Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

ታክሲያችን ሺ ሰማንያን አልፋ፣ ግንፍሌን ተሻግራ ወደ ወወክማ አቅጣጫ ስታመራ አራት ኪሎ መድረሳችንን አወቅነው፡፡ አራት ኪሎ መንበረ መንግሥት – የመንግሥት መቀመጫ ብቻ አይደለችም፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መናኸርያም ነች፡፡ ቅድመ አብዮት ሲጠራበት ከነበረው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በፊት፣ ከ65 ዓመታት አስቀድሞ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ሲወለድ አዋላጇ አራት ኪሎ ነበረች፡፡ ሚያዝያ 27 አደባባይ ላይ የቆመው የድል ሐውልትም ወለል ብሎ ይታያል፡፡ በአካባቢው የዘንድሮ የዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎች ጋዋናቸውን ተላብሰው ይተላለፋሉ፡፡ በሐምሌ ጨለማ፣ በክረምቱ የተመራቂዎች ብርሃን ከአራት ኪሎ እስከ ስድስት ኪሎ ደምቆ ይታያል፡፡ በዘመናት ተማሪዎቹን ከሚመርቅበት የስድስት ኪሎ ዋና ግቢ ተፋትቶ ከቦሌው ሚሌኒየም አዳራሽ የተጣበቀው የአዲስ አበባው ዩኒቨርሲቲ ምሩቃን የምረቃ ድባቡን ለማድመቅ ከቦሌ ወደ አራት ኪሎ ሲመለሱ ይታያሉ፡፡ ‹‹ምነው ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎቹን ከባለግርማ ሞገሱ የቀድሞው ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ግቢ ማስመረቁን ተወው?›› አሉ አዛውንቱ፡፡ አጠገባቸው የተቀመጠው ጎረምሳ፣ ‹‹ተመራቂዎች ስለበዙ ሁሉንም በአንድነት በተንጣለለው አዳራሽ ለመመረቅ ብለው ነው፤›› አላቸው፡፡ ‹‹ምን ተመራቂ ቢበዛ እንደወትሮው ከፋፍሎ ማስመረቅ እንጂ ከትምህርት ዐውድ ጋር ከማይያዝ ከራቀ ቦታ እንዴት ይሆናል? ከነሙሉ ክብሩ…›› ሲባል’ኮ ተመራቂዎች ለዓመታት በተመላለሱበት በየተማሩበት ሕንፃ ከግቢው አፀድ ጋር ፎቶ ሲነሡ የሚፈጥርባቸውን ስሜት ቦሌ አያገኙትም፡፡ ባለግርማው ደብር (ተራራ) ነው? ወይስ ወግር (ኮረብታ)? እስቲ መልሱልኝ›› አሉ፡፡ ታክሲያችን የድል ሐውልቱን አልፋ ሄደች፡፡ በዳግማዊ ምኒልክ ጎዳና ግራና ቀኝ የኢትዮጵያና የእስራኤል ሰንደቅ ዓላማዎች እየተውለበለቡ ነው፡፡ ሰሞኑን መዲናችን ጎራ ያሉትን የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ለመቀበል መውለብለባቸው ነበር፡፡ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኔታንያሁ በፓርላማችን ከንግሥተ ሳባና ንጉሥ ሰሎሞን ጀምሮ የነበረውን ግንኙነት እያስታወሱ ኢትዮጵያን ማወደሳቸው ደስ ይላል፤›› ብላ አንዷ ወይዘሪት ሐሳቧን ጣል ስታደርግ አዛውንቱ ተቀበሏት፡፡ ‹‹ደግ ብለሻል ስለኛና ስለእስራኤል ከአፍሪካ ጋርም ስላላቸው ግንኙነት መናገራቸው ጥሩ፡፡ ስለ ዴር ሱልጣን ገዳማችን ምነው ትንፍስ አላሉ? ለዘመናት ችግር ውስጥ ያለው ከግብፅ ጋር ከይዞታ ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት እየተደረገ ስላለው ነገር አለመስማታችን ቅር አሰኝቶኛል፡፡ በሁለትዮሽ ውይይት ላይ ስለመነሣቱም አልሰማንም፡፡›› ታክሲው እየተሽከረከረ ነው፤ እኔም በሐሳብ ማዕበል እየተናጥሁ ነው፡፡ ‹‹ከዚህ ሳለ ግንዱ ኢየሩሳሌም ደረሰ ገመዱ›› የሚለው የእንቆቅልህ ምናውቅልህ ጥያቄ መልሱ ሐሳብ ቢሆንም፤ እኔ በሐሳብ ሳይሆን ከአንድ ኦሊምፒያድ በፊት የጎበኘሁት ዴር ሱልጣን ገዳም ታወሰኝ፡፡ ከአያሌ ምታመታት ጀምሮ በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት፣ የተቀበረበት፣ እንዲሁም የተነሣበት ስፍራ በጎልጎታ ተራራ ላይ በሚገኘው ዴር ሱልጣን ገዳም የሚገኘው ይዞታችን፣ በመፈራረስ ላይ ከመሆኑ የተነሣ እጅግ አስጊ ደረጃ ላይ መድረሱን መነኮሳቱ መናገራቸው እኔም በእማኝነት ማየቴን አስታውሳለሁ፡፡ በዴር ሱልጣን ገዳም ዙርያ ከኢትዮጵያ ሌላ የግብፅ (ኮፕት)፣ የግሪክ፣ የሶርያ፣ የአርመን ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናትና የሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አጥቢያዎቻቸውን መሥርተው ይገኙበታል፡፡ ከእነዚህ ሁሉ ከሰላም ይልቅ ጠብ ያለው በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ገዳማቸውን እንዳያድሱ ግብፆቹ ለዓመታት እንደተከላከሉ ነው፡፡ ገዳሙ ከሺሕ ዓመት ግድም ጀምሮ በጭቃ እንደተሠራ የለበሰውም ቆርቆሮ እያፈሰሰ ነው፤ የመፀዳጃ ቤቱም ከሩቅ ጠረን የሚያመጣ ነው፡፡ በአንድ በሠለጠነች አገር ውስጥ እንደዚህ ዓይነት አኗኗር መኖሩ ያሳፍራል፡፡ ጀርመናዊው የፊልም ባለሙያ ዘጋቢ ፊልም ሁሉ ሠርቶበታል፡፡ በዴር ሱልጣን ገዳም ችግር መከሰት ከጀመረ ከ240 ዓመታት በላይ ነው፡፡ የይዞታ ባለቤትነት ለማረጋገጥም ከ170 ዓመት በላይ በፍርድ ቤት ክርክር የነበረበት ነው፡፡ ይኼን ውጣ ውረድ ለማስተካከል በተለይ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ጀምሮ እስካሁን የተለያዩ ጥረቶች ቢደረጉም መፍትሔ አልባ ሆኗል፡፡ ቅዱስ ፓትርያርኩ አቡነ ማትያስ በቅርቡ እስራኤልን ሲጎበኙ ማሳሰባቸው አልቀረም፡፡ የመሰንበቻውን የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጉብኝት ተከትሎ ሁለቱ አገሮች ከተፈራረሙባቸው ጉዳዮች አንዱ ቱሪዝምን የሚመለከት ነበር፡፡ ስለ ዴር ሱልጣን ማንሳታቸውን አልሰማንም፤ ሹማምንቱም አልነገሩንም፣ ሚዲያውም አላወጋልንም፡፡ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በተለይም ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ስለ ዴር ሱልጣን ገዳም ሲያነሡም ሰምቼም አላውቅ፤ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትራችንና ጠቅላይ ሚኒስትራችን ስለ ኢየሩሳሌም ይዞታችን ስላነሡት ነገር እኔ በበኩሌ አልሰማሁም፡፡ ማነው የሚጮህልን? ኧረ መላ በሉ! (ወልደዮሐንስ ገብረሥላሴ ዐምዱ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...