Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ በግል ትምህርት ቤቶች ላይ ውሳኔና ማስጠንቀቂያ ሰጠ

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ በግል ትምህርት ቤቶች ላይ ውሳኔና ማስጠንቀቂያ ሰጠ

ቀን:

– ሁሉም የግል ትምህርት ቤቶች ፋይል ተከፍቶባቸዋል

– በ2009 ዓ.ም. አጋዥ መጻሕፍት እንዳይሸጡ ክልከላ ተጣለባቸው

– ክፍያ በቢሮው መመርያ መሠረት እንዲያስተካክሉ ተነገራቸው

– ክፍያ ሲጨምር የማይቃወሙት ወላጆች ባለአክሲዮኖች ናቸው ተባለ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ በከተማው የሚገኙ የግል ትምህርት ተቋማት ዕውቅና፣ ፈቃድ አሰጣጥና ዕድሳት፣ አደረጃጀቶች፣ ሥርዓተ ትምህርቶች፣ የተማሪዎች የምዘና ሥርዓት አፈጻጸም፣ የግብዓት አቅርቦት፣ አገልግሎት አሰጣጥ፣ የዝውውር ፖሊሲ ትግበራ፣ የመረጃ አያያዝና ሌሎች ተግባራትን በሚመለከት የመስክ ጉብኝትና ምርመራ አድርጐ ውሳኔና ማስጠንቀቂያ ሰጠ፡፡ ቢሮው ከአጠቃላይ የትምህርት ጥራት አግባብነት ሬጉላቶሪ ኤጀንሲና ከንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን ጋር ሐምሌ 4 ቀን 2008 ዓ.ም. በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው፣ በአዲስ አበባ ከተማ ከ1,500 በላይ የግል ትምህርት ቤቶች አሉ፡፡ በተለይ አጠቃላይ የትምህርት ጥራትና አግባብነት ሬጉላቶሪ ኤጀንሲ በግል ትምህርት ቤቶች ላይ የሚስተዋሉ ፈርጀ ብዙ ችግሮች በመኖራቸው፣ በአካልና በተለያዩ መንገዶች የደረሱትን የቅሬታ አቤቱታዎች ተከትሎ በተመረጡና በተለይ በርካታ ወላጆች አቤቱታ ባቀረቡባቸው የተወሰኑ ትምህርት ቤቶች ላይ በአካል በመገኘት የኢንስፔክሽን ሥራ መሥራቱን ገልጿል፡፡ ኤጀንሲው የግል ትምህርት ተቋማት የዕውቅና ፈቃድና ዕድሳት አተገባበርን፣ የመምህራን ፕሮፋይልን፣ በትምህርት ቤቶቹ የሚዘጋጁ አጋዥ መጻሕፍት አጠቃቀምን፣ የአፍ መፍቻ ቋንቋ አጠቃቀምን፣ የተማሪዎች የምዘና ሥርዓት አፈጻጸምን፣ የግብዓት አቅርቦትን፣ የትምህርት ተቋማት አመራሮች ከወላጆች ጋር ያላቸውን ተሳትፎ፣ መምህራን ከተማሪዎች፣ ከወላጆችና ከባለሀብቶች ጋር ያላቸው የሥራ ግንኙነትን፣ የትምህርት ዝውውር ፖሊሲ ትግበራንና የተቋማቱ የመረጃ አያያዝና አደረጃጀትን በሚመለከት ምርመራ ማካሄዱን አስታውቋል፡፡ ሁሉም የትምህርት ተቋማት በተጠቀሱት ነጥቦች ላይ ችግር ያለባቸው ሆነው ቢገኙም በተለይ ጊብሰን ዩዝ አካዳሚ ትምህርት ቤት፣ ፊውቸር ታለንት ትምህርት ቤት፣ ኢትዮ ፓረንትና ስኩል ኦፍ ቱሞሮ ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ ችግር ተገኝቶባቸው ዕርምጃ የተወሰደባቸውና ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው መሆኑን ኤጀንሲው አስታውቋል፡፡ ኤጀንሲው ወላጆችም ሆኑ ትምህርት ቤቱ ትኩረት እንዲያደርጉባቸው ውሳኔና ማስጠንቀቂያ ከሰጠባቸው ትምህርት ቤቶች መካከል፣ ጊብሰን ዩዝ አካዳሚ ትምህርት ቤት አንዱ ነው፡፡ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ከ5ኛ እስከ 12ኛ ክፍል የሚያስተምር ቢሆንም፣ ከ5ኛ እስከ 8ኛ ክፍል የሚያስተምረው ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ ያለፈቃድና ዕውቅና መሆኑን ገልጿል፡፡ የወረዳውና የክፍለ ከተማው ትምህርት ጽሕፈት ቤቶች ለምን ዝም እንዳሉና ተጠያቂ እንደሚሆኑ ኤጀንሲው አስረድቷል፡፡ ትምህርት ቤቱ ግን እስከ ሐምሌ 15 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ ዕውቅና፣ ፈቃድና ዕድሳት እንዲወስድ አሳስቦ ከተባለው ቀን ቢያልፍ ዕርምጃ የሚወስድ መሆኑን ገልጿል፡፡ ጊብሰን ዩዝ አካዳሚ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ዕውቅና የተሰጠው ዝቅተኛውን ደረጃ ሳያሟላ መሆኑን የጠቆመው ኤጀንሲው፣ የ9ኛ እና የ10ኛ ክፍል ተማሪዎችን ብቻ አስፈላጊውን ግብዓት አሟልቶ እንዲቀጥል አሳስቦ፣ የ11ኛ እና 12ኛ ክፍል የመሰናዶ ተማሪዎችን የማስተማር ብቃት ስለሌለው መታገዱን አስታውቋል፡፡ በተመሳሳይ ስኩል ኦፍ ቱሞሮ ትምህርት ቤትም በጉለሌ ክፍለ ከተማ 11ኛ እና 12ኛ ክፍል የሚያስተምረው ያለዕውቅና መሆኑን ጠቁሞ፣ ድርጊቱ ሕገወጥ በመሆኑ እንዳያስተምር ማገዱን ገልጿል፡፡ ሲያስተምር ቢገኝ ሕጋዊ ዕርምጃ እንደሚወስድም አክሏል፡፡ ፊውቸር ታለንት ትምህርት ቤት ‹‹ኢንተርናሽናል›› የሚል ስያሜ መስጠቱን ተከትሎ ስያሜውን እንዲያስተካክል የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ማስጠንቀቂያ መስጠቱን ያስታወሰው ኤጀንሲው፣ ለ2009 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን ተማሪዎችን ከመመዝገቡ በፊት ‹‹ኢንተርናሽናል›› የሚለውን ስያሜ ማንሳት እንዳለበት ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት ማንሳቱን አሳውቋል፡፡ የከተማ አስተዳደሩን ሥርዓተ ትምህርት እየተጠቀሙና በይዘት ኢንተርናሽናል ያልሆኑ ትምህርት ቤቶች በሙሉ እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ ‹‹ኢንተርናሽናል›› የሚለውን ስያሜ እንዲያነሱ አሳስቧል፡፡ አጋዥ መጻሕፍትን በሚመለከት በተለይ የተጠቀሱት ትምህርት ቤቶች እስከ 1,600 ብር አስገድደው እንደሚሸጡ የገለጸው ኤጀንሲው፣ የሚያዘጋጁዋቸውን መጻሕፍት ከ2009 ዓ.ም. ጀምሮ እንዳይሸጡ መወሰኑን ገልጾ፣ ትምህርት ቢሮው ያዘጋጃቸውን መጻሕፍት ብቻ በዋጋቸው እንዲሸጡ አሳስቧል፡፡ አጋዥ መጻሕፍት በማለት የሚያዘጋጁትን በላይብረሪ ማስቀመጥ ወይም በነፃ መስጠት የሚችሉ መሆኑንም አክሏል፡፡ ከክፍል ክፍል ዝውውርን በሚመለከት የአገሪቱን የትምህርት ፖሊሲ የተከተለና ትምህርት ቢሮው በሚያወጣው ማለፊያ ነጥብ ብቻ እንዲጠቀሙም ውሳኔ አሳልፏል፡፡ ክፍያን በሚመለከት ተገቢ ያልሆነና የወላጆችን ገቢና የኑሮ ሁኔታ ያላገናዘበ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ክፍያ መጠየቁ (በተለይ አራቱ ትምህርት ቤቶች) ተገቢ አለመሆኑን የገለጸው ኤጀንሲ፣ በ2009 ዓ.ም. የትምህርት አገልግሎትና የመመዝገቢያ ክፍያ ትምህርት ቢሮው ባወጣው መመርያ መሠረት ብቻ እንዲሆን፣ ከወላጆች ጋር ውይይት አድርጐ በተደረሰበት ስምምነት መሠረት መወሰኑን አስታውቋል፡፡ በተለይ ምዝገባን በሚመለከት ወላጆች ልጆቻቸውን ከማስመዝገባቸው በፊት የሚያስመዘግቡበት የትምህርት ተቋም ዕውቅና ያለው መሆኑን፣ ለመጪው የትምህርት ዘመን የታደሰ መሆኑን ካረጋገጡ በኋላ እንዲሆን ኤጀንሲው አሳስቧል፡፡ የኢትዮጵያ የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መርከቡ ዘለቀ በበኩላቸው እንደገለጹት፣ የግል ትምህርት ተቋማት መጻሕፍት አሳትመው የመሸጥ ፈቃድ ሳይኖራቸው፣ ‹‹አጋዥ መጻሕፍት›› በማለት እስከ 1,600 ብር ይሸጣሉ፡፡ ይኼ ደግሞ ያለ ንግድ ፈቃድ መነገድ ስለሆነ ወንጀል ነው፡፡ የሕጋዊ ነጋዴዎች የንግድ ውድድርን ማዳከምና ሸማቹ ወይም አገልግሎት ፈላጊውን ጉዳት ላይ መጣል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የትምህርት ተቋማቱ የራሳቸው ተማሪ ከክፍል ክፍል ስለተዘዋወረ ለምዝገባ ተብሎ ከ1,000 ብር በላይ እንዲከፍል እንደሚገደድ የገለጹት አቶ መርከቡ፣ ያለምንም ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ይኼንን ድርጊት መፈጸም ከሕግ አግባብ ውጪ መሆኑንና እንደሚያስጠይቅም አስረድተዋል፡፡ ሁሉም የግል ትምህርት ተቋማት የሚጠይቁት የምዝገባ ክፍያ ተቀራራቢና ከፍተኛ በመሆኑ፣ ወላጆች አማርጠው አገልግሎቱን እንዳያገኙ እንዳደረጋቸው ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመው፣ ይኼ ደግሞ አገልግሎት ፈላጊዎችን አማራጭ እንዳያገኙ ማድረግ በመሆኑ ወንጀል መሆኑን በድጋሚ አስረድተዋል፡፡ ተቋማቱ ‹‹ኢንተርናሽናል›› በማለት አሳሳች ማስታወቂያዎችን በመጠቀምና በትምህርት ቤታቸው ውጭ በር ላይ የውጭ ዜጋ በማቆም ጭምር የወላጆችን ሥነ ልቦና በመስረቅ የማሳሳት ተግባራትን እንደሚፈጽሙ የጠቆሙት አቶ መርከቡ፣ ወላጆች ትክክለኛ ማስረጃ ይዘው ወደ ሕግ እንዳይሄዱ በብጫቂ ወረቀት በልጆቻቸው አማካይነት ትዕዛዝ አዘል ግዴታዎችን እንዲፈጽሙ ስለሚያደርጉ ተቆጣጣሪው አካል ዕርምጃ ሳይወስድ መቆየቱን አስረድተዋል፡፡ የትምህርት ዘመን ሳይጠናቀቅ (ሰኔ 30) ምዝገባ ማካሄድና ቦታ እንደሌላቸው ማስፈራራት የተቋማቱ የሁልጊዜ ድርጊት መሆኑን ጠቁመው፣ ትምህርት ቢሮው ያወጣውን መመርያ ማለትም ‹‹የትምህርት ዘመን ሰኔ 30 ሲጠናቀቅ የግል ትምህርት ተቋማት ከሐምሌ 1 እስከ ሐምሌ 30 እንዲመዘግቡና የመንግሥት ትምህርት ተቋማት ከነሐሴ 1 ጀምሮ እንዲመዘግቡ›› የሚለውን የጣሰ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ድርጊቱም ሕገወጥና አገልግሎት ፈላጊዎቹ የማማረጥ ሕጋዊ መብታቸውን እንዲያጡ የሚያደርግ ተገቢ ያልሆነ ተግባር መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ወላጆች ከ700 እስከ 1,600 ብር ለአጋዥ መጻሕፍት እንዲከፍሉ ከመደረጋቸውም በተጨማሪ፣ ከሶፍት እስከ ቀለም ግዥ ድረስ እንደሚታዘዙም ከወላጆች አቤቱታ መረዳት እንደሚቻል አቶ መርከቡ አስረድተዋል፡፡ በከተማው የሚገኙ ከ1,500 በላይ የግል ትምህርት ቤቶች ላይ የክስ ፋይሎች መከፈታቸውን የጠቆሙት አቶ መርከቡ፣ በ206 ላይ ጥብቅ ክትትል ተደርጐ ከ190 በላይ ለሚሆኑት በጣምራ ማስጠንቀቂያ በጽሑፍ እንደተሰጣቸው አሳውቀዋል፡፡ 56 ተቋማት ቅሬታ ያቀረቡ ቢሆንም፣ ሌሎች ተደምረው 77 ትምህርት ቤቶች ላይ ምርመራ መጀመሩንና በሌሎቹ ላይ ክስ መመሥረቱን አቶ መርከቡ ተናግረዋል፡፡ በ2009 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን ሦስቱ አካላት በጥምረት ጥብቅ ክትትል እንደሚያደርጉና የተሻለ የትምህርት ዘመን እንደሚሆን ምኞታቸውን የተናገሩት የአስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዴላሞ ኦቴሮ፣ ውሳኔ የተላለፈላቸውና ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው የግል ትምህርት ተቋማት ራሳቸውን አሻሽለው ትውልድን በተገቢው ሁኔታ መቅረፅ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ የተቋማቱ መምህራን፣ ባለሀብቶች፣ ወላጆችና የሚመለከታቸው አካላት በመወያየትና ችግሮችን ተረዳድተው በመፍታት ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥርዓቱ ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን እንዲያደርጉም ጠይቀዋል፡፡ ችግሮች የሚታዩት በግል ትምህርት ተቋማት ብቻ ሳይሆን በመንግሥት ትምህርት ተቋማት፣ በዕርዳታና በሃይማኖት ትምህርት ተቋማትም ጭምር መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው፣ እንደ ግል ተቋማት የባሰባቸው እንዳልሆኑ ግን ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...