Thursday, July 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የኤሌክትሪክ ኃይል ሥርጭትና ያረጁ ምሰሶዎች ጉዳይ

መረጃዎችን ለመመልከት ጐራ የምልባት አንዲት የኢንተርኔት ካፌ አለች፡፡ ከአንድ ሳምንት በፊት ሳሪስ አካባቢ ወደምትገኘው የኢንተርኔት ካፌ በማቅናት አገልግሎት ለማግኘት ከአንዱ ኮምፒውተር ፊት ለፊት ተቀመጥኩ፡፡ በጠባቧ ቤት ውስጥ ያሉት ስድስት ወንበሮች በሙሉ በተጠቃሚዎች ተይዘዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከእኔ ቀድመው የመጡት እንደ እኔው ኮምፒውተሮቹን ከፍተን ወደምንፈልገው የመረጃ መረብ መግባት አልቻልንም፡፡ የኮምፒውተሩ መስኮት ግን ክፍት ነው፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል ስለመኖሩም ፊት ለፊት የተደረደሩት ኮምፒውተሮች ስክሪን ላይ የሚፈናጠቀው ብርሃን ያረጋግጥልናል፡፡ ትንሿ ኢንተርኔት ካፌ ውስጥ ያለው አምፑል በርቷል፡፡ ስለዚህ የኤሌክትሪክ ኃይል መኖሩ እርግጥ ነበር፡፡ ኔትወርክም ቢሆን አለ፡፡ ነገር ግን ወደየጉዳያችን እንዳንገባ እንቅፋት የሆነብን ኮምፒውተሮቹ የሚያስፈልጋቸውን የኃይል መጠን ማግኘት ባለመቻላቸው ነበር፡፡ የፌስ ቡክ ገጹን ከፍቶ ለመመልከት የመጣ፣ የኢሜል አድራሻቸውን ከፍቶ ለመጻጻፍ አሊያም፣ ዓለም እንዴት አድራና አርፍዳ ይሆን በማለት ድረ ገጾችን ለመጐብኘት የመጡ ሁሉ ከምፒውተሮቹን ከፍተን ለመጠቀም የማቱሳላን ዕድሜ ለሚያክል ጊዜ በትዕግሥት መጠበቅ ነበረብን፡፡ በኮምፒውተሩ ስክሪን ላይ ደጋግሞ የሚታየው የኃይል እጥረት ስለመኖሩ የሚያሳብቀው ምልክት በየሙከራዎቻችን ጣልቃ በመግባት ጊዜያችንን ሰረቀው፡፡ ኢንተርኔት ካፌው እንዲህ ያለ ነገር ሲያጋጥም የመጀመሪያው ጊዜ አለመሆኑንም ተረዳን፡፡ የዚያን ዕለቱ ግን የበዛ ሆነ፡፡ በተደጋጋሚ የሚፈጠረው የኃይል እጥረት ኮምፒውተሮችን ማንቀሳቀስ ሲሳነውና ለመጠቀም ሲቸገሩ ጊዜ ትዕግሥት ያጡት ተነስተው ይወጣሉ፡፡ ጊዜው ያላቸው ደግሞ ሄድ መለስ የሚለው ኃይል እስኪስተካከል ይጠብቃሉ፡፡ ዕድል ከቀናቸው ያሰቡትን ያከናውናሉ፡፡ የኃይል መዳከም ማማረሩ እንዳለ ሆኖ አንዳንዴም ከአቅም በላይ የሚለቀቅ የኤሌክትሪክ ኃይል ይመጣል፡፡ እንዲህ ያለው የተዘበራረቀ የኃይል ሥርጭት በርካታ ተቋማትን ሲረብሽና ሥራቸውን ሲያደናቅፍ ይታያል፡፡ በኢንተርኔት ቤቷ አካባቢ የሚገኙ ንግድ ቤቶችንና መኖሪያ ቤቶችን ሲረብሽም ታዝቤያለሁ፡፡ ችግሩ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ብቻም ሳይሆን፣ ኢንተርኔት ካፌዋ በምትገኝበት አካባቢ ያሉ ነዋሪዎችም ደጋግሞ እንደሚያጋጥማቸው ተረድቻለሁ፡፡ እንጀራ ለመጋገር የተዘጋጀች የቤት እመቤት፣ የኃይል እጥረቱ እጇን አጣጥፋ እንድትቀመጥ ያስገድዳታል፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል ሥርጭቱ መቼ እንደሚስተካከል ስለማታውቅ እንጀራ ለመጋገር ትፈተናለች፡፡ አንዳንዴ የኤሌክትሪክ ኃይሉ ጉልበት መውረድ ሌሎች በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠሩ ዕቃዎችን ሁሉ አጥፍቶ አንዱን እንኳን ለመጠቀም የማያግዝ ይሆናል፡፡ እንዲህ ያሉት አስተያየቶች የጥቂቶች ወይም በጥቂት ቦታዎች ላይ ብቻ የሚስተዋሉ አይደሉም፡፡ ኢንተርኔት ካፌዋ የምትገኝበት አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች ለሚፈልጉት አገልግሎት ሊውል የሚችል ኃይል ማግኘት ባለመቻላቸው ሳቢያ፣ ከሰልን በጀታቸው የወጪ ዝርዝር ውስጥ ስለማስገባታቸው የነገሩኝም አሉ፡፡ የኢንተርኔት ቤቷ ባለቤቶችና ንግድ ቤቶች ግን እንደ ቤት ወይዛዝርቶቹ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጐታቸውን ለመሙላት በከሰል መጠቀም ግን አይችሉም፡፡ ችግሩ በተደጋጋሚ እያጋጠማቸው በመሆኑ መፍትሔ ለማግኘት ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ቢያመለክቱም የተስተካከለ ነገር የለም፡፡ ማመልከቻቸው ውጤት አላመጣ ያላቸው ተገልጋዮች፣ የበለጠ እያሳሰባቸው የመጣው ግን የኃይል እጥረቱ ብቻ አይደለም፡፡ አንዳንዴ የኤሌክትሪክ ኃይል ጉልበቱ አንሶ ይቆይና ድንገት ሳይታሰብ ከመጠን በላይ የሚለቀቅበት አጋጣሚ ሲከሰትም፣ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠሩ ንብረታቸው ከዛሬ ነገ ይቃጠሉ ይሆን የሚለው ነው፡፡ የኃይል አቅርቦቱ ተመጥኖ የማይለቀቅበት ምክንያት ባይታወቅም፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ያለው የኤሌክትሪክ ሥርጭት ወይም ልቀት ግን ሥራ ከማስተጓጐል ባለፈ ለንብረት መውደም ምክንያት ሊሆን መቻሉ አይጠረጠርም፡፡ ችግሩ ከታወቀ በወቅቱ ማስተካከል ተገቢ ነው፡፡ ችግሩን አውቆና አይቶ ፈጣን ምላሽ ያለመስጠቱ ግን ለምን? የሚለውን ጥያቄ ያስነሳል፡፡ የኤሌክትሪክ መቆራረጥ አንፃራዊ በሆነ መልኩ ቢቀንስም፣ ከኃይል ልቀት አኳያ ለሚነሳው ጥያቄ ግን መፍትሔ ሊሰጠው ይገባል፡፡ የኤሌክትሪክ አገልግሎትና ተያያዥ ጉዳዮችን ካነሳን አይቀር አንድ ነገር ልጨምር፡፡ ጉዳዩ በከተማችን የሚታዩ፣ ያረጁ የኤሌክትሪክ ምሰሶዎችን ይመለከታል፡፡ እርጅና የጐዳቸው የኤሌክትሪክ መስመር ተሸካሚ ምሰሶዎች የሚቀየሩት መቼ ይሆን? ለመታደስ የግድ ወድቀው አደጋ እስኪያደርሱ መጠበቅ ተገቢ ባይሆንም፣ አንዳንድ ቦታዎች ላይ የምናያቸው ምሰሶዎች ግን በቃን ብለው እስኪወድቁ የሚጠበቁ ይመስላል፡፡ በተለይ በዚህ በክረምቱ ወራት፣ እነዚህ ምሰሶዎች በዝናብ ሊወድቁ እንደሚችሉ ሲታሰበን ሥጋታችንን እጥፍ ድርብ ያደርገዋል፡፡ አንዳንድ ምሰሶዎች በመኖሪያ ግቢ ውስጥ መተከላቸውም አሮጌዎቹን መቀየር ቢያስፈልግ እንኳ እንዴት እንደሚቻል ግራ ያጋባል፡፡ አንድ ምሰሶ ምን ያህል ጊዜ ሊያገለግል እንደሚችል ቢገመትም፣ ለአገልግሎት የዋለበትን ጊዜ አስልቶ የአገልግሎት ጊዜው ያበቃውን ለይቶ ለመቀየር በዚህ በመረጃ የተደገፈ ዕርምጃ እየተወሰደ ስለመሆኑ እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ ለዚህም ይመስላል ከባድ ዝናብ ሲጥል የሚገነደሱ ምሰሶዎችን የምንመለከተው፡፡ ኅብረተሰቡም አጠራጣሪና ለመውደቅ የሚዳዳቸው ምሰሶዎችን ሲመለከት ለኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት የመጠቆም ልማድ ቢኖረው ይበጃል፡፡ መሥሪያ ቤቱም እርምቱን ለማከናወን ፈጣን አገልግሎቱን ይሰጥ ዘንድ ይለመናል፡፡ በከተማችን የሚታየው ሥርዓት አልባ የኤሌክትሪክ ምሰሶ አተካከል ጉዳይም ትኩረት የሚሻ ነው፡፡ በሥርዓት ባለመሰቀላቸው ከተሸካሚ ምሰሷቸው ላይ በቋፍ የተንጠለጠሉና ከዛሬ ነገ ይወድቁ ይሆን የሚያሰኙ የትራንስፎርመሮች ጉዳይም ክትትል ያሻዋል፡፡ አንድ ቀን ሊወድቅ ይችላል ብለን የምንፈራቸው ትራንስፎርመሮች አደጋ ከማድረሳቸው በፊት በተለይ በዚህ ክረምት ወቅት የላሉትን ማጠባበቅ፣ ንብረትና ነዋሪውንም ከአደጋ መጠበቅ ትልቅ ኃላፊነት ነውና መሥሪያ ቤቱ ግዴታውን ይወጣ፡፡ ለችግሮች መፍትሔ የምንሰጠው አደጋ ከደረሰ በኋላ መሆን እንደሌለበት ይገንዘብ፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት