Wednesday, February 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የግል አልሚዎችን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ባለቤት የሚያደርግ የ1,980 ሜጋ ዋት ጨረታ ወጣ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

– የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በድምሩ 3,977 ሜጋ ዋት ለማመንጨት በጨረታ ሒደት ላይ ነው

– ከተለያዩ የውጭ ኩባንያዎች ጋር ቀደም ሲል የተፈረሙ የመግባቢያ ስምምነቶች ታግደዋል

አቅም ያላቸው የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎችን በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ጣቢያ ባለቤት የሚያደርጉ 1,980 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያላቸው ሁለት ፕሮጀክቶች ጨረታ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ማውጣቱ ታወቀ፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከላይ የተገለጸውን ጨምሮ በድምሩ 3,977 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚያስችሉ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ጨረታ በማውጣት በግምገማ ሒደት ውስጥ እንደሚገኝ፣ ከተቋሙ ድረ ገጽ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን በኢትዮጵያ ብቸኛው የኤሌክትሪክ ኃይል ገንቢ፣ አመንጪ፣ አስተላላፊና በሽያጭ ለኅብረተሰቡ አቅራቢ ሆኖ ከምሥረታው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የቆየ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ኮርፖሬሽኑ ለሁለት ከተከፈለ በኋላ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከሽያጭ በስተቀር አመንጪና አስተላላፊ ሆኗል፡፡ በ2005 ዓ.ም. በወጣው የኢትዮጵያ ኢነርጂ ባለሥልጣን አዋጅ ላይ፣ የግል ባለሀብቶች በግዙፍ የኃይል ማመንጨት ሥራ እንዲሰማሩና ኃይል ለመንግሥት ብቻ እንዲሸጡ የሚያስችል ድንጋጌ ተካቷል፡፡ ይህንን መሠረት በማድረግም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከአዲስ አበባ 750 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው የጋምቤላ ብሔራዊ ክልል ውስጥ የሚገኘውን ታምስ ወንዝ ለማልማት የቀረፀውን 1,700 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም የሚኖረውን የታምስ ኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ፕሮጀክት፣ አቅም ያላቸው የግል ባለሀብቶች እንዲያለሙት ግልጽ ጨረታ አውጥቷል፡፡ በዚህ ግልጽ ጨረታ መሳተፍ የሚፈልጉ የገንዘብ አቅም እንዲሁም በኃይል ማመንጨት ልምድ ያላቸው ኩባንያዎች ፍላጐታቸውን እ.ኤ.አ. እስካለፈው ጁላይ 1 ቀን 2016 እንዲያቀርቡ ጠይቋል፡፡ ተቋሙ ያቀረበው የፍላጐት ማሳወቂያ ሲሆን፣ ፍላጐታቸውን ከገለጹ ኩባንያዎች መካከል አንዱን ለመምረጥ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ውስን ጨረታ ውስጥ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ሌላው በግል አልሚዎች ተገንብቶ፣ ኃይል በማመንጨትና ጣቢያውን በባለቤትነት በማስተዳደር የሚያመነጨውን ኃይል ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በሽያጭ እንዲቀርብ የፍላጐት ማሳወቂያ ጨረታ የወጣበት 280 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው የጨሞጋ ይዳ ኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ነው፡፡ የዚህ ፕሮጀክት ግንባታ የፍላጐት ማሳወቂያ ጊዜ ተጠናቆ በውስን ጨረታ ሒደት ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል በተጨማሪ ሁለት የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችም በግል አልሚዎች በባለቤትነት እንዲለሙና የሚገኘው ኃይል በሽያጭ እንዲቀርብ የወጣው የፍላጐት ማሳወቂያ ጊዜ ባለፈው ሳምንት ተጠናቆ፣ በግምገማ ሒደት ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶች በትግራይ ክልል የሁመራና የመቀሌ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ሲሆኑ፣ እያንዳንዳቸው 100 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም እንዳላቸው ተጠቁሟል፡፡ ሌሎች ቀሪ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች በመንግሥት ባለቤትነት የሚያዙ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያወጣው የፍላጐት ማሳወቂያ ጨረታ እንደሚያመለክተው ፍላጐት ያላቸው ኩባንያዎች የፕሮጀክቶቹን ወጪ የመሸፈን የፋይናንስ አቅም ወይም ብድር የማመቻቸት ኃላፊነት የሚጣልባቸው ሲሆን፣ ፕሮጀክቶቹ የሚከናወኑት በምሕንድስና ግዥና ግንባታ (ኢፒሲ) ውል መሠረት መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በዚህ መንገድ እንዲገነቡ የተፈለጉትና በጨረታ ሒደት ላይ የሚገኙት ፕሮጀክቶች 97 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው ብርብር አንድና 476 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው ብርብር ሁለት ጥቅል ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡ ሌሎቹ በተመሳሳይ መሥፈርት እንዲገነቡ የሚፈለጉት የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች 424 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው የላይኛው ዳቡስ፣ 250 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም የሚኖረው ገናሌ ዳዋ ስድስት ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ ሦስት የንፋስ ኃይል ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡ እነርሱም 300 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም የሚኖረው አይሻ የንፋስ ኃይል፣ 100 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም የሚኖረው ደብረ ብርሃን የንፋስ ኃይልና 150 ሜጋ ዋት አቅም የሚኖረው አዳማ ሦስት የንፋስ ኃይል ማመንጫዎች ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግንባታዎችን ማለትም ግልገል ጊቤ ሁለት፣ ጊቤ ሦስትና ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን የያዘው የጣሊያኑ ኩባንያ ሳሊኒ ባለፈው ሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ 2,200 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም የሚኖረውን ኰይሻ የኃይል ማመንጫ ግድብ ለመገንባት፣ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር መስማማቱን የሚገልጽ መግለጫ አውጥቷል፡፡ ኩባንያው ለግንባታው የሚያስፈልገውን 2.8 ቢሊዮን ዶላር ከጣሊያን የብድር ኤጀንሲ እንደሚያቀርብም በመግለጫው ተገልጿል፡፡ ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው በመንግሥት ባለቤትነት በኢፒሲ ውል እንዲገነቡ ለቀረቡት ፕሮጀክቶች ሊመረጡ የሚችሉ ኩባንያዎች፣ በተለይም በፕሮጀክቶቹ ውስጥ የፀሐይና የንፋስ ኃይል ማመንጫዎች ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቁ በመሆናቸው የሚያቀርቡት ብድርም በዚያው ልክ ከፍተኛ እንደሚሆን ይገመታል፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በኢፒሲ ውል ለማስገንባት ላቀዳቸው ፕሮጀክቶች፣ በኢፒሲ ውል አስተዳደርና የግንባታ ቁጥጥር ልምድ ያለው አማካሪ ኩባንያ ለመቅጠርም በተመሳሳይ ግልጽ ጨረታ አውጥቷል፡፡ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የቀረፁት ፓወር አፍሪካ ኢኒሼቲቭ ትኩረት ካደረገባቸው አገሮች ዋነኛዋ ኢትዮጵያ ስትሆን፣ ይኼው የእርሳቸው ኢንሼቲቭም ከዓለም ባንክ፣ ከአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን፣ ከኖርዌይ፣ ከስዊዲን፣ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) እና ከእንግሊዝ ዓለም አቀፍ ትብብር ጋር በመሆን የኢትዮጵያ መንግሥት በኃይል ማመንጫ ግንባታዎች የግል ባለሀብቶችን በስፋት እንዲያሳትፍ የሚረዱ የሕግና ተቋማዊ አቅም ለመፍጠር እየተባበሩ እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ አዜብ አስናቀ በ2008 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት በፓርላማ ግምገማ ላይ በሰጡት አስተያየት፣ በገንዘብ አቅርቦት ችግር የተነሳ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለመገንባት ከታቀደው 17 ሺሕ ሜጋ ዋት የኃይል አቅርቦት ውስጥ 50 በመቶው በግል ባለሀብቶች ተሳትፎ እንዲከናወን መንግሥት መወሰኑን ገልጸው ነበር፡፡ የፕሬዚዳንት ኦባማ ፓወር አፍሪካ ኢኒሼቲቭም ይህንኑ ያሳሰበ መሆኑና ወደዚህ ምዕራፍ ለመሸጋገርም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የግል አልሚዎችን ማሳተፍ እንዲቻለው፣ ግልጽና አወዳዳሪ የጨረታ ሥርዓት እንዲሁም አቅም ያለው ተቆጣጣሪና ወጪን መሠረት ያደረገ የኤሌክትሪክ ሽያጭ መቀበያ ታሪፍ የማስቀመጥ አቅም እንዲኖረው በመተባበር ላይ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለተገለጹት ፕሮጀክቶች ያወጣው ጨረታም በዚህ መሠረት የተቃኘ ማሳያ እንደሆነ መገመት ይቻላል፡፡ በተለይም ከዚህ ቀደም ተቋሙ ከተለያዩ ኩባንያዎች ጋር የኃይል ማመንጫ ግንባታዎች ለማከናወን የገባቸው የመግባቢያ ስምምነቶች መታገዳቸውን፣ የተገለጹት የፍላጐት ማሳወቂያ ጨረታዎች ብሎም የግምገማ ሒደቶች በግልጽ የጨረታ ሒደት የሚከናወኑ እንደሆኑ በድረ ገጹ ባሰፈረው መግለጫ አረጋግጧል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች