Wednesday, February 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከ2.5 ቢሊዮን ብር በላይ ግዙፍ ወጪ የነዳጅ ማከማቻ ለመገንባት ዝግጅት እየተደረገ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ከ2.5 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ይጠይቃል የተባለ ግዙፍ አዲስ ዘመናዊ የነዳጅ ማከማቻ በዱከም ከተማ ለመገንባት ዝግጅት እያደረገ ነው፡፡ በአዋሽ ሰባት ያስገነባው የነዳጅ ማከማቻ ቢጠናቀቅም፣ አገልግሎቱን ለመጀመር የባቡር መስመር ዝርጋታ እየተጠበቀ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ከኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው፣ ከ240 ሚሊዮን ሊትር በላይ ነዳጅ እንዲይዝ ታስቦ የሚገነባው የዱከም ግዙፍ የነዳጅ ማከማቻ ዲዛይን ሥራ፣ ዓለም አቀፍ ጨረታ ወጥቶ ለኩባንያዎች የጨረታ ሰነዱ በመሸጥ ላይ ነው፡፡ 

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ኃይለ ማርያም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ግዙፉ የነዳጅ ማከማቻ የዲዛይን ሥራ ከተጠናቀቀ በኋላ በሦስት ዓመታት ውስጥ ገንብቶ ለመጨረስ ታቅዷል፡፡ የነዳጅ ማከማቻው የዲዛይን ጨረታ ከሦስት ሳምንት በኋላ ተዘግቶ አሸናፊ ከሚሆነው ኩባንያ ጋር ስምምነት ይፈጸማል ተብሏል፡፡

የነዳጅ ማከማቻ ዲዛይኑን ለመሥራት አሸናፊ የሚሆነው ኩባንያ በስድስት ወራት ውስጥ ሥራውን አጠናቆ ወደ ግንባታ ጨረታ ይገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ለዚህም ዓለም አቀፍ ጨረታ ይወጣል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ለዚህ ግዙፍ ግንባታ የሚሆን አሥር ሔክታር መሬት በዱከም መረከቡን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የዱከሙ የነዳጅ ማከማቻ የሚገነባው በትንሹ ከ240 ሚሊዮን ሊትር በላይ ነዳጅ ለመያዝ በሚያስችል ደረጃ ዲዛይኑ የሚሠራ ሲሆን፣ ነዳጅ የመያዝ አቅሙም ከዚህም በላይ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ ይህ የነዳጅ ማከማቻ በዘመናዊ መንገድ የሚገነባ መሆኑንና ከአዋሽ ሰባት ማከማቻ ጋር በመሆን የሚፈጥረው አቅም፣ አገሪቱ በተሽከርካሪዎች ከጂቡቲ የምታመላልሰውን ነዳጅ ሙሉ በሙሉ በባቡር ማጓጓዝ ያስችላል ተብሏል፡፡ የነዳጅ ሥርጭቱም ከጂቡቲ መሆኑ ቀርቶ ከሁለቱ ማከማቻዎች እንዲሆን እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡ አዲሱ ነዳጅ ማከማቻ ለአገሪቱ ለመጀመርያ ጊዜ የአውሮፕላን ነዳጅ በአገር ውስጥ የመያዝ ዕድል የሚሰጥ እንደሚሆን ተጠቁሟል፡፡

በዕቅዱ መሠረት ከዱከም ከሚገነቡት ከ15 በላይ የነዳጅ ታንከሮች ውስጥ ከ60 በመቶው በላይ ለነጭ ናፍጣ ማከማቻ የሚውሉ እንደሆነ፣ ለነጭ ናፍጣ ማከማቻ የሚውሉ ታንከሮች ከ160 ሚሊዮን ሊትር የመያዝ አቅም እንደሚኖራቸው፣ ቀሪዎቹ የአውሮፕላን ነዳጅ፣ ቤንዚንና ኬሮሲን እንደሚያከማቹ ታውቋል፡፡ 

የዱከም ግንባታ እስኪያልቅ ድረስም ግንባታው የተጠናቀቀው የአዋሽ ሰባት ነዳጅ ማከማቻ፣ በባቡር የሚመጣውን ነዳጅ በአገር ውስጥ እንዲከፋፈል ማድረግ ይጀምራል ተብሏል፡፡ እያንዳንዳቸው አምስት ሚሊዮን ሊትር የመያዝ አቅም ያላቸው ስድስት ጋኖች ያሉት ሲሆን፣ ይህም ዋነኛ ዓላማውም በባቡር የሚመጣውን ነዳጅ በመቀበል የነዳጅ ሥርጭቱን በአገር ውስጥ ለማድረግ ነው፡፡ ከዱከም አንፃር የአዋሽ ሰባቱ አቅሙ አነስተኛ ቢሆንም፣ ወደ ሥራ ሲገባ ግን በተሽከርካሪ ከሚመላለሰው ነዳጅ 40 በመቶውን በባቡር በማስመጣት ማከማቸት እንደሚችል ተገልጿል፡፡ ይህም በቀጥታ ከጂቡቲ በተሽከርካሪዎች ይገባ የነበረውን ነዳጅ በዚህ ማከማቻ በመያዝ 40 በመቶ የአገሪቱ የነዳጅ ሥርጭት ከዚሁ ማከማቻ ይሆናል ማለት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በቀን 380 ቦቴዎች በየቀኑ ነዳጅ የሚያመላልሱ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ታደሰ፣ የአዋሽ ሰባት ማከማቻ በየቀኑ ከጂቡቲ ነዳጅ ያመላልሱ የነበሩ ከ140 ያላነሱ ተሽከርካሪዎችን ያስቀራል፡፡ 

ከ170 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ወጥቶበታል የተባለው የአዋሽ ሰባት የነዳጅ ማከማቻ አገልግሎቱን ለመጀመር፣ ከኢትዮ ጂቡቲ የምድር ባቡር ዋና መስመር ጋር መገናኘት ይኖርበታል፡፡ ይህ ካልሆነ በተሽከርካሪ አምጥቶ ማከማቸትና ማሠራጨቱ አዋጭ አለመሆኑም ተገልጿል፡፡ 

የኢትዮ ጂቡቲ የምድር ባቡር ስታንዳርድ ጌጅ አክሲዮን ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጥላሁን ሳርካ (ኢንጂነር) እንደገለጹት ደግሞ፣ ወደ አዋሽ ሰባት ነዳጅ ማከማቻ የሚገባው የባቡር መስመር በቅርቡ ይጀመራል የሚል እምነት አለ፡፡ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ወደ አዋሽ ሰባት ዲፖ የሚገባውን የባቡር

መስመር ለመዘርጋት እየተዘጋጀ መሆኑን፣ ለነዳጅ ማጓጓዣ የሚሆን 110 ተጎታች ባቡሮች መገዛታቸውን ገልጸዋል፡፡
እንደ አቶ ታደሰ ገለጻ፣ ከባቡር ጋር መተሳሰር ከጊዜ በተጨማሪ ወደ ጂቡቲ ለሚደረገው ጉዞ የሚወጣውን ነዳጅ ጭምር እንዲቆጠብ ያደርጋል፡፡ ከሁሉም በላይ ባቡሩ በአጭር ጊዜ ነዳጅ ወደ ማከማቻ ማድረሱ በነዳጅ ሥርጭት ላይ አዎንታዊ የሆነ ተፅዕኖ ያሳድራል ብለዋል፡፡ አንድ የባቡር ተጎታች ብቻ ሰባ የነዳጅ ጫን ተሽከርካሪዎች ያመጡ የነበረውን ነዳጅ የሚተካ መሆኑንም ለአብነት ጠቁመዋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች