በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ልዩ ስሙ ገላን ኮንዶሚኒየም ተብሎ በሚጠራው አካባቢ፣ ለአካለ መጠን ያልደረሰች ሕፃን ተማሪ ለመጥለፍ የሞከሩ ሁለት ወጣቶች፣ እያንዳንዳቸው በአሥር ዓመታት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ተፈረደባቸው፡፡ ፍርደኞቹ ዱጉማ ኤዴቻና ደምስ አያኖ ሕፃን ተማሪ ዘውድነሽ አታክልቲን ለመጥለፍ በማሰብና በመዘጋጀት፣ መጋቢት 26 ቀን 2008 ዓ.ም. ከቀኑ 9፡00 ሰዓት ላይ ሙከራውን መፈጸማቸውን፣ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አቃቂ ቃሊቲ ምድብ ችሎት የሰጠው ፍርድ ይገልጻል፡፡ ፍርደኞቹ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1)ን እና 589(1) ሥር የተደነገገውን በመተላለፍ፣ ሕፃኗን በሰሌዳ ቁጥር (ኦሮ) 3-36728 ሚኒባስ ታክሲ ውስጥ አፍነው በማስገባት ይዘዋት ሊሰወሩ ሲሉ አብረዋት የነበሩ ተማሪዎች በመጮህና ድንጋይ በመወርወር ሲከተሉ፣ የአካባቢው ሰው መንገዱን በድንጋይ በመዝጋት ሊያስጥሏቸው መቻላቸውን ፍርዱ ይገልጻል፡፡ ሕፃኗን ተማሪ አንደኛ ተከሳሽ በፊቷ ላይ የሞባይል መብራት በማብራት እየደነሰ እንዳታልፍ መንገድ ሲዘጋባት በመውደቋ፣ እሱ ወገቧን ሲይዝ ሁለተኛ ፍርደኛ እግሮቿን በመያዝ ሚኒባሱ ውስጥ እንዳስገቧትም ፍርዱ ይዘረዝራል፡፡ የፌደራል ዓቃቤ ሕግ ክስ መሥርቶና አሥር የሰው ምስክሮችን አቅርቦ ካሰማ በኋላ፣ ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ በማለት የቅጣት ፍርዱን ሰጥቷል፡፡ ሦስተኛ ተከሳሽ (የታክሲው ሾፌር) ድርጊቱን ሊፈጽም የቻለው ተገዶ መሆኑን በማስረዳቱ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ቁጥር 149(2) መሠረት በነፃ መሰናበቱም ተገልጿል፡፡ ሁለቱ ተከሳሾች ድርጊቱን የፈጸሙት በተበዳይዋ ትምህርት ቤት አካባቢ በመሄድና ራሷን መከላከል የማትችል ሕፃን ልጅን በማስገደድ ለመጥለፍ በመሆኑ፣ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 84(1ሐ) መሠረት ጭካኔን የሚያሳይና በ84(1መ) መሠረት ደግሞ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበው የቅጣት ማክበጃን ፍርድ ቤቱ ተቀብሎ፣ አንደኛና ሁለተኛ ተከሳሾች እያንዳንዳቸው በአሥር ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ፍርድ ሰጥቷል፡፡ አንደኛ ተከሳሽ ቅጣት የተጣለበት በሌለበት መሆኑም ተገልጿል፡፡