Monday, March 4, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊመልዕክተኛ ሞተረኞች

መልዕክተኛ ሞተረኞች

ቀን:

ቀይ የትራፊክ መብራት በርቶ መኪኖች ከእንቅስቃሴ ሲገቱ፣ በመኪኖቹ መሀል ተላልፈው ፊት ለፊት የሚደረደሩ ሞተረኞች መመልከት የተለመደ ሆኗል፡፡ ይህ በግላቸው እንዲሁም በድርጅት ሞተርን እንደ አማራጭ መጓጓዣ የሚጠቀሙ ቁጥር መጨመሩን ሊያመለክት ይችላል፡፡ ከሞተረኞቹ መካከል እንደ የኢትዮጵያ ፖስት አገልግሎት ድርጅት ያሉ ቀደምት ድርጅቶች ቅጥረኞችና የዲኤችኤልን የደንብ ልብስ ለብሰው ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላው በፍጥነት የሚጓጓዙም ይገኙበታል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ምግብና ቁሳቁስ በታዘዙበት ቦታ በማድረስ የተሰማሩ የግል ድርጅቶች ሞተረኞች እየተቀላቀሉ ነው፡፡ አፋጣኝ የጫት አቅርቦትም በዚህ ረገድ ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡ ዴሊቨሪ ሰርቪስ (ሰዎች አንዳች ነገር ወደ ፈለጉት ቦታ እንዲወሰድላቸው ሲጠይቁ የማጓጓዝ አገልግሎት) በተቀናጀ መልኩ እየተካሄደ ይገኛል፡፡ ምግብ፣ መጠጥ፣ ዶክመንት፣ አበባና ላፕቶፕ ብዙዎች እንዲጓጓዙላቸው ከሚጠይቁት ውስጥ ናቸው፡፡ እነዚህን በአጭር ጊዜ ከአንድ ስፍራ ወደ ሌላው የማጓጓዝ ቢዝነስ በተቀረው ዓለም ዘመናት አስቆጥሯል፡፡ በአገራችን መሰል አገልግሎት የተጀመረው በቅርቡ ቢሆንም፣ ዕቃ ለማዘዋወር የተለያዩ መንገዶች ነበሩ፤ አሉም፡፡ የጹሑፍ መልዕክትን ከቦታ ቦታ በማዘዋወር ረገድ በአፄ ምኒልክ ዘመን ወደ አገራችን የገባው የፖስታ አገልግሎት ይጠቀሳል፡፡ መልዕክተኛ ወይም ፖስተኛ ይባሉ የነበሩት የድርጅቱ ሠራተኞች በእንጨት ጫፍ ስንጥቅ ፖስታ ሰክተው በእግራቸው ይጓጓዙ ነበር፡፡ ዝናብና ፀሐይ እየተፈራረቀባቸው፣ ረሀብና ጥማትን እየቻሉ የፖስታ አገልግሎት ዛሬ ለደረሰበት መሠረት የጣሉ የእነዚህ ፖስተኞች ምሥል፣ ዛሬ የድርጅቱ አርማ ነው፡፡ ዕቃ በማጓጓዙ ረገድ ድርጅቱን ጨምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተሰማርተዋል፡፡ ሞተር፣ መኪና፣ መርከብ፣ አውሮፕላን ይጠቀማሉ፡፡ ቀደም ባሉት ጊዜያት ፈረስና ግመል ለመጓጓዣነት ውለዋል፡፡ ከስድስት ወራት በፊት ሥራ የጀመረው ተላላኪ ዴሊቨሪ ሰርቪስ ዋነኛ ትኩረት ደንበኞች ከሚፈልጉት ሬስቶራንት ያሉበት ድረስ ምግብ ማድረስ ቢሆንም፣ አበባና ዶክመንቶችም ያጓጉዛሉ፡፡ በድረ ገጻቸው ሬስቶራንቶች፣ ከሚያቀርቡት ምግብና የዋጋ ዝርዝር ጋር ይገኛል፡፡ በስልክ ወይም ኦንላይን ማዘዝም ይቻላል፡፡ ከማክሰኞ እስከ እሑድ ከምሳ ሰዓት እስከ ምሽት የሚሰጡት አገልግሎት፣ የአዲስ አበባን አራቱም አቅጣጫ ያዳርሳል፡፡ ከድርጅቱ ባለድርሻዎች አንዷ አደይ ፍስሐጽዮን እንደምትናገረው፣ ድርጅቱን ያቋቋሙት የአገልግሎቱ ፍላጎት መኖሩን ከግምት በማስገባት ነው፡፡ ሐሳቡ በአገሪቱ ብዙም ስላልታወቀ ፈቃድ ከማግኘት ጀምሮ ፈተናዎች ገጥመዋቸዋል፡፡ ‹‹ከጠበቅነው በተሻለ ደንበኞች ቢኖሩንም አሁንም ሐሳቡ ሁሉም ዘንድ ደርሷል ማለት አይቻልም፤›› ትላለች፡፡ ደንበኞቻቸው በቤታቸው ወይም ሥራ ቦታ ሆነው ያዛሉ፡፡ ካዘዙት ምግብ፣ መጠጥ ወይም አበባ ዋጋ ውጪ 60 ብር ለሞተረኞቹ ይከፍላሉ፡፡ ያዘዙት ነገር በአንድ ሰዓት ውስጥ እንደሚደርስ ድርጅቱ የሚያሳውቃቸው ሲሆን፣ ከዘገየ 50 በመቶ ቅናሽ ይደርግላቸዋል፡፡ አገልግሎቱን የሚጠቀሙ ኢትዮጵያውያንና የውጭ ዜጎችም እየተበራከቱ መምጣታቸውን አደይ ትናገራለች፡፡ እንደ ችግር ከምትጠቅሳቸው መካከል የመሠረተ ልማት ዝርጋታ መጓተት ትልቁን ድርሻ ይወስዳል፡፡ ሌሎች አገሮች ካለው አገልግሎት አንፃር የኢትዮጵያው ውጣ ውረድ ቢኖረውም፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ለውጥ እንደሚመጣ ታምናለች፡፡ አሁን ከሚሰጡት አገልግሎት በተጨማሪ ማንኛውም ዓይነት ዕቃ ቢሆን የማድረስ ፍላጎት አላቸው፡፡ ‹‹ጊዜ ገንዘብ ነው፤ የሰዎች ሕይወትም በሩጫ የተሞላ ነው፡፡ ዕቃ ሲረሳ ወይም በፍጥነት ወደ አንድ ቦታ መላክ ሲፈለግ ማጓጓዝ እንፈልጋለን ይህን አገልግሎት ለመጀመር ግን የደንበኞቻችንን እምነት ማግኘት ይኖርብናል፤›› ትላለች፡፡ ከቦታ ቦታ መዘዋወር የሚያሻቸው ክንውኖች፣ የኦንላየን ግብይትና ሌሎችም የዴሊቨሪ ሰርቪስ የሚያስፈልጋቸው ቢዝነሶች መስፋፋታቸው፣ የደንበኞቻቸውን ቁጥር እንደሚያሳድገው ታስረዳለች፡፡ በዓለም ላይ በእጅጉ የተስፋፋው አገልግሎቱ ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱም ጥሩ ጅማሮ እንደሆነ ታምናለች፡፡ በተላላኪ ዴሊቨሪ ሰርቪስ ድረ ገጽ አዲስ አበባ ውስጥ የሚታወቁ ሬስቶራንቶችን፣ ድርጅቱ የሚጠቁማቸው ሬስቶራንቶችንና የምግቦቻቸውን ዝርዝር ማግኘት ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያ፣ የጣልያን፣ የቻይናና ሌሎችም አገሮች፣ ሥጋ ነክና፣ የአትክልት ምግቦች በአማራጭነት ቀርበዋል፡፡ ወደ ዴሊቨር አዲስ ድረ ገጽ ሲገቡ እንደ አካፑልኮ፣ አንቲካ፣ ቻይና ባርና ሲሹ ያሉ ሬስቶራንቶችን ዝርዝር ያገኛሉ፡፡ ሬስቶራንቶቹ ያሉበት አካባቢና ሬቲንግ (በአገልግሎታቸው የተሰጣቸው ኮከብ ብዛት) ተያይዞ ይጻፋል፡፡ ደንበኞች ከሬስቶራንቶቹ እስከ አራት ኪሎ ሜትር ርቀት ካሉ 60 ብር፣ ከአራት እስከ ሰባት ኪሎ ሜትር ርቀት 75 ብር ይከፍላሉ፡፡ ኦንላየንና በስልክም የሚያዙ ሰዎች ያሉበትን አካባቢ ያሳውቁና ሞተረኞች በጂፒኤስ ያገኟቸዋል፡፡ የዴሊቨር አዲስ ዋና ሥራ አስኪያጅ ፈገግ ፀጋዬ ቢዝነሱን የጀመረው በሌሎች አገሮች ካለው ተሞክሮ በመነሳት ነው፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት ሥራ ሲጀምሩ ከነበረው አንፃር ነገሮች እየተሻሻሉ ቢመጡም፣ የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎት መቆራረጥ ሥራቸውን ይፈታተኑታል፡፡ መንገድ ሲዘጋጋ ወይም ዝናብ ሲሆን፣ ሞተረኞች ለመንቀሳቀስ ይቸገራሉ፡፡ ከአጎራባች የአፍሪካ አገሮች አንፃር ዘርፉ ብዙ እንደሚቀረውም በመናገር፣ ‹‹እነዚህ ቢስተካከሉ ብዙ ድርጅቶች ቢዝነሱን መቀላቀል ይችላሉ፤›› ይላል፡፡ አሁን ከእሑድ ውጪ በሁሉም ቀናት ከምሳ ሰዓት እስከ ምሽት ይሠራሉ፡፡ አንዳንድ ሬስቶራንቶች ሙሉ በሙሉ የነሱን አገልግሎት ብቻ እንዲጠቀሙ (ኤክስክሉሲቭ) ስምምነት ያደርጋሉ፡፡ የተጠቃሚዎች ፍላጎት በመኖሩም አገልግሎቱን ከአዲስ አበባ ውጪ የማስፋፋት ዕቅድ አላቸው፡፡ በተመሳሳይ ሙዳይ ጊፍት ሾፕ ስጦታ የማድረስ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ከኢትዮጵያ ውጪ የሚኖሩ ሰዎች ኢትዮጵያ ላሉ ወዳጆቻቸው አበባ፣ በግ፣ ውስኪና ሌላም ስጦታ እንዲላክላቸው ያዛሉ፡፡ የክሬዲት ካርድ ሲስተም አለመዘርጋቱ የክፍያ ሥርዓቱን ፈታኝ እንደሚያደርገው የሚናገሩም አሉ፡፡ በድርጅት ከሚንቀሳቀሱት በተጨማሪ የዴሊቨሪ ሰርቪስ በግላቸው የሚሰጡ ሞተረኞችም የደንበኞቻቸውን የዕለት ተለት እንቅስቃሴ ቀላል ለማድረግ ሲሞክሩ ይታያሉ፡፡ ለምሳሌ የመብራት፣ ውኃና ስልክ ክፍያ ከመፈጸም ጀምሮ የደንበኞችን ጨረታ የሚያስገቡና ግብር የሚከፍሉ ሞተረኞች አሉ፡፡ ሞተረኞቹ በመጠነኛ ክፍያ ስዎችንም ያጓጉዛሉ፡፡ ይህን አገልግሎት ከሚሰጡ አንዱ ሞተረኛ ግርማይ መኰንን ነው፡፡ በተለያዩ ድርጅቶች ተቀጥሮ ዕቃ የማመለላስ ሥራ ለዓመታት የሠራ ሲሆን፣ አሁን በተላላኪ ዴሊቨሪ ሰርቪስ ይሠራል፡፡ ምግብና መጠጥ እንዲሁም እንደ ላፕቶፕ ያሉ ቁሳቁሶችን ለማመላለስ የተሠራ ሳጥን ሞተሩ ላይ ተገጥሞለታል፡፡ ቅዳሜና እሑድ ሥራ የሚበዛባቸው ቀኖች ሲሆኑ፣ ደንበኞች ለቤተሰቦቻቸው፣ ለጓደኞቻቸው አንዳንዴም ለተለያዩ ዝግጅቶች ያዛሉ፡፡ የታዘዙትን ነገር ለመሸመት በሚሄዱባቸው ቦታዎች ማንነታቸው በደንብ ልብሳቸው ስለሚታወቅ ትብብር እንደሚደረግላቸው ይናገራል፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ በሞተሩ ያልደረሰበት ቦታ ባይኖርም፣ ከገርጂ ሰንሻይን፣ ኦልድ ኤርፖርትና አዋሬ አካባቢ ብዙ ትዕዛዞች ይደርሱታል፡፡ እንደ ቃሊቲ ያሉ የትራፊክ መጨናነቅ ባለባቸው ሰፈሮች በአንድ ሰዓት ውስጥ ትዕዛዝ ለማድረስ ቢያስቸግርም የቻለውን ያህል ይጥራል፡፡ ‹‹የትኛውም ዓይነት ነገር ሲጓጓዝ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ ከፍተኛ ዋጋ ያላቸውና በቀላሉ የማይተኩ ሲሆኑ ኃላፊነቱ የበለጠ ይከብዳል፤›› የሚለው ግርማይ፣ ብዙዎች ከምግብና መጠጥ ውጪ አገልግሎቱን ለመጠቀም የማይደፍሩት ለዚህ ሊሆን እንደሚችል ያምናል፡፡ የዴሊቨሪ ሰርቪስ አገልግሎት ተጠቀሚዎች ቁጥር እየጨመረ እንደመጣና የሚያገኙት አገልግሎት ቀላል ነገሮችን በማጓጓዝ መወሰን እንደሌለበት ይናገራል፡፡ ሞተር በቀላሉ፣ በአጭር ጊዜ ምግብም ይሁን ቁሳቁስ ለማዘዋወር አመቺ መጓጓዣ በመሆኑ አገልግሎቱ በመላው አገሪቱ ቢስፋፋ መልካም ነው ሲልም ይገልጻል፡፡ ወጪው እንደሚሄድበት ሰፈር ርቀት ቢወሰንም፣ በሳምንት እስከ 230 ብር ለነዳጅ ያወጣል፡፡ አቶ ኢዮብ ረዳ የሚኖረው ገርጂ ኮንዶሚኒየም ውስጥ ሲሆን፣ በኮንዶሚኒየሙ የሚገኙ ካፌዎች የሚሰጡትን ዴሊቨሪ ሰርቪስ ዘወትር ይጠቀማል፡፡ ዴሊቨሪ አዲስን እንደ መንዲና ሲሹ ካሉ ሬስቶራንቶች ምግብ ሲፈልግ ያዛል፡፡ ለዓመታት አሜሪካ የኖረው ኢዮብ፣ ዴሊቨሪ ሰርቪስ ዓለም ላይ ከሚገኝበት ደረጃ አንፃር ብዙ እንደሚቀረው ይናገራል፡፡ ‹‹ድርጅቶቹ ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ በመጠቀምና ከዓመታት በፊት ሥራውን ከጀመሩ አገሮች ተምረው የተሻለ አገልግሎት መስጠት ይችላሉ፤›› ይላል፡፡ ከ29 ዓመታት በፊት አሜሪካ ውስጥ የመጀመሪያ ሥራው ፒዛ በስልክ የሚታዘዝበት (ፒዛ ሀት ነምበር) እንደነበር ያስታውሳል፡፡ እሱ ከሠራበት ጊዜ አንፃር ደንበኞች ፈጣን አገልግሎት የሚያገኙበት መንገድ እየተሻሻለ መምጣቱን እንዳስተዋለም ይገልጻል፡፡ ደንበኞች በቀላሉ ትዕዛዝ የሚያስተላልፉባቸው አፕልኬሽኞች ቢሠሩ፣ የመኖሪያ ቤቶች አድራሻ በቀላሉ የሚገኝበት ሥርዓት ቢዘረጋ ሁኔታዎች ይሻሻላሉ፡፡ ‹‹ዴሊቨሪ ሰርቪስ የሚሰጡ ድርጅቶች ስልክ ሲያነሱ ከሚሰጡት መልስ ጀምሮ፣ የደንበኞቻቸውን ትዕዛዝ የሚያደርሱበት ስዓትና ከደንበኞቻቸው ጋር የሚፈጥሩት ግንኙነት ለቢዝነሱ ዕድነት ወሳኝ ነው፤›› በማለትም ያስረዳል፡፡ በእሱ አስተያየት፣ ለደንበኞች ብዙ አገልግሎት ሰጪ አማራጮች መቅረባቸው ይበረታታል፡፡ አገልግሎቱ አስፈላጊ ስለሆነና የሆነ ቦታ መጀመር ስላለበት ያሉት እንቅስቃሴዎች አስደሳች ቢሆኑም፣ ድርጅቶች ራሳቸውን ማስተዋወቅና የደንበኞች አገልግሎትን ማጠናከር ያስፈልጋቸዋል፡፡ አራት ኪሎ አካባቢ የምትኖረው ወ/ት ትሑት ከበደ፣ የዴሊቨሪ ሰርቨስ ስለሚሰጡ ድርጅቶች የሰማችው በቴስት ኦፍ አዲስ የምግብ ፌስቲቫል ላይ ነው፡፡ በሞተር ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ተሞክሮም አላት፡፡ ወንድሟ ደግሞ ማህተም መርገጫና ዶክመንቶችም በሞተረኛ ይልካል፡፡ ‹‹አገልግሎቱ በአገራችን መኖሩ መልካም ቢሆንም፣ ዕቃዎቹ ሲዘዋወሩ ኃላፊነቱን የሚወስድ አካል ወይም ኢንሹራንስ የግድ ያስፈልጋል፤›› ትላለች፡፡ ከኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በተጨማሪ ቀላል ዕቃዎችን በአጭር ጊዜ የሚያደርሱ ዴሊቨሪ ሰርቪስ ሰጪዎች መኖራቸው አሁን ካለው አኗኗር ዘዬ ጋር አብሮ እንደሚሄድ ታምናለች፡፡ አውቶብስ ተራ ወይም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሄዶ በተሳፋሪዎች ወይም በሹፌሮች ዕቃ መላክ ከዴሊቨሪ ሰርቪስ ጋር ተመሳሳይነት አለው ትላለች ትሑት፡፡ በዘልማዳዊ መንገድ የሚካሄዱ መሰል እንቅስቃሴዎች ዘምነው በተደራጀ መንገድ መከናወን እንዳለባቸውም ትናገራለች፡፡ የዴልቨሪ ሰርቪስ ሌላው ገጽታ የጫት ዴሊቨሪ ነው፡፡ መስቀል ፍላወር ፣ ገርጂና ሃያሁለት አካባቢ ያሉና የሌሎች ሰፈሮች ጫት ቤቶችም፣ አገልግሎቱን መስጠት ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ ፈላጊዉ ቅርብ ከሆነ በእግርና በሳይክል ይደረስ የነበረው ጫት አሁን በሞተር ይሄዳል፡፡ ከዓመት በላይ በዚህ መንገድ የተጠቀመው ግዛቸው ደረጀ (ስሙ ተቀይሯል)፣ ‹‹የጫት ዴሊቨሪ በጣም የተስፋፋ ቢዝነስ ነው፤›› ይላል፡፡ ፈላጊዎቹ የትኛውም ቦታ ሆነው ቢያዙ ያሉበት ድረስ በሞተር ይወሰድላቸዋል፡፡ በእርግጥ ደንበኞቹ በሚያዙበት ጫት ቤት ሻጮች መታወቅ አለባቸው፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት የጫት ዴሊቨሪ የሚሰጡት ጫት አካፋፋዩች ብቻ ቢሆኑም፣ አሁን መጠነኛ ጫት ቤቶች ሳይቀር ሞተረኛ ያሰማራሉ፡፡ ሞተረኞቹ ለደንበኞች ኦቾሎኒ፣ ለስላሳና ውኃም ያደርሳሉ፡፡ ብዙዎቹን ሞተረኞች የሚከፍሏቸው ጫት ቤቶቹ ቢሆኑም ደንበኞች ጉርሻ እንደሚሰጡም ግዛቸው ይናገራል፡፡ ጫት መቃም የሚጀመርባቸው ስዓቶች ላይ ሞተረኞቹ ሥራ ይበዛባቸዋል፡፡ አገልግሎቱ በአዲስ አበባ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ ግዛቸው መቐለ ላይ በሳይክል ሐዋሳ ደግሞ በባጃጅ የጫት ዴሊቨሪ መጠቀሙን ይናገራል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...