Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትከውስጥ ተቃውሞና ከጎረቤት ባለጋራነት ጋር መወሳሰብ የሌለበት ጉዳይ

ከውስጥ ተቃውሞና ከጎረቤት ባለጋራነት ጋር መወሳሰብ የሌለበት ጉዳይ

ቀን:

የእስራኤሉን ጠቅላይ ሚኒስትር የአፍሪካ በተለይም የኢትዮጵያ ጉብኝት የሚመለከተው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ገና ከመግባታቸው በፊት ሳምንቱ መጀመርያ አንስቶ ይነሳ የነበረው የታሪካዊ ግንኙነታችን ጉዳይ፣ ከዚህ ቀደም ያነበብኩትን በየአጋጣሚውም እየተመላለስኩ የምጎበኘውን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይና የደኅንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ መጽሐፍ እንደገና እንድቃኝ አደረገኝ፡፡ በ1995 ዓ.ም. የታተመው ይህ መጽሐፍ እንደ ስያሜው የኢትዮጵያን ‹‹የውጭ ጉዳይ የደኅንነት ፖሊሲና ስተራቴጂ›› ይወስናል፡፡ ‹‹ሁሉም ነገር ወደ ልማትና ወደ ዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ብለን ከዚህ የሚያዘናጋንን ነገር በሙሉ ወደ ጎን ትተን፣ ከእብሪት ከጀብደኝነት ነፃ ከሆነን ኑሯችንን በማሻሻል ላይ ለመረባረብ ቆርጠን›› መነሳታችንን ይናገራል፡፡ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲው ያለፉት መንግሥታት ድንፋታ፣ ቀረርቶትና እብሪት ጭምር ለአደጋ ሲያጋልጠን መኖሩን ይገልጻል፡፡ ያኔም ከ13 ዓመታት በፊት ሲቀረፅ ጉድለቶች አልነበሩበትም ባይባልም ዛሬ ደግሞ በጊዜ ሒደት ተመልሰው መታየት ያለባቸው ጉዳዮች ቢኖሩም፣ የኢኮኖሚና የዴሞክራሲ ግንባታን ዋነኛው የትኩረት ነጥብ አድርጎ ከውስጥና ከውጭ የሚመጡ አደጋዎችን ለማስወገድ የሚያስብና የሚሠራ፣ ሰላምና ልማትን የሚደግፍ፣ ውጫዊ ወዳጅነትን የሚያዳብር፣ አደጋዎችን አስቀድሞ ተንብዮ በውይይትና በድርድር ለማቃለል፣ የማይቃለለውን ለመቋቋም መሪ ሆኖ የሚያገለግል የውጭ ጉዳይና የደኅንነት ፖሊሲ ማበጀት እሰየው ነው፡፡ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ከኢትዮጵያም በኩል የጣልቃ ገብነትና የተስፋፊነት ትንኮሳ በጭራሽ እንደማይኖርና እንደማይመጣ፣ ይልቁንም ለጋራ ጥቅም የምንሠራ መሆኑን ለጎረቤቶቻችን ማሳወቅና በተግባርም ማረጋገጥ ብልህነት ነው፡፡ ፖሊሲው ከአገሮች ጋር፣ በተለይም ለመካከለኛው ምሥራቅ ጋር የሚኖረንን የግንኙነት ፖሊሲ በሚዘረዝረው ክፍሉ ውስጥ ከመካከለኛው ምሥራቅ የቀረብን በመሆናችን መካከለኛው ምሥራቅ በታሪካችን ውስጥ በበጎም ሆነ በመጥፎ ከፍተኛ ተፅዕኖ ማሳደሩን እንዲያውም ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ካሳደሩት ተፅዕኖ ይልቅ የመካከለኛው ምሥራቅ ተፅዕኖም የላቀ መሆኑን ያስረዳል፡፡ በአሉታዊ ገጽታቸው የሚጠቀሱ ያላቸውንም ጉዳዮች ይዘረዝራል፡፡ የዓባይን ወንዝ ጉዳይ ያነሳል፡፡ ‹‹በኢትዮጵያና በመካከለኛው ምሥራቅ መካከል ባለው ግንኙነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳረፈው ሌላው ጉዳይ ድንቁርና (Ignorance) አለማወቅ ነው፡፡ ላይ እንደተገለጸው በኢትዮጵያና በመካከለኛው ምሥራቅ መካከል ለሺሕ ዓመታት የዘለቀ ግንኙነት የነበረ ቢሆንም፣ በዚያው መጠን አንዱ ሌላውን በትክክል የሚያውቅበት ሁኔታ አልተፈጠረም፡፡ ኢትዮጵያውያን መካከለኛውን ምሥራቅ በተለይም የዓረቡን ዓለም ከሩቁ በጥርጣሬ ከመመልከት አልፈው አገሮችን በሚገባ አጥንተውና አውቀው በተሟላ ዕውቀት ላይ የተመሠረተ አቋም የሚወስዱበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ ይኽም እስከዛሬ የዘለቀ ጉዳይ ነው፡፡ ‹‹በተመሳሳይ መልክም በመካከለኛው ምሥራቅ በተለይም በዓረቡ ዓለም ያሉ ሕዝቦች ኢትዮጵያን በጥርጣሬና በንቀት ከመመልከት አልፈው በሚገባ ለማወቅ ያደረጉት ጥረት የለም፡፡ ስለሆነም ግንኙነቱ ባለማወቅ ላይ በተመሠረተ፣ ጥርጣሬ፣ ጥላቻና ንቀት ሲሰቃይ የነበረና ያለም ነው ማለት ይቻላል፡፡ የተለያዩ ኃይሎች ባለማወቁ ላይ ተመሥርተው የጥላቻና ጥርጣሬ ዘር በመዝራት ቀጣይ ሥራ ስለተሠራበት ችግሩ እንዲባባስ አድርጎታል፡፡ ‹‹በዓረቦችና በእስራኤል መካከል ቅራኔ ከተፈጠረ ወዲህ ይህ ቅራኔ ኢትዮጵያ ከመካከለኛው ምሥራቅ ጋር ባላት ግንኙነት ላይ የበኩሉን አሉታዊ ተፅዕኖ ሲያሳርፍ ቆይቷል፡፡ በአንድ በኩል ዓረቦቹም ሆኑ እስራኤላውያኑ ኢትዮጵያ የራሷን ጥቅም በሚያስጠብቅ አኳኋን ግንኙነቶችን እንድትመሠርት ሳይሆን፣ ከአንዱ ጋር ወግና በሌላው ላይ በጠላትነት እንድትሠለፍ የሚጠይቁ ነበሩ፡፡ ኢትዮጵያም ይህንኑ ሳትቀበል የራሷን ነፃ አቋም ከመውሰድ ይልቅ ከአንዱ ወይም ከሌላው ጋር በመወገን ስትላጋ ኖራለች፤›› ይላል፡፡ ከግብፅ፣ ከዓረብ ባህረ ሰላጤ አገሮች፣ ከሰሜን አፍሪካ አገሮች እንዲሁም ከእስራኤል ጋር የሚኖረንን ግንኙነት ለየብቻና በነፍስ ወከፍ ወደ ሚመለከተው ዝርዝር ክፍል ከመግባቱ በፊት የፖሊሲ ሰነዱ በመካከለኛው ምሥራቅ የምንከታተለው ፖሊሲ ከ‹‹ሁሉም ነገር ወደ ልማትና ወደ ዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ››፣ በተጨማሪ ‹‹ብቃት ባለው ጥናትና ምርምር በዕውቀት ላይ በተመሠረተና በተለያዩ ስሜቶች የማይነዳ መሆን አለበት፤›› በማለት ይወስናል፡፡ የውጭ ጉዳይና የደኅንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ መጽሐፉ ከእስራኤል ጋር የሚኖረንን ግንኙነት ለብቻው በሚመለከትበት ክፍሉ፣ ‹‹እንደ ሌሎቹ የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ሁሉ ከእስራኤል ጋር የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት እንዳለንና በርካታ የይሁዲ የሃይማኖት ተከታይ ኢትዮጵያውያን እንደነበሩና ብዙዎቹም በአሁኑ ወቅት በእስራኤል ተቀማጭ እንደሆኑ›› እንደሚታወቅ፣ ‹‹ከእስራኤል መንግሥትም ጋር በመሀል ግንኙነቱ የተቋረጠበት ሁኔታ የነበረ ቢሆንም በአጠቃላይ ጤናማ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ግንኙነት ተፈጥሮ ቆይቷል ማለት ይቻላል፤›› ይላል፡፡ ቀጥሎም ኢትዮጵያ ከእስራኤል ጋር የሚኖራትን ግንኙነት የፖሊሲ መሠረት ይዘረዝራል፡፡ ወደዚያ ከመግባታችን በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ጉብኝት መዳረሻ አካባቢ ስለተነሳው ‹‹ለዘመናት የቆየ›› ታሪካዊ ግንኙነት መጀመርያ እንመልከት፡፡ አዲስ ዘመን ጋዜጣ በአንድ ወቅት ማለትም ኢትዮጵያ ከእስራኤል ጋር ያላትን የዲፕሎማቲክ ግንኙነት ስታቋርጥ ‹‹በዓለም ሰላም ጉሮሮ ውስጥ የተሳካ አጥንት››፣ እንዲሁም ‹‹እንደ ጥፋት ሰይፍ በሰው ህሊና ላይ የተንጠለጠለ ችግር›› ያለው የመካከለኛው ምሥራቅ ውዝግብ የሥር የመሠረት መነሻ አገረ እስራኤል በ1948 ዓ.ም. ከመቋቋሟ በፊት ይቀድማል፡፡ የጁዳይዝም (የአይሁድ) የልደት ሥፍራና የእስራኤል መንግሥት (Kingdom of Israel) የሚባለው የጥንታዊ የሂብሩ ሳይት የሆነው ፓላስታይን የሚባለው አገር በ20ኛው ምዕተ ዓመት መጀመርያ ላይ የአይሁዶች የመሰባሰቢያ ሥፍራ ሆነ፡፡ ጽዮናዊነት በሚባለው ንቅናቄ ተደራጅቶና ተበረታትቶ ፍልሰት ወደዚህ ሥፍራ ተፋፋመ፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1918 እስከ 1948 በዘለቀው በመላው የዚህ ሥፍራ የብሪቲሽ አስተዳደር ዘመን አይሁዶች ከፍልስጤም ነዋሪዎች ጋር ተጋጩ፡፡ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ውስጥ (ከ1939 እስከ 1945) የመንግሥታቱ ድርጅት ይህንን ሥፍራ የአይሁድና የዓረብ መንግሥታት የሚቋቋሙበት አገር ምድር አድርጎ የሚከፋፍል ፕላን አወጣ፡፡ ዓረቦች ተቃወሙት፡፡ አይሁዶች ተቀበሉት፡፡ በዚህም አገረ እስራኤል እ.ኤ.አ. በ1948 ተመሠረተች፡፡ እስራኤሎች መንግሥት የመሠረቱበትም ሆነ የኛ ነው የሚሉት፣ እንዲሁም ዓረቦች የኛ ብለው የሚጠሩት ይህ የአይሁድ (ጁዳይዝም) የልደት ቦታና የንጉሥ ሳኦል የተከታዮቹም የንጉሥ ዳዊትና የንጉሥ ሰለሞን አገር የንጉሠ ነገሥት መንግሥት ሥፍራና ምድር ስያሜው ፍልስጤም ነበር፡፡ የብሪቲሽ አስተዳደር የሚያውቀውም በዚህ ነው፡፡ በየትኛው ስም ተጠራ፣ እስራኤልም ሆነ፣ ፍልስጤም ተባለ እነ ሳኦል፣ ዳዊትና ሰለሞን የገዙት መንግሥት ሥፍራ ነው የሚባለው ግን ይኸው ምድር ነው፡፡ ከዚህ ምድር ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለን ስንል የኖርነው ባፈ ታሪክ ብቻ ሳይሆን በሕገ መንግሥት ደረጃ ጭምር ነው፡፡ የ1948 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት ‹‹የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥትነት ከኢትዮጵያ ንግሥተ ከንግሥት ሳባና ከእየሩሳሌም ንጉሥ ከሰለሞን ከተወለደው ከቀዳማዊ ምኒልክ ነገድ ሳይቋረጥ ተያይዞ ከመጣው ከንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ዘር ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትውልድ ሳይወጣ ምን ጊዜም ይኖራል፤›› ሲል ይደነግግ ነበር፡፡ ይህ ዛሬ በማስታወቂያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዜና ትንታኔ ዘገባ ውስጥ ጭምር የምንሰማው ትረካ ‹‹ታሪካዊ ሀቅ›› ብቻ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ሕፃናትም ነበረው፡፡ ከኢትዮጵያ ታሪክና ማንነት ጋር የሚሳከረው የንግሥተ ሳባ ታሪክና ‹‹ሞዓ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ›› ባይነት የመጣው ከአገው ነገሥታት ሥልጣን ለመንጠቅ ሲባል ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ‹‹ታሪካዊ ሀቅ ስለመካድ›› የሚደነግግ የወንጀል ሕግ ባይኖርም፣ ዓለም ያወቀውንና በስንትና ስንት መጽሐፍ የተመዘገበውን ታሪክ ለመለወጥ መሞከር መጠየቅ ራሱ ክህደት ነው ማለት፣ ዛሬም የሕዝብ የእምነት ድጋፍና ‹‹የምሁራን ትንታኔ›› ጭምር ዋልታና ማገር ሆኖ የሚበጠበቅ ዕምር ነገር ነው፡፡ የትኛውንም የታሪክ ትንታኔ ስህተትነት በማስረጃ ማሳየት ተገቢ መሆኑና መባሉ ቀርቶ እንኳን በኅብረተሰብ ታሪክ ይቅርና በቅዱስ የእምነት መጻሕፍት ላይም የታሪክ ምርምር በሚደረግበት ዘመን ውስጥ ሆነን ሳባ ከንጉሥ ሰለሞን የፀነሰችበትን ታሪክ መሸከም ዛሬም ግዴታችን ሆኗል፡፡ የኢትዮጵያ መሪነት ‹‹ከቀዳማዊ ምኒልክ ነገድ›› ከተቋረጠ፣ ያ ቀርቶ ሪፐብሊክ ከተቋቋመ ከ42 ዓመታት በኋላም የንግሥተ ሳባ ስምና ዝና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያችን የዜና ትንታኔ የደም ሥር መሆኑ አልቀረም፡፡ በዚህ ረገድ ከእስራኤል ጋር የሚኖረንን የግንኙነት ፖሊሲ የሚዘረዝረው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲው ሻል ያለ አተያይ ያስመዘግባል፡፡ ‹‹እንደ ሌሎቹ የመካለኛው ምሥራቅ አገሮች ሁሉ ከእስራኤልም ጋር የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት አለን፤›› ይላል፡፡ የፖሊሲው ሰነድ ‹‹እንደ ሌሎቹ የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ሁሉ ከእስራኤም ጋር የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት›› እንዳለን ገልጾ፣ ከእስራኤል መንግሥትም ጋር በመሀል ግንኙነቱ የተቋረጠበት ሁኔታ የነበረ ቢሆንም፣ በአጠቃላይ ጤናማ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ግንኙነት ተፈጥሮ ቆይቷል ማለት እንደሚቻል ይገልጻል፡፡ በኢትዮጵያና በእስራኤል መንግሥታት መካከል የዲፕሎማሲ ግንኙነት የተፈጠረውና መፈጠርም የቻለው ከ1948 ዓ.ም. በኋላ ሲሆን፣ የተቋረጠው ግን ከጥቅምት 13 ቀን 1966 ዓ.ም. ጀምሮ ነው፡፡ በዚሁ ዕለት ማክሰኞ ጥቅምት 13 ቀን 1966 ዓ.ም. በንጉሠ ነገሥቱ በራሳቸው በተሰጠ መግለጫ አማካይነት እስራኤል እ.ኤ.አ. በ1967 ዓ.ም. በጦር ኃይል የያዘቻቸውን ግዛቶች ለቅቃ ባለመውጣቷ ምክንያት፣ እነዚሁኑ ግዛቶች ለቅቃ እስከምትወጣ ጊዜ ድረስ ኢትዮጵያ ከእስራኤል ጋር ያላትን የዲፕሎማሲ ግንኙነት አቋርጣለች ተባለ፡፡ ይህንን የኢትዮጵያ፣ የአብዛኛውን የአፍሪካ አገሮች መሰል ውሳኔ ዕውን ያደረገውና ያጣደፈው የ1973 (ጥቅምት 1966 ዓ.ም.) የዓረቦችና የእስራኤል ጦርነትና በስምምነቱ ምክንያት የደረሰው የነዳጅ የፖለቲካ መሣሪያነት ነው፡፡ በኢትዮጵያና በእስራኤል መካከል የነበረው የዲፕሎማሲ ግንኙነት ከተቋረጠበት የአቋም ምክንያት ይልቅ፣ ግንኙነቱ እንደገና የተመሠረተበት ሁኔታና አቋም ይበልጥ ግልጽና የማይሸፋፍኑት ነበር፡፡ ጉዳዩ ከምፅዋ መደብደብና መያዝ ታሪክ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ታሪኩም በአጭሩ እንደዚህ ነው፡፡ በ1982 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ በደርግና በአማፂያን መካከል የሚደረገው ጦርነት የመጨረሻው መጀመርያ ላይ ደርሶ ምፅዋ ተያዘች፡፡ የምፅዋ መጠቃትና በሻዕቢያ እጅ መውደቅ ከነፍስ አድን ዕርዳታ መደናቀፍ አንፃር የአሜሪካም ጭምር ተቃውሞ ገጥሞት ነበር፡፡ የደርግ ተቃውሞና ምላሽ ግን ከዚህም ያለፈ ሆነ፡፡ የኢትዮጵያን መፈራረስ በሚሹ የውጭ ኃይሎች ዕርዳታ ተወርሬአለሁ፣ ዓለም ይወቅልኝ አለ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዳር ድንበሩን ማስከበር መብቱና ግዴታው ነው ብሎም በቦምብ መደብደቡን ተያያዘ፡፡ ውጊያውንም ከዓረብና ከእስራኤል ቅራኔ ጋር አጠላለፈው፡፡ ደርግ ሳያውቀው እስራኤል ኢትዮጵያ ገብታ ቤተ እስራኤሎችን አጓጉዛ ወሰደች፡፡ መሳቂያ ካደረገችው ከእስራኤል ጋር ውስጥ ለውስጥ የጀመረውን ነገር ግን የአደባባይ ሚስጥር የሆነውን ወዳጅነት መትረፊያ ብሎ ይዟል፡፡ ይህን ማድረጉ ከአካባቢው የዓረብ አገሮች ጋር፣ ኒሻን ከሸለመችው ከሶሪያ ጋርም ሊያናክሰው እንደሚችል ያውቃል፡፡ ደርግ አሸንፋለሁ ብሎ ሳይሆን መጨረሻ ላይ ብቻውን የቀረውን የዳር ድንበር ‹‹ካርድ›› መጠቀም መረጠ፡፡ በዚህ ካርድ ማጭበርበር መቻልና አለመቻሉ ህልውናዬን ይወስናል ብሎም ከእስራኤል ጋር ተዛመደ፡፡ ወደ እስራኤል ሲለጠፍ ዓረብ ጎረቤቶችም በተቃራኒው ለእነ ሻዕቢያ ያላቸው ድጋፍ ፈጦ ወጣ፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ የሉዓላዊነቱ የዳር ድንበሩ መፈክር ይበልጥ ይሠራል እታመናለሁም አለ፡፡ ደርግ እስራኤልን የተጠጋው ይህን በመሰለ የጦርነት ሜዳ ማሸነፊያ ያለውን መሣሪያ ይዞ እንጂ ሌላ አልነበረም፡፡ መጋቢት 1982 ዓ.ም. የኢትዮጵያና የእስራኤል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙንት መመሥረት ይፋ ተደረገ፡፡ የመካከለኛው ምሥራቅ ውዝግብ ዛሬም በዓለም ጉሮሮ ውስጥ የተሰካ አጥንት ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ሌላም ጣጣ፣ ጠንቅና መዘዝ አስከትሏል፡፡ ከአገራቸው የተገፉት ፍልስጤማውያን በቁራጭ መሬት ላይ እንደ አገር የመቋቋም ትንሽዬ ፍትሕ እንኳን ያጡበት የዓለማችን ታላቁ የሰው ልጅ መብት ረገጣ የሚገኘው እዚሁ ውስጥ ነው፡፡ ለሽብርና ለአሸባሪነት ምቹ መነቃቂያ ድባብ ሆኖ ያገለገለው የፍልስጤም ጥያቄና ከእሱ ጋር ተያይዞ የተፈጠረው ፀረ እስራኤልና ፀረ አሜሪካ ሙቀት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከነዳጅ ጥቅም ጋር የተያያዘ ጭፍራ የማበጀት ትግልና ጣልቃ ገብነት አለ፡፡ ከዚህ ቀደም ብለን በሌላ ጽሑፍ ጭምር እንዳልነው የምንኖርበት አካባቢ የመንግሥታቱ ድርጅት በርካታ የተለያዩ ውሳኔዎች የሰጠበት፣ የአፍሪካ ኅብረትም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሆኖ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ አቋሙን የገለጸበት ‹‹ከፍልስጤም ሕዝብ ጋር ዓለም አቀፋዊ የትግል አጋርነት ቀን›› ተብሎ በየዓመቱ ኖቬምበር 29 የሚያከብረው፣ ፍትሐዊ መፍትሔ ያጣውና እየባሰበት የመጣው የፍልስጤም ጥያቄ የሚገኝበት ቀጣና ነው፡፡ የእስራኤልና የፍልስጤም ጉዳይ ደግሞ ከሃይማኖት ወገናዊነት ጋር የሚምታታበት፣ የአመለካከት ድህነትና መተነኳኮስ የበዛበት፣ የአገር ማንነትና የእምነት መብት በሃይማኖቱ የአመጣጥ ዕድሜና በአማኞች ብዛት የመለካት ችግር ሥር የሰደደበት ነው፡፡ በእስራኤል፣ በኢራንና በሳዑዲ ዓረቢያ የሚደነቋቆል የሶማሊያና የየመን የትርምስ እሳት የሚንቀለቀልበት አካባቢ ነው፡፡ አካባቢውን ከፀረ እስራኤል ትግልና ኃይሎች ጋር ለማጠላለፍ ተግተው የሚሠሩ ያሉበት ቀጣና ነው፡፡ በሰላም ሊፈታ ያልቻለ የአገር ውስጥ ተቃውሞ እንዲኖር የሚሹ ይህንኑ ከጎረቤት ባለጋራነት ጋር ሸርበው ለማተረማመስ የተሠለፉበት አካባቢ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ልማት ለህልውናዬ አደጋ ነው ብለው አቋም የያዙና የኢትዮጵያን መጠንከር ከሥጋት የሚቆጥሩ፣ ከዚህ ቀደምም የኤርትራን ትግል በማዳከሚያነት ሲጠቀሙበት የነበሩ ሰሜናዊ የዓባይ ወንዝ ተጠቃሚ አገሮች በዚህ ዓይነት ውስብስቦሽ ውስጥ ቢያንስ ቢያንስ በሥውር እንሳተፍ የሚሉበት አካባቢ ነው፡፡ ይኼንን ሁሉ ጥልፍልፎሽ ማየትና መመርመር አለብን፡፡ ከአገሮች ጋር የሚኖረንን የግንኙነት ፖሊሲ ከእያንዳንዱ አገር አኳያ በነፍስ ወከፍ የሚዘረዝረው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይና የአገራዊ ደኅንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ሰነድ፣ ከእስራኤል አንፃርም ኢትዮጵያ ልትከተለው ይገባታል የሚለውን የፖሊሲ አቅጣጫና ቢጋር ያመለክታል፡፡ ከእስራኤል ጋር ያለን ግንኙነት መነሻውና መድረሻው በግልጽ የተቀመጠው አገራዊ ጥቅማችንና የልማትና የአገራዊ ህልውና አጀንዳችን ሊሆን እንደሚገባው፣ ይህንን ለማድረግ የሚያስችለንን ፖሊሲ ቀርፀን ተግባራዊ ማድረግ እንዳለብን፣ ‹‹በእስራኤሎችና በዓረቦች መካከል ያለው ቅራኔ በዋነኛነት ሁለቱን የሚመለከት ስለሆነ የኢትዮጵያ ዓላማ አገራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ ከሁለቱም ወገኖች ጋር ጥቅሟን የሚያስጠብቅ ግንኙነት መመሥረት እንጂ፣ አንደኛውን ወይም ሌላኛውን በማስደሰት ወይም በማስቆጣት ላይ የተመሠረተ ፖሊሲ ማስቀመጥ›› አይገባንም የሚለው የፖሊሲ ሰነድ፣ ጉዳዩን በዚሁ ብቻ አበቃ አይልም፡፡ ‹‹በእስራኤልና በዓረቦች መካከል ያለው ቅራኔ በዋነኛነት ሁለቱን የሚመለከት›› ነው ብሎም የአገራዊ ጥቅማችንና የልማትና የአገራዊ ህልውና አጀንዳችን ነገር በዚሁ ተካተተ አይልም፡፡ ይልቁንም አከታትሎና ከዚህም በመነሳት ብሎ፣ ‹‹የዓለም አቀፍ ሕግ መከበሩ ቅራኔዎች በሰላም መፈታታቸው ለሰላምና መረጋጋት ብሎም ለአገራዊ ጥቅማችን መከበር መሠረት በመሆኑ፣ በፍልስጤም ጉዳይ በእነዚህ መርሆዎች መሠረት እንዲፈታ መደገፍ›› እንደሚኖርብን፣ ‹‹የፍልስጤም ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን መብቱ እንዲከበርና ጉዳዩም በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ እንዲፈታ መደገፍ አለብን፡፡ ይህንን አቋም በመያዛችን ማንንም የሚያስቆጣ መሆን የለበትም፡፡ ቢያስቆጣም ባያስቆጣም አገራዊ ጥቅማችንን የሚያስጠበቅ ፖሊሲ ስለሆነ ልንከተለው ይገባናል፤›› ይላል፡፡ የእስራኤልና የፍልስጤም ጉዳይ መፍትሔ ቀርቶ የመፍትሔ ተስፋ ባጣበት፣ ፍልስጤሞች በትጥቅ ትግል ቢሉ በሕዝብ አመጽ፣ ከዚያም መስመር ወጥተውና የእስራኤልን መንግሥትነት አውቀው በአቤቱታና በድርድር ቢሞክሩም ጠብ የሚል ነገር አጥተው በስቃይና ግብግብ የማይለወጥ ሕይወት ውስጥ አለኝታ የለሾች በሆኑበት፣ የድርድር ድራማው ባለበት ረግጦ በተሰናከለበትና በወረራ የተያዘ የሰው አገር በሥፍራ የሚቀነስበትና የሚጠቃለልበት አሠራር ከልካይ በሌለበት፣ የሁለት ልዕለ ኃያላን ፍጥጫ ከቀረ ወዲህ ተመድ ፍጥጫውን የማቻቻል ታህል እንኳን የነበረውን የተፅዕኖ አቅም ባጣበት፣ እዚያው እስራኤል ውስጥ አነሰም በዛ ፍትሕን ልሞክር የሚል ፖለቲከኛ ወደ ሥልጣን እንዳይመጣ የቀኝ አክራሪነት ምንተፍረት የለሽ አይናውጣነት በእስራኤል ፖለቲካ ውስጥ በተንሰራፋበት ሁኔታ ውስጥ፣ ከላይ የጠቀስነው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ የፖሊሲ ሰነድ የያዘው አቋም ‹‹ማንንም የሚያስቆጣ›› ባይሆን አይገርምም፡፡ ችግሩም ከእኛ የፖሊሲ ሰነድ አይደለም፡፡ ከአገራቸው የተገፉት ፍልስጤማውያን በቁራጭ መሬት ላይ እንደ አገር የመቋቋም ትንሽዬ ፍትሕ እንኳን ያጡበት የአሜሪካና የአውሮፓ ተጠያቂነት ያለበት የዓለማችን ታላቁ የሰው ልጅ መብት ረገጣ የደረሰበት የከፋ ደረጃ ያስከተለው ችግር ነው፡፡ ለዓለም አቀፋዊ ሕግ መከበር መቆማችንን ለዴሞክራሲና ለሰብዓዊ መብት ያለንን ተቆርቋሪነትና ወገንተኛነት ከአገራዊ ጥቅማችንና ከልማትና ከአገራዊ ህልውና አጀንዳችን ጋር ካዋደድነው፣ በዚህም ላይና በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ብሔራዊ ንቃተ ህሊና ከገነባን አንዱን ወይም ሌላውን ማስቆጣት ያለበት ፖሊሲም ቢሆን አገራዊ ጥቅማችንን የሚያስጠብቅ ፖሊሲ በመሆኑ አያሳስበንም፡፡ ከዚህ አጠቃላይ አነጋገር ውስጥ ተፈልፍለው የሚወጡ በርካታ ዓቢይ ጉዳዮች አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል የመጀመሪያው ሰላማዊና ሕጋዊ ትግል በውስጣችን የግንኙነታችን መነሻ መሆን አለበት፡፡ የተለየና የሚቃረን ሐሳብን የማቅረብ ነፃነትን ጥቅሜ ብሎ ማድመጥ፣ መከራከርና ቅያሜ ሳይዙ መለያየት ባህላችን መሆን አለበት፡፡ የይፋና የጓዳ የፖለቲካ መድረኮችን ዝርዝር ሐሳቦችን ከማፍራትና ከመፈልፈል ጋር የሚተዋወቅ በዚህም ዙሪያ በነፃ መደራጀትን በፀጋ የሚቀበል ባህል መስፈን አለበት፡፡ የትኛውም ዓይነት የብሶት ጥያቄ፣ ቅሬታ በውይይት በክርክርና በድርድር ወይም በሌላ ዴሞክራሲያዊ ሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ ካልሆነ በቀር ወደ ጉልበት አይሄድም ብለን፣ የእነዚህንም ተቋማት ከገነባን የፖለቲካ ጠብ ወደ ጠመንጃ እንዳይሄድ ከተደረገ በሰላም ሊፈታ የማይችል የውስጥ ተቃውሞ አይኖርም፡፡ የጐረቤት ጠላትነትም የት አባቱ ይደርሳል ብለን ሰላም አግኝተን የምንተኛበት አይደለም፡፡ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል አለ የሚባለው የድንበር ችግር መፍትሔ እንዲያገኝና ሶማሊያም እንድትቋቋም በፅናት መታገል ለኢትዮጵያ ወሳኝ ጥቅሟ ነው፡፡ ይህን ስናደርግ በሰላም ሊፈታ ያልቻለ የውስጥ ተቃውሞ አይኖርብንም፡፡ ወይም ከጐረቤት ባለጋራነት ጋር የተሸረበ የውስጥ ተቃውሞ ችግር አያጋጥመንም፡፡ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይና የደኅንነት ፖሊሲ ለአደጋ ተጋላጭነታችንን መቀነስ በሚለው ውስጥ የተብራራውም ይኸው ነው፡፡ ድህነታችን፣ ኋላቀርነታችንና የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ሥርዓት ሥር አለመስደድ ለአገራዊ ህልውና ጥቅማችን ዋነኛ አደጋ እንደሆነ ይገልጽና ከውጭ የሚመጣ አደጋም በዚሁ በዋናው ሥጋት ምንጭ ላይ የተመሠረተ ነው ይላል፡፡ እንኳንስ አሸባሪነት የትጥቅ ትግልም ዛሬ የትግል ሥልት መሆኑ ቀርቷል፡፡ የትጥቅ ትግል ሌላው ቢቀር ረዥም ጊዜ የሚወስድ ከመንግሥት ጋር አገርን አብሮ የሚያደቅና የሚያወድም ነው፡፡ ለረዥም ዓመታት ሲተኩሱ፣ ፈንጂ ሲዘሩና መሠረተ ልማት ሲያወድሙ ኖረው ሥልጣን ከጨበጡ በኋላ መልሶ ግንባታ ማለት ዛሬም ትናንትም እብደት ነው፡፡ የሰላማዊ ትግል ጉዳይ የሚሰበከው ለተቃዋሚዎች ብቻ አይደለም፡፡ ለመንግሥትም ጭምር ነው፡፡ ከሕገወጡ ይበልጥ ሕጋዊውና ሰላማዊው መንገድ ተመራጭና ቀላል የሚያደርግ የፖለቲካና የባህል አሠራር ማልማትና ማበረታታት አለበት፡፡ በሕጋዊነት መቀጠል ወይም ወደ ሕገወጥነት መዞር እያሉ የጫካውን መንገድ በሚያመላክት ፕሮፓጋንዳ መቀስቀስ፣ ተቃዋሚዎች ተመርረው ወደ ስደትና ወደ ጫካ ቢሄዱ እንደተገላገሏቸው መቁጠር ሰላማዊ ትግልን አያበረታታም፡፡ አሸባሪነት ደግሞ ከትጥቅ ትግል የተለየ ነው፡፡ ሰዎችን በነሲብ የሚያጭደውና የሚያጠቃው ሽብር በትግል ባህርይው የሰዎችን መብት የዳጠ ነውና የዴሞክራሲ አማጭ ለመሆን አይችልም፡፡ ያም ሆነ ይህ ለአሸባሪነት ምቹ መነቃቂያ ድባብ ሆኖ ያገለገለው ምላሽ ያጣው የፍልስጤም ጥያቄና ከእሱ ጋር ተያይዞ የተፈጠረው ፀረ እስራኤልና ፀረ አሜሪካ ስሜትና ሙቀት ነው፡፡ በጊዜያት ውስጥ እስላማዊ ጽንፈኞች ፀረ ምዕራብ ጣልቃ ገብነትንና ፀረ እስራኤልነትን መታወቂያቸው እያደረጉ መጡ፡፡ ፖለቲከኞቻቸውም ሃይማኖታዊ ጽንፈኝነትን በመሣሪያነት መጠቀም ጀመሩ፡፡ በፍልስጤሞች የትጥቅ ትግል ውስጥ ለትኩረት ማግኛነትና ለማስገደጃነት ይውል የነበረው እገታና ፈንጂ ማጥመድም ተስፋፍቶና ከፍቶ ለተለያየ ዓላማ ማስፈጸሚያ ይውል ገባ፡፡ እንዲያውም ለሽብር መስፋፋት የማዕዘን ድንጋይ ሆነው ያገለገሉት የፍልስጤም ጉዳይ አድሎኛ አያያዝና ዓለም አቀፋዊ ሽብርን በወታደራዊ ዘመቻ የማጥፋት ሙከራ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይህንን ማወቅ፣ ማጥናትና መመርመር ይገባናል፡፡ በዓለም አቀፋዊ አሸባሪነት ዓይን ውስጥ እንዳንገባ፣ አሸባሪነት በአገራችን ውስጥ ምንም ዓይነት ምክንያት እንዳያገኝ፣ በአገር ውስጥ ቅጥያውን ለማብቀልና ለማመስ፣ በውጭ ያሉ ዜጐችን ዒላማ ለማድረግ ‹‹የሚመቸው›› ሁኔታ እንዳይፈጠር በየአቅጣጫው መጣር የሁላችንም ብሔራዊ ግዴታ ነው፡፡ ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...