ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በፕሪሚየር ሊግ ክለቦችና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድኖች ተሰልፈው ከሚጫወቱት የእግር ኳስ ተጨዋቾች መካከል በስኬታማነት ከሚጠቀሱት ውስጥ በደቡብ የአገሪቱ አካባቢ የሚገኙት በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡ በዘንድሮው የፕሪሚየር ሊግ የዓመቱ ኮከብ ተጨዋች ተደርጎ የተመረጠው ከዲላ ከተማ የተገኘው የቅዱስ ጊዮርጊሱ አስቻለው ታመነ አንዱ ተጠቃሽ ነው፡፡ በብሔራዊ ሊግ ዲላ ከተማን ወክሎ መጫወት ከጀመረ በኋላ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አጥቂ ጌታነህ ከበደ አማካይነት በ2006 ዓ.ም. ለደደቢት እግር ኳስ ክለብ ሁለት ዓመት ማሳለፍ ችሏል፡፡ ከደደቢት እግር ኳስ ክለብ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከተዘዋወረበት 2008 ዓ.ም. በኋላ ለብሔራዊ ቡድንም በመሠለፍ ጥሩ ጊዜ ማሳለፍ ችሏል፡፡ ከግብ ጠባቂነት በስተቀር በሁሉም የሜዳ ክፍል እንደሚጫወት የሚነገርለት አስቻለው፣ በዘንድሮ ፕሪሚየር ሊግ ከመሀል ተከላካይነት የቀኝ ተመላላሽ ተጨዋቾች በመሆንም አቅሙን በማሳየት አስመስክሯል፡፡ ከዚህ ውጤታማ ተጨዋቾች ጋር ዳዊት ቶሎሳ ቆይታ አድርጓል፡፡ ሪፖርተር፡- ወደ ፕሪሚየር ሊግ የገባህበት ሒደት ምን ይመስላል? አስቻለው፡- ወደ ፕሪሚየር ሊግ የመጣሁት ልክ ዲላን ከተማን ወክዬ ብሔራዊ ሊግ መጫወት ስጀምር ነው፡፡ በመጀመሪያው ዓመት ግን የመሰለፍ ዕድል አላገኘሁም ነበር፡፡ ከዛም በሁለተኛ ዓመት ተሳትፎዬ ላይ ብዙ የመሰለፍ ዕድል አገኘሁ፡፡ ወላይታ ድቻ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ባደገበት ወቅት ከክለቡ ጥያቄ ቀረበልኝ፡፡ ጥያቄውን ብቀበልም ቀደም ብሎ ዲላ እያለሁ የአንድ ዓመት የውል ስምምነት ስለነበረብኝ ያንን የአንድ ዓመት ስምምነት መጨረስ አለብህ በመባሌ እሱን ጨረስኩ፡፡ ከዛም በጌታነህ ከበደ ጥረት ወደ ደደቢት እግር ኳስ ክለብ መቀላቀል ቻልኩ፡፡ ደደቢት ከመፈረሜ ቀደም ብሎ ደብረ ዘይት ላይ ሙከራ ማድረግ ነበረብኝ፡፡ ሙከራ ካደረግኩ በኋላም በአመራሮቹ ተቀባይነት ማግኘት ቻልኩ፡፡ ከ2006 እስከ 2007 ዓ.ም. ለሁለት ዓመት ተፈራረምኩ፡፡ ሪፖርተር፡- ቀደም ብሎ ስትጫወትበት ከነበረው ብሔራዊ ሊግ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ስትገባ የነበረህ ስሜት እንዴት ነበር? ምንስ የተሻለ ነገር አገኘህ? አስቻለው፡- ማንኛውም እግር ኳስን የሚጫወት ተጫዋች የመጀመሪያ ምኞቱ የሚሆነው በአገሪቷ ከተሰባሰቡት ታላላቅ ተጫዋቾች ጋር በመገናኘት ችሎታውን ማሳየት ነው፡፡ ስለዚህ እኔም በቴሌቪዥን መስኮት ከምመለከታቸው ታላላቅ ተጫዋች ጋር ተሰልፌ መጫወትን ስመኝ ነበር፡፡ በጊዜው ደደቢት ያሉትን ተጫዋች ስመለከት የተሻለ መሥራት እንዳለብኝ ነው የተረዳሁት፡፡ በተጨማሪም ብሔራዊ ሊግ ላይ ስትጫወት ብዙ ችግሮች ይኖራሉ፡፡ እነዛም ችግሮች ብቃትህን እንድታሻሽል ላያደርግህ ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም ብሔራዊ ሊግ ላይ ያለው አጨዋወት ሕግ የሌለውም ሊመስልህ ይችላል፡፡ በተጨማሪም ክህሎትን ለማዳበር የተሻለ አሠልጣኝ ላታገኝ ትችላለህ፡፡ ፕሪሚየር ሊግ ላይ ግን ምንም እንኳ አንዳንድ ችግሮች ቢያጋጥምህም በሊጉ ላይ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ስላሉ ከእነሱ ጋር እየተነጋገርህ ችግሮችን መፍታት ትችላለህ፡፡ የተፈጠሩ ችግሮችንም አፋጣኝ መልስ ሲያገኙ ትመለከታለህ፡፡ ስለዚህ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ስቀላቀል በጣም ደስተኛ ነበርኩ፡፡ ሪፖርተር፡- አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች ወደ እግር ኳስ የሚገቡት ሠፈር ውስጥ ወይም ትምህርት ቤት ላይ የሚያሳዩትን ብቃት በመመልከት ሰዎች በሚሰጧቸው አስተያየት ነው፡፡ ከቤተሰብህ ውስጥ እናትህ ብቻ እንድትቀጥል ፍላጎት እንደነበራቸው ይነገራል፡፡ አንተ እግር ኳሱን ልትመርጥ የቻልከው እንዴት ነው? አስቻለው፡- በእርግጥ እግር ኳስን ስጀምር ከፍተኛ ድጋፍ ስታደርግልኝ የነበረችው እናቴ ነበረች፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ትምህርት ቤት ላይ በማደርገው እንቅስቃሴ የስፖርት አስተማሪዎቼ፣ የተለያዩ የእግር ኳስ አሠልጣኞች ‹‹አንተ በዛው መቀጠል ከቻልክ ወደፊት ትልቅ ተስፋ አለህ›› በማለት አስተያየት የቸሩኝ ነበሩ፡፡ ፕሮጀክት ላይም ‹‹አንተ ለኳስ የተፈጠርክ ልጅ ነህ›› ይሉኝ ነበር፡፡ ግን እግር ኳስ ብቻ ስታተኩር ትምህርት ላይ የሚኖረው ውጤት ጥሩ አይሆንም፡፡ ስለዚህም አባቴ ከፍተኛ ክልከላ ያደርግብኝ ነበር፡፡ ምክንያቱም እንድማር ነው የሚፈልገው፡፡ ስለዚህ በወቅቱ አባቴ የመስክ ሠራተኛ ስለነበረ እናቴ በድብቅ ትደግፈኝ ነበር፡፡ በዛ ሁሉ ጫና ውስጥ አሁን ለደረስኩበት ቦታ ላደረሰኝ እግር ኳስ ያለኝ ትልቅ ፍቅር ነው፡፡ በእኔና አባቴ መካከል የተፈጠረው ድብብቆሽ እኔ ውስጥ የነበረው ከፍተኛ የእግር ኳስ ፍቅር ነው፡፡ ያ ማለት የእግር ኳስ ፍቅር ስላለኝ ብቻ እዚህ ደረጃ ደርሻለሁ ማለት አልችልም፡፡ ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፌና እንዲሁም አሠልጣኞቼ የሚሰጡኝን ልምድ በአግባቡ በመተግበርና እነሱ ከሚሰጡኝ ሥልጠና በግሌም በመጨመርና ጠንክሬ በመሥራት ነው፡፡ ሪፖርተር፡- በደደቢት እግር ኳስ ክለብ በነበረህ ቆይታ፣ እንዲሁም አሁን ባለህበት ቅዱስ ጊዮርጊስ የአንድ ዓመት ቆይታ ሊጉ ላይ መስተካከል አለበት የምትለው ነገር አለ? አስቻለው፡- በዚህ የሦስት ዓመት ቆይታዬ ውስጥ የተለያዩ ችግሮችን መመልከት ችያለሁ፡፡ በዚህ ዘመን እግር ኳስ ማለት ከመዝናኛነትም አልፎ በተለያዩ የዓለማችን አገሮች ለፖለቲካ ግብዓትም ሲጠቀሙበት እንመለከታለን፡፡ ይኼ ማለት ደግሞ እግር ኳስን ዘጠና ደቂቃ ተጫውቶ ጎል ማስቆጠር ብቻ ሳይሆን ከዛም ባሻገር ለኅብረተሰቡ ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ስለዚህ በአንድ የውድድር ዘመን እግር ኳሱ በሰላማዊ መንገድ እንዲከወናወን የሁሉም ሰው ኃላፊነት ይሆናል ማለት ነው፡፡ በተለይ የዘንድሮ የፕሪሚየር ሊግ ዓመት በደጋፊዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት ሰው ሲጎዳ ተመልክተናል፡፡ ለዚህም እንደምክንያት ዳኝነትን ያነሳሉ፡፡ ዳኝነትን የሚመራው ሰው ነው፡፡ ሰው ደግሞ መሳሳት አይችልም ማለት ይከብዳል፡፡ ስለዚህ የዳኝነትን ውሳኔ መቀበል ያስፈልጋል፡፡ ዳኞችም ቢሆኑ ውድድሩ ከእነሱ ውጪ ማካሄድ እንደማይቻል ተረድተው ትክክለኛ የሆነ ዳኝነት ማዳበር አለባቸው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ግን ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ፣ መንግሥትም ትኩረት ሰጥቶት መሠራት ግድ ይለዋል፡፡ በተጨማሪም ፌዴሬሽኑ የፕሮግራም አወጣጥን በአግባቡ ማስኬድ አለበት፡፡ ውድድሩ በሥነ ሥርዓት መምራት ካልቻለ አስቸጋሪ ነው፡፡ ለዚህም በምሳሌነት ውድድሩ ቶሎ ባለመጀመሩ ምክንያት ምን ዓይነት ሜዳ ላይ ማጠናቀቅ እንደተቻለ ሁሉም መመልከት የቻለው ጉዳይ ነው፡፡ በፕሪሚየር ሊግ ላይ ብቻ ሳይሆን ክትትሉ በብሔራዊ ሊግም ሆነ በሌሎች ውድድሮች አስፈላጊውን ትኩረት መስጠት አስፈላጊ ነው ባይ ነኝ፡፡ ሪፖርተር፡- በግልህ ወደ ሊጉ ከመጣህ ያጋጠመህ ችግር አለ? አስቻለው፡- እግር ኳስ ተጫዋች ስትሆን በተለይ በሊጉ ላይ ስትጫወት የተለያዩ ችግሮች ሊያጋጥሙህ ይችላል፡፡ ዋናው ነገር ተጫዋች የያዘውን ዓላማ አለመርሳትና ጠንክሮ መሥራት አዋጭ ነው ባይ ነኝ፡፡ እኔ አሠልጣኞች ከሚሰጡኝ ልምምድ በተጨማሪ በግሌ የተሻለ ቦታ ለመድረስ እየሠራሁ ነው፡፡ ምክንያቱም ጠንክሬ መሥራት ከቻልኩ እነዚህን ችግሮች በቀላሉ ማለፍ እችላለሁ፡፡ እስካሁን ትልቅ ፈታኝ ነገር ገጥሞኛል የምለው ነገር የለም፡፡ እንደ ችግር ላነሳቸው የምችላቸው ቢኖሩ በጣም ጥቃቅን ነገሮች ናቸው፡፡ እሱንም ቢሆን ልምድ ካላቸው ትምህርት በመውሰድ ለመፍታት ሞክሬያለሁ፡፡ ሪፖርተር፡- በ31ኛው የአፍሪካ አገሮች ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥሪ ተደርጎልህ እየተጫወትህ ትገኛለህ፡፡ ለብሔራዊ ቡድን መጫወት እንዴት አገኘኸው? አስቻለው፡- እንደማንኛውም ተጫዋች መጀመሪያ ፕሪሚየር ሊግ ላይ መጫወት የመጀመሪያ ዕቅድ ይሆናል፡፡ ከዛ በላይ ግን አገርን ወክሎ እንደመጫወት ትልቅ ነገር የለም፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያን ባንዲራ ይዘህና ለብሰህ ነው ወደ ሜዳ ምትገባው፡፡ ስለዚህ በወቅቱ እኔ ጥሪ ሲቀርብልኝ ትልቅ ደስታ ነው የተሰማኝ፡፡ ከዛም ባሻገር በእነዚህ ውድድሮች ላይ መሳተፍ በራሱ ራስህን እንድፈትሽና እንድገመግም ነው ያስቻለኝ፡፡ ምክንያቱም በእነዚህ ውድድሮች ላይ ከተለያዩ ታላላቅ ክለቦች ላይ ከሚሳተፉ ፕሮፌሽናል ተጫዋቾች ጋር ነው የምጫወተው፡፡ ሪፖርተር፡- በዚህ የሦስት ዓመት የእግር ኳስ ቆይታህ በዘንድሮ የፕሪሚየር ሊግ እንቅስቃሴ ኮከብ ተጫዋች ሆነህ መመረጥ ችለሃል፡፡ በአጠቃላይ ለአንተ ስኬታማነት ማመስገን የምትፈልገው አካል አለ? አስቻለው፡- በመጀመሪያ ለዚህ ስኬት ፈጣሪን ማመስገን ፈልጋለሁ፡፡ ከዛ በመቀጠል የቀድሞ የደደቢትና የብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌን ማመስገን ፈልጋለሁ፡፡ እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አጥቂ ጌታነህ ከበደና ቤተሰቦቼን ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ ሪፖርተር፡- በቀጣይ የእግር ኳስ ቆይታህ ምን ዕቅድ አለህ? በትውልድ ከተማህ ዲላ ወክለው እግር ኳስን ለሚጫወቱ ታዳጊ ልጆች ያቀድከው ነገር አለ? አስቻለው፡- እስካሁን በመጣሁበት የእግር ኳስ ሕይወት ምንም እንኳ ስኬታማ ብሆንም ወደፊት የበለጠ መሥራት እንዳለብኝ አምናለሁ፡፡ ለዚህም ጥንካሬ በመሥራት የተሻለ ደረጃ ደርሼ ወደ ውጪ አገር ሄጄ መጫወት እፈልጋለሁ፡፡ በትውልድ አገሬ ዲላ ከተማ ከፍተኛ ችሎታ ኖሯቸው ዕድሉን ያላገኙ ብዙ ተጫዋቾች አሉ፡፡ ለእነሱ ባገኘሁት ልምድ የተቻለኝን ደጋፍ አደርጋለሁ፡፡ እንዲሁም በትዕግሥት ጠንክረው እንዲሠሩ የተቻለኝን ማድረግ እፈልጋለሁ፡፡ በተጨማሪም ዲላ ከተማ ላይ የምረዳቸው ታዳጊ ልጆች አሉ፡፡ ለእነሱም ቀደም ብሎ ባደረግናቸው የቻን ውድድር ላይ ያገኘሁትን ትጥቅ ማበርከት ችያለሁ፡፡ በቀጣይም ባለኝ አቅም ድጋፌን እቀጥላለሁ፡፡