Tuesday, April 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

እስኪ እየተሳሰብን!

ሰላም! ሰላም! ሰሞኑን ባሻዬ እየደጋገሙ “ነብር ዥንጉርጉርነቱን ኢትዮጵያዊም ኢትዮጵያዊነቱን ሊለውጥ እንዴት ይቻለዋል?” ሲሉኝ አልጥመኝ ብሏል። የለውጥ ኃዋርያት እንደ አሸን እየፈሉ እንደ ጤዛ በበነኑባት አገሬ፣ ነብር ለሚባል አውሬ በተሰናዳ የተፈጥሮ ድንጋጌ ቀለበት ውስጥ ኢትየጵያ ብቻ ስሟ መነሳቱ ዛሬ መጠየቅ ያለበት ይመስለኛል። አይመስላችሁም? ምነው እኔ እኮ ‘ኑ ተሰብስበን አውቶብስ እናቃጥል ተቋም እናፈራርስ’ አላልኩም። መቼም እዚህ አገር ጥያቄ መጠየቅ ማለት መንገድ መቆፈርና ንብረት ማውደም የሚመስለው ብዙ ነው። ብዙ ባይሆን ተቃጥሎ አቃጣዩ ይበዛ ነበር እንዴ? እሱን እኮ ነው የማወራው። “ታዲያ ያላስተማሩንን ከየት እናምጣው?” አለኝ በቀደም የባሻዬ ልጅ። “እኛ ራሳችን ማምጣት አንችልም እንዴ? ምናለበት በእኛ ቢጀመር?” ስለው፣ “ልፋ ብሎህ” ብሎ ሳቀብኝ። ሳቁ ከየት እንደሚቀዳ ይገባኛል። በውይይትና በንግግር ችግራችንን መፍታት እንችላለን ሲሉ ደማቸው ደመ ከልብ ሆኖ ከቀረው የየዋህ ምሁራን ደም የተቀዳ እንደሆነ ይገባኛል። ሳቅ ከደም ሲቀዳ አይቶ የማያውቅ ፈረንጅ አለ ካሉዋችሁ እንደምንም ተጣጥራችሁ ወደ ታሪካዊቷ አገር ኢትዮጵያ ጎራ እንዲል የግብዣ ወረቀት መላክ አለባችሁ። እስከ መቼ ነው እኛ ብቻ ፈረንጅ አገር የምንጋበዘው? እንዲያውም ለጭስ አልባው ኢንዱስትሪ መበረታታት የበኩላችንን የምናዋጣበት መንገድ ይኼ ይመስለኛል። ‘የቱ መንገድ?’ ብሎ የሚጠይቅ የረፈደበት ካለ ከደም ታሪክ ሳቅ የሚቀዳበት ብቸኛው የኢትዮጵያውያን የሕይወት ዘይቤ እለዋለሁ። ግድ የለም ማብራሪያውን በእኔ ጣሉት። እና ምን እያልኩ ነበር? አዎ ይህቺ ሰውና ነብርን ከእስከ ታሪክ ፍፃሜ ድረስ በአይለወጤ ሕግ የምታስተባብር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ብዙ ታስገርመኛለች። አንዳንዴም እያየነው የማናየውን ነገር መልሳ እያመጣች በጥሞና እንዳጤነው ታስገድደኛለች። ነብር ዥንጉርጉርነቱን ኢትዮጵያዊም ኢትዮጵያዊነቱን ከተባለ ዘንድ እስኪ አባባሉን የሚያፈርስ ምሳሌ ከታሪክ እናስስ። አልቀረብንም አቦ! አሁን ታሪክ አሳሽ ነኝ አሉ! ደላላው አንበርብር ምንተስኖት የሚለው ስሜ ‘ክርስቶፈር ምንተስኖት’ ካልተባለ አንሰማህም አትሉኝም መቼም። ነገሩ እንዳያያዛችን ከሆነ ባትሉኝ ነው የሚገርመኝ። ልብ አድርጉልኝ፡፡ ያ ከነብር የማይቀያየር ማንነት ጋር በአቻነት የተጠቀሰውና የማይለወጥ የተባለው ኢትዮጵያዊነት አንዱ ገጽታው ይኼ መሆኑ ነው። ‘እንዴት?’ ስትሉ ሰማሁ። እግዜር ይስጣችሁ። ዘንድሮ እኮ የገባውና ያልገባውን መለየት አልቻል ብሏል። ምክንያቱም ‘ለማን? ለምን? እንዴት? ወዴት?’ ማትሪክ ላይ ካልሆነ አልጠቀምባቸው ብለናል። ‘በምን አወቅክ ማትሪክ ላይስ እንዳለ?’ … ሆሆ፣ ደግሞ ብላች ብላችሁ ፈተናውን የሰረቅከው አንተ ነህ ልትሉኝ ነው? ግን ግን እናንተ ሆዬ፣ ዘንድሮ እንዲህ ማትሪክ ፈተና ‘ሜትሪክስ’ የሆነችው ለምንድነው? በዘንድሮው ማትሪክ ውጤት የመጣላቸው ተማሪዎች ‘ማርስ’ ላይ ነው የከፍተኛ ትምህርታቸውን የሚከታተሉት ተብሎ ነው? ታዲያ እንዲያ ካልሆነ አምናና ካቻምና ‘ድንቄም ትምህርት! ድንቄም ዩኒቨርሲቲ። ይኼው ስንት ዓመት ለፍተን ተምረን የተረፈን ድንጋይ መፍለጥ ነው’ ሲባል እንዳልነበር ምን ተገኝቶ ነው ጥያቄ መመንተፍ ሥራ የሆነው? ሌባ እስኪያዝ የያዘው ሥራ ነው ያሉት ሰውዬው ናቸው። ግን ገርሞኝ እኮ ነው። ታሪክ ላስስ ብዬ ጀምሬ ነው አይደል እዚህ ውስጥ የገባሁት? ነብር ዥንጉርጉርነቱን ኢትዮጵያዊም ኢትዮጵያዊነቱን የማይለቅበት ማሳያ ቁጥር ሁለት … የጀመርነውን መቼም ጨርሰን አናውቅም! አራት ነጥብ። ካላመናችሁኝ ታሪካችሁን አንብቡ። የሰው ባንክ ቡክ ማንበብ ይብቃ! ይህ ጀምሮ ያለመጨረስ ሥልት በሌሎች አገሮች ያለ ቢሆንም (ምንም ቢሆን ምን የሰው ዘር ያው የሰው ነውና) እኛ ላይ ገኖ ይታይብናል። ለምን? በሉ። ለምን አላችሁ? እሺ አሁን ለምን ‘አንልም!’ አላላችሁም? ለምን ‘በሉ’ የተባላችሁትን ሁሉ ትላላችሁ? ለምን እመኑ ያሏችሁን ሁሉ ታምናላችሁ? ለምንስ ሙቱ ለምንስ ኑሩ እንዳሏችሁ ትሞታላችሁ ትኖራላችሁ? ‘ነብር ዥንጉርጉርነቱን ኢትዮጵያዊም ኢትዮጵያዊነቱን አይቀይርም’ ሲል ጥቅሱ ይኼ ሦስተኛ ማመሳከሪያ ሆኖ መቅረብ የሚችል መሰለኝ። ሙቱ ሲሉን መሞትና ኑሩ ሲሉን መኖር! እስኪ እንደነዱን መነዳት ይብቃን! እንግዲህ ጨዋታ መሰለኝ የያዝነው። ዛሬ ሲያቀብጠኝ ጥቅል ርዕስ ለምን እንደመረጥኩ አልገባኝም። ብቻ በቀደም አንድ ስካኒያ ተሳቢ እያያሻጥኩ ቃሊቲ አካባቢ ለምሳ የሆነች የጀበና ቡና የሚፈላባት ወልጋዳ የጭቃ ቤት፣ ሽሮ አዝዤ ተቀምጫለሁ። ደንበኛዬ አብሮኝ አለ። ተዘፍኖለት የማይቦነው የእኛ አገር አቧራ እንደምታውቁት የፍዳና የላባችንን ቀን ሲመርግብን፣ ቀዳዳችን እንኳ አይቀረውም። ይሁን ብሎ ማለፍ ብቻ ነው። አቧራን በማስወገድ በአስፋልትና በኮብልስቶን ንጣፍ መንገድ ሙሉ ለሙሉ መራመድ እስክንችል ድረስ ይሁን ብሎ መተው ይበጃል እሺ። እኔ የማይበጃችሁን አልመክርም። እና ከዚያ ደንበኛዬ ጋር ስለሐበሻና ሐበሻዊነት እያነሳን እንጫወታለን። ደንበኛዬ ዳያስፖራ መሆኑን ያወቅኩት በኋላ ነው። “በቃ ይኼ አገር ለውጥ አይወድም ጃል፣ ሰው በጣም ይቀረዋል፤” እያለ ይቦተረፍብኛል። የሚለው ልክ ሳይሆን ቀርቶ ሳይሆን ያበሸቀኝ በመሀል በመሀል እሱ ያስተዋለውንና ያነፃፀረውን እኔ እንደማላውቀው ደምድሞ ላስተምርህ ስላለኝ ብቻ ነው። ልብ አድርጉልኝ። የማናውቀውን ሲነግሩን ብቻም አይደል፣ የምናውቀውም ሲደገምብን ደም ደም የሚለን እኛ ሐበሾች ብቻ ነን። (የግል አስተያየቴ እስከሆነ ድረስ ‘ብቻ’ የሚለውን ቃል ብቻውን እስኪቀር የመጠቀም መብቴ በሕገ መንግሥታችን ስም የተጠበቀ ነው አደራ) ታዲያ ደንበኛዬ ለውጥ አንወድም እያለ ትንሽ ትልቁን ሲኮንነው አላስችለኝ ብሎ “ስማ እንጂ!” አልኩት። “እኔ የዛሬን አያድርገውና ከፊል አውሮፓን አይቻለሁ። ሕዝቡ እዚያም እዚህም ያው ሁለት ዓይን፣ አንድ አፍንጫ፣ ሁለት ጆሮ፣ ሁለት እጅ ያለው የሰው ዘር ነው። እዚያም ልጉም እዚህም ልጉም አለ። እዚያም ሰልባጅ ለባሽ እዚህም ሰልባጅ አንጋች አለ። ግን እኔን ሳይገባኝ የቀረው የለውጥ ትርጉሙ ብቻ ነው?” ስለው ደንገጥ ብሎ አይቶኝ አንደበቱ ተሳሰረ። እውነት እውነት እላችኋለሁ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ቃላት እንጂ ሕይወት ተለዋውጣ አታውቅም! ካላመናችሁ ያለማመን ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው የተጠበቀ ነው ከማለት ውጪ፣ ዘመናትንና ታላላቅ ሥልጣኔዎችን የጊዜንና የሥፍራን ንፍቅ ሰብሮ የሚያስጎበኝ የፈጣሪ አቅም የለኝም፡፡ አዎ እኔን ለቀቅ፣ በለውጥ ስም የሚነግደውን ጠበቅ! አሁን ይኼን ያጫወትኳችሁ ወደ ህዳሴያችንና ትርጉም ለመምጣት ነው። ባሻዬ እንደነገሩኝ የቃሉ ጥሬ ትርጉም መታደስ ከሚለው የመጣ ነው፡፡ እንዲያውም ሰሞኑን በመልሶ ማልማቱ የህዳሴያችን ዕቅድ ምክንያት ቤታቸው በግብረ ኃይል የፈረሰባቸው የአጎታቸው ልጅ አንዱን ክፍል ይዘው ሲሰነብቱ ያጫወቱኝን ልንገራችሁ። “ልጅ አንበርብር እንደምታውቀው በአገራችን ታደሰ የሚለው ቃል ለሰው እንጂ ለአገር ገጽታ ለውጥ ሲያገለግል አታውቀውም። በመጀመሪያ ቃሉ ግስ ነበር። ሕይወት ግስ (ድርጊትና ድርጊት አመልካች ኑሮ ማለታቸው ነው) ስታጣ አየህ በስም ብቻ ታጅብሃለች። አንድም ለማፅናናት አንድም ለማሾፍ መሆኑ ነው፤” ካሉ በኋላ፣ የአጎታቸው ልጅ ጣልቃ ገቡ። “ቆይ እሺ አሁን የአገር ገጽታ ግንባታ የእኔን የሞቀ ኑሮ ከማፍረስ ጋር በምን ይገናኛል?” አሉ። “በልማት” አለ የባሻዬ ልጅ እየሳቀ። “ልማት ማለት ምን ማለት ነው?” አሉት። “ልማት ህልምና እንግሊዝኛ እንደፈቺው ስለሆነ መልስ የለኝም፤” ከማለቱ የባሻዬ ልጅ፣ ቤቱ በምፀት ፈገግታ ነፍሰጡር ጅብ በሰላም በመገላገሏ ሰበብ ያካፋል የሚባለውን ሰማይ መሰለ። “ሰው እያስኮረፉ አገር ማደስ አለ?” ሲሉ ደግመው ሰውዬው ባሻዬ ቆጣ ብለው፣ “በልማ ዝም ብለህ የምትበላውን ዋጥ ዋጥ አድርገው። የማይናገረው እህል እያለልህ የማይሰሙህን ሰዎች ሙጥኝ ማለት ምንድነው?” ሲሏቸው ወዲያው ካፊያው አባራ። ህዳሴው ግን ይቀጥላል አይዟችሁ! በሉ እንሰነባበት። ማንጠግቦሽ ያለወትሮዋ ሰሞኑን ጠይቃኝ የማታውቀውን ነገር ጠይቃኛለች። ያለ ልማዷ የአገር ባህል ቀሚስ ካልገዛህልኝ እያለች መቆሚያ መቀመጫ አሳጥታኛለች። ያ ያልኳችሁን ባለተሳቢ ጆሮውን ብዬ ደህና ኮሚሽን እንደያዝኩ መጀመሪያ ያደረግኩት የባሻዬን ልጄ ይዤ ሽሮ ሜዳ መሄድ ነው። ምናልባት በቅርቡ እንደ ባሻዬ የአጎት ልጅ ሽሮሜዳም ስምሽን ቀይሪ ተብላ ስትነጫነጭ እናያት ይሆናል። ከመሀል ከተማው የግንባታ ውክቢያ ርቃ እንዳለች እንደነበረችው ሳያት በደላላዊ አዕምሮዬ አስብ የነበረው ‘እዚህ ሠፈር በማሻሽጠው የመሬት ኮሚሽን ዱባይ ቦታ ካልገዛሁ ሞቻለሁ’ እያልኩ ነበር። ማንጠግቦሽ የምትወደው ዓይነት ጥልፍ ያለበት ቀሚስ ዓይኔ እንደገባ ሳላቅማማ ገዝቼ ወደ ሠፈሬ ተመለስኩ። የባሻዬ ልጅ በጊዜ ገብተህ ከመተኛትህ በፊት አንድ ሁለት እንበል ሲለኝ ሰዓቴን አየሁ። ገና 11 ሰዓት ነው። ለሥራ አውሮፓ የሄዱ ሰዎች ከነገሩኝ አንዱ ይገርመኝ የነበረው እስከ ምሽቱ አምስት ሰዓት ብው ያለ ብርሃን አለ የሚባለው ትዝ አለኝና እሺ አልኩት። ጎበዝ እኛ እኮ ከዶሮ ቀድመን ብንሰበሰብ አይገርምም። መገረም ከፈለጋችሁ ግን ይህቺም ኑሮ ሆና ግማሽ ቀን በእንቅልፍ የምንሸኘው ነገር ይገርማል። እናም ተያይዘን ወደ ተለመደችዋ ግሮሰሪ ስንገባ ከአፍ እስከገደፏ ሞልታ ጠበቀችን። “ሰው ፀንቶ በመጠጣትና በመስከር ህዳሴውን ለማብሰር የቆረጠ ይመስላል፤” ስለው የባሻዬ ልጅ ፈገግ ብሎ፣ “ሥጋቴ ህዳሴው እውን ሲሆን ሰው እንዳይጠፋ ነው፤” አለኝ። “እንዴት? እንዴት? ሰው ደግሞ ጠፍቶ ያውቃል? ባይሆን ትውልድ ያልፋል፤” ስለው፣ “ሰውማ ይጠፋል አንበርብር። አታየውም ሰውና መንግሥት እያደር እንዴት ሆድና ጀርባ እንደሆነ። ግስጋሴያችንና ራዕያችን ከግንዛቤያችንና ከዝግጅታችን ጋር አልሄድ ብሏል። ጭራሽ ከምንጨምረው የምናጣው በዝቷል። መንግሥትም ሥልጣኔ እንደሚመጣ ደግሞም ሥልጣኔ እንደሚያልፍ ዘንግቶታል። ሰውና ልቡ ግን ልብ አድርግ የሚነቃነቁ ነገሮች አይደሉም። ትዕግሥትና ጆሮ መስጠት ቁጣን ያረግባሉ። አለበለዚያ ግን ነገር ይበላሻል አንበርብር . . . ነገር ይበላሻል! እየሆነ ያለው እሱ ነው፤” ሲለኝ ብርግግ አልኩ። ኧረ የሰው አገሩ የት ነው ጎበዝ? ልቡ ነው ከተማው? ልብ እየደማ ከተማ ሲለማ እውን ገላ ያምርበት ይሆን? “በህጥር በስንቡል መቼ እጠኑኝ ይላል፣ እመር ያለው ገላ እንዲያው ደርሶ ያምራል፤” አለ ያገሬ ሰው። እስኪ እየተሳሰብን። መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት