Sunday, June 16, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ሰሚ ያጣ ጩኸት

በአንተነህ አዲስ ‹‹መልካም አስተዳደር፣ ግልጽነት፣ ተጠያቂነት፣ ለሕዝብ ጥያቄ ምላሽ መስጠት…›› የሚባሉት ቃላት ዘመን ያዘመናቸው የሪፖርት ማድመቂያዎች፣ ከእኔ በላይ ላሳርን የሚያዘምሩ የንግግር ማሳመሪያዎች፣ ሥልጣንን የሚያደላድሉ ሕዝበ አልባ ቃላት ከሆኑ ሰነባብተዋል፡፡ በየመሥሪያ ቤቱ ኮሪደርና በየኃላፊው ቢሮ ባማረ ፍሬም ተንጠልጥለው የሚታዩት አሥራ ሁለቱ የሥነ ምግባር መርሆዎች የድንጋይ ዘመን ተረቶች ይመስሉ ዘንድ ከተግባር ከተፋቱ፣ ከህሊና ከራቁ ከራርመዋል፡፡ እንደ አማረ ፍሬያቸው ተግባራቸው ሰምሮ፣ እንደ ጎላ ጽሑፋቸው ውሏቸው ኑሯችንን ታድጎ መልካም አስተዳደር ያሰፍኑልናል ብለን የተመኘናቸው የሥነ ምግባር መርሆዎች የሚታዩ እንጂ የማይበሉ ፍሬዎች ሆነዋል፡፡ መርሆዎቹን እያዩ ከመደሰት ይልቅ መከፋትን፣ ከመሳቅ ይልቅ ማልቀስን፣ ከመኩራት ይልቅ ማፈርን ዕጣ ክፍላችን አድርገናል፡፡ ዱሮ ዱሮ መጥፎም ሆነ መልካም ዕጣ ክፍል የሚሰጠው ከፈጣሪ ነበር፡፡ እናም የማትጋፋውን፣ የማትከሰውን፣ የማትሞግተውን ስጦታ ተቀብለህ ትኖራለህ፡፡ ዛሬ ዛሬ ግን ዕጣ ክፍላችን የሚወሰነው በማንጋፋቸው ምድራዊ ኃላፊዎች ሆኗል፡፡ ትክክል አይደለም ብለህ ትከሳለህ ግን ትሸነፋለህ፡፡ ኧረ ሕግ ተጥሷል ብለህ ትሟገታለህ ግን ትረታለህ፡፡ አንተ ዘንድ ካለ መቶ እውነትና ማስረጃ ይልቅ ኃላፊዎች ጠረጴዛ ላይ የወደቀች አንዲት ስንጥር ውሸት ሕይወትህን ታጨልማለች፣ ጥንካሬህን ትጋፋለች፣ ተስፋህን ትበትናለች፡፡ ያኔ… እውነት፣ እውቀት፣ ዕምነት ቅንነት፣ ግልጽነት ዋጋቸው ረክሶ፣ ክብራቸው ተገሶ፣ በነጠፉበት ለት፣ መጮህ ምን ሊፈይድ፣ ምን ሊያመጣ መላ፣ እህህን ስንቅ አድርጎ፣ ከመብሰክሰክ ሌላ፣ ከመቃጠለ ሌላ…ብለህ መቆዘም ዕጣ ክፍልህ ይሆናል፡፡ እናም ‹‹መልካም አስተዳደርን እናሰፍናለን›› የሚል መፈክር ባየህ ወይ በሰማህ ቁጥር በአንተ ሕይወት ላይ የተለጠፈ ስላቅ ቢመስልህ አያስደንቅም፡፡ ያላዩት አገር አይናፍቅምና፡፡ ከላይ የዘረዘርኩትን ሐሳብ ያነሳሁት ያለምክንያት አይደለም፡፡ ከአንድ ወር በፊት ወደ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ባቀናሁበት ወቅት ለጉዳዬ የተሰጠኝ ምላሽ ከምንዘምርለት የመልካም አስተዳደር መዝሙር ጋር የተፋታ ሆኖ ስላገኘሁት እንጂ፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በ2008 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን የአሥራ ሁለተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከተፈተኑት ተማሪዎች መካከል ከፍተኛ ነጥብ ያላቸውን ተማሪዎች ተቀብሎ በሳይንስና በኢንጂነሪንግ የትምህርት ዘርፍ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲና በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ለማስተማር ማስታወቂያ ያወጣል፡፡ ሁለቱም ዩኒቨርሲቲዎች ተወካዮቻቸውን በበርካታ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በመላክ የሚያስተምሩትን የትምህርት ዓይነት የሚገልጽ በራሪ ወረቆቶች እንዲበተን ያደርጋሉ፡፡ ጉዳዩ የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲን የሚመለከት በመሆኑ የበተነውን በራሪ ወረቀት ለግንዛቤ ይሆናችሁ ዘንድ ላስቃኛችሁ፡፡ ዩኒቨርሲቲው በራሪ ወረቀቱ ላይ፣ በ“Applied Natural Science” ዘርፍ “Biomedical Engineering, Biotechnology, Industrial Chemistry, Space Technology /Areas of Study” ለማስተማር የተዘጋጀ መሆኑን የሚገልጽ ዝርዝር አውጥቷል፡፡ ይኼንን ወረቀት ያዩና በአሥራ ሁለተኛ ከፍል መልቀቂያ ፈተና ከ400 እስከ 565 ነጥብ ያመጡ ተማሪዎች ከወላጆቻቸው፣ ከመምህራኖቻቸውና ከጓደኞቻቸው ጋር በመመካከር፣ እንዲሁም ፍላጎታቸው ግምት ውስጥ በማስገባት ተመዘገቡ፡፡ የመግቢያ ፈተናም ተቀብለው 38 ተማሪዎች አለፉ፡፡ ነገር ግን የተማሪዎቹ ቁጥር ማነስ ያሳሰበው የሚመስለው ዩኒቨርሲቲ ሌላ ማስታወቂያ በብዙኃን መገኛዎች አስነገረ፡፡ በዚህ ጊዜ የዘረዘራቸው የትምህርት ዘርፎች ግን በመጀመርያው በራሪ ወረቀት ላይ የቀረቡት አልነበሩምና ተማሪዎቹ ትምህርት ከመጀመራቸው በፊት ዩኒቨርሲቲውን ስለሁኔታው ግልጽ እንዲያደርግላቸው ጠየቁ፡፡ የዩኒቨርሲቲው አስተዳደርም ተማሪዎቹን ሰብስቦ፣ ‹‹እናንተ ከፍተኛ ነጥብ ያላችሁና ተወዳድራችሁ የገባችሁ ናችሁ፡፡ ይኼንን ያደረግንበት ምክንያት የተመረጡ ተማሪዎችን ሳይንቲስት ለማድረግ በማሰብ ነው፡፡ ሳይንቲስት ለመሆን ደግሞ የመጀመሪያ ዘርፍ ዲግሪ ሊኖራችሁ ይገባል፡፡ በዚያው በመቀጠል ሁለተኛ ዲግሪያችሁን (Master’s Degree) በራሪ ወረቀቱ ላይ በተገለጸው መሠረት ይሰጣችኋል፤›› በማለት ትልቅንና የሚያስጎመዠውን ተስፋ መገቧቸው፡፡ ንጋትን የዘነጋ ባዶ ተስፋ አንድ በተሰጠጣቸው ተስፋ ሁሉም ተማሪዎች ተደሰቱ፡፡ ፈጣን ምላሽ በማግኘታቸውም ረኩ፡፡ አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የገቡበትን ቀን መረቁ፣ አወደሱ፡፡ በደስታ የተዋበ ተስፋቸው ፍሬ ያፈራ ዘንድ ጠንክረው መሥራት እንዳለባቸው ለራሳቸው ቃል ገቡ፡፡ በመምህራኖቹ ዘንድ ‹‹እንደ ዘንድሮ ዓመት ጎበዝ ተማሪ ገብቶ አያውቅም፤›› እስኪባል ድረስ በሞራል መሥራትን ተያያዙት፡፡ ግና… ደስታና ሞራላቸው ከአንድ ሴሜስተር የዘለለ ዕደሜ ለመቁጠር አልታደለም፡፡ እውነትና ንጋት እያደር ጠራና ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ዩኒቨርሲቲው አዲስ በራሪ ወረቀት በተነ፡፡ በራሪ ወረቀቱም ላይ የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በመጀመርያም ሆነ በሁለተኛ ዲግሪ የሚያስተምረው Applied Biology, Applied Pysics, Applied Chemistry, Applied Geology, “Applied Mathematics” መሆኑን የሚገልጽ ነበር፡፡ ይህ በራሪ ወረቀት ለተማሪዎች መርዶ ነጋሪ ነበርና ተደናገጡ፡፡ ወረቀቱ የተበተነው አማራጮች ሁሉ በተሟጠጡበት ወቅት በመሆኑ ሐዘናቸውን አከበደው፡፡ ‹‹…እኛ ከፍተኛ ነጥብ ያለን ተማሪዎች በመሆናችን ከሕክምና ጀምሮ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች መመደብ ስንችል ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርን አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲን አምነን መጥተን እንዴት እንታለላን? ይኼ ምርጫ መቅረብ የነበረበት መጀመርያ ነበር፡፡ የሕገ መንግሥቱን አንቀት 12 ንዑስ አንቀጽ አንድ ላይ ‘የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንግድ መከናወን አለበት’ በማለት የሚለውን ሕግ በአደባባይ መጣስ ከአንድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የሚጠበቅ ነው ወይ?›› በማለት በተለያዩ ደረጃ ላያ ያሉ ኃላፊዎችን አነጋገሩ፡፡ የዩኒቨርሲው አመራሮች የሰጡት መልስ ግን እጅግ የሚያሳፍር በአመራር ላይ ካለ ‹‹ምሁር›› የሚጠበቅ አልነበረም፡፡ ‹‹‹…የመጀመርያውን ወረቀት ያዘጋጀው ሰው ሞቷል፡፡ … በራሪ ወረቀቱ ላይ የእኔ ፎቶ የለም እኔን አትጠይቁኝ፡፡ ብትፈልጉ ተማሩ ባትፈልጉ ከስድስቱ በአንደኛው በር መውጣት ትችላላችሁ፡፡ እኛ የምናስተምራችሁ በመጀመርያ ዲግሪ ብቻ ነው፤›› የሚሉ ሥነ ምግባር የጎደላቸው፣ እውነት የጠማቸው፣ ከኢትዮጵያዊ ባህላችን ጋር አብረው የማይሄዱና የተሳከሩ መልሶች ነበሩ፡፡ ተማሪዎቹ በዩኒቨርሲቲው መልስ አዘኑ፡፡ ከትልቁ የትምህርት ተቋም በተነገረው ትንሽ መልስ አፈሩ፡፡ በአንድ ሴሚስተር ውስጥ ፍየልና ቅዝምዝም በሆኑት ሁለት መልሶች ተገረሙ፡፡ ‹‹….መንግሥት ባለበት አገር፣ የሕገ መንግሥት የበላይነት በተረጋገጠበት አገር፣ የሰብዓዊ መብት በተከበረባት አገር እንዴት ያልፈለግነውን፣ ያልመረጥነውን፣ ቀድሞ ያልተነገረንን ትምህርት ለመማር እንገደዳለን?…›› በማለት ቅሬታቸውን ለማቅረብ ተወካዮቻቸውን ወደ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ላኩ፡፡ አቤቱታቸውን ካላቸው መረጃና ማስረጃ ጋር አያይዘው አቀረቡ፡፡ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የበላይ ኃላፊዎችም የቀረበላቸውን ቅሬታ ተቀብለው፣ ‹‹ዩኒቨርሲው የሚያስተምረው መጀመርያ በበተነው በራሪ ወቀት ላይ የተዘረዘሩትን የትምህርት ዓይነቶች መሆኑን ነው እኛም የምናውቀው፡፡ አሁን እናንተ ባሳያችሁን በራሪ ወረቀት ላይ ያሉትን የትምህርት ዓይነቶች አናውቃቸውም፡፡ ስለዚህ በአስቸኳይ ከዩኒቨርሲቲው ጋር ተነጋግረን መልስ እንሰጣችኋለን፤›› ብለው የግል ሞባይል ስልክ ቁጥራቸውን ሳይቀር ሰጥተውና አጽናንተው መለሷቸው፡፡ ቁም ነገርን የተራበ ባዶ ተስፋ ሁለት የተማሪዎቹ ተወካዮች አዲስ የተገነባላቸውን ተስፋ ተቀብለው ለጓደኞቻቸው አካፈሉ፡፡ ‹‹እልፍ ቢሉ እልፍ ይገኛል›› የተባለበት ዘመን ላይ አለመሆናቸውን ስላላወቁ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን መልስ ናፈቁ፡፡ በተሰጣቸው ስልክ ቁጥር ከሻይ ወጪያቸው ቀንሰው ደጋግመው ደወሉ፡፡ አዲስ ተስፋም ከመሥሪያ ቤቱ ደረሳቸው፡፡ ‹‹ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር በእናንተ ጉዳይ ተነጋግረን በመጀመሪያው በራሪ ወረቀት ላይ የተጠቀሱትን የትምህርት ዘርፎች ለማስተማር እንደማይችል ነግሮናል፡፡ ስለዚህ ሦስት አማራጮች አሏችሁ፡፡ ወደ አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ መቀየር፣ አዳማ ባለው የትምህርት ዘርፍ መቀጠል የሚፈልጉትን ማስቀጠል፣ ወደ ኢንጂነሪንግ ዘርፍ መቀየር የሚፈልጉትን መቀየር፡፡ ከእነዚህ የምትፈልጉትን እንደትመርጡ ወስነናል፡፡ ውሳኔውን ለዩኒቨርሲቲው የላክን ስለሆነ ይነግሯችኋል ጠብቁ፤›› ተባሉ፡፡ ማለቂያ የሌለው ባዶ ተስፋ ሦስት ተማሪዎቹ ዩኒቨርሲቲውን ደጋግመው ቢጠይቁም ውኃ ቢወቅጡት ዓይነት ሆነባቸው፡፡ ይባስ ብሎ ሁለተኛ በዚህ ጉዳይ ላይ መነጋገር እንደማይፈልጉ ከማስፈራሪያ ጋር ገለጸላቸው፡፡ በመልሱ ያልተደሰቱት ተሪማዎች ተወካዮቻቸውን ከመላክ ይልቅ፣ ሁሉም ተሰብስበው ቢሄዱ ተደማጭ እንሆናለን ብለው በማስብ ወደ ሰላሳ የሚጠጉ ተማሪዎች ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተነስተው ወደ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አቀኑ፡፡ አቤቱታቸውን ለሁለተኛ ጊዜ በማቅረብም አስቸኳይ መልስ እንዲሰጣቸው ጠየቁ፡፡ ሚኒስቴሩም እንዲያውቁት አደረጉ፡፡ ጥያቄያቸውን የተቀበለው አካልም በአስቸኳይ መልስ እንደሚሰጣቸውና አንድ ተወካይ ወደ አዳማ መጥቶ እንደሚያነጋግራቸው ቃል ገብቶ መለሳቸው፡፡ ተሰፋ በሰጠህ ቁጥር ዕዳ እየገባህ መሆኑን አትርሳ የሚለውን አባባል የዘነጋ ባዶ ተስፋ አራት ቀን አልፎ ቀን ቢተካም የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ውሳኔ ለተማሪዎቹ ሊቀርብ አልቻለም፡፡ ይመጣል የተባለው ተወካይን የበላው ጅብ አልጮህ አለ፡፡ ከእንግዳው ይልቅ ዩኒቨርሲቲው ቀረበና ‹‹ጥያቄያችሁ የፖለቲካ ፍላጎት ባላቸው ሰዎች የሚመራ መሆኑን ደርሰንበታል፡፡ የጠየቃችሁት የትምህት ዘርፍም በዓለም ላይ የሌለ ስለሆነም አርፋችሁ ብትማሩ ይመረጣል፡፡ ከዚህ ውጪ ትምህርታችሁን እየተዋችሁ ለአቤቱታ የምትሯሯጡ ከሆነ ዩኒቨርሲቲው ለማባረር ይገዳደል፤›› በማለት ገለጸላቸው፡፡ ሁሉ በጁ፣ ሁሉ በደጁ የሆነው ዩኒቨርሲቲ በሥነ ዜጋ ትምህርቱ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ ስምንት ንዑስ አንቀጽ ሦስት፣ ‹‹ማንኛውም ሰው በኃይል ተገዶ ወይም ግዴታ ለሟሟላት ሲባል ማንኛውንም ሥራ እንዲሠራ ማድረግ የተከለከለ ነው›› የሚለውን ሕግ ባስተማረበት ክፍል ተማሪዎች የማይፈልጉትን፣ በጭራሽ ያልመረጡትን ትምህርት በግዳጅ ሊያስተምር መነሳቱ የትኛውን ሕግ ተግባራዊ እያደረገ ይሆን? ወይስ ጌታዋን የተማመነች…ሆኖበት? አቤቱታቸውን ሰምቶ፣ ብሶታቸውን አዳምጦ ትክክለኛውን ፍርድ የሚሰጥ አካል ያጡት ተማሪዎች ይመለከተዋል ወዳሉት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሳይንስ፣ የመገናኛ ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ችግራቸውን በደብዳቤ አቀረቡ፡፡ ደብዳቤአያቸውን የተቀበለው አካልም ‹‹በአምስት ቀናት ውስጥ መልስ ይሰጣችኋል ጠብቁ፤›› አላቸው፡፡ የተባሉት አምስት ቀናት አለፉ፡፡ ያልተጠቀሱት አሥር ቀናት ተደገሙ፡፡ ያልታሰቡት አሥራ አምስት ቀናት ተቋጩ፡፡ መልሱ ግን እንደ መንግሥተ ሰማያት ራቀ፡፡ ‹‹የዘገየ ፍርድ እንደተከለከለ ይቆጠራል ያሉት ተማሪዎች እንባቸውን ያብስላቸው ዘንድ ወደ ዕንባ ጠባቂ ቢሮ ማመልከቻቸውን አቀረቡ፡፡ ይኼ ጽሑፍ እስከተጻፈበት ጊዜ ድረስ መልስ በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ ይታያችሁ መንግሥታችን የመልካም አስተዳዳር ዕጦት አንኳር ችግር መሆኑን ተቀብሎ ለመቅረፍ በሚሯሯጥበት በዚህ ጊዜ፣ ተበደልን ላሉ ተማሪዎች ፍትሕ የሚሰጥ አካል እንዴት ይጠፋል? ይህ በእንዲህ እያለ የልጆቻቸውን አጣብቂኝ ውስጥ መግባት ያሳሰባቸው ጥቂት ወላጆች ጥያቄው የልጆቻችን ብቻ ሳይሆን የእኛም ነው በማለት ጣልቃ ለመግባት ተገደዱ፡፡ ልጆቻችንን እንደየአቅማችን ከአሥራ ሁለት እስከ አሥራ አምስት ዓመት አስተምረን፣ ደረሱንልን ብለን ዓይን ዓይናቸውን ስናይ እንዴት በመንግሥት ተቋም ለዚያውም በአደባባይ ይታለላሉ? በማለት ጥያቄያቸውን አንስተው ወደ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሄዱ፡፡ ይመለከታቸል የተባሉ ሁለት የሥራ ኃላፊዎችን አነጋገሩ፡፡ አንደኛውን ኃላፊ በስልክ ነበርና ያገኙት፣ ‹‹የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የራሱ አስተዳደር ያለው ስለሆነ እኛ ጣልቃ አንገባም፡፡ እናንተ ወላጆች ሄዳችሁ ለምኑት፤›› አላቸው፡፡ ወላጆች ግን፣ ‹‹ልጆቻችን ለምነው ሳይሆን በብቃታቸው ተፈትነው፣ አልፈው የገቡ በመሆኑ ማንንም ለመለመን ህሊናችን አይፈቅድም፡፡ ችግር በልመና የሚፈታ ከሆነ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን ለተማሪዎቹ ያንን ሁሉ ተስፋ መስጠት ለምን መረጠ?›› በማለት ሳይስማሙ ቀሩ፡፡ ይታያችሁ የተጭበረበሩ ተማሪዎችን መብት ለማስከበር ልመና አንዱ የአሠራር ሥልት የሆነበት ዘመን? አውቆ የተኛን ለምኖ መቀስቀስ አዲስ የሳይንስ ግኝት ይሆን? መልካም አስተዳዳር ሲያወሩት የቀለለ፣ ሲተገብሩት ግን ከጂብራልተር አለት የከበደ የሆነባቸው ወላጆች ወደ ሌላው ኃላፊ ቢሮ አመሩ፡፡ የሚመለከታቸውን ኃላፊም በግንባር ቀርበው ጉዳያቸውን አስረዱ፡፡ ኃላፊው፣ ‹‹የተማሪዎቹ ጥያቄ የፖለቲካ ችግር ባለባቸው ሰዎች የሚመራ፣ የጠየቁት ትምህርትም በዓለም ላይ የሌለ ነውና እናንተ ወላጆች አትግቡበት፡፡ እኛ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመነጋገር እንፈታዋለን፤›› በማለት ዩኒቨርሲቲው የሰጠውን መልስ ደገሙላቸው፡፡ ወላጆች ግን ተማሪዎቹ ያነሱት ጥያቄ የመብት ጥያቄ ነው፡፡ ጥያቄያቸው ‹‹እኛ የመጣነው በመጀመርያው በራሪ ወረቀት ላይ የሰፈሩትን የትምህርር ዓይነቶች ለመማር ነው፤›› የሚል ነው፡፡ ይኼ መብት ነው፡፡ መብት የማይሆነው ዩኒቨርስቲው የማያውቀውን ትምህርት እንዲያስተምራቸው ሲጠይቁ ነው፡፡ ነገር ግን ልጆቹ የጠየቁት ዩኒቨርሲቲው አስተምራለሁ ብሎ የዘረዘረውን የትምህርት ዘርፍ እንጂ የራሳቸውን ምናብ አይደለም፡፡ አንዳንዶቹ የትምህርት ዓይነቶች እኮ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የሚሰጡ ናቸው፡፡ (እዚህ ላይ በገባው ቃልና በዘረዘረው የትምህርት ዘርፍ መሠረት እያስተማረ ያለው የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ሊመሰገን፣ ሊወደስ ይገባዋል ቃል የዕምነት ዕዳ መሆኑን አስመስክሯልና) እንደተባለው የፖለቲካ ችግር ያለበት ተማሪ ካለ በሕግ አግባብ መየጠቅ እንጂ፣ በፖለቲካ አሳቦ የመብት ጥያቄ አለመመለስ ከመልካም አስተዳር ችግሮች አንዱ መሆኑን መረዳት ይገባል፡፡ ለመሆኑ ጥፋቱ የማን ነው? የሚያስተምሩትን ትምህርት ባትዘረዝር ኖሮ ልጆቻችን በትምህርት ሚኒስቴር ይመደቡ ነበር፡፡ እናንተንም የመጀመርያ ምርጫቸው አያደርጉም ነበር በማለት ወላጆች በተሰጣቸው መልስ ሳይስማሙ ቀሩ፡፡ የተሻለና የመጨረሻው አማራጭ አድርገው የያዙት ሚኒስትሩን ማነጋገር ነበርና በጸሐፊያቸው በኩል ቀጠሮ እንዲያዝላቸው ጠየቁ፡፡ ይሁን እንጂ ሚኒስትሩ የበታች ኃላፊዎቹ ከሰጡት መልስ ውጪ የተለየ መልስ እንደሌላቸው ወላጆችን ማናገር እንደማይፈልጉ ገለጹ፡፡ በዚህ ጊዜ የፍቅር እስከ መቃብር የበዛብህን ግጥም ለማስታወስ ተገደድኩ፡ …ዳሩ ዳኛ የለም ልተወው ግድ የለም፡፡… ግን ደግሞ መተው ፈሪነት ነው፡፡ ያለነው በአፄው ዘመን ባይሆንም፣ ብታንኳኳ ወይ ብትቆረቁር የመልካም አስተዳዳር በር ከተዘጋ ቢከራከርም፣ ያንተ እውነት ለዕምነት ባይታደልም የቢሮክራሲን ውጣ ውረድ ለመፋለም አንድ ቀሪ መንገድ አለ፡፡ የግል ሚዲያ፡፡ እናም እውነቱን ሕዝብ እንዲያውቀው በማሰብ ምርጫዬን የግል ጋዜጣ አደረግኩ፡፡ በመግቢያዬ ላይ የመልካም አስተዳደር፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ከሪፖርት ማድመቂያነት ያለፈ አቅም የሌላቸው መካን ቃላት ሆነዋል ያልኩት ያለምክንያት አይደለም፡፡ ‹‹ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው አሠራር በማስፈን መልካም አስተዳደርን ዕውን እናደርጋለን›› የሚለው መፈክር ከመድረክ ያለፈ ሠፈርና ዕደሜ የለውም፡፡ ቢኖረውም ኖሮ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በነፃነት በሚርመሰሙሱባት አገር ተበድያሁ ብሎ ቅሬታ ያቀረበ ሰው ችግሩ ይፈታለት ነበር እንጂ፣ ወደ ፖለቲካ ችግር አይላከክም ነበር፡፡ ምናልባት የምናወራለት መልካም አስተዳዳር ለጎረቤት አገሮች ከሆነ ሐሳቤን አንስቻለሁ፡፡ እንደኔ ዕምነት ሰዎች የሚጠዩቁት ጥያቄ በትክክል መሆኑን ውስጣቸው እያወቀው እውነተኛውን መልስ ቢሰጡ ሌሎችን ያስቀይማል ብለው ሲያስቡ ወይም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ራሳቸው የችግሩ አካል መሆናቸውን ሲያውቁ፣ ለማድበስበስ በማሰብ መልሳቸው በቁጣና በሰበብ አስባብ የተሰናከለ ይሆናል፡፡ ለዚያም ነው ተማሪዎች ያነሱት ጥያቄ መልስ ያጣው እንጂ የአልበርት አንስታይን ሐሳብ ሆኖባቸው እንዳልሆነ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ እነዚህ ልጆች ዜጎች ናቸው፡፡ ከተሳሳቱ ፊት ለፊት ተነጋግሮ ማሳመን፣ ማረም፣ ካላወቁ ማሳወቅ፣ መንገዳቸውን ከሳቱ መመለስ ከዩኒቨርሲቲው የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡ የወላጅን ቦታ የተካው ዩኒቨርሲቲው ቀናውን መንገድ ሊያሳየቸው፣ መልካሙን ጎዳና ሊጠቁማቸው ሲገባ ባልወለደ አንጀቱ ተጋግዞ ተስፋቸውን ማጨለም ለምን እንደመረጠ ግልጽ አይደለም፡፡ እዚህ ላይ ተማሪዎቹ ወደ ዩኒቨርሲቲው የገቡት በትምህርት ሚኒስቴር በዕጣ ከመመደብ ይልቅ የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የዘረዘራቸው የትምህርት ዓይነቶች አጓጉተዋቸው እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ዳሩ ምን ያደርጋል ጉጉት ብቻ ሆኖ ቀረ፡፡ በሌላ በኩል ዩኒቨርሲቲው በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሥር ሲሆንና አዲስ ፕሮግራም ሲጀምር መንግሥት ከፍተኛ በጀት እንደመደበለት እየታወቀ ያላሟላቸው ነገሮች ካሉ ተማሪዎችን ከመቀበሉ በፋት እንዲያሟላቸው ማበረታታት ሲገባ፣ የቆፈረውን ጉድጓድ እንዲያረዝመው ማበረታታት ለምን እንደመረጠ ግልጽ አይደለም፡፡ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም ቢሆን የተማሪዎቹ ጥያቄ ትክክል ካልሆነ ቁርጥ ያለ መልስ ሰጥቶ ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ማድረግ፣ ጥያቄያቸው ትክክል ከሆነ ደግሞ ውሳኔውን አሳውቆ የሚስተካከልበትን መንገድ መፈለግ ሲገባው ‹‹ተማሪዎቹም ስህትት ሠርተዋል፣ ዩኒቨርሲቲውም አጥፍቷል›› በሚል የዋለለ መልስ የተማሪዎቹን ዕደሜ በአንድ ዓመት መቀነስ አግባብነት ያለው አካሄድ አይመስለኝም፡፡ ዕድልና ዕድሜ መጠባበቂያ የላቸውም፡፡ ቆመው አይጠብቁም፡፡ እናም ከእጅ እንዳመለጠ ስኒ አቅልሎ ማየት አገሪቱን ለመቀየር ‹‹ቆርጦ›› ከተነሳ መሥሪያ ቤት የሚጠበቅ አይደለም፡፡ በየመሥሪያ ቤቱ የሚያጋጥሙ የመልካም አስተዳደር ህፀፆች አገር አቀፍ ችግርን የመውለድ አቅም እንዳላቸው መገንዘብ ብልህነት ነው፡፡ ዛሬ ተስፋ የቆረጡ ተማሪዎች ነገ ስደትን ቢመርጡ፣ ዛሬ በዩኒቨርሲቲውና በተባባሪዎቹ ሰንካላ ምክንያት ትምህርት ያቆሙ ወጣቶት ከዚህ ዓይነት ዓይን ያወጣ ማታለል አንደበት በሌለው ባህር መበላት ይሻላል ብለው ቢወስኑ ማንም አይጠቀምም፡፡ ተቋሞቻችን አገር ወዳድ ዜጎችን የሚያፈሩ እንጂ በማጭበርበር ገብተው፣ በማጭበርበር የተካኑ ትውልዶችን መፈልፈያ መሆን የለባቸውም፡፡ ስለሆነም የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም ሆነ የአዳማ ዩኒቨርሲቲ ቆም ብለው ሊያስቡ ይገባል፡፡ አጀማመራቸውን ለምን ፈተና በዛበት ብለው ራሳቸውን መጠየቅ ብልጠት ነው፡፡ የፖለቲካ ሰበብ ወንዝ ቀርቶ መንገድ እንደማያሻግር መረዳት አለባቸው፡፡ ፖለቲካ ላይ የሚለጠፍ ችግር የጧት ጤዛ ነው፡፡ ሲያረፋፍድ የሚረግፍ፡፡ መፍትሔው ግልጽነትና ተጠያቂነት የተጎናፀፈ አሠራር ማስፈን ነው፡፡ በሌላ በኩል ጉዳዩ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የሚመለከታቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ችግሩ በግልባጭ እስኪደርሳቸው መጠበቅ የለባቸውም፡፡ ባሉበት መንቀሳቀስና የጉዳዩን አሳባቢነት አጣርተው ችግሩ በቀጣይ የሚመጡ ተማሪዎች ላይ እንዳይደግም ማድረግ አለባቸው፡፡ የተመደበው በጀት የአገሪቱን ዕድገት በማፋጠን በኩል በትክክል እየሰጡ መሆናቸውን ማጣራት፣ የተማሪዎቹ ክትትልና እርካታ ምን እንደሚመስል ማየት ይገባል፡፡ የዩኒቨርሲቲው የትምህርት ሥርዓት በሚሊዮኖች ብር የሚቆጠር ችግር እንደተተበተበው የፋይናንስ ሥርዓት ከመዝረክረኩ በፊት ሁለት ጊዜ ማሰብ ከትናንት አዙሪት መውጣት ነው፡፡ አለበለዚያ በትምህርት ሚኒስቴር ሥር ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች በምን ተለየና ራሱን ችሎ ለመቆም መንግሥት ፈቀደለት የሚል ጥያቄ በአንድ ወቅት መጠየቁ አይቀሬ ይሆናል፡፡ እርግጠኛ ነኝ ያኔ ችግሩ የፖለቲካ ችግር ነው አይባልም፡፡ በመጨረሻም ትናንት በሊቢያ በረሃ ውስጥ ታስረው በመማቀቅ ላይ ላሉት ኢትዮጵያውያን እንደጮህን ሁሉ ዛሬ አማራጮቻቸውን በጠራራ ፀሐይ ተቀምተው ያለፈቃዳቸው በግዳጅ ያልፈለጉትን ትምህርት እንዲማሩ ለተፈረደባቸው ተማሪዎች የዜግነት ግዴታችንን ልንወጣላቸው ይገባል፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ትምህርት የሚያቋርጡ ተማሪዎች ቁጥር አሳሳቢ በሆነበት በአሁኑ ወቀት በዩኒቨርሲቲውና በሳይንስና ቴክኖሎጂ ውሳኔ አዝነው ትምህርታቸውን ለማቋረጥ የተገደዱ ተማሪዎች ሕይወት ሊከነክን ይገባል፡፡ ይህን ስናደርግ የመልካም አስተዳዳር ዕጦትን የማንሸከም መሆናችንን አስመሰከርን ማለት ነው፡፡ መልካም አስተዳዳር ከሰማይ የሚወርድ ህብስተ መና አይደለም፡፡ በየረጃው ያሉ ኃላፊዎች የልጆቻቸውና የወገኖቻቸው በስቃይ የተሞላ ሕይወት አሳስቧቸው ትክክለኛውን ውሳኔ የሚሰጡበት የህሊና ፍርድ እንጂ! ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles