በመላ አገሪቱ በዘንድሮ የክረምት ወቅት 13 ቢሊዮን ብር ወጪ የተደረገባቸው 4.3 ቢሊዮን ልዩ ልዩ ዓይነት የዛፍ ችግኞች ተከላ ይፋ ሆነ፡፡ ከአዲስ አበባ እስከ አዳማ በተዘረጋው የፈጣን መንገድ ግራና ቀኝ ዳርቻዎች ላይም የዛፍ ችግኞች ተከላ ተካሄደ፡፡ የአገር አቀፍ ችግኝ ተከላ ይፋ የሆነውና በዳርቻዎች ላይ ተከላ የተካሄደው ሐምሌ 9 ቀን 2008 ዓ.ም. በተከናወነው ሥነ ሥርዓት ነው፡፡ ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር በሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት የአገር አቀፉ የችግኝ ተከላ የሚከናወነው በአንድ ሚሊዮን ሔክታር መሬት ላይ ሲሆን፣ ለተግባራዊነቱም በየክልሎች ከሚገኙና ጉዳዩ በይበልጥ ከሚመለከታቸው የሕዝብ ክንፎች ጋር ምክክር ተደርጓል፡፡ በዚህም መሠረት እንደየአካባቢው የዝናብ ሁኔታ ቀደም ብለው መትከል የጀመሩ አካባቢዎችና ክልሎች ቢኖሩም በግለሰብ፣ በማኅበረሰብና በተቋም ሰፊ የተከላ ሥራ በተያዘው ወር የሚፈጸም ይሆናል፡፡ የአዲስ አበባ አዳማ የፈጣን መንገድ በሚሸፍነው 76 ኪሎ ሜትር ግራና ቀኝ ዳርቻዎች ላይ የተተከሉት ችግኞች ለሥነ ምኅዳሩና ለመንገዱ ተስማሚ የሆኑና በጥናት የተለዩ ዘጠኝ የዛፍ ዝርያዎች ናቸው፡፡ ጥናቱ የተከናወነው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከክፍያ መንገዶች ኢተርፕራይዝ፣ ከአካባቢ ደን ምርምርና ከኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩቶች ጋር በመተባባር ነው፡፡ የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣንና የኦሮሚያ ክልል የምሥራቅ ሸዋ ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት ለተከላው የሚያስፈልገውን ችግኝ በነፃ በማቅረብ ላቅ ያለ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን አስረድተዋል፡፡ ከዶ/ር ሽፈራው ገለጻ ለመረዳት እንደተቻለው በተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ፣ በአፈርና ውኃ እቀባ 12 ሚሊዮን ሔክታር ለምቶ ከንክኪ ነፃ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ይህ ውጤት ሊገኝ የቻለውም ሕዝቡ በሙሉ ፈቃደኝነቱ ከ30 እስከ 40 ቀናት ያህል ጊዜውን ሰውቶ በልማቱ ላይ በመረባረቡ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ አፈጻጸም ደግሞ ሕዝቡ ለአረንጓዴ ልማት መነሳሳቱን የሚያሳይ ነው፡፡ ‹‹ከዓለም የእርሻና የምግብ ድርጅት ጋር በመሆን አገራዊ የደን ሽፋናችን ዓለም አቀፍ መስፈርቱን በጠበቀ መንገድ ተጠንቶ 15.5 በመቶ መድረሱ ተረጋግጧል፡፡ ሌላው የአገራችን የተራቆቱ አካባቢዎችንና ቀጣይ የልማት አቅሞችን የመለየት ሥራ ተከናውኗል፡፡ በዚህም ሰፊ ሚሊዮን ሔክታሮች ማልማት እንደምንችል አረጋግጠናል፤›› ብለዋል፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ አገሪቱ የዓለም አቀፍ የደን ዘርፍ በካይ ጋዝ ልቀት ቅነሳ ፕሮግራም ተሳታፊ እንደመሆኗ መጠን ከትግበራ በኋላ ወደ ካርቦን ግብይት ሊያስገባት የሚያስችላትን የዘርፉን መነሻ ልቀት መጠን ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ ዘዴ በመለካትና በመመጠን በተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ድርድር ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ለግምገማ አቅርባለች፡፡ ይኽም ሁኔታ አገሪቱን በአፍሪካ ቀዳሚ ያደረጋት ሲሆን፣ በአሁኑም ወቅት የቴክኒክ ግምገማ ውጤት ይዘቱ ተጠናቋል፡፡ በዚህም የተነሳ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የግምገማውን ውጤት ከጽሕፈት ቤቱ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ዘመናዊ የደን ልማትን በማካሄድ ለገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን የሚሰጡ እንዲሁም የተጎዱ አካባቢዎችን በፍጥነት እንዲያገግሙ የሚያደርጉ የደን ዘርፍ አቅም ግንባታ ፕሮግራሞች ተዘርግተው ለተሞክሮ ቅመራ እንዲሆን በአራት ክልሎች በሚገኙ ዘጠኝ ወረዳዎች ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፡፡ በዚህም ፕሮግራም በየወረዳው 1,200 ሔክታር የችግኝ ተከላ 16,000 ሔክታር የተጎዱ መሬቶች እንዲያገግሙ የሚያደርግ ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡ ከዚህም ጎን ለጎን ባለፉት ዓመታት በተለይም በመጀመርያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሸን ዕቅድ ዘመን የተካሄደውን ችግኝ ተከላ ዕድገት ደረጃና የዕድገት ሁኔታ ለመመዘን የሚያስችል ጥናት ተካሂዷል፡፡ በአራቱም ክልሎች የተካሄደው የዚሁ ጥናት ያሳየው የፅድቀት መጠን 59 ከመቶ መሆኑ ተገልጿል፡፡ የተሻለ ዕድገትና የዕድገት ሁኔታ በታዩባቸው አካባቢዎች የስኬቱ ምንጭ ችግኙን በባለቤትነት የመያዝና በተስማሚ ሥነ ምኅዳር መሬትና ጉድጓድ ዝግጅት ውስጥ በመተከሉ፣ እንዲሁም ከተከላ በኋላ በቂ እንክብካቤና በተለይም በወቅቱ የማረም፣ የመኮትኮት፣ ውኃ የማጠጣትና ከሰውና ከእንስሳት የንክኪ የመጠበቅ ሥራ በመከናወኑ መሆኑን ተረጋግጧል፡፡ ከዚህ አኳያ የደን ልማቱን በዋናነት እየተፈታተነ ያለው አንዱና ዋነኛው ምክንያት የባለቤትነትና የተጠያቂነት ጉዳይ እንዲሁም ለደን ልማት ሊውሉ የሚችሉ መሬቶችን በአግባቡ ለይቶና አዘጋጅቶ እንክብካቤ አለመደረጉ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ስለሆነም የደን ዘርፉ በሚቀጥሉ አሥር ዓመታት የሚጓዝበትን ጎዳና የተመረጡ አገራዊ ዓላማዎችን ለማሳካት የሚያስችሉ፣ አማራጮችን የሚተኩ የአሥር ዓመት የደን ልማት ፕሮግራም ከልማት አጋሮችና በዘርፉ ልምድ ካላቸው የውጭ አማካሪዎች ጋር በመሆን በመዘጋጀት ላይ ነው፡፡ አቶ ደመቀ መኰንን የኢፌድሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ‹‹የደን ሀብታችንን ከጥፋት ለመታደግና አዳዲስ ደኖች ለመፍጠር ስኬታማ ሥራዎች የተሠሩ ቢሆንም ከጥሩ ተሞክሮዎቻችን በመማር በምርምርና በሙያ የተደገፈ ጥረቶችን ማድረግ ወቅታዊ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ከዕድገቶቻችን ጋር ተያይዞ በገበያ ላይ ያለውን ፍላጎት በአገር ውስጥ ምርቶች ማሟላት ባለመቻላችንም ከውጭ እንድናስገባ ተገደናል፤›› ብለዋል፡፡ በዚህ ምክንያት የአገሪቱ ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋልና ተጨማሪ ደኖችን መፍጠር ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ሆኗል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በየአካባቢው የደን ልማቱን ማጎልበት ከአየር ንብረት ጋር ተያይዞ ሊመጡ የሚችሉ የተፈጥሮ አደጋ ሥጋቶችን ለመከላከል የሚያስችል አቅም እንደሚፈጥር ይታመናል፡፡ የደን ሀብት ለአገር ውስጥ ፍጆታና ለውጭ ገበያ ያለውን ፋይዳ በማስፋት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን ለማሳደግ እንደሚያስችል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡ የዛፍ ተከላና እንክብካቤ ባህልን በማሳደግ፣ የደን ሀብትን በአግባቡ በመንከባከብና የደን ልማት ዘርፉ ለአገሪቱ የሚኖረውን ፋይዳ በመገንዘብ ማኅበረሰቡ በላቀ ደረጃ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ ግድ ይላል፡፡ ለመጪው ትውልድ የተሻለች ኢትዮጵያን ለማውረስ በሚደረገው ጥረት የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ የመገንባት ራዕይን በሕዝቡ ተሳትፎ ለማረጋገጥ በጋራ ቁርጠኝነት መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ በየክልሉ አሳታፊ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራዎችን በተደራጀ የሕዝብ ንቅናቄ ለመሥራት በመቻሉ በከፍተኛ ደረጃ ተራቁተው የነበሩት ተራራዎች አፈራቸውና እርጥበታቸው ተጠብቆ የዕፅዋት ሽፋናቸውም ተሻሽሎ የገቢ ምንጭ መሆን መጀመራቸውም ተጠቅሷል፡፡ ይኽም ቢሆን የደን ሀብቱ ሙሉ ለሙሉ ከጭፍጨፋና ከመራቆት ተጠብቋል ለማለት አይቻልም፡፡ አሁንም በተለያዩ አካባቢዎች ሕገወጥ ጭፍጨፋዎችና የደን ሽፋን መመናመንን ተከትሎ የመጡ የጎርፍና የአፈር ክለት ችግሮች በግልጽ ይስተዋላሉ፡፡ ስለሆነም ዓመታዊ የደን ተከላ ሥራን ከወትሮ በተለይ ውጤትን መሠረት ባደረገ ዕቅድና ሥልት ማከናወን ያስፈልጋል፡፡ የሚተከሉትም ችግኞች ወደ ዛፍ፣ ዛፎቹ ደግሞ ወደ ደን የሚቀየሩ ሊሆን ይገባል፡፡ የአገር አቀፍ የችግኝ ተከላ ይፋ በሆነበት ዕለት በአዲስ አበባ አዳማ የፍጥነት መንገድ ላይ የሚተከሉት ችግኞች ነገ ዛፍ ሆነው ለአባቢዎች ነዋሪ፤ መንገዱን ለሚጠቀሙ አሽከርካሪዎና ተጓዦች አዕምሮን የሚያድሱና ዓይን ማረፊያ እንዲሆኑ በማሰብም እንደሆነ ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም የትራፊክ አደጋን የሚቀንሱ፣ የአካባቢውን ሥነ ምኅዳር የሚጠብቁ የመንገዱን አገልግሎት የሚያራዝሙና ካርቦን በማከማቸት የአረንጓዴ ልማት ሥልት ዓላማዎቻችንን ለማሳካት የሚያስችሉ እንዲሚሆን እምነታቸው መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ በሥነ ሥርዓቱ ላይ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ በአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ዘርፍ የተሰማሩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች በችግኝ ተከላው ዙሪያ ያተኮሩ መልዕክቶችን ያስተላለፉ ሲሆን፣ በሥፍራው ተሠልፎ ይጠባበቅ የነበረው የፖሊስ ሠራዊት የሙዚቃ ማርሽ ቡድን ልዩ ልዩ ጣዕመ ዜማዎችን ሲያሰማ የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ‹‹አቆልቋይ›› በሚል ርዕስ ያዘጋጀው መዝሙርና ድራማ ለዝግጅቱ ድምቀት ሆኗል፡፡ በነፃ ከታደለው ብሮሸር ለመረዳት እንደተቻለው ለችግኝ ዝግጅት ወጪ የሆነው ገንዘብ ሊታወቅ የቻለው በዓመት ለችግኝ ተከላ የሚወጣው ገንዘብ፣ ጉልበትና ጊዜን በማስላት ነው፡፡ በዚህ ዓመት የሚተከሉት ችግኞች ከ15 ዓመታት በኋላ የደን ሽፋኑን አሁን ካለበት 15 በመቶ በእጥፍ በማሳደግ የአገሪቱን ኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊና አካባቢያዊ ሁኔታዎችን ወደ ላቀ ደረጃ ያደርሳሉ፡፡ ከዚህም ሌላ አሁን ያለውን 250 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ካርቦን በ2014 ዓ.ም. ወደ 50 በመቶ ለመቀነስ የተያዘው ዕቅድ ሊሳካ የሚችለው ያሉት ደኖች በአግባቡ ሲጠበቁና ተጨማሪ ደኖችን ለማልማት ሲቻል ብቻ ነው፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት የደኑ ዘርፍ ለአጠቃላዩ የአገር ውስጥ ምርት በቀጥታ ስድስት በመቶ፣ በተዘዋዋሪ ደግሞ ስምንት በመቶ በድምሩ የ14 በመቶ ድርሻ አለው፡፡