Saturday, February 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኤሌክትሪክ ኃይል ዜድቲኢ የገነባውን የ33 ሚሊዮን ዶላር የኤሌክትሪክ ኦፕቲካል መስመር ፕሮጀክት ተረከበ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

– የሁዋዌ ድርሻ በነሐሴ ወር እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል

ከ1,200 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት በሚሸፍኑ በ37 ዋና ዋና መገናኛ ጣቢያዎች ተከፋፍሎ ላለፉት 17 ወራት በቻይናው ዜድቲኢ ኩባንያ በኩል (የነበረው ድርሻን መሠረት በማድረግ) ሲዘረጋ የቆየውና ‹‹ኦፕቲካል ግራውንድ ዋየር›› የተሰኘውን ፕሮጀክት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ተረከበ፡፡ ‹‹የኦፕቲካል ግራውንድ ዋየር›› በተባለው ፕሮጀክት የኤሌክትሪክ ኃይል ማሠራጫ መስመሮችን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ የግንኙነት መረጃዎችን ለማስተላለፍ፣ እንዲሁም እንደ መብረቅ ያሉ አደጋዎችን ለመከላከል የሚያስችል የኦፕቲካል ፋይበር መስመሮች የተዘረጉት በ1,234 ኪሎ ሜትር ርዝመት ነው፡፡ ዜድቲኢ የተሳተፈበት የፕሮጀክት ክፍል በአንድ ዓመት ከአምስት ወር ተኩል ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት መዘጋጀቱ ታውቋል፡፡ በመሆኑም ዜድቲኢና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኃላፊዎች ርክክብ ያደረጉበት ሥነ ሥርዓት ማክሰኞ ሐምሌ 5 ቀን 2008 ዓ.ም. አከናውነዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አዜብ አስናቀ እንደገለጹት፣ ኦፕቲካል ግራውንድ ዋየር የተሰኘው ፕሮጀክት ከዚህ ቀደም የነበሩትን መስመሮች በፋይበር ኦፕቲክ በታገዙ መስመሮች ለመተካት እየተገነባ የሚገኝ የብሔራዊ የኃይል መሠረተ ልማት ፕሮጀክት አካል ነው፡፡ በመሆኑም እስካሁን በአገሪቱ ሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ ለተዘረጋው 1,234 ኪሎ ሜትር መስመር 33 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ሲደረግ፣ የፋይናንሱ ምንጭም የቻይናው ኢንዱስትሪያል ኤንድ ኮሜርሺያል ባንክ (አይሲቢሲ) መሆኑን ኢንጂነር አዜብ ጠቁመዋል፡፡ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የብሔራዊ የኃይል ቋት መሠረተ ልማት ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ሀብታሙ ውቤ ለሪፖርተር እንዳብራሩት፣ አዲሱ የኦፕቲካል ግራውንድ ዋየር ፕሮጀክት ተግባር የኃይል ማከፋፈያና ማሠራጫ ጣቢያዎችን ከማዕከል ሆኖ ለመቆጣጠር የሚያስችሉ የኮሙዩኒኬሽን መስመሮች ያረጁና የሚጠቀሙት ባንድዊድዝም በጣም አነስተኛ በመሆኑ፣ በአዲስ ቴክኖሎጂ መተካት አስፈልጓል፡፡ በአዲሱ ቴክኖሎጂ አማካይነት ከማዕከል ለመቆጣጠር የሚያስችል አስተማማኝ መረጃ በማግኘት ያልተቋረጠ የኃይል ማከፋፈልና ማሠራጨት ሥራ ለማከናወን ይረዳል፡፡ እንደ አስተባባሪው ገለጻ፣ ከፋይበር መስመሮች በተጨማሪ ኦፕቲካል ግራውንድ ዋየር የተሰኘውን ቴክኖሎጂ ከምድር በላይ መዘርጋቱም መስመሮቹ ምንም ዓይነት የመቆራረጥ ሥጋት እንዳያጋጥማቸው፣ ደኅንነታቸውን ለማስጠበቅ ማስቻሉ ትልቅ ጠቀሜታ እያስገኘ ነው፡፡ ከኃይል ማሠራጫና ማከፋፈያ መስመሮች መሀል አብሮ የሚዘረጋው ኦፕቲካል ፋይበር፣ ኢትዮ ቴሌኮም እንዲጠቀምበት እያስቻለ እንደሚገኝም አቶ ሀብታሙ አስረድተዋል፡፡ በዚህም መሠረት በአሁኑ ወቅት ከአምስት ሺሕ ኪሎ ሜትር ያላነሰ የፋይበር ኦፕቲክ መስመር ላይ ኢትዮ ቴሌኮም ተጠቃሚ እየሆነ እንደሚገኝ፣ ከዚህ በፊት በፋይበር መስመሮች ላይ ይደርስበት የነበረውን መቆራረጥ በማስቀረትም ትልቅ ጥቅም እያስገኘለት በመሆኑ፣ ወደፊት ስለሚኖረው አጠቃቀም በሁለቱ ተቋማት መካከል ውይይቶች በመካሄድ ላይ እንደሚገኙ አቶ ሀብታሙ ጠቅሰዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከማንም ወገን ንክኪ ነፃ የሆነ የፋይበር መስመር ከዋናው የኤሌክትሪክ ቋት ለኢትዮ ቴሌኮም ለማቅረብ የሚችልበት አቅም እንደፈጠረ አስታውቀዋል፡፡ በርካታ የውጭ ኃይል አመንጪ ተቋማት በዚህ መልክ የሚዘረጓቸውን የፋይበር ግራውንድ መስመሮች በማከራየት ትልቅ ገቢ እንደሚያገኙ ታውቋል፡፡ በዜድቲኢ ወገን ፕሮጀክቱን የመሩት አቶ ዓባይ ተስፋዬ ለሪፖርተር እንዳብራሩት፣ በመሠረታዊነት ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኃይል መስመሮችን ሥርጭት የተመለከቱ የድምፅና የዳታ መረጃዎችን ለመለዋወጥ ከማስቻል በተጨማሪ፣ በኤሌክትሪክ ማሠራጫ መስመሮች ላይ የመብረቅና ሌሎች አደጋዎች እንዳይደርሱ ለመከላከል የሚያስችሉ የፋይበር ኦፕቲክ መስመሮች ተዘርግተዋል፡፡ በመሆኑም በመላ አገሪቱ 37 መገናኛ መስመሮች የተዘረጉበት የዜድቲኢ ፕሮጀክት አካል በአዲስ አበባ 14 መስመሮችን አካቷል ያሉት አቶ ዓባይ፣ ከአዳማ እስከ መተሐራ፣ ከድሬዳዋ ሐረር እስከ ጂግጂጋ፣ ከባህር ዳር እስከ አላማጣ፣ ከመቀሌ እስከ አሸጎዳ፣ ከመቀሌ እስከ አዲግራት፣ ከመቀሌ እስከ ዓደዋ ባለው አካባቢ የሚገናኙ መስመሮች ተዘርግተዋል፡፡ በተጨማሪም በአዲስ አበባ ቃሊቲ የሱ፣ ሰሜን አዲስ አበባ በተለይም ገፈርሳ አካባቢ፣ እንዲሁም መካከለኛው አዲስ አበባ ቃሊቲ ያለውን መስመር አካቶ በጠቅላላው ከ1,200 ኪሎ ሜትር በላይ የኦፕቲካል ግራውንድ ዋየር መስመር ዝርጋታ ተከናውኗል፡፡ ዜድቲኢ የተሳተፈበት ይህ አገራዊ ፕሮጀክት ሌላኛውን የቻይና ኩባንያ ሁዋዌንም ያካተተ ሲሆን፣ ሁዋዌ ከዜድቲኢ በ200 ኪሎ ሜትር ብልጫ ያለው ማለትም ከ1,234 ኪሎ ሜትር መስመር ላይ 200 ኪሎ ሜትር ጭማሪ ያለው ሥራ ለማከናወን ከአንድ ዓመት ከአምስት ወር ተኩል በፊት መረከቡን አቶ ሀብታሙ አስታውሰዋል፡፡ ይህ ፕሮጀክት መቼ እንደሚጠናቀቅ ይፋ አልተደረገም፡፡ ሆኖም ከብድር ማመቻቸትና ከሌሎች ታሳቢ ሁኔታዎች አኳያ የየፕሮጀክቶቹ ስምምነቶች እንደሚታዩ አቶ ሀብታሙ አስረድተዋል፡፡ ከሁዋዌ ኩባንያ የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው፣ ኩባንያው 1,554 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውን የደቡብና የምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢን ፕሮጀክት በመተግበር ላይ ነው፡፡ በነሐሴ ወር አጠናቆ ለማስረከብ መዘጋጀቱን ለሪፖርተር አስታውቋል፡፡ ዜድቲኢ በገባው ውል መሠረት በወቅቱ ማስረከቡን አቶ ሀብታሙ ጠቅሰው፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች የተሳተፉበት የዜድቲኢ ፕሮጀክት የኤሌክትሪክ ኃይል ሥርጭት ሳይቋረጥ የተዘረጋ ነው ብለዋል፡፡ ሥራውን በሚያከናውኑ ሠራተኞች ላይ አደጋ ሊደርስ እንደሚችል ከመነሻው ሥጋት ፈጥሮ እንደነበር፣ ሆኖም ምንም ዓይነት አደጋ ሳያስከትል ሊጠናቀቅ መቻሉ ትልቅ ዕፎይታን ያስገኘ ውጤት መሆኑን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች