20 ሚሊዮን ያላነሱ መንገደኞች በዋናው የአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት በኩል ይስተናገዳሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ወ/ሮ ሕይወት ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ድርጅቱ በቦሌ የመንገደኞች ማስተናገጃ አማካይነት በአሁኑ ወቅት እስከ 8.5 ሚሊዮን ተጓዦችን ከማስተናገድ ባሻገር ዘመናዊ አገልግሎቶችን ለማቅረብ እየሠራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡ ባለፈው ዓመት የኤርፖርት መኪና ማቆሚያ አገልግሎትን እንዲያስተዳድር የተቀጠረው የአሜሪካው ዩ ስትሪት ፓርኪንግ የተባለው ኩባንያ ያከናወናቸውን ተግባራትም ካሳወቁት መካከል ሲሆን፣ ኩባንያው ለፓርኪንግ የተመደበለት ቦታ ከፍተኛ ጥበት እንዳለበት በኢትየጵያ የድርጅቱ ኃላፊ አቶ ተኮላ መሰለ ገልጸዋል፡፡ አቶ ተኮላ ለሪፖርተር እንዳብራሩት፣ በቀን ከ500 ያነሱ ተሽከርካሪዎችን ለማስተናገድ የተከለለው ማቆሚያ፣ በአሁኑ ወቅት እንደምንም ከ3,000 ያላነሱ ተሽከርካሪዎችን እንዲያስተናግድ ተደርጓል፡፡ ይብሱን ደግሞ ለአዲሱ ማስፋፊያ የተከለለው ቦታ የመኪና ማቆሚያ ቦታ ጥበትን አስከትሏል ብለዋል፡፡