Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልአለ ፈለገሰላም ኅሩይ የዘመናዊ ሥዕል አባት ሠዓሊና መምህር

አለ ፈለገሰላም ኅሩይ የዘመናዊ ሥዕል አባት ሠዓሊና መምህር

ቀን:

(ሐምሌ 1915 – ሐምሌ 2008)

ስለሃያኛው ምታመት የኢትዮጵያ ሥነ ጥበብ ጥንተ ፍጥረት በተለይም ስለ ሥነ ጥበብ ትምህርት ዘመናዊ መስመርን መያዝ አስመልክቶ ሆነ ሲፃፍ ቀድመው የሚነሱ ዓይነተኛ ባለሙያ አለ ፈለገሰላም ኅሩይ ናቸው፡፡ በ1951 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ዘመናዊ የሥዕል/ሥነ ጥበብ ትምህርት እንዲጀመር መሠረት የጣሉ ተጠቃሽ ሊቀ ጠበብት ናቸው፡፡ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሐምሌ 16 ቀን 1950 ዓ.ም. የተመረቀው የአዲስ አበባ ሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት መሥራችና ቀዳሚ ዳይሬክተርም ሆነውለታል፡፡ ኖረውለታል፡፡ ቅድመ አለ የሥዕል/የሥነ ጥበብ ተግባር ከጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀምሮ የነበረ ነው፡፡ ሥዕሉም የራሱ የትምህርት ገበታ ነበረው፡፡ በቤተ ክህነት ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ሁነኛ ቦታ እንደነበረው የሚያሳየው በአገሪቱ ገዳማትና አድባራት የሚገኙት ጥንታዊ ሥዕሎች መኖራቸው ነው፡፡ ነባሩን ትውፊታዊውን የኢትዮጵያ ሥነ ጥበብ ትምህርት ለማዘመን ከ19ኛው ምታመት ሁለተኛ አጋማሽ ወዲህ እንቅስቃሴ መጀመሩ ይወሳል፡፡ ከዘመነ መሳፍንት በኋላ አሐዳዊ መንግሥት የመመሥረት፣ የአማርኛ ቦታውን ከግእዝ መረከብ፣ ትምህርት ቤቶች መመሥረት በሥነ ጥበቡ ረገድ ዓይነተኛ ቦታ ነበራቸው፡፡ አንዱ ማሳያ ከ170 ዓመታት በፊት የተመሠረተው የዓዲግራት (ጎልዓ) ዘመናዊ ትምህርት ቤት ከሚያስተምራቸው ትምህርት ቤቶች መካከል ሥነ ቅርፅና ሥዕል መገኘቱ ነው፡፡ ዘመናዊ የሥነ ጥበብ ትምህርት የንቅናቄ ደወል የተወለደው በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን ነበር፡፡ በቤተክህነት ትምህርት የሠለጠኑ ሠዓልያን ከሁሉም ሥፍራ እንጦጦ ሲሰባሰቡና ሲሠሩም ነበር፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ በዘመናቸው አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ፣ ተሰማ እሸቴ ሥነ ጥበብን እንዲያጠኑ ወደ አውሮፓ መላካቸው አንዱ ማሳያ ነበር፡፡ ከሩብ ምታመት ባነሰ የሥዕል ዘመናዊነት እንቅስቃሴ ማዕከሉን ከእንጦጦ ወደ አዲስ አበባ አራት ኪሎ ካደረገ በኋላም በ1930ዎቹ ከሚጠቀሱት ጠቢባን መካከል አበበ ወልደ ጊዮርጊስ፣ አገኘሁ እንግዳና ዘሪሁን ዶሚኒክ ይጠቀሳሉ፡፡ በሕግ መወሰኛ ምክር ቤት (ፓርላማ) ውስጥ ዘውዳዊው ሥርዓቱን የሚመለከቱ ሥዕሎች የተሣሉበት የፓርላማ ስቱዲዮ መንደርደርያም ነው፡፡ የሥዕል ትምህርት እንቅስቃሴው ጫፍ የደረሰው 1950 ዓ.ም. ላይ የአዲስ አበባ ሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት ሲመሠረት፤ ወጣኙም ፈጣሪውም አለፈለገ ሰላም በአስተማሪነትና በዳይሬክተርነት ተከሥተው እስከ 1967 ዓ.ም. በመሩበት ነበር፡፡ አለ ፈለገሰላም ሲገለጹ አቶ አለ ፈለገሰላም በሰላሌ ፍቼ ከተማ ሐምሌ 24 ቀን 1915 ዓ.ም. ተወለዱ፡፡ የሁለት ወር ጨቅላ ሳሉ አባታቸው አቶ ፈለገሰላም ኅሩይ መስከረም 1916 ዓ.ም. በፈረስ ጉግስ ጨዋታ ምክንያት በማረፋቸው ያደጉት በአያታቸው ቤት ነው፡፡ አያትየው ሠዓሊ አለቃ ኅሩይ ‹‹ልጄ ፈለገሰላም አልሞተም፣›› ለማለት ‹‹አለ›› ብለው ስም አወጡላቸው፡፡ አጎታቸው ብላታ እምአዕላፍ ኅሩይ አዲስ አበባ እስከወሰዷቸው ድረስ በአያታቸው በአለቃ ኅሩይና በወ/ሮ አፀደ ደስታ ቤት አደጉ፡፡ አለቃ ኅሩይ በሠዓሊነታቸው ዳግማዊ ምኒልክ የሚያመሰግኗቸው፣ በሳቸው ትዕዛዝም ምስላቸውን፣ የእንጦጦ ማርያምና ራጉኤል እንዲሁም የሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ሥዕላት ይሥሉ ነበር፡፡ ብላታ እምአዕላፍ ኅሩይም መንፈሳዊውንም ዓለማዊውንም ሥዕል በመሥራት የሚታወቁ በብርሃንና ሰላም ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ማተሚያ ቤት ተቀጥረው ይሠሩ ከነበሩት ሠዓልያን አንዱ ነበሩ፡፡ ‹‹ደማቆቹ /ፀሓያተ ሌሊት/ ከተሰኘው መጽሐፍ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት ሠዓሊ አለ ስለዐውደ ሕይወታቸው መነሻ እንዲህ ገልጸውለታል፡፡ ‹‹አያቴ ስለ ሣሏቸው የቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሥዕሎችና ከዚህም የተነሳ የታወቁ ሠዓሊ እንደነበሩ ሲወራ እስማለሁ፡፡ በተረፈ ለእኔ ያሳዩኝ ነገር የለም፡፡ እንዲያውም እኔን የላኩኝ የቅኔ ትምህርት እንድማር ወደ ዲቁና ነበር፡፡ ጥቂት ጊዜ መንፈሳዊ ትምህርት ተማርሁ፡፡ ብዙ ሳይቆይ በጣሊያን ጦርነት ጊዜ በአርበኝነት ዘምቶ የነበረው አጎቴ እምአዕላፍ ኅሩይ ከጦርነቱ መልስ የቤተሰብን ደኅንነት ለመጠየቅ መጣ፡፡ ወደ አዲስ አበባ ሲመለስ እኔን ‹አንተ መማር ያለብህ ዘመናዊ ትምህርት ነው› በማለት ይዞኝ ተመለሰ፡፡ በወቅቱ በጦርነት ችግር ተዘግተው የነበሩት ትምህርት ቤቶች ሁሉ የተከፈቱበት ጊዜ ስለነበረ፣ አጎቴ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት አስገባኝ፡፡ ከዚህም የተነሳ ከጦርነቱ በኋላ በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ከገቡት የመጀመርያዎቹ ተማሪዎች መካከል አንዱ ሆንኩኝ፡፡›› ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ (1928-1933) የመጀመርያዎቹ ዓመታት በአንድ አጋጣሚ፣ ከፋሺስቶች ግድያ ያመለጡት አለ ፈለገሰላም፣ ወደ ውጭ አገር ሄደው ዘመናዊ የሥዕል ትምህርት እንዲማሩ የረዳቸውን ገጠመኝም ሠዓሊው በማስታወስ እንዲህ ይገልጹታል፡፡ ‹‹አንድ ቀን ግርማዊነታቸው ተማሪዎችን ለመጎብኘት ወደ እኛ ትምህርት ቤት መጡ፡፡ በጉብኝታቸው መሀል የእኔን ሥዕሎች ተመለከቱና ‹ይህን የሣለው ማነው?› ሲሉ ጠየቁ፡፡ እኔ እንኳ በአጋጣሚ ከልጆቹ መካከል አልነበርሁም፤ ግን መምህራኑ ስሜን ጠርተው እኔ መሆኑን ነገሯቸው፡፡ በማግሥቱ ንጉሡ ይፈልጉሃል ተብዬ ቤተ መንግሥት ሄድሁ፡፡ ንጉሡም ከዚያን በፊት በሌላ ትምህርት አንደኛ በመውጣቴ ሸልመውኝ ነበር፡፡ ከሌሎች ልጆችም ጋር ወደ ውጭ አገር ለትምህርት ትሄዳላችሁ ተብለን በማናውቀው ምክንያት ሳንሄድ ቀርተናል፡፡ አሁን ከፊታቸው ቆሜ ሲያዩኝ አስታወሱኝና፡- ‹አንተ እስካሁን አልሄድክም እንዴ?› ሲሉ ጠየቁኝ፡፡ እኔም ንጉሥ ሆይ አለሁ አልኳቸው፡፡ ‹በል አሁን ጥሩ ሠዓሊ ሆነህ ተገኝተሃልና ወደ ውጭ አገር ሄደህ ሥዕል ተማር› በማለት ስላዘዙ ሁኔታዎች ሁሉ በአፋጣኝ ተከናውነው አሜሪካ ቺካጎ አርት ዩኒቨርሲቲ ራሴን አገኘሁት፡፡›› አለ ፈለገ በቺካጎ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን ካገኙ በኋላ አሜሪካ መቆየቱን አልፈቀዱትም፡፡ በአያታቸው የተጀመረው በአጎታቸው የቀጠለው ሥነ ጥበብ ከዘመናዊው ዕይታ ጋር በማዛመድ ብሂል ከትውፊት በማስተሳሰር፣ ነውን ከነበር በማቆራኘት ለአዲሱ ትውልድ ማድረስን በመፍቀድ አዲስ አበባ መመለስን ሰነቁ፡፡ ከዚያ በፊት በአውሮጳ ከተለያዩ የጥበብ መዲናዎች ልምድን ለመቅሰም መነሻቸውን ፈረንሣይ አደረጉ፡፡ በዚያ ከነበሩት የታሪክ ምሁሩ ዶ/ር ብርሃኑ አበበ ጋር መተዋወቃቸው በጃቸው፡፡ አቶ አለ ከዓመታት በፊት ከአንድ የውጭ ሚዲያ ጋር ሲያወጉም፣ ‹‹ዶ/ር ብርሃኑ እከሌን ብታይ ይሻላል እያለ ሙዚየሞችን አሳየኝ፤ ከኔ ጋር ብዙ ቀን ቆየ ማርሴይ፣ ሮም፣ ሲሲሊ የነማይክል አንጄሎ፣ የሬኔሳንስ ሠዓልያን የነራፋይሌ፣ ዳቪንቺ ሥዕሎችና ሐውልቶች ጎብኝቼ ወደ አገር ቤት ተመለስኩ፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ከባዕድ እየጎረስክ ወደ ዘመድ ዋጥ›› እንዲሉ እንደተመለሱ አደርገዋለሁ ብለው ያሰቡት የሥዕል ትምህርት ቤትን በአዲስ አበባ መመሥረት ነበር፡፡ በቀደመው ዘመን ተማሪዎች ትምህርታቸውን አጠናቀው ሲመለሱ ከንጉሠ ነገሥቱ አፄ ኃይለ ሥላሴ ፊት እየቀረቡ እጅ ይነሱ ስለነበር፣ በአጋጣሚው ጃንሆይን ሲያገኙ የተናገሩት ‹‹በአገራችን የሥዕል ትምህርት ቤት እንዲከፈትና የኔም ተግባር በሚከፈተው የሥዕል ትምህርት ቤት ማስተማር እንዲሆን እፈልጋለሁ፤›› የሚል ነበር፡፡ በትምህርትና ሥነ ጥበብ ሚኒስቴር ተመድበው በልጆች መማርያ መጻሕፍት ላይ ሥዕሎችን መሥራት ቢጀምሩም፣ ትምህርት ቤቱን የመክፈት ርዕያቸውን ለመጀመር ግን የመንግሥትን ውሳኔ አልጠበቁም፡፡ ራስ ደስታ ሆስፒታል አካባቢ በሚገኘውና በሚኖሩበት ቤት ግቢ ውስጥ በጣሊያኖች በተሠራው መጋዘን ውስጥ አስፈላጊውን ቁሳቁስ በማሟላት ቅዳሜና እሑድ ማስተማር ጀመሩ፡፡ ‹‹ሥዕል ለመማር የምትፈልጉና ፍቅሩ ያላችሁ ሁሉ በነፃ ልትማሩ ትችላላችሁ›› የሚለውን ጥሪያቸውን የተቀበሉ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ትምህርቱን ተከታተሉ፡፡ የትምህርትና ሥነ ጥበብ ሚኒስቴር ዋና ዳይሬክተር አቶ ከበደ ሚካኤል እገዛና ድጋፍ ከክረምቱ ባለፈ በበጋውም ማስተማሩን ተያያዙት፡፡ ካስተማሩዋቸው ተማሪዎች ማለፊያዎቹን በመምረጥ ያዘጋጁትና በልዕልት ተናኘ ወርቅ ኃይለ ሥላሴ የተመረቀው ዐውደ ርዕይም ትምህርት ቤት የመመሥረት ርዕያቸውን ዕውን የሚሆንበትን አጋጣሚ ፈጠረላቸው፡፡ ለዐውደ ርዕዩ ታዳሚዎች ባደረጉት ዲስኩርም፣ ‹‹በአገራችን የሥነ ጥበብ ተግባር ብዙ ነበር፤ የአክሱም ሐውልቶችን ያነፁ፣ ላሊበላን የቀረፁ፣ በጎንደርና ጎጃም ሥዕልን የሠሩ አሁን የሉም፣ ብቅ አላሉም፤ በኛ ጊዜ መጥፋት የለባቸውም፤ ነፍስ እንዲዘሩ መደረግ አለበት፡፡ ወደነበርንበት ትልቅ ተግባር በዓላማ መጓዝ አለብን፤›› በማለት ጥሪ አቀረቡ፡፡ በዐውደ ርዕዩ የቀረቡትን ሥዕሎችም እንዲገዙ በጠየቁት መሠረትም ብዙዎቹ ተሸጠላቸው፡፡ በዕለቱም ግሪካዊ ከበርቴ የሰጠውን 50,000 ብር ጨምሮ 78,000 ብር ተሰበሰበ፡፡ ለጃንሆይም ያስረከቡት ‹‹በራሴ ጥረት ይችህን ገንዘብ አግኝቻለሁ ተማሪ ቤት ይሥሩልን፤›› በማለት ነበር፡፡ ‹‹በአፄው ትዕዛዝም 150,000 ብር ተጨምሮበት የአዲስ አበባ ሥነ ጥበብ ትምህር ቤት ተከፈተ፡፡ በንጉሠ ነገሥቱ የልደት ቀን፣ ሐምሌ 16 ቀን 1950 ዓ.ም. ትምህርት ቤቱ ተመርቆ ሲከፈት ንጉሠ ነገሥቱ አፄ ኃይለ ሥላሴ ያስገነዘቡት ዐቢይ ነጥብ፣ በሥነ ጥበብ ታላቅ ሞያ ያላቸው ወጣቶች ሁሉ ጥንታዊውን አሠራር ሳይለቁ ከዘመናዊው ጋር እያዋሐዱ እንዲሄዱ የሚለው ነበር፡፡ አለ ፈለገሰላም ይህን መሠረተ ሐሳብ ከጥንቱም ቢሆን የሰነቁት ሐሳብ ነበር፡፡ በአለ ፈለገ ሰላም ሕይወት ዙሪያ ዘጋቢ ፊልም ያዘጋጀው ታዋቂው የፊልም ዳይሬክተርና ጋዜጠኛ መኰንን ሚካኤል፣ ሠዓሊና መምህሩን አለ ሲገልጽ ‹‹ሥዕላችን ባህሉን ሳይለቅ ዘመናዊነት እንዲይዝ አድርገዋል፤›› ብሏል፡፡ አያይዞም ‹‹እሳቸው [አለ] ቺካጎ አርት ኢንስቲትዩት ቢሄዱም፣ ቢማሩም ያንን ዘመናዊ ሥነ ጥበብና ዕውቀት ይዘው ቢመለሱም ጭልጥ ብለው የአውሮጳን የሥዕል ስታይል አልያዙም፡፡ የኢትዮጵያን ባህል ጠብቀዋል፤›› ሲሉም ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ሠዓሊና መምህሩ አለፈለገ ሰላም ለ16 ዓመታት በመምህርነት አስተማሩ፣ በዳይሬክተርነት መሩ፡፡ በገጸ ታሪካቸው እንደተመለከተው፣ በኢትዮጵያ የዘመናዊ የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት በሠዓሊ አለ ፈለገሰላም መመሥረት ለኢትዮጵያ የሥነ ጥበብ ታሪክ እጅግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ለማበርከት ችለዋል፡፡ እነ ሠዓሊ ገብረ ክርስቶስ ደስታ፣ እነ እስክንድር በጎሲያን፣ እነ ታደሰ ግዛውና እንዲሁም ሌሎች የትምህርት ቤቱ ምሩቃን የሆኑ ታላላቅ ሠዓልያን በትምህርት ቤቱ ውስጥ በማስተማር ከፍተኛ ዕድልም አስገኝቶላቸዋል፡፡ የደርግ መንግሥት ሲመጣ ሠዓሊና መምህር አለ ፈለገሰላም በራሳቸው ፍላጎት ሥራቸውን ለቀው ወደ ባህል ሚኒስትር በመግባት የቅርስ ጥገና ክፍል ኃላፊ በመሆን በየገዳማቱና በየአብያተ ክርስቲያናቱ ተከማችተው የነበሩትን ቅዱሳን መጻሕፍትና ሥዕላት ሥርዓት ባለው መልኩ እንዲጠበቁና እንዲጠገኑ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ ሠዓሊና መምህር አለ ፈለገሰላም በኢትዮጵያ ባሉ ታላላቅ አድባራትና ገዳማት የሠሯቸው ድንቅ የሥዕል ሥራዎች አያሌ ናቸው፡፡ አንዱ የመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል 1947 ዓ.ም. ሲሠራ፣ ትውፊታዊና ዘመናዊ የሥነ ጥበባት ሙያዎች ባዋሐደ መልኩ የኢትዮጵያን የቅዱሳን ታሪክና ድርሳናት አጢነው፣ በዓይነቱ ልዩ የሆነውን የቅድስት ሥላሴን ሥዕልና በጉልላቱ ላይ የተሣለውን የቅድስት ክርስቶስ ሠምራን ሥዕል ከሌሎች ቅዱሳን ሥዕላት ጋር በማስተጋበርና ውብ በማድረግ መሣላቸው ይጠቀሳል፡፡ በናዝሬት/አዳማ የቅድስት ማርያምን፣ በአዲስ አበባ የጎፋ ገብርኤልን፣ እንዲሁም የቁልቢ ገብርኤልን፣ በመርካቶ የቅዱስ ሚካኤል ካቴድራልንና በመርካቶ የቅዱስ ራጉኤልን ቤተክርስቲያንና በዋሽንግተን ዲሲ የመድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን እንዲሁም በሌሎች የሚገኙ ቅዱሳን ሥዕላት በመሥራት አሻራቸውን አስቀምጠዋል፡፡ ከነዚህ ቅዱሳን መካናት የቅድስት ሥላሴ ሥዕል በጃፓን በሐር ጨርቅ ላይ ታትሞ ለካቴድራሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም በይዘቱና በጥራቱ እጅግ ውብ የሆነው የአዲስ አበባ ሒልተን ሲመሠረት የላሊበላውን የሰላማዊ ፍቅርና የዕድል ተምሳሌት የሆነውን መስቀለ ጌጥ ምስል (ከስዋስቲካ ምስል ጋር የሚመሳሰለውን) እንዲቀናበር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ እንደገናም በዘመነ ደርግ የዚህን መስቀለ ጌጥ ምስል ለቀን መቁጠሪያ ሥዕል በሴቶች የጥበብ ልብስ ላይ ስለአደረጉ ትርጉሙ ተለውጦ የፋሺዝም (ናዚዝም) ምልክት ነው ብሎ መንግሥት ለእንግልት ዳርጓቸው ነበር፡፡ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት በ93 ዓመታቸው ሐምሌ 4 ቀን 2008 ዓ.ም. ያረፉት አለ ፈለገሰላም፣ ሥርዓተ ቀብራቸው ሐምሌ 6 ቀን በደብረ ሊባኖስ ከመፈጸሙ በፊት በዋዜማው ሐምሌ 5 ቀን፣ በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የመታሰቢያ ዝግጅት ተደርጎላቸው ነበር፡፡ በዕለቱ በቀረበው ዐውደ ታሪካቸው እንደተገለጸው፣ ሥዕሎቻቸው የኢትዮጵያ ትውፊታዊንና ዘመናዊ የእውነታ አሣሣልን ያቀናጁ፣ ብሔራዊና ኢትዮጵያዊ ድባብን የተላበሱ፤ ስሜትንና ህሊናን የሚስቡና የተረጋጉ ሥዕላት ናቸው፡፡ ይህንንም ብዙዎቹ የሥነ ጥበብ ታሪክና ሒስ ምሁራን ይመሰክራሉ፡፡ እኒህ ድንቅ ሥራዎቻቸው በአሜሪካ፣ በጀርመን፣ በህንድ፣ በሶቪየት ኅብረት፣ በቼኮዝላቫኪያ፣ በግሪክና በዩጎዝላቪያ ታይተዋል፡፡ ሠዓሊና መምህር አለ ፈለገሰላም ከሙያቸው ውጪ የተለየ ክህሎት ነበራቸው፡፡ ስፖርት (ዮጋ) የመሥራት፣ ንብ የማነብና ዓሳ የማጥመድ ወዘተ. የመዝናኛ ልምድ እንደነበራቸው ይታወቃል፡፡ ሠዓሊና የሥነ ጥበብ መምህሩ አለ ፈለገሰላም ከባለቤታቸው ወ/ሮ አስቴር ክፍለእግዚእ የአንድ ሴት (መሠረት አለ) እና የአንድ ወንድ ልጅ (ቴዎድሮስ አለ) አባት ሲሆኑ፣ የሦስት የልጅ ልጆችና የአንድ ልጅ ቅድመ አያት ነበሩ፡፡ መወድስ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከስድስት ዓመት በፊት፣ አለ ፈለገሰላም ላበረከቱት የሥዕል አለኝታነት ክብር ለመግለጽ፣ የመሠረቱትን ትምህርት ቤት በስማቸው እንዲጠራ አድርጓል፡፡ በኢትዮጵያ ሦስተኛው ሚሊኒየም ዋዜማም፣ በአሜሪካ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የተመሠረተውና ‹‹ሲድ›› (SEED) በሚል ምሕፃር የሚታወቀውን ዓመታዊ ሽልማት የሸለማቸው ‹‹በሥዕልዎ ባህላችን ስለገለጹና ዘመናዊ የሥዕል ጥበብን ለኢትዮጵያ ስላስተዋወቁ›› በማለት ነበር፡፡ ‹‹ደማቆቹ የአንዳንድ ታዋቂ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት የሕይወት ውልብታ›› በሚል ከስምንት ዓመት በፊት መጽሐፍ ያሳተሙት ሰሎሞን ጥላሁንና ሥምረት ገብረማርያም፣ ታሪካቸውን ከጻፉላቸው ታዋቂ ኢትዮጵያውያን አንዱ አለ ፈለገሰላም ኅሩይ ነበሩ፡፡ በታሪካቸው መካተቻ ላይ የጻፉት መወድስ እንዲህ ይላል፡፡ ለኢትዮጵያ ሥዕል አምላክ ሲያስብለት አለ አመለጠ ከፋሺስቶች ጥይት ቀለሙን ነከረ ሸራውን ወጠረ ጥበቡን ሊጠበብ የዘሩን ቈጠረ የፈረንጁን ሥዕል ተምሮ መጣና ዐውደ ገብ አረገው በኢትዮጵያ ቃና የንጉሥ ደጅ ጠንቶ ወትውቶ ለበላይ ሥዕልን በኢትዮጵያ አረገው ዘመናይ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...