በ40/60 ቤቶች ፕሮግራም 164 ሺሕ ነዋሪዎች ተመዝግበው እየተጠባበቁ ቢሆንም፣ ባለፉት አራት ዓመታት አንድም ቤት ለተጠቃሚዎች አለመተላለፉ አሁንም ቅሬታ አስነሳ፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ40/60 ቤቶች ፕሮግራም እየገነባቸው ያሉትን ቤቶች በተለያዩ ጊዜያት ለተጠቃሚ እንደሚያስተላልፍ ቢገልጽም፣ እስካሁን አንድም ቤት ለተጠቃሚዎች አለማስተላለፉ ቅሬታ እንደፈጠረባቸው ዕድሉን የሚጠባበቁ ነዋሪዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ሐምሌ 4 ቀን 2008 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ ከኮንትራክተሮች ጋር ባካሄደው ግምገማዊ ሥልጠና፣ በሠንጋ ተራና በክራውን ሳይቶች የተገነቡ 1,292 ቤቶች በአማካይ 96.12 በመቶ ቢጠናቀቁም፣ ለቆጣቢዎች የሚተላለፉበት ቀን በይፋ አለመገለጹ እንዳሳሰባቸው ነዋሪዎች ጨምረው ገልጸዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይፋ ካደረጋቸው አራት የመኖሪያ ቤት ፕሮግራሞች አንዱ የሆነውን የ40/60 ፕሮግራም ተግባራዊ እንዲያደርግ፣ የቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ ተቋቁሟል፡፡ በዚህ መሠረት ኢንተርፕራይዙ እስካሁን ድረስ በ13 ሳይቶች 38,790 ቤቶችን በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡ ኢንተርፕራይዙ የሚገነባቸውን ቤቶች የውስጥ ዲዛይን ለውጥ በማድረግ እየተገነቡ ያሉትን ቤቶች ቁጥር 39,229 ማድረሱን አስታውቋል፡፡ የአዲስ አበባ ቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ የጥናት፣ በጀትና ዕቅድ ቡድን መሪ አቶ አብረሃም ተስፋዬ በወቅቱ ባቀረቡት ሪፖርት እንደገለጹት፣ በክራውንና በሠንጋ ተራ ሳይቶች የተገነቡትን ቤቶች በመስከረም 2008 ዓ.ም. ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍ በስድስት ሳይቶች የተጀመሩትን ቤቶች ግንባታ 80 በመቶ ለማድረስ፣ በአምስት ሳይቶች የተጀመሩትን ደግሞ 40 በመቶ ለማድረስ ታቅዶ ነበር፡፡ ነገር ግን በክራውንና በሠንጋ ተራ ሳይቶች የሚገኙት ቤቶች አለመተላለፋቸውንና በሌሎች ሳይቶች የሚገኙትም ከተወሰኑት በስተቀር ዝቅተኛ የሥራ አፈጻጸም እንደተመዘገበባቸው አቶ አብርሃ አስረድተዋል፡፡ የሥራ አፈጻጸሙ ደካማ የሆነው በዋነኝነት በአስተዳደሩ በኩል ባሉ የፋይናንስ ፍስት ችግሮች፣ በብረት፣ በሲሚንቶ፣ በውኃና በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ምክንያት እንደሆነም ተጠቅሷል፡፡ በአንፃሩ በኮንትራክተሮች በኩል በቂ የሰው ኃይል አሰማርቶ ግንባታውን በአግባቡ አለማካሄድ ሌላኛው ተጠቃሽ ምክንያት እንደሆነም ተመልክቷል፡፡ እነዚህን የ40/60 ቤቶች ለማግኘት ከተመዘገቡት መካከል 155 ሺሕ ነዋሪዎች ቁጠባቸውን ሳያቋርጡ መቀጠላቸው፣ አሥር ሺሕ ተመዝጋቢዎች ደግሞ ቁጠባ ማቋረጣቸው፣ ከ13 ሺሕ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ሙሉ ክፍያ በማጠናቀቅ ቤታቸውን ለመረከብ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ተመዝጋቢዎች የቤቶቹ ግንባታ ተጠናቆ መተላለፍ ባለመጀመሩ ምክንያት በሚናፈሱ አሉባልታዎች እየተሸበሩ መሆኑንም እየገለጹ ነው፡፡ በተለይ መሰንበቻውን በሠንጋ ተራ ሳይት ብሎክ አምስት፣ አራተኛ ፎቅ፣ የቤት ቁጥር ዘጠኝ ለተጠቃሚ የተላለፈ ይመስል መጋረጃ ተሰቅሎ፣ ቤቱም ፀድቶ መመልከታቸው ሥጋታቸውን እንዳባባሰ ተመዝጋቢዎች ገልጸዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኃይሉ ቀነዓ ለማንም የተላለፈ ቤት አለመኖሩንና ቤቶች የሚተላለፉት በሥርዓት ነው ብለዋል፡፡ ‹‹ይህ ቤት የተሟላ ገጽታ እንዲኖረው የተደረገው ለናሙና ነው፤›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡ ‹‹ቤቶቹ ሲጠናቀቁ ምን ዓይነት ገጽታ ይኖራቸዋል የሚለውን ለሚመለከተው አካል ለማሳየት ተብሎ የተሠራ ሥራ ነው፤›› በማለት አቶ ኃይሉ ተመዝጋቢዎች ሥጋት ሊገባቸው እንደማይገባ ተናግረዋል፡፡ ኢንተርፕራይዙ ቤቶች የሚተላለፉበትን ዋጋ ለመከለስ ኮሚቴ አዋቅሮ ሲያጠና ቆይቷል፡፡ አቶ ኃይሉ እንዳሉት ጥናቱን የበላይ አካል ከተመለከተው በኋላ ይፋ ይደረጋል፡፡