Monday, October 2, 2023

በደቡብ ሱዳን የነፃነት ቀን ዋዜማ የተቀሰቀሰው ጦርነት ሥጋቶች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ከብዙ ዓመታት ደም መፋሰስ በኋላ የዛሬ አምስት ዓመት ሐምሌ ወር ላይ ነበር ነፃነቷን ያወጀችው፡፡ ባለፈው ቅዳሜ የነፃነቷ ቀን የተሰረዘ ሲሆን፣ ከዋዜማው ጀምሮ ጦርነት ተቀስቅሷል፡፡ የተጠበቀው ሰላም ባይገኝም ለበርካታ አሠርት የእርስ በርስ ግጭት ምክንያት የነበረው የመገንጠል ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ፣ ከአምስት ዓመት በፊት አዲስ አገር ተብላ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) መመዝገቧ ይታወሳል፡፡ ሆኖም በይደር የቆዩት የድንበርና የአንዳንድ ግዛቶች የባለቤትነት ጥያቄዎች አንድ ዓመት ባልሞላው ጊዜ ውስጥ ሁለቱም አገሮች ተመልሰው ወደ ጦርነት እንዲገቡ አድርገዋል፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያን ጨምሮ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጣልቃ ገብነት በተደረገው የሽምገላ ጥረት፣ ግጭቱ ቀዝቀዝ ብሎ አካባቢው ለአጭር ጊዜ ሰላም ሰፍኖበት ነበር፡፡ በርካታ ተንታኞች ደቡብ ሱዳን በመገንጠሏ የማይመለሱ የውስጥ ጥያቄዎች አፍጥጠው ይጠብቋታል ብለው ቀድመው ተንብየው ነበር፡፡ እምብዛም ሳይቆይ በአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርና ምክትል ፕሬዚዳንት ሪክ ማቻር መካከል የተከሰተው አለመግባባት የብሔር ገጽታ ይዞ ወታደሩ ድረስ በመዝለቅ፣ አሥር ሺሕ ለሚቆጠሩ ሰዎች ሕልፈት ምክንያት ሆኗል፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችም እንዲፈናቀሉና እንዲሰደዱ አድርጓል፡፡ ከሦስት ዓመታት በፊት የተከሰተው ይኼው የእርስ በርስ ግጭት በኢትዮጵያ መንግሥት ፊታውራሪነት የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) ቀውሱን ለመፍታት መንቀሳቀሱም ይታወሳል፡፡ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ የጋራ መንግሥት ለማቋቋም የቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ተቀባይነት አግኝቶ የሁለቱም ወገኖች የፀጥታ ኃይሎች እንዲቀላቀሉና ሥልጣን ለመከፋፈል ተስማምተው ነበር፡፡ በስምምነቱ መሠረት አንዳንድ የኃላፊነት ቦታ ላይ ሽግሽግ የተደረገ ሲሆን፣ ሁለቱም መሪዎች የቀድሞ ቦታቸው ይዘው እንዲቀጥሉ ተወስኗል፡፡ ለሦስት ዓመታት ያህል ከአገር ውጭ ሆነው ሲፋለሙ የቆዩት ዶ/ር ሪክ ማቻር በቅርቡ ለመጀመርያ ጊዜ ጁባን የረገጡ ሲሆን፣ ከተፋለሟቸው ከፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ጋር ተጨባብጠው አገሪቷ የሰላም ንፋስ ነፍሶባት ነበር፡፡ በዚሁ አጭር ጊዜ ተመልሰው ወደ ጦርነት ይገባሉ በማለት የገመቱም ጥቂት ነበሩ፡፡ የአገሪቱ መንግሥትና የጦር ኃይል በሁለቱም ባለሥልጣኖች መካከል አለመግባባት ከተፈጠረ በኋላ ጎራ በመለየት ተሳትፎ አድርጓል፡፡ ወደ ብሔር ግጭት ያመራበት ምክንያትም ሁለቱ መሪዎች የተቀናቃኝ ብሔሮች ተወላጆች በመሆናቸው ነው፡፡ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር በደቡብ ሱዳን በቁጥር ቅድሚያ የሚይዘው የዲንካ ብሔር አባል ሲሆኑ፣ ተቀናቃኛቸው ዶ/ር ማቻር በበኩላቸው ከኢትዮጵያ የሚዋሰኑት የኑዌር ብሔር አባል ናቸው፡፡ የኑዌር ብሔር በኢትዮጵያ ጋምቤላ ክልልም የሚገኝ ሲሆን፣ አንዳንድ ጊዜ ኢትዮጵያ በሳልቫ ኪር ቡድን የገለልተኝነት ጥያቄ እንዲነሳበት አስተዋጽኦ አድርጓል በማለት የሚገልጹ ሪፖርቶች አሉ፡፡ በነፃነት ቀን ዋዜማ ዘቴሌግራፍ፣ ቢቢሲና ሌሎች ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ደቡብ ሱዳን የሚገኙ ምንጮችን ጠቅሰው እንደዘገቡት ከሆነ፣ ሰሞኑን በሁለቱ መሪዎች ደጋፊዎች በድንገት በዋና ከተማዋ ጁባ የተነሳው ግጭት እየተባባሰ መጥቷል፡፡ በከተማዋ በአንድ የፍተሻ ቦታ የሳልቫ ኪር ደጋፊ እንደሆኑ የተነገረላቸው ወታደሮች በኑዌር ብሔር ታጣቂዎች ላይ ከፈቱት የተባለው ተኩስ የጫረው ግጭት እነሆ ለአምስት ቀናት ዘልቋል፡፡ እንደ ሚዲያዎቹ ዘገባ ከሆነ በተከፈተው ተኩስ 272 ሰዎች ወዲያው ሕይወታቸው ሲያልፍ፣ በጁባ ከተማ አካባቢ የሚገኙ የተመድ መጠለያ ካምፖችም ለጥቃት ተጋልጠዋል፡፡ በተነሳው ጦርነት ሁለቱም መሪዎች በየፊናቸው ባወጡዋቸው መግለጫዎች ወገኖቻቸው ተኩስ እንዲያቆሙ ያሳሰቡ ቢሆንም፣ በአገሪቱ ጦርነት እንዳያገረሽ ተሰግቷል፡፡ ሐምሌ 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች በአካል ተገናኝተው ለመነጋገር ሞክረዋል ቢባልም፣ ግንኙነታቸው በስምምነት ስለመጠናቀቁ ማረጋገጫ አልተገኘም፡፡ የዶ/ር ማቻር ወታደራዊ ቃል አቀባይ የሆኑት ኮሎኔል ዊልያም ጊቲዝያዥ፣ የአለቃቸው የምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ማቻር ኦፊሴላዊ መኖሪያ ቤት ላይም ጥቃት መሰንዘሩን አስታውቀዋል፡፡ ‹‹ደቡብ ሱዳን ዳግም ወደ ጦርነት እየገባች ነው፤›› ብለዋል፡፡ የሁለቱም ወገኖች ቃል አቀባዮች ተኩስ ቀድሞ ማን ከፈተ በሚለው ላይ ጣት እየተቀሳሰሩ ይገኛሉ፡፡ በሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት እየተከሰተ ያለው ለጥቂት ወራት የጁባ ነዋሪዎች ሰላም ካገኙ በኋላ ነው፡፡ አገሪቱ ነፃነቷን ያወጀችበት አምስተኛ ዓመት ክብረ በዓል ዋዜማ ላይ መሆኑ ሌሎች ጥያቄዎች እያስነሳ ነው፡፡ የነፃነቱ ቀኑ ባለፈው ቅዳሜ ታስቦ እንዲውል የተወሰነ ቢሆንም፣ በአገሪቱ በተከሰተው የገንዘብ እጥረትና የኢኮኖሚ ውድቀት የተነሳ መሰረዙ መሆኑ ይነገራል፡፡ የጀርመን ድምፅ ሬዲዮ ዘጋቢ ከአካባቢው እንደዘገበው፣ የነፃነት ቀን በዓሉ መሰረዝ የጁባ ነዋሪዎችን እጅግ አበሳጭቷል፡፡ ሚካኤል አቲቲ የተባሉ ነዋሪ ለሬዲዮው ‹‹ለአገራችን አስፈሪ ውሳኔ ነው፤›› ብለዋል፡፡ በዓሉ በገንዘብ እጥረት ምክንያት መሰረዙ ብቻ ሳይሆን፣ የጦርነትና የኢኮኖሚ ውድቀትን በተመለከተ የሚነዛው ወሬ ለአገሪቱ መጥፎ ገጽታ እንዳለው በመግለጽ፣ ሌሎች የደቡብ ሱዳን ዜጎች በተመሳሳይ ብስጭታቸውን እየገለጹ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ደቡብ ሱዳን ከአምስት ዓመታት በፊት ከሰሜን ሱዳን ነፃነቷን የተቀዳጀችበትን ክብረ በዓል ለማክበር 450 ሺሕ ዶላር የሚጠይቅ በመሆኑ፣ አገሪቱ ይህንን ያህል ገንዘብ ለማውጣት አቅም የለኝም በማለት ነበር እንዲሰረዝ ያደረገችው፡፡ አንዳንዶች እንደሚገምቱት ደግሞ፣ በወታደሮች መካከል የተከሰተው የተኩስ ልውውጥም ከዚሁ በዓል መሰረዝ ጋር ሊያያዝ ይችላል፡፡ ሁለቱም ወገኖች በድጋሚ ተኩስ እንዲቆም ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፣ ሁለቱም ለጋዜጠኞች በሰጡዋቸው ቃለ ምልልሶች በአገሪቱ ጦርነት ተመልሶ እንዳይነሳ ሥጋት እንዳደረባቸው አመልክተዋል፡፡ የተመድ ዋና ጸሐፊ ባን ኪ ሙን ሁኔታው እጅግ ያሳሰባቸው መሆኑን፣ የፀጥታው ምክር ቤት በደቡብ ሱዳን ላይ የጦር መሣሪያ ዝውውር ማዕቀብ በአስቸኳይ እንዲጥል አሳስበዋል፡፡ እንዲሁም በአካባቢው የተፈለገው ሰላም እንዳይመጣ እንቅፋት ሆነዋል ያሉዋቸውን የሁለቱም ወገኖች መሪዎች ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ እንዲረቀቅ ጠይቀዋል፡፡ ባን ኪ ሙን በንግግራቸው፣ ‹‹የተቀሰቀሰው ጦርነት እጅግ አስደንጋጭ ነው፡፡ ወደኋላ የመመለስ አሳዛኝ አዝማሚያ አለው፡፡ የአገሪቱን ያለፈውን ስቃይ ያባብሳል፡፡ ለሰላም ያለው ቁርጠኝነትም እስከዚህም መሆኑን ያመለክታል፤›› ብለዋል፡፡ ቀደም ሲል በአሜሪካ መንግሥት ሐሳብ አቅራቢነት በመሪዎቹ ላይ ማዕቀብ ለመጣል የውሳኔ ሐሳብ ለተመድ ቀርቦ ነበር፡፡ ጉዳዩ መጀመርያ በአፍሪካ ኅብረት፣ በኢጋድና በኢትዮጵያ እንዲያልቅ በሚል ተግባራዊ ሳይሆን ቀርቷል፡፡ ኢትዮጵያም የደቡብ ሱዳንን ቀውስ ለመፍታት በሙሉ አቅም መንቀሳቀሷ አይዘነጋም፡፡ የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ሥዩም መስፍን አስታራቂ ቡድኑን በልዩ መልዕክተኛነት እንዲመሩ መደረጋቸው ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -