Tuesday, July 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክየሠራተኛ መታሰር በሥራ ውል ላይ የሚኖረው ውጤት

የሠራተኛ መታሰር በሥራ ውል ላይ የሚኖረው ውጤት

ቀን:

ይህን ጥያቄ ያቀረበው በአንድ የግል ድርጅት የሚሠራ የሒሳብ ባለሙያ ነው፡፡ ሰውዬው ለስምንት ዓመታት በሠራበት በዚህ ድርጅት በሥራውና በሥነ ምግባሩ የተመሰከረለት ነው፡፡ ከቀናት በአንዷ ግን ያላሰበው ነገር ተከሰተና ለክስ ተዳረገ፡፡ በመኖሪያ አካባቢው በተፈጠረ አንድ ከባድ የወንጀል ድርጊት ተጠርጥሮ ከታሰረ ሁለት ወራት አለፈው፡፡ እስሩ የተፈጸመው ከሥራው ላይ ተወስዶ በመሆኑ አሠሪው አውቆታል፡፡ ለሁለት ወራት ከታሰረ በኋላ የ50,000 ብር ዋስ በመጥራት በመለቀቁ ሥራ ቦታው በመሄድ ሪፖርት አደረገ፡፡ ሠራተኛው ላቀረበው ወደ ሥራዬ ልመለስ ጥያቄ የአሠሪው አማካሪዎች በሁለት ተከፍለዋል፡፡ የተወሰኑት ከሥራ ገበታው ለዚህን ያህል ወራት መቆየቱ አሠሪውን ስለሚጎዳ ሊሰናበት ይገባል ይላሉ፡፡ ይህ ምክር ሠራተኛው ከሥራው እንዲሰናበት የሚያስገድድ በመሆኑ የሠራተኛውን የሥራ ዋስትና የሚጎዳ ነው፡፡ የሌሎች አቋም ደግሞ ሠራተኛው ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ከሥራው የተለየ በመሆኑ ወደ ሥራው ሲመለስ አሠሪው ሊቀበለው ይገባል የሚል ነው፡፡ በዚህ አቋም መሠረት አሠሪው ሠራተኛው ከሥራ በተለየበት ጊዜ ላልሠራው ሥራ ደመወዝ የመክፈል ግዴታ የሌለበት ሲሆን፣ እስሩ ዋስትናን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ሲቋረጥ ወደ ሥራው ሊመለስ ይገባል፡፡ ይህ አቋም የሠራተኛውን የሥራ ዋስትና የሚጠብቅ ነው፡፡ የሁለቱም ጽንፍ ክርክሮች የተለያዩ የአሠሪና ሠራተኛ ሕጉን ድንጋጌዎች መሠረት በማድረግ የሚቀርቡ ሲሆን፣ ክርክሮቹን በጥሞና ለተመለከተ ሰው የሕግ ክፍተት መኖሩን ልብ ማለት ይቻላል፡፡ ይህ ጽሐፍ የሁለቱን ጽንፍ ክርክር በሕጉ ድንጋጌዎች ዕይታ በመመልከት ሕጉ መፍትሔ የሚሰጥ ስለመሆን አለመሆኑ መመርመር ነው፡፡ በተለይ ሕጉ የሥራ ውል ስለሚቋረጥበትና ስለሚታገድበት ሁኔታ የሚደነግግበት አናቅጽ ለጉዳዩ መፍትሔ የሚሰጥ መሆን አለመሆኑ ይመመረመራል፡፡ እስር ለዕግድ እንደ ምክንያት የሥራ ውል በሚታገድበት ጊዜ ውሉ ሳይቋረጥ የሠራተኛው የመሥራት ግዴታና የአሠሪው ደመወዝ የመክፈል ግዴታ ለጊዜው አይኖርም፡፡ የአሠሪና ሠራተኛ ሕጉ የሥራ ውል ማገድን ትርጉም፣ የማገድ ምክንያቶችን፣ ስለ ሥነ ሥርዓቱና ስለ ውጤቱ ከአንቀጽ 17 እስከ 22 በተመለከቱት ድንጋጌዎች በዝርዝር ይገዛል፡፡ በአዋጁ ከተቀመጡ የማገጃ ምክንያቶች አንዱ በአንቀጽ 18(3) ከእስር ጋር በተያያዘ አስገዳጅ ሁኔታ ሲከሰት ነው፡፡ ሠራተኛው ከ30 ቀን ለማይበልጥ ጊዜ ሲታሰርና የሠራተኛው መታሰር በ10 ቀን ውስጥ ለአሠሪው ሲነገረው ወይም አሠሪው ማወቅ ሲገባው የሥራ ውል ሊታገድ ይችላል፡፡ እስር /Detention/ ሲባል የአንድ ግለሰብ የመዘዋወር ነፃነት ገደብ የሚጣልበትን ሁኔታ የሚያመለክት ሲሆን፣ ይህንኑም በዋናነት የሚፈጽመው ከአንድ የወንጀል ድርጊት ጋር በተያያዘ ምርመራ የማካሄድ ሥልጣን የተሰጠው የፖሊስ አካል ነው፡፡ በዚህም ድንጋጌ የተቀመጠው እስር /Detention/ ከፍርድ በኋላ ከሚሰጠው እስር /Imprisonment/ እንደሚለይ ልብ ማለት ይገባል፡፡ የመጀመሪያው ግለሰብ ተጠርጥሮ ወንጀሉ ሲመረመር የዋስትና መብት ተከልክሎ ለጊዜው ነፃነቱን የማያጣበት እስር ሲሆን፣ በሁለተኛው ግን ግለሰቡ ወንጀሉን መፈጸሙ በፍርድ ቤት ተረጋግጦና ኃላፊነቱ ተመሥርቶ በእስር ቅጣት የሚወሰንበት ነው፡፡ የተነሳንበት ጉዳይ በአዋጁ አንቀጽ 18(3) ሥር በተገለጸው ‘እስር’ የሚወድቅ ነው፡፡ ምክንያቱም ሠራተኛው ከሥራው ገበታው ተነሥቶ የታሰረው ፈጸመ የተባለውን ወንጀልን ለመመርመር ነው፡፡ የሠራተኛው እስር ግን በድንጋጌው መሠረት የማገጃ ምክንያት ለመሆን የ30 ቀን ገደብና የማሳወቅ ግዴታዎች በጣምራ ሊሟሉ ያስፈልጋል፡፡ ሠራተኛው የታሰረው ከሥራ ቦታው ላይ ተነሥቶ በመሆኑ አሠሪው ያውቃል ተብሎ የሚገመት ቢሆንም፣ የሠራተኛው እስር ከ30 ቀናት የሚበልጥ በመሆኑ ጉዳዩ የሥራ ውል መታገድ የሕግ ድንጋጌ ሥር እንዳይወድቅ ያደርገዋል፡፡ ከ30 ቀናት የሚበልጥ እስር የሥራ ውል እንዲታገድ ምክንያት እንደማይሆን ከአንቀጽ 18 (3) የተቃርኖ አመክንዮ (Acontrario reasoning) መረዳት ይቻላል፡፡ እስር ለስንብት እንደ ምክንያት የአሠሪና ሠራተኛ ሕጉ እስር ለስንብት ምክንያት መሆን የሚችለው ሠራተኛው በወንጀል ድርጊት ተጠያቂ ሆኖ እስር ሲወሰንበት እንደሆነ ይደነግጋል፡፡ ሕጉ ሠራተኛው በወንጀል ተጠያቂ ሲሆን አሠሪው የሥራ ውሉን ያለማስጠንቀቂያ እንዲያቋርጥ በሁለት ሁኔታዎች ይፈቅድለታል፡፡ የመጀመሪያው ሠራተኛው በጥቅሉ በወንጀል ድርጊት ጥፋተኛ ሆኖ ሲገኝ ሲሆን፣ ይህም ከሥራ ሊያሰናብተው የሚችለው በዚሁ ጥፋተኛነት ምክንያት ሠራተኛው ለተመደበበት ሥራ ብቁ ሆኖ ሳይገኝ ሲቀር ነው፡፡ ስለዚህ ሁሉም ዓይነት የወንጀል ድርጊት ሳይሆን ፈጸመ የተባለው ወንጀል ከሠራተኛው የሥራ ባህሪይ ጋር ግንኙነት ያለው መሆን ይኖርበታል፡፡ ለምሳሌ በተነሳንበት ጉዳይ የሒሳብ ባለሙያው ሠራተኛ በእምነት ማጉደል ክስ ቀርቦበት ጥፋተኛ ቢባል ምንም እንኳ ድርጊቱ በአሠሪው ላይ የተፈጸመ ባይሆን ያለማስጠንቀቂያ እንዲያሰናብተው ሕጉ ይፈቅዳል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ከወንጀል ድርጊት ጋር የተያያዘው የስንብት ምክንያት በአዋጁ አንቀጽ 27(1) (በ) የተደነገገው ነው፡፡ ሠራተኛው የወንጀል ክስ ቀርቦበትና ጥፋተኛ ተብሎ ከ30 ቀናት ለሚበልጥ ጊዜ የእስራት ፍርድ ከተጣለበት አሠሪው ያለማስጠንቀቂያ ሠራተኛውን ለማሰናበት እንዲችል ሕግ ይፈቅድለታል፡፡ ይህ ምክንያት ከመጀመሪያው የሚለይ ሲሆን፣ ወንጀሉ ከሥራው ጋር ስለሚገናኝ ስለማይገናኝ የሚፈጸም አይደለም፡፡ አሠሪው ከ30 ቀናት በላይ የተፈረደበትን ሠራተኛ ፍርዱን ሊጨርስ እንዲመልስ ማስገደድ የአሠሪውን ትርፋማነት እጅጉን ስለሚጎዳ የተቀመጠ የስንብት ምክንያት ነው፡፡ አንቀጽ 27(1) (በ) ለተነሳንበት ጉዳይ ጠቀሜታ አይኖረውም፡፡ ምክንያቱም በዚህ ድንጋጌ መሠረት ሠራተኛውን ያለማስጠንቀቂያ ለማሰናበት ሠራተኛው በወንጀል ድርጊት ኃላፊ ተብሎ ከ30 ቀናት በሚበልጥ የፍርድ እሥራት ሊቀጣ ይገባል፡፡ በዚህ ጉዳይ የተገለጸው ሠራተኛ ግን ከ30 ቀናት በላይ የታሰረ ቢሆንም፣ የእስሩ ምክንያት ተፈርዶበት ሳይሆን ወንጀሉ እስከሚመረመር ድረስ ነው፡፡ የሠራተኛው ጥፋተኛ መሆን አለመሆን ወደፊት የሚታይ ጉዳይ በመሆኑ በምርመራ ወቅት ከተፈጸመው እሥራት ጋር የሚያያዝ አይደለም፡፡ በመሆኑም አንድ አሠሪ በወንጀል ተጠርጥሮ ከ30 ቀናት በላይ የታሰረን ሰው በዚህ ድንጋጌ መሠረት ያለማስጠንቀቂያ ለማሰናበት አይችልም፡፡ ከ30 ቀናት በላይ ሳይፈረድበት የታሰረስ? ከዚህ በላይ ስለ ዕግድና ስንብት ከተመለከት ናቸው ድንጋጌዎች ለመረዳት እንደሚቻለው ከ30 ቀናት በላይ ተጠርጥሮ የታሰረ ሠራተኛ ሊታገድም ያለማስጠንቀቂያም ሊባረር አይችልም፡፡ እንዳይታገድ እስሩ ከ30 ቀናት ይበልጣል፡፡ ሕጉ ከ30 ቀናት በላይ የሆነ እሥራት ለዕግድ ምክንያት እንደማይሆን በዝምታው ከልክሏል፡፡ በሌላ በኩል በዚህ ምክንያት ሠራተኛውም ያለማስጠንቀቂያ እንዳይሰናበት እስሩ የወንጀል ተጠያቂነት ተረጋግጦ የተሰጠ የእስር ፍርድ አይደለም፡፡ ከድንጋጌዎቹ ከ30 ቀናት በላይ ያልተፈረደበት ሠራተኛ ለሥራው ብቁ ከመሆን ጋር ካልተያያዘ ያለማስጠንቀቂያ ለማሰናበት ምክንያት አይሆንም፡፡ በሁለቱም መንገድ ሕጉ ጉዳዩን ለመግዛት ክፍተት እንዳለበት መረዳት ይቻላል፡፡ ባለሙያዎች የሚሰጧቸውም ሁለት ጽንፍ ተቃራኒ አስተያየቶች ሕጉ የፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት በሚደረግ አተረጓጎም የሚፈጠር ነው፡፡ አንዳንድ የሕግ ባለሙያዎች ለማገጃ ምክንያት የማይሆን እስር ያለማስጠንቀቂያ ሠራተኛውን ለማሰናበት ምክንያት ይሆናል ይላሉ፡፡ የሕጉ አቀራረጽ እስከ 30 ቀናት ያለው እሥራት በዕግድ፣ ከዚያ በላይ ያለው ደግሞ በስንብት እንዲካተት ተፈልጎ መሆኑን የሚገልጹ አሉ፡፡ ይህ አቋም ቅቡል እንዳይሆን የሚያደርጉት የተወሰኑ ምክንያቶች አሉ፡፡ አንደኛ የሥራ ውል መታገድንና በእስር ምክንያት ያለማስጠንቀቂያ ማሰናበትን የሚያስተሳስር ምንም ዓይነት ድንጋጌ የለም፡፡ ትስስሩ በሌለበት ከ30 ቀናት በላይ የሆነ እስር ማስጠንቀቂያ ለማሰናበት ምክንያት ይሆናል ማለት አይቻልም፡፡ በሌላ በኩል ሕጉ እስርን (Detention) ያለማስጠንቀቂያ ከማሰናበት ጋር ሊያያዝ እንደማይገባ ለማሳየት የእሥራት ፍርድን የተመለከቱ ድንጋጌዎችን ብቻ ቀርጿል፡፡ ስለዚህ እስር ያለማስጠንቀቂያ ከማሰናበት ውጭ ባሉ ሁኔታዎች ሊሸፈን ካልቻለ በቀር ለማሰናበት ምክንያት አይሆንም፡፡ ከ30 ቀናት በላይ የታሰረን ሠራተኛ ያለማስጠንቀቂያ እንዲሰናበት ማድረግ ሕግ ከመሥራት እኩል ነው፡፡ ሠራተኛው ሊሰናበት አይገባም የሚሉት ባለሙያዎች አቋም የተሻለ አሳማኝ መሆኑን ከላይ ከተሰጠው ትንታኔ መረዳት ይቻላል፡፡ ከሕጉ ክፍተት መደምደም የሚቻለው ቢያንስ ከ30 ቀናት በላይ የታሰረ ሠራተኛ በእስሩ ምክንያት ያለ ማስጠንቀቂያ ሊሰናበት እንደማይገባ ነው፡፡ አንዳንዶች አሠሪው በኅብረት ስምምነት ወይም በሥራ መመርያ ከ30 ቀናት በላይ የሚቆይ እስር ያለማስጠንቀቂያ ለማሰናበት ምክንያት እንደሚሆን ከተገለጸ ሠራተኛው ሊሰናበት ይችላል ይላሉ፡፡ ይህም አስታራቂ ሐሳብ ቢሆን የተፈጻሚነቱ ወሰን አከራካሪ ነው፡፡ ምክንያቱም በአንድ በኩል እንዲህ ዓይነት የኅብረት ስምምነት ድንጋጌ ለሠራተኛው የተሻለ ጥበቃ እስካላደረገ ድረስ በሕጉ አንቀጽ 134 መሠረት ተፈፃሚነት የለውም፡፡ የኅብረት ስምምነቱ ድንጋጌ የፍርድ እስርን እንጅ በምርመራ ጊዜ የሚደረግ እስርን ያለማስጠንቀቂያ ለማሰናበት ምክንያት ከሚያደርገው ሕግ ያነሰ ጥበቃ ይሰጣል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የአዋጁ አንቀጽ 27(1)(ተ) የኅብረት ስምምነት ተጨማሪ ያለማስጠንቀቂያ የማሰናበት ምክንያቶች መደንገግ የሚችለው ከሠራተኛው ጥፋት ጋር በተያያዘ በመሆኑ እስርን የተመለከቱ ኩነቶች አይሸፈኑም፡፡ የሕጉ ክፍተት እንዴት ይሞላ? ከ30 ቀናት በላይ የታሰረን ሠራተኛ ስድስት ወራትም ሆነ ዓመት ታስሮ ሲመጣ ሳይፈረድበት ስለታሰረ ወደ ሥራው ሊመለስ ይገባል ማለት ፍትሐዊ አይሆንም፡፡ ይህ የአሠሪውን ሥራ ከመጉዳቱም በላይ ትርፋማነቱን ይቀንሰዋል፡፡ የሕጉ ዝምታ መነሻ የሚያደርገው የወንጀል ምርመራ ጊዜ አነስተኛ በመሆኑ ለስንብት ምክንያት ሊሆን አይገባም ከሚል ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም ዋስትና የሚያስከለክሉ የወንጀል ዓይነቶችና ሌሎችም ቢሆን የፍርድ ቤቶችን አሠራር ለተመለከተ ሰው የሕጉ ዝምታን የሚሰብር መፍትሔ እንደሚያስፈልግ ይረዳል፡፡ መፍትሔዎቹ የሕግን ጽንሰ ሐሳብና ባህርይ መሠረት ያደረጉ ካልሆኑ ደግሞ በፍርድ ቤት ተቀባይነት ስለማይኖራቸው ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ ሕጉን አሻሽሎ ከ30 ቀናት በላይ የታሰረን ሠራተኛ ጉዳይ የሚመለከት ድንጋጌ ማስቀመጥ የተሻለው አማራጭ ቢሆንም ሕግ ማሻሻል በቀላሉ የሚቻል ባለመሆኑ መዘናጋት አያስፈልግም፡፡ አሠሪዎች የሕግን መሠረታዊ መርሆዎች በማይጥስ መልኩ ጉዳዩን በኅብረት ስምምነት በመሸፈን መፍትሔ መስጠት ይችላሉ፡፡ ከ30 ቀናት በላይ እስከ ተወሰኑ ጊዜያት (ለምሳሌ ሁለት ወራት) ተጨማሪ የማገጃ ምክንያቶች አድርጎ በኅብረት ስምምነት መደንገግ ለሠራተኛው የተሻለ ጥቅም ስለሚስጥ ቅቡልነቱ አያከራክርም፡፡ ያም ሆኖ የሕጉ አንቀጽ 18 እስከ 22 ተጨማሪ የማገጃ ምክንያቶች በኅብረት ስምምነት እንዲጨመሩ ይፈቅዳሉ ወይስ አይፈቅዱም የሚለው መታየት ይኖርበታል፡፡ ጸሐፊው ሕጉ ተጨማሪ የማገጃ ምክንያቶች ለሠራተኛው እስከጠቀሙ ድረስ እንደማይከለክል ስለሚያምን መፍትሔው ጥሩ አማራጭ ነው፡፡ ሆኖም ከሕጉ መሥፈርት (Standard) የላቀ ጥቅም ለማይሰጡ አሠሪዎች መፍትሔው እንደማይዋጥላቸው ይታመናል፡፡ እንደዚህ ያሉቱ ደግሞ ከ30 ቀናት በላይ የተፈጸመ እስርን በማስጠንቀቂያ ለማሰናበት ምክንያት እንዲሆን በኅብረት ስምምነት ወይም በሥራ መመርያ ቢያካትቱ የሕጉን ክፍተት ይሞሉታል፡፡ ከማገድ በላይ ያለማስጠንቀቂያ ከማሰናበት መለስ ያለው ይህ መፍትሔ የተሻለ ቅቡል ለመሆኑ ማስረጃ ይፈልግ፡፡ አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...