Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊለነፍስ ያሠጉ ዝርፊያዎች

ለነፍስ ያሠጉ ዝርፊያዎች

ቀን:

በግምት ምሽት አሥራ ሁለት ሰዓት ገደማ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ያን ያህልም አልጨለመም፡፡ እናቷ በወቅቱ አክስቷ ቦሌ አካባቢ ተከራይታ ትኖር ከነበረበት ግቢ በር ላይ መኪናውን አቆመች፡፡ ከእናቷ ጐን ጋቢና የነበረችው አክስቷ ከመኪና ስትወርድ ከእናቷ ጐን ለመሆን የኋላ በሩን ከፍታ ወረደች፡፡ እናትና አክስቷ ግን ጨዋታቸውን ስላልቋጩ ቦርሳዋን እንደያዘች ውጭ ቆማ ጥቂት ደቂቃዎችን ማሳለፍ ነበረባት፡፡ ሦስት ወጣት ወንዶች አልፈዋቸው ሔዱ፡፡ እንደገናም ተመለሱ፡፡ ይህን ጊዜ ደስ የማይል ስሜት ስለተሰማት ቦርሳዋን ጠበቅ አደረገች፡፡ ለሦስተኛ ጊዜ ተመልሰው አንደኛው በኋላ በኩል ቦርሳዋን ለመንጠቅ ሞከረ፡፡ ትከሻዋ ላይ የነበረው ቦርሳዋን አንድ እጀታ በደንብ አድርጐ ይዞ ለመሮጥ ይሞክር ጀመር፡፡ እሷ ደግሞ ሌላኛውን እጀታ አጥብቃ ይዛ እሱ ሲሮጥ እሷም መከተል ጀመረች፡፡ እሱን አንደኛው ጓደኛው እጁን ከፊት ይዞት ፍጥነቱን እንዲጨምር ሊረዳው ይሞክራል፡፡ በዚህ ሁሉ ትግል አንዷን የቦርሳዋን እጀታ አለቀቀችም ነበር፡፡ ነገር ግን ኃይል ስለበዛባት መሬት ላይ መጐተት ጀምራ ነበር፡፡ ሁኔታው በቅፅበት የሆነ ነው፡፡ ምንም ዓይነት ድምፅ ባለማውጣቷ ጨዋታቸው ላይ የነበሩት እናትና አክስቷ ዞር ሲሉ ባዩት ነገር ደንግጠው መጮህ ጀመሩ፡፡ ከርቀት ወደዚያ አቅጣጫ የሚመጣ መኪና መብራት መታየት ጀመረ፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ መቀጠል እንደማይችሉ፤ የእሷንም የቦርሳዋን እጀታ አለመልቀቅ የተረዱት ዘራፊዎች ጥለዋት ሮጡ፡፡ ፊቷ ተጋግጦ ሌላ የሰውነቷ ክፍልም ተጐድቶ ነበር፡፡ ጉልበቷ ግን ለረዥም ጊዜ ተጐድቶ እንደነበር ትናገራለች፡፡ ‹‹ይህ ከመሆኑ ከሳምንት በፊት ናይሮቢ ሔጄ ነበር፡፡ ብዙ ሰው እንዳትዘረፊ ተጠንቀቂ ብሎኝ ነበር፡፡›› በማለት ለእንደዚህ ያለው ነገር እጋለጣለሁ ባላለችበት ቦታና ጊዜ ነገሮች መፈጠራቸው አስገርሟት አሳዝኗትም እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ የዝርፊያ ሙከራ በተደረገባት በዚያው ምሽት ከጥቂት ዕርምጃ በኋላ ቦታው ላይ ይዘዋወሩ የነበሩ ፖሊሶችን አግኝተው ሁኔታውን ገለጹላቸው፡፡ ጉዳዩን የሰሙት የፀጥታ ኃይል አባሎች ምላሽ ግን መልካም አልነበረም ትላለች፡፡ ዘራፊዎቹ የጐዳና ተዳዳሪዎች እንደሚሆኑ እነሱን ማግኘትም ከባድ እንደሆነ ነበር የተገለጸላት፡፡ በመጨረሻ ጉዳዩን ፖሊስ ጣቢያ ብታመለክትም ምንም የተገኘ ነገር የለም፡፡ እሷን ይህ ባጋጠመ በጥቂት ወራት ውስጥ ደግሞ ለ30 ዓመታት በኖሩበት አካባቢ አባቷ ምሽት ላይ ተደብድበው ተዘርፈዋል፡፡ በዚህም ጊዜ ለፖሊስ ያመለከቱ ቢሆንም የተገኘ ነገር የለም፡፡ ምንም እንኳ የተወሰነ ጉዳት ቢደርስባትም ፓስፖርቷን፣ ቦርሳዋ ውስጥ የነበረ በማዘጋጀት ላይ የነበረችው መጽሐፏን ረቂቅን፣ ስልኳን የመሰሉ ዋጋ ያላቸው ነገሮች ማትረፍ ችላለች፡፡ አባቷም ቢደበደቡም ገንዘባቸው ቢዘረፍም ሕይወታቸው ግን ተርፏል፡፡ ዝርፊያና ንጥቂያ የሕይወታቸው መጥፊያ የሆነ ግን አሉ፡፡ ስልክ፣ ላፕቶፕ ወይም ገንዘብ ለመዝረፍ በፈለጉ ዘራፊዎች እስትንፋሳቸውን ያጡ ጥቂት አይደሉም፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች በተለይም እንደ ኮተቤ፣ ጣፎ ያሉ ከከተማ ወጣ ያሉ አካባቢዎች ላይ አመሻሽ ላይ ወደ ቤት በመግባት ላይ ሳሉ በዘራፊዎች ተደብድበው ሕይወታቸውን ያጡ አሉ፡፡ በተለያየ አጋጣሚ ከሚሰሙት ከእነዚህ አጋጣሚዎች መገመት የሚቻለው ዘራፊዎች አስፈራርተው ገንዘብም ይሁን ዋጋ ያወጣል ያሉትን ነገር ከመውሰድ ይልቅ ስለሚዘርፉት ሰው ነፍስ ለሰኮንድ እንኳ ሳይጨነቁ ዕርምጃ ወስደው ኪስ መፈተሽን አማራጭ እያደረጉ መሆኑን ነው፡፡ ሕይወታቸው ያለፈ ወይም በድብደባ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በመጨረሻ ከኪሳቸው የሚገኘው ሁለት ወይም ሦስት መቶ ብር ወይም ተመሳሳይ ዋጋ የሚያወጣ ስልክ ሆኖ ሲገኝ የሰው ልጅ በሕይወት ለመኖር፣ ለሰውነት የሚሰጠው ቦታ ምንኛ ዋጋ እያጣ ነው? የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ አፍንጮ በር ኢትዮ ኮሪያ ፓርክ አካባቢ ሲኖሩ ከ20 ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል፡፡ ምሽት ሁለት ሰዓት ካለፈ የድረሱልኝ ጩኸት መስማት በአካባቢው እንግዳ ነገር እንዳልሆነ ይናገራሉ ወይዘሮ ተስፋነሽ (ስማቸው ተቀይሯል)፡፡ ሳይጨልም አሥራ ሁለት ሰዓት ገደማም በአካባቢው ዝርፊያ መኖሩን የሚናገሩት ወይዘሮ ተስፋነሽ ወደ እሳቸው ቤት በመሔድ ላይ የነበረች የቅርብ ዘመዳቸው በተገለጸው ሰዓት ቦርሳዋን ተቀምታ በትንሹ በጩቤ ጫር የተደረገችበት አጋጣሚ መኖሩንም ያስታውሳሉ፡፡ እሳቸው እንደሚሉት ሳይጨልም በቀንም ቦርሳ ነጥቆ መሮጥ (ቅርብ ወዳለው ወንዝ መግባት) በተደጋጋሚ የሚስተዋል ነገር ነው፡፡ ለዝርፊያ ነው አይደለም በሚለው ላይ እርግጠኛ መሆን ባይቻልም ሰዎች ተገድለው ወንዝ ውስጥ የተገኙበት አጋጣሚም ጥቂት የሚባል አይደለም፡፡ እንደ እሳቸው ያሉ የአካባቢው ኗሪዎች ብቻም ሳይሆኑ በተለያየ እንደ ሥራና ትምህርት ባሉ ምክንያቶች አካባቢውን የሚያዘወትሩም ትንሽም ቢሆን ጨለም ካለ በአካባቢው ማለፍ እንደማይደፍሩ ይናገራሉ፡፡ ብዙዎቹም የሚፈሩት መዘረፍን ብቻ ሳይሆን በአጋጣሚው ሕይወቴን አጣለሁ ብለው ነው፡፡ አካባቢው ላይ ያለውን የዝርፊያ ሁኔታ የገለጹልን ወይዘሮ ተስፋነሽ ‹‹የሚገርመው በዙሪያችን ሦስት ፖሊስ ጣቢያዎች መኖራቸው ነው›› በማለት ተቃርኖውን ይገልጻሉ፡፡ የተነጠቁትን ሞባይል ስልክ ለማስመለስ ዘራፊዎችን ተከትለው ጨለማ ውስጥ በመግባታቸው ሕይወታቸውን እንደዋዛ ያጡ አሉ፡፡ ሕይወቴን አጣለሁ ብለው በፍፁም በማያስቡበት በሠፈራቸው ብሎም ከደጃፋቸው ላይ በዘራፊ ተደብድበው የሞቱም አሉ፡፡ ንጥቂያና ቅሚያ በምሽት ቢያይልም በቀን በጠራራ ፀሐይ ሲፈጸምም ታይቷል፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች ንጥቂያና ቅሚያን የዕለት ተዕለት ተግባራቸው ያደረጉ ዘራፊዎች በተቃራኒው በላባቸው ለማደር አካባቢው ላይ በሚገኙ እንደ ላዳ ሾፌር ወይም ሱቅ በደረቴ ባሉ ሁሉ ይለያሉ፡፡ ቦሌ አካባቢ ከሚንቀሳቀሱ የውጭ አገር ዜጐች በቀን ገንዘብና ስልክ ነጥቀው ለማምለጥ የሞከሩ ቀማኞችን ይዘው በተደጋጋሚ ለፖሊስ አሳልፈው መስጠታቸውን ነገር ግን ቀማኞቹን በሰዓታት ውስጥ እዚያው ቦታ ላይ በማየታቸው ተመሳሳይ ነገር ሲፈጸም እየተመለከቱ ምንም ላለማለትና ላለማድረግ መወሰናቸውን የገለጹልን የላዳ ሾፌሮች አሉ፡፡ ሳይደክሙ በአቋራጭ ለመክበር አልያም በላባቸው ከማደር ይልቅ በሰው ላብ መኖርን የመረጡ ዝርፊያና ንጥቂያን አማራጭ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ ሲያደርጉም እየታየ ነው፡፡ ሰዎች እዚህ ውሳኔ ላይ ደርሰው ወደ ተግባር የሚገቡት ከዚህ እንዲጠበቁ የሚያደርጉ ውስጣዊና ውጫዊ የቁጥጥር መንገዶች ሲላሉ ነው ይላሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሶሲዮሎጂ ዲፓርትመንት መምህር የሆኑትና ፒኤችዲያቸውን በመሥራት ላይ የሚገኙት አቶ ክቡር ተገኘ ወርቅ፡፡ ውስጣዊ የቁጥጥር መንገድ የሚሉት በሃይማኖት ትምህርትና እሴት የማኅበረሰቡ እሴትና በቤተሰብ አስተምሮ በአስተዳደግ ወቅት የተሠራ ሰዎች ወደ ስርቆትና መሰል ነገሮች እንዳይገቡ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ ውጫዊው ደግሞ የፍትህ ሥርዓቱ ለሥርቆት እና መሰል ተግባሮች የሚያስቀምጠው ቅጣት ነው፡፡ ስለዚህ ልስረቅ ልቀማ ቢባል ህሊና ይታገላል፣ የፍትህ ሥርዓቱ የሚጥለው ቅጣትም ያስፈራል፡፡ እነዚህ ውስጣዊና ውጫዊ የቁጥጥር መንገዶች ግን በተለያየ ምክንያት ሲሸረሸሩ ይስተዋላል፡፡ አማራጭ ያጣ ሁሉ ስርቆትና ቅሚያን አማራጭ ያደርጋል ማለት ባይሆንም ያሰቡት ለመድረስ ሳይቻል፣ ሲቀር አማራጭ ሲጠፋ ዝርፊያን አማራጭ የሚያደርጉ እንዳሉ ግልጽ ነው፡፡ ሁኔታዎች ሲመቻቹ ማለትም እንደ ሱስ፣ ቁጥጥር መላላትና የቅጣት ቀላል መሆን ዓይነት ነገሮች ደግሞ ነገሩን የሚያባብሱ መሆናቸው በጥናት ተመልክቷል፡፡ ለምሳሌ ምንም እንኳ ተጨማሪ ሌላ ጥናት የሚያስፈልገው ቢሆንም አቶ ክቡር የሠሩት ጥናት እንደሚያሳየው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ወይም ለጐዳና ተዳዳሪዎች ማረሚያ ቤት የሚያስፈራ ነገር አይደለም፡፡ ስለዚህም በተደጋጋሚ ወንጀል እየፈጸሙ ማረሚያ ቤት ሊገቡ ይችላሉ፡፡ ስለዚህም እንደነዚህ ያሉ ነገሮችን ከሥራቸው ለመፍታት መሥራት ያስፈልጋል፡፡ እገሌ የሕንፃ ባለቤት የሆነው ይሔን ያን ሠርቶ አይደለም ወይ፣ ባለሥልጣናቱ በሙስና እንዲህ እያደረጉ አይደለም ወይ እያሉ ብዙዎችን ሥርዓቱንም በመውቀስ እኔ ለዚያውም ተቸግሬ ይህን ዕርምጃ ብወስድ ምን አለበት? የሚል ዓይነት አመለካከትም በሰዎች ዘንድ እየተፈጠረ እንዳለ አቶ ክቡር ያስረዳሉ፡፡ ይህ የሚያሳየው ደግሞ ሰዎች ምናልባትም የሆነ ጊዜ ላይ ነውርና ያልተገባ ይሉት የነበረን ነገር ለማድረግ ለራሳቸው ምክንያት መስጠት እየቻሉ ያሉበት ጊዜ ላይ መደረሱን ነው፡፡ እንደ ቅሚያና ነጠቃ ያሉ ሌብነቶች ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር መቀነሱን በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የከባድ ወንጀል ምርመራ ኃላፊ ኮማንደር ዓለማየሁ አያልቄ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል በተደራጀ መልኩ የሚፈጸም ዝርፊያ በተለይም በአዲስ አበባ የለም የሚባልበት ደረጃ ላይ መድረሱን ይናገራሉ፡፡ ንፅፅሩን የሚያሳዩ ቁጥሮችን ለመስጠት እንደማይችሉ የሚናገሩት ኮማንደሩ ለዚህ በምክንያትነት የሚያስቀምጡት ኮሚሽኑ የሥራ አፈጻጸሙን ገና ያልገመገመ መሆኑን ነው፡፡ ቅሚያና ነጠቃ ቀንሷል የሚሉት ኮማንደር ዓለማየሁ ሁኔታው ኅብረተሰቡን በሚያማርር ደረጃ አለመሆኑን ለማስረገጥ ይሞክራሉ፡፡ እሳቸው እንደሚሉት ይህ የሆነው ደግሞ በአሥሩም ክፍላተ ከተሞች የፖሊስ ኃይሎች ሁሌም ስለሚሰማሩ፤ ፖሊሶቹም ከተባሉበት ቦታ ላይ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆኑን የሽፍት ኃላፊዎች በሬዲዮ መገናኛና በአካል ስለሚያረጋግጡ ነው፡፡ እሳቸው ይህን ቢሉም በፌደራል ፖሊስ በሚጠበቀው የገርጂ የፓርላማ የጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ እንኳን የፓርላማ አባላት ተደብድበው መዘረፋቸውን ከቀናት በፊት መዘገባችን ይታወቃል፡፡ ለፓርላማ አባላቱ ጥበቃ እንዲደረግላቸው መመሪያ እንዲተላለፍ የተጠየቀ ሲሆን፣ ጉዳዩን በተመለከተ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነሩን አቶ አሰፋ ባዩን ማነጋገራቸውን፣ የፓርላማ አባላት በሚኖሩበት አካባቢ አሁንም ጠንካራ ጥበቃ እንዲደረግ ማሳሰቢያ መሰጠቱን አቶ አባዱላ ገመዳ ተናግረዋል፡፡ የፓርላማ አባላት መዘረፍና መደብሰብን ተከትሎ የተወሰደው ዕርምጃ ጥሩ ቢሆንም የተራ ሰላማዊ ዜጐች በተራ ዝርፊያና ቅሚያ ሕይወታቸውን ማጣትም እኩል ትኩረት ያሻዋል፡፡ ይህ አጋጣሚ ትኩረት ተሰጥቶ ልዩ ጥበቃ በሚደረግበት አካባቢ እንዲህ ከተደረገ በሌሎች ቦታዎች ኗሪው ምን ያህል የተጋለጠ መሆኑን ሊያሳይም ይችላል፡፡ ያነጋገርናቸው ብዙዎች ለፖሊስ አመልክተው ምንም የተፈጠረ ነገር የለም ቢሉ፤ ቀማኞችን እጅ ከፍንጅ ይዘን ለፖሊስ አሳልፈን ብንሰጥም ከሰዓታት በኋላ ቀማኞችን ከማየት ውጭ በተመሳሳይ መልኩ ምንም የተፈጠረ ነገር የለም ያሉን ቢኖርም ኮማንደር ዓለማየሁ ግን ተጐጂዎች አመልክተው ፖሊስ የማይዝበት አጋጣሚ እንደማይኖር በልበ ሙሉነት ይናገራሉ፡፡ የእሳቸው እርግጠኝነት ሲታይ በፖሊስ ጥበቃ ላይም እምነት አጣን የሚለው የሰዎች አስተያየት መሠረቱ ምንድን ነው የሚል? ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ሰዎችን ከወንጀለኞች፣ ከነጣቂና ቀማኛ ይጠብቁ ዘንድ በተለያዩ አካባቢዎች የሚሰማሩ የፖሊስ አባላቶች ኃላፊነታቸው ግዴታቸውን አለመወጣታቸው አንድ ጥፋት ሆኖ ከዚህ አልፈው ከሌቦች ጋር እስከመተባበር ይደርሳሉ የሚል አስተያየትም በተደጋጋሚ እንደሚሰነዘር ለኮማንደር ዓለማየሁ ጥያቄ አንስተን ነበር፡፡ ‹‹ሁሉም ፖሊስ ንፁህ ነው ማለት አይቻልም›› በማለት ይህም ትልቅ ግምት በሚሰጠው ደረጃ ችግር ነው የሚባል እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡ በተያዘው የበጀት ዓመት ከሥነ ምግባር ጉድለት ጋር በተያያዘ ተገምግመው ዕርምጃ የተወሰደባቸው ፖሊሶች መኖራቸውን ግን ይጠቁማሉ፡፡ ኮማንደሩ ለማስረዳት እንደሚሞክሩት የቅሚያና የንጥቂያ ወንጀል የሚፈጸምባቸው አካባቢዎች ተለይተው ይታወቃሉ፡፡ በደፈጣና በቅኝት ፖሊስ ወንጀለኞችን ለመያዝ ይሞክራል፡፡ ቢሆንም ግን የሰው ኃይል ውስነነትና የዘራፊዎቹ ዕርምጃ የተጠና መሆን በተወሰነ መልኩ ፈተና ነው፡፡ በሌላ በኩል የሪፖርተር የኮሚሽኑ ምንጮች እንደሚሉት ደግሞ እጅ ከፍንጅ ለተያዙ ነጣቂና ቀማኞች ወዲያው በአፋጣኝ ፍርድ ይሰጥ የነበረበት አሠራር መዳከሙ ችግር ሆኗል፡፡ ምን ዋጋ አለው ቀማኛና ነጣቂዎች ወዲያው ይለቀቃሉ የሚለው ነገር በፖሊሶች በኩልም አለ፡፡ የዚህ ዓይነቱ እሳቤ ካለ ቀማኛና ነጣቂን ተከታትሎ የማስቀጣቱ ሥራ እንዴት በአግባቡ ይሠራል የሚል ጥያቄ አንስተን ነበር፡፡ ‹‹መጨረሻውን እያወቅነው እንሠራለን›› የሚል መልስ ነው ያገኘነው፡፡ ቅሚያ፣ ነጠቃና ስርቆት ላይ የሚጣለው ቅጣት ቀላል (በአዋጅ 665/669 መሠረት) የሚባል እንደሆነ ይህም የራሱ ተፅዕኖ እንዳለው አስተያየታቸውን የሰጡም አሉ፡፡ ሰዎች ከምንም በላይ በሚያውቁትና በኖሩበት አካባቢ በነጣቂና በዘራፊ ሕይወታቸውን እስከማጣት በሚደርሱበት፣ ማኅበረሰቡ ሊጠብቀው ከወንጀል ሊከላከለው ኃላፊነት በወሰደው ፖሊስ ላይ ያለው እምነት መሸርሸር በጀመረበት፣ ሰዎች በፍርኃት ስርቆትና ወንጀልን አይተው ከመጠቆምና የዜግነታቸውን ከመወጣት ይልቅ እንዳላየ ማለፍን በመረጡበት በዚህ ሁኔታ ውስጥ ተጠያቂ የሚሆነው አንድ አካል ብቻ አይሆንም፡፡ የፍትህ ሥርዓቱ ተዋናዮች፣ ማኅበረሰቡ ቤተሰብም የራሳቸው የተጠያቂነት ድርሻ ይኖራቸዋል እንጂ፡፡ ማን በምን ደረጃ ተጠያቂ ነው የሚለው ግን አጠያያቂ ይሆናል፡፡

ምሕረት አስቻለው እና ታምሩ ጽጌ

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...