Thursday, February 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለባንኮች ተቀማጭ ገንዘብ የዋስትና ሽፋን የሚሰጥ ግዙፍ ኩባንያ ሊመሠረት ነው

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

– ብሔራዊ ባንክ የኩባንያውን መመሥረቻ ረቂቅ ይፋ አደረገ በ

ኢትዮጵያ በፋይናንስ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ባንኮች፣ ከደንበኞቻቸው ለሚያሰባስቡት ተቀማጭ ገንዘብ ዋስትና ለመስጠት ያስችላል የተባለ ግዙፍ የኢንሹራንስ ፈንድ ኩባንያ ሊቋቋም ነው፡፡ በአገሪቱ በፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ ግዙፍ ኩባንያ ሆኖ ይወጣል ተብሎ የሚጠበቀውን ይህን ተቋም ለመመሥረት፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የኩባንያውን መመሥረቻ ረቂቅ ባለፈው ሳምንት ይፋ አድርጓል፡፡ የኩባንያውን ይዘትና ዝርዝር ጉዳዮችን የያዘው ረቂቅ ባንኮች አስተያየት እንዲሰጡበት የተላከላቸው መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ እንደ ምንጮች ገለጻ፣ ኩባንያው የሚመሠረትበት ዋነኛ ዓላማ ለባንኮች ተቀማጭ ገንዘብ ዋስትና ለመስጠትና አስቀማጮችም በባንክ በሚያስቀምጡት ገንዘብ እምነታቸው የበለጠ የጠነከረ እንዲሆን ማስቻል ነው፡፡ የሚመሠረተው ኩባንያው መንግሥታዊ ተቋም ይሆናል ተብሏል፡፡ የኩባንያው ዋነኛ ሥራም ለተቀማጭ ገንዘቡ ዋስትና ይሆናል የተባለውን ፈንድ በየዓመቱ ባንኮቹ ከሚሰበሰቡት ተቀማጭ ገንዘብ 0.18 በመቶ በማስላት እንዲያስገቡ ማድረግ ነው፡፡ ከተቀማጭ ገንዘቡ 0.18 በመቶ ተሰልቶ ለአዲሱ ኩባንያ ገቢ የሚደረገው ገንዘብም እንደ ዓረቦን ይታያል፡፡ ባንኮች የሚያስቀምጡት ገንዘብ የሕዝብ በመሆኑ በአንድ አጋጣሚ ባንኮች ቢከስሩ ወይም ተቀማጭ ገንዘቡን አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ክስተት ቢፈጠር፣ አዲሱ ኩባንያ ከሚሰበስበው ፈንድ ላይ ባንኮች ተበድረው እንዲጠቀሙ ያስችላል፡፡ በጥቅሉ ግን በሕዝብ ተቀማጭ ገንዘብ ምክንያት ባንኮች ችግር ቢገጥማቸው፣ የሚቋቋመው ኩባንያ ከችግራቸው እንዲወጡ እንደሚያስችል በረቂቁ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የባንክ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ፡፡ የተቀማጭ ገንዘብ ዋስትና የሚሰጡ ኩባንያዎች በሌሎች አገሮች የተለመዱ መሆናቸውንም ይገልጻሉ፡፡ እንዲህ ያለውን አገልግሎት ለመስጠት መታሰቡ መልካም መሆኑን የባንክ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን አሁን በሥራ ላይ ያሉት አብዛኞቹ የአገሪቱ ባንኮች ኪሳራ ላይ የሚጥል ሥጋት የማይታይባቸው በመሆኑ፣ የአዲሱ ኩባንያ መቋቋም ጊዜውን የጠበቀ እንዳልሆነ የሚገልጹም አሉ፡፡ የሕዝብ ገንዘብ ደኅንነቱ እንዲጠበቅ ማድረግ አስፈላጊነቱ ላይ ምንም ተቃውሞ የሌላቸው መሆኑን የሚገልጹት እነዚሁ አስተያየት ሰጪዎች፣ የሕዝብን ገንዘብ አደጋ ላይ የሚጥል ምንም ዓይነት ክስተት ሳይኖር አዲሱን ኩባንያ ማቋቋም ባንኮችን ለተጨማሪ ወጪ ሊዳርግ ይችላል የሚል ሥጋት ያቀርባሉ፡፡ በተለይ አሁን ባለው አሠራር የባንኮች የተቀማጭ ገንዘብ ደኅንነትን ለመጠበቅ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እያንዳንዱ ባንክ ከዓመታዊ ተቀማጭ ገንዘቡ አምስት በመቶ እየተሰላ በመጠባበቂያነት እንዲቀመጥ መደንገጉ እየታወቀ፣ እንደገና በአዲሱ ኩባንያ አማካይነት ሊሰበሰብ የታሰበው ፈንድ ሲታከል የባንኮችን ወጪ እንደሚጨምር አመልክተዋል፡፡ ስለዚህ ኩባንያው የሚፈጠር ከሆነ ለመጠባበቂያ ተብሎ ባንኮች የሚያስቀምጡት ገንዘብ ሊቀር ይገባልም ይላሉ፡፡ ሌሎች የባንክ ባለሙያዎች ደግሞ አዲሱ ኩባንያ እንዲሠራ የታሰበው አንድ የኢንሹራንስ ኩባንያ ሊሠራው እንደሚችለው ዓይነት ሥራ በየዓመቱ ዓረቦን የሚሰበስብ በመሆኑ፣ አዲስ ኩባንያ ከመፍጠር የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የተቀማጭ ገንዘብ ዋስትና ሽፋን እንዲሰጡ መፍቀድ ይሻል ነበር ብለዋል፡፡ በአገሪቱ ውስጥ የሚንቀሳቀሱት ሁለቱ የመንግሥት ባንኮችና 16ቱ የግል ባንኮች በአሁኑ ወቅት ያላቸው ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘብ ከ415 ቢሊዮን ብር በላይ ይሆናል፡፡ ባንኮቹ ካላቸው ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘብ ውስጥ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተቀማጭ ገንዘብ መጠን ከ287 ቢሊዮን ብር በላይ የደረሰ ሲሆን፣ 16ቱ የግል ባንኮች የተቀማጭ ገንዘባቸው መጠን ከ128 ቢሊዮን ብር በላይ እንደደረሰ በቅርቡ የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች