Wednesday, September 28, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ልዩነትን በኃይል ለመፍታት መሞከር መዘዙ የከፋ ነው!

  ልዩነት የነበረ፣ ያለና ወደፊትም የሚኖር ተፈጥሯዊ ፀጋ ነው፡፡ የሰው ልጆች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ አመለካከቶች ስለሚኖሯቸው፣ ልዩነት ምንጊዜም ይኖራል፡፡ ልዩነትን አክብሮ ጤናማ ግንኙነት መመሥረት የዴሞክራሲ መገለጫ ሲሆን፣ ልዩነትን በኃይል ለመፍታት መሞከር ግን የግጭትና የውድመት ምክንያት ነው፡፡ ዴሞክራሲ የተለያዩ ሐሳቦች በእኩልነት የሚስተናገዱበት የሐሳብ ገበያ በመሆኑና ዋናው ዳኛም ሕዝብ ስለሆነ፣ ልዩነትን በኃይል ለመፍታት የሚደረገው ሙከራ የኋላቀርነት መገለጫ ነው፡፡ ይልቁንም ልዩነትን ሲቻል በውይይት ካልሆነ ደግሞ በክርክር መልክ በማቅረብ የሕዝብን ይሁንታ ማግኘት ተመራጭ ነው፡፡ ሕዝባችን በቋንቋ፣ በባህል፣ በእምነትና በመሳሰሉት ልዩነቶችን አክብሮ የመኖር ታላቅ እሴት የገነባ ሲሆን፣ ይህ እሴት በፖለቲከኞች ዘንድ ዋጋ ማጣቱ ከማስገረም አልፎ ያሳዝናል፡፡ ባለፈው ግማሽ ክፍለ ዘመን በፖለቲከኞች ዘንድ የታየው ግብግብ ይህንን ሀቅ በሚገባ ያረጋግጣል፡፡ የዴሞክራሲ አራቱ ምሰሶዎች ማለትም ፍትሕ፣ እኩልነት፣ ነፃነትና የሕዝብ ውክልና በተግባር የሚረጋገጡት ልዩነቶችን በሠለጠነ መንገድ መያዝ ሲቻል ብቻ ነው፡፡ እነዚህ የዴሞክራሲ ምሰሶዎች የዜጎችን መብቶችና ነፃነቶች በማረጋገጥ ማኅበራዊ ፍትሕ የነገሠበት ሥርዓት ለመመሥረት ያግዛሉ፡፡ በብዙ አገሮችም ተግባራዊ ተደርገዋል፡፡ የመንግሥት ሥልጣን በጠመንጃ ሳይሆን በሕዝብ ይሁንታ በሚረጋገጥባቸው አገሮች የልዩነቶች አደባባይ መውጣት ዴሞክራሲን ያፋፋዋል እንጂ አይጎዳውም፡፡ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሐሳባቸውን በነፃነት መግለጽ የሚችሉት፣ የሚደራጁት፣ የፈለጉትን የሚደግፉት ወይም የሚቃወሙት ልዩነት በተከበረበት ሥርዓት ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ልዩነትን አለመቀበልና እኔ ያልኩትን ብቻ ፈጽም የሚባልበት ሥርዓት ዴሞክራሲ ሳይሆን የለየለት አምባገነንነት ነው፡፡ ዜጎችን በዘር፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ አመለካከትና በመሳሰሉት በመፈረጅ ልዩነትን ለማስተናገድ አለመፈለግ በብዛት እየታየ ነው፡፡ አደጋ ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ራሱን የነገሮች ሁሉ መጀመሪያና መጨረሻ በማድረግ ተቀናቃኞቹን የፖለቲካ መጫወቻ ሜዳውን ሲያጠብባቸውና ሲዘጋጋባቸው፣ ተቃዋሚዎችም በዚያው መጠን የጥላቻና የፍረጃ አባዜ ውስጥ ገብተው ልዩነትን ያዳፍናሉ፡፡ አንዱ ወገን ፀረ ዴሞክራሲ አቋም አንግቦ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሰናክል ሲሆን፣ ሌላው በፅናት ታግሎ ፋና ወጊ መሆን ሲገባው አጓጉል ተግባር ውስጥ ይገኛል፡፡ ሰላማዊው የፖለቲካ ትግል ውሉ እንደጠፋበት ልቃቂት ተጎልጉሎ መያዣ መጨበጫ እያጣ፣ ልዩነትን በሰላማዊ መንገድ ከማስተናገድ ይልቅ ኃይል እየተመረጠ ነው፡፡ በዴሞክራሲ ስም የሚምሉና የሚገዘቱ ልዩነትን ጌጥ ማድረግ ሲገባቸው የጥፋቱን መንገድ እየተያያዙት ነው፡፡ በሕዝብ መዳኘት የሚገባቸው የፖለቲካ ኃይሎች ከሕዝብ ፍላጎት ውጪ ጠመንጃ ነካሽ መሆን እየመረጡ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በጭፍን ጥላቻ ውስጥ ተዘፍቀው ለመነጋገር ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ነው፡፡ አገር ከድህነት ተላቃ የብልፅግና ማማው ላይ የምትደርሰው ሰላም፣ ዴሞክራሲ፣ የሕግ የበላይነትና የሕዝብ ወሳኝነት ሲረጋገጥ ብቻ ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ የፖለቲካ ምኅዳሩን ዘጋግቶ ፓርላማውን ለብቻው በመቆጣጠሩ ምክንያት በአገሪቱ ከፍተኛ ቅሬታ ተፈጥሯል፡፡ ሁሉም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በእኩልነት ባልተወዳደሩበት ምርጫ ከነአጋሮቹ ሙሉ በሙሉ የፓርላማ ወንበሮችን ሲቆጣጠር፣ ከሕዝብ በኩል የሚነሳበትን ቅሬታ አለማሰቡ አሳዛኝ ነው፡፡ ሕዝብ ከቀረቡለት አማራጮች መካከል የፈለገውን እንዲመርጥ ዕድል ሳያገኝ፣ በአገሪቱ ውስጥ የተለያዩ ፍላጎቶችን የሚወክሉ አማራጮች በነፃነት ሳይንሸራሸሩና በአጠቃላይ ለልዩነቶች ክብር ሳይሰጥ በምርጫ ተወዳድሬ አሸነፍኩ ማለት ይዋል ይደር እንጂ ውጤቱ ምን እንደሆነ በተግባር እየታየ ነው፡፡ ልዩነት የሕዝቡ መለያ ሆኖ ኅብረ ብሔራዊት አገር መሥርቶ ሲኖር፣ በአንድ ዓይነት የፖለቲካና የኢኮኖሚ አስተሳሰብ ብቻ ትተዳደራለህ ማለት የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገለጫ አይደለም፡፡ የምርጫው ሒደት የፈለገውን ያህል ነፃና ዴሞክራሲያዊ ቢሆን እንኳ እንዲህ ዓይነት ውጤት ሲከሰት ያስደነግጣል፡፡ ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር አይሄድምና፡፡ በተቃዋሚው ጎራ በኩል የሚታየው አዝማሚያ ደግሞ ልዩነትን ከማክበር ይልቅ፣ ወይ ከእኔ ጋር አለበለዚያም ከጠላቴ ጋር የሚል ይመስላል፡፡ በተለያዩ ድረ ገጾችና በማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚተላለፉት መልዕክቶች የለየላቸው አምባገነኖች እየተፈለፈሉ መሆናቸውን እያመላከቱ ነው፡፡ ግለሰቦችንና ቡድኖችን በማንነታቸው ጭምር ከሚዘልፉና ከሚያንቋሽሹ ጀምሮ፣ ምንም ዓይነት ተቃራኒ ሐሳብ መስማት የማይፈልጉ እየተበራከቱ ናቸው፡፡ ከዴሞክራሲያዊ አስተምህሮ ያፈነገጡና ልዩነትን ለመቀበል የሚቸግራቸው ወገኖች ዜጎችን በሚያራምዱት አቋም ምክንያት በአደባባይ ሲኮንኑ ይታያሉ፡፡ በተለይ ሰላማዊውን የፖለቲካ ትግል ትተው ሌላ ትግል ውስጥ ነን የሚሉ ወገኖችና ደጋፊዎቻቸው፣ ከእነሱ ዓላማ ጋር የማይገናኝ አንዳችም ልዩነት መስማት አይፈልጉም፡፡ እነዚህ ወገኖች በለስ ቀንቷቸው ሥልጣን ቢይዙ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ለማሰብ ነቢይ መሆን አያስፈልግም፡፡ ሕዝብን ከሕዝብ ለማናከስ የሚደረጉ አደገኛ እንቅስቃሴዎች በአክራሪ ግለሰቦችና ቡድኖች አማካይነት እየተደረጉ ነው፡፡ በእነዚህ ወገኖች ዘንድ የዴሞክራሲ ፍቺ ምን እንደሆነ አይታወቅም፡፡ ይኼም ሌላው አደጋ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ግጭቶች ይስተዋላሉ፡፡ እነዚህን ግጭቶች ከመነሻቸው ለመከላከልና ሰላማዊ ድባቡን ለማስቀጠል የሚያስችሉ አገር በቀል የግጭት አፈታት ሥልቶች ጠፍተው አይደለም፡፡ በማኅበረሰቡ ውስጥ ትልቅ ግምት ያላቸው እነዚህ የግጭት መፍቻ ሥልቶች ተግባራዊ ቢደረጉና ዴሞክራሲያዊ አካሄዶች ሥራ ላይ ቢውሉ ኖሮ፣ ልዩነቶች ከአቅም በላይ ሆነው ለሕይወት መጥፋት፣ ለአካል መጉደልና ለንብረት ውድመት ሰበብ አይሆኑም ነበር፡፡ ሕዝብ ጥያቄ አለኝ ሲል መንግሥት በአግባቡ ካላዳመጠ፣ ሕዝብን እንወክላለን የሚሉ ወገኖች ያልሆነ አቅጣጫ ከያዙ ውጤቱ ጥፋት ነው፡፡ ልዩነት ተፈጥሯዊ መሆኑን ማመንና አቀራረቡንና አፈታቱን ማሳመር የፖለቲካ ኃይሎች ድርሻ መሆን ሲገባው፣ ከቀናው ጎዳና ይልቅ ጠመዝማዛው እየተመረጠ አገር መከራዋን ታያለች፡፡ ሕዝብ የጥፋት ሰለባ ይሆናል፡፡ ይኼ ለበርካታ ዓመታት የቀጠለ የአገር በሽታ፣ አሁን ደግሞ የብሔር ገጽታ እንዲይዝና ሕዝብ እርስ በርሱ እንዲፋጅ ቅስቀሳ እየተደረገበት ነው፡፡ ከበስተጀርባ የመሸጉ ኃይሎችም በሥውር ደባውን ተያይዘውታል፡፡ ሁሌም እንደምንለው ማኅበራዊ ፍትሕ መስፈን አለበት፡፡ እኩልነት መረጋገጥ አለበት፡፡ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር አለባቸው፡፡ የሕዝቡ የሥልጣን ባለቤትነት መረጋገጥ አለበት፡፡ የአገሪቱ ሀብት በፍትሐዊ መንገድ ለሁሉም መዳረስ አለበት፡፡ አድልኦና መድልኦ መወገድ ይኖርባቸዋል፡፡ ዜጎች በአገራቸው ጉዳይ ንቁ ተሳትፎ የማድረግ መብት አላቸው፡፡ ይህ ሁሉ በተግባር እንዲረጋገጥ የሕግ የበላይነት ወሳኝ ነው፡፡ ማንም ሰው በሕግ ፊት እኩል እንደመሆኑ መጠን፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት መኖር አለበት፡፡ ሕገወጥነት የአገር ፀር ነው፡፡ ሰላማዊው የፖለቲካ ትግል ፍሬ እንዲያፈራ የዴሞክራሲ ምሰሶዎች በፅናት ይቁሙ፡፡ ፈረንሣዮች ‹‹ልዩነት ለዘለዓለም ይኑር›› እንደሚሉት ለልዩነት ትልቅ ትኩረት ይሰጥ፡፡ ኢትዮጵያውያን በሙሉ በገዛ አገራቸው በነፃነት ይኖሩ ዘንድ ሁሉም ወገን ልዩነትን ያክብር፡፡ ዴሞክራሲ የሚረጋገጠው ልዩነት ሲከበር ብቻ ነው፡፡ በልዩነት ውስጥ አንድነት፣ በአንድነት ውስጥ ልዩነት መኖሩ ጠቃሚ መሆኑን መተማመን ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ተፈጥሯዊ ፀጋ አናበላሸው፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ልዩነትን ለመፍታት መሞከር መዘዙ የከፋ ነው!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  የአውሮፓ ኅብረት ተወካይ በተመድ ጉባዔ ‹‹የትግራይ መንግሥት›› በማለት ላደረጉት ንግግር ማስተካከያ እንዲደረግ ኢትዮጵያ ጠየቀች

  በስዊዘርላንድ ጄኔቭ እየተካሄደ በሚገኘው 51ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ)...

  የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት ሕገወጥ ገንዘብ አስተላላፊዎችን አስጠነቀቀ

  የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት በሕገወጥ የገንዘብ ማስተላለፍ ድርጊት ተሰማርተዋል ያላቸው...

  መንግሥት የሥራ ግብር ምጣኔን እንዲቀንስ ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) መንግሥት የሠራተኛውን የኑሮ ጫና...

  ኦፌኮ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን ጨምሮ ስምንት አመራሮች እንደታሰሩበት አስታወቀ

  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለክልሉ ደብዳቤ ጽፏል የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  በቤንዚንና ነጭ ናፍጣ ላይ ጭማሪ ተደረገ

  ከዛሬ መስከረም 18 ቀን 2015 ዓም እኩለ ሌሊት ጀምሮ...

  ‹‹ለሰላምና ለዕርቅ መሸነፍ የለብንም›› ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ

  የሰው ልጅ ጠብን በዕርቅ፣ በደልን በይቅርታ፣ ድህነትን በልማት፣ ክህደትን...

  መፍትሔ አልባ ጉዞ የትም አያደርስም!

  ኢትዮጵያ ችግሮቿን የሚቀርፉ አገር በቀል መፍትሔዎች ላይ ማተኮር ይኖርባታል፡፡...

  ጦርነቱና ውስጣዊ ችግሮች

  መስከረም 14 ቀን 2015 ዓ.ም. የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  መፍትሔ አልባ ጉዞ የትም አያደርስም!

  ኢትዮጵያ ችግሮቿን የሚቀርፉ አገር በቀል መፍትሔዎች ላይ ማተኮር ይኖርባታል፡፡ ከዚህ ኢፍትሐዊ ዓለም መፍትሔ ይገኛል ብሎ መጠበቅ የማይቻልበት ጊዜ ላይ እየተደረሰ ነው፡፡ የዓለምን ሚዛን ያስጠብቃሉ...

  ብልሹ አሠራሮች እንዲወገዱ ሕግና ሥርዓት ይከበር!

  በኢትዮጵያ ምድር ጦርነትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አጠናቆ ሙሉ ለሙሉ ፊትን ወደ ልማት ለማዞር ያለው ፍላጎት አሁንም ፈተና እየገጠመው ነው፡፡ ኢትዮጵያ አዲሱ ዓመት ሲብት በሙሉ...

  የግብይት ሥርዓቱ የሕገወጦች መፈንጫ አይሁን!

  በጥቂቶች ስግብግብነት ብዙኃኑ ሕዝብ እንዳይጎዳ ተገቢ ሞራላዊ፣ ሕጋዊና ፖለቲካዊ ዕርምጃዎች ሲወሰዱ ድጋፍ መስጠት ይገባል፡፡ ሰሞኑን መንግሥት በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ሱር ታክስና ኤክሳይስ ታክስን ጨምሮ፣...