Friday, April 19, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ክቡር ሚኒስትር

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሾፌራቸው ጋር ወደ ቢሮ እየሄዱ ነው]

 • ምንድን ነው አንተ ይኼ?
 • ምኑ ክቡር ሚኒስትር?
 • ሰላማዊ ሠልፍ ነው እንዴ?
 • የምን ሰላማዊ ሠልፍ?
 • ሰላማዊ ሠልፍ እንዲያደርጉ ማን ፈቀደላቸው?
 • ሰላማዊ ሠልፍ ለማድረግ እኮ ማሳወቅ እንጂ ማስፈቀድ ግዴታ አይደለም፡፡
 • እኮ እኔ ሳላውቀው እንዴት ይደረጋል?
 • እርስዎ ደግሞ ይኼ አይመለከትዎትም እኮ፡፡
 • ሚኒስትር መሆኔን አትርሳ፡፡
 • ለዚያውም ክቡር ሚኒስትር እንጂ፡፡
 • ስለዚህ ሁሉም ነገር ይመለከተኛል፡፡
 • እሺ ለማንኛውም ይኼ ግን ሰላማዊ ሠልፍ አይደለም፡፡
 • ታዲያ ምንድን ነው?
 • የሥጋ ሠልፍ ነው፡፡
 • የምን የሥጋ ሠልፍ?
 • ሰው ሥጋ ሊገዛ ተሠልፎ ነዋ፡፡
 • ይኼ ምን እንደሚያሳይ ታውቃለህ?
 • ችጋርን ነዋ የሚያሳየው፡፡
 • አንተ እውነትም ኪራይ ሰብሳቢ ነህ፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • በቃ አፍራሽ ነህ ስልህ፡፡
 • እኮ ምን አደረግኩ?
 • ይኼ እኮ የሚያሳየው አገሪቷ የደረሰችበትን ዕድገት ነው፡፡
 • እኮ እንዴት ሆኖ?
 • ሰው በቀን ሦስቴ ከመብላት ወጥቶ ሥጋ መብላት ጀምሯላ፡፡
 • ኧረ አያስቁኝ፡፡
 • ምኑ ነው የሚያስቀው?
 • ቀልድዎት ነዋ ያሳቀኝ፡፡
 • የምን ቀልድ ነው?
 • በግ የሚገዛ የነበረ ሰው እኮ ነው አሁን ችጋር አግኝቶት አንድ ኪሎና ሁለት ኪሎ ሥጋ ለመግዛት የተሠለፈው፡፡
 • በነገራችን ላይ ብዙ ሥጋ ለጤንነት ጥሩ አይደለም፡፡
 • ምን አሉኝ?
 • አየህ ሙሉ በግ መብላት ለጤና ጥሩ ስላልሆነ፣ አንድና ሁለት ኪሎ መግዛቱ ጠቃሚ ነው፡፡
 • ኧረ ክቡር ሚኒስትር ቀልዱን ያቁሙት፡፡
 • ስማ ቀልድ አይደለም፤ ዕድገታችን የተጠና ነው፡፡
 • እንዴት የተጠና ማለት?
 • አየህ አሜሪካና አውሮፓ ቢያድጉም ሕዝባቸው ያገኘውን እያጋበሰ የውፍረት ችግር ተጠቂ ሆኗል፡፡
 • አሁን በጣም ቀልደኛ መሆንዎትን ተረድቼያለሁ፡፡
 • ስማ አትክልትና ፍራፍሬ ነው ለጤና ጥሩ፡፡
 • ወይ አትክልትና ፍራፍሬ?
 • ምነው?
 • ይኸው ጤፍን ካየሁት ስንት ጊዜ? በሩቁ እኮ ነው የማውቀው፡፡
 • ለምን?
 • እንዲያውም የሌላ አገሩ ሩዝ ዘመዴ ከሆነ ስንት ጊዜዬ?
 • እሱም የዕድገቱ ምልክት ነው፡፡
 • እንዴት ሆኖ?
 • አየህ የዕድገት ሞዴላችን ከሩቅ ምሥራቅ የተቀዳ ስለሆነ፣ ሩዝም ምግባችን እንዲሆን የፈለግነው ለዚያ ነው፡፡
 • ኧረ አይቀልዱ እባክዎት?
 • ስማ ሩዝ ስትበላ ልክ እንደ ቻይኖቹ ሰውነትህ ቀልጣፋ ስለሚሆን ምርታማ ትሆናለህ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር የምር ቀልድ ይችላሉ፡፡
 • ቀልድ አይደለም፣ የዕድገታችን ሞዴል አካል ነው ስልህ?
 • ምኑ?
 • አመጋገባችን አትክልትና ፍራፍሬ መሆኑ፡፡
 • እና እርስዎ ሥጋ ትተዋል?
 • እርግፍ አድርጌ ነዋ፡፡
 • ቅድም ቤት ያየሁት አራት እግር ያለው የሚጮኸው ምንድን ነበር?
 • ምኑ?
 • እንትን ነበር እንዴ?
 • ምን?
 • ጐመን!

[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሯቸው ሲገቡ አማካሪያቸውን አገኙት]

 • ምነው አረፈዱ ክቡር ሚኒስትር?
 • እንዴት አላረፍድ?
 • ምን ገጠመዎት?
 • መንገድ ሁሉ ተቦዳድሷል አይደል እንዴ?
 • ክረምት እኮ ሁሌ እንደዚህ ነው፡፡
 • እኔ እኮ ምን እየተሠራ እንደሆነ ነው የማይገባኝ?
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • እንደዚህ ዓይነት መንገድ ማን ነው የሚሠራው?
 • እየቀለዱ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • የምን ቀልድ ነው? ማነው መንገዱን የሚያሠራው?
 • መንግሥት ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ቀልድ ነው የተያዘው፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • ሕዝቡ ደግሞ መንገዱ እንደዚህ መበላሸቱን እያወቀ ለምን እንደሚጠቀምበት ነው የማይገባኝ?
 • ምን ማድረግ ይችላል?
 • መኪናውን ቤቱ አቁሞ በእግሩ መሄድ ነዋ፡፡
 • ጭራሽ?
 • እንዴ ምን ነካህ? ለጤና ራሱ ይጠቅማል እኮ፡፡
 • እየቀለዱ መሆን አለበት?
 • ስማ ሌላ አገር እኮ ሰው በብስክሌት ነው የሚሄደው፡፡
 • እና ሰው መኪናውን ቤቱ አቁሞ በእግሩ ይሂድ እያሉኝ ነው?
 • ታዲያ መንገድ እንደዚህ ተበላሽቶ መኪና መጠቀም አለባቸው?
 • ዋናው ችግር እኮ መንገድ በጥራት አለመሠራቱ ነው፡፡
 • ድሮስ ከኪራይ ሰብሳቢ ኮንትራክተር ምን ይጠበቃል?
 • እ…
 • የውጭ አገሮቹም ኮንትራክተሮች ቢሆኑም ኪራይ ሰብሳቢ መሆን ጀምረዋል፡፡
 • ታዲያ ምን ተሻለ?
 • መፍትሔውንማ አውቀዋለሁ፡፡
 • ምንድን ነው መፍትሔው?
 • ኮንስትራክሽን ዘርፍ ውስጥ እገባበታለሁ፡፡
 • ማን?
 • እራሴው!

[ክቡር ሚኒስትሩ ውጭ የሚገኝ ኢንቨስተር ወዳጃቸው ጋ ደወሉ]

 • ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት ነህ?
 • ምን ልታዘዝ?
 • ጮማ ሥራ ይዤ መጥቼልሃለሁ፡፡
 • ምንድን ነው እሱ?
 • ይኸው መንገዳችን እኮ የኮንሶ የእርከን እርሻ ነው የሚመስለው፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • በቃ ተቆፋፍሮ ተቆፋፍሮ መንገዱ ሁሉ ተበላሽቷል፡፡
 • ይኼ በየጊዜው ተመረቀ ምናምን እያላችሁ የምታስወሩለት መንገድ?
 • ምን እዚህ ከተወራ ይበቃል እኮ?
 • እና የምን ሥራ ነው ያመጡት?
 • ኮንስትራክሽን ዘርፉ ውስጥ ልገባ ነው፡፡
 • አይ ክቡር ሚኒስትር፣ አባ መላ እኮ ነዎት፡፡
 • እህሳ፡፡
 • ከእርስዎ ብልጣብልጥነት ጋር ሲወዳደር ብልህ ሰው ራሱ ቂል ነው እኮ የሚባለው፡፡
 • ስለዚህ ከአንተ አንድ ነገር እፈልጋለሁ፡፡
 • ምን ልታዘዝ?
 • በቃ የኮንስትራክሽን ማሽኖች ዋጋ አጣርተህ በቫይበር ላክልኝ፡፡
 • ምንም ችግር የለም፡፡
 • እኔ ከጀርመን ማሽን ውጪ ሌላ አልፈልግም፡፡
 • ምንም አያስቡ፡፡
 • በቃ በሰላሳ ደቂቃ ውስጥ አጣርተህ ላክልኝ፡፡
 • እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ የቫይበር መልዕክቱ ሳይደርሳቸው አንድ ሰዓት ስለሞላው ውጭ ያለው ወዳጃቸው ጋ መልሰው ደወሉ]

 • አንተ ሰለሰዓት ምንም አታውቅም እንዴ?
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • በሰላሳ ደቂቃ ላክልኝ ብዬህ፣ አንድ ሰዓት ሞላህ እኮ፡፡
 • እኔማ በአሥራ አምስት ደቂቃ ውስጥ ነው የላኩት፡፡
 • ታዲያ ለምን አልደረሰኝም?
 • አሁን ስሰማ ኢትዮጵያ ውስጥ ቫይበር ተቋርጧል አሉኝ፡፡
 • ሕይወታቸውን ነዋ የማቋርጠው!

[ክቡር ሚኒስትሩ ቴሌ ደወሉ]

 • ጤና ይስጥልኝ ማን ልበል?
 • ማን ልበል?
 • አዎን ማን ልበል?
 • እንዴት ብትንቀኝ ነው?
 • አላወቅኩም ማን ልበል?
 • ክቡር ሚኒስትር ነኛ፡፡
 • ውይ ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፣ ያው ብዙ ሰው ስለሚደውልልን ነው፡፡
 • ለመሆኑ ቫይበር አይሠራም እንዴ?
 • ቫይበር እንኳን ይሠራል፤ እኛ አቋርጠነው ነው፡፡
 • ለምንድን ነው የተቋረጠው?
 • ያው ተማሪዎች ማትሪክ ፈተና ላይ ስለሆኑ እንዳይሰረቅ ብለን ነው፡፡
 • ቢሰረቅ እኛ ምን አገባን?
 • ምን አሉኝ?
 • እዚህ አገር ስንተ ነገር ይሰረቃል አይደል እንዴ ፈተና ቢሰረቅ ምን አለበት?
 • እ…
 • እኛ ስንት ነገር እንዳንሰርቅ ቫይበር ለምን ይቋረጣል?
 • በቫይበር ይሰርቃሉ እንዴ?

[ክቡር ሚኒስትሩ መልሰው ውጭ ያለው ወዳጃቸው ጋ ደወሉ]

 • አቤት ክቡር ሚኒስትር?  
 • በቃ በኢሜይል ላክልኝ፡፡
 • አሁን እልክልዎታለሁ፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ ኢሜል ሳይደርሳቸው አንድ ሰዓት ስለሞላ፣ መልሰው ውጭ ያለው ወዳጃቸው ጋ ደወሉ]

 • አንተ ጀርመን እየኖርክ እንዴት ስለሰዓት ጥቅም አይገባህም?
 • በሚገባ ነው እንጂ የሚገባኝ፡፡
 • እና ኢሜል እስካሁን እንዴት አላክም?
 • እኔማ ከላኩት ቆየሁኝ፡፡
 • ታዲያ እንዴት አልደረሰኝም?
 • አሁንማ ስሰማ ኢንተርኔት ራሱ ተቋርጧል ተብሏል፡፡
 • ተላለቅና!

[ክቡር ሚኒስትሩ መልሰው ቴሌ ደወሉ]

 • ጤና ይስጥልኝ፡፡
 • ስማ፡፡
 • ማን ልበል?
 • አሁንም ማን ልበል?
 • ይቅርታ አላወቅኩም፡፡
 • እሱን አሳይሃለሁ፡፡
 • ማን ልበል?
 • ክቡር ሚኒስትር ነኝ፡፡
 • ይቅርታ ያው እንደነርኩዎት ብዙ ሰው ስለሚደውል ነው፡፡
 • አሁን ደውዬልህ መልሰህ ማንነቴን ትጠይቀኛለህ?
 • ምን ልርዳዎት?
 • ኢንተርኔት ተቋርጧል እንዴ?
 • አዎን አቋርጠነዋል፡፡
 • ለምን?
 • ያው ተማሪዎቹ ፈተና እንዳይሰራረቁ፡፡
 • እነሱ እንዳይሰራረቁ ሲባል አገሪቷ ወደኋላ ትራመድ፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • ሥራ እኮ ቆሟል፡፡
 • እ…
 • ለመሆኑ መሪ ቃላችሁ ‹‹Connecting Ethiopia to the future›› የሚል ነበር አይደል?
 • አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አሁን ግን ‹‹Connecting Ethiopia to the past›› መባል አለበት፡፡
 • ይሻላል?
 • መፍትሔውማ ምን እንደሆነ አውቄዋለሁ፡፡
 • ምንድን ነው መፍትሔው?
 • ሊብራላይዝ ማድረግ፡፡
 • ምኑን?
 • ቴሌን!

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ ግምገማ ከሾፌራቸው ጋር እየሄዱ ነው]

 • ምነው ፊትህ ጨፍግጓል?
 • ክቡር ሚኒስትር በጣም አሞኛል፡፡
 • ምን ሆነህ?
 • ይኼ ከተማ ውስጥ የበዛው ነገር ይዞኛል፡፡
 • ምንድን ነው እሱ?
 • አተት፡፡
 • ቪኤት ነው ያልከኝ?
 • ኧረ ይኼ ኮሌራው፡፡
 • ኮሮላው?
 • እንዴት እርስዎ ያለ ቶዮታ አያውቁም እንዴ?
 • እኮ ምንድን ነው ያልከኝ?
 • አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት፡፡
 • ምንድን?
 • አተት!

[ክቡር ሚኒስትሩ እየተገመገሙ ነው]

 • ክቡር ሚኒስትሩ በጣም አብዝተውታል፡፡
 • እውነት ነው ሥራ በጣም በዝቶብኛል፡፡
 • እየቀለዱ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • የምን ቀልድ ነው? ሥራ በጣም በዝቶብኛል፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ሙስና ነው ያበዙት፡፡
 • የሚሠራ ሰው እኮ ሊሞስን ይችላል፡፡
 • እ…
 • ሙስና የማይሠሩ ሰዎች ሥራ እንደማይሠሩ ምልክት ነው፡፡
 • እርስዎ ምን እንደሆኑ ያውቃሉ?
 • ምንድን ነኝ?
 • አተት፡፡
 • ምንድን ነው አተት?
 • አጭበርባሪ፣ ተንኮለኛና ትምክህተኛ!

 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...

እጥረትና ውጥረት!

ጉዞ ከስድስት ኪሎ ወደ ቃሊቲ፡፡ ‹‹ይገርማል ቀኑ እንዴት ይሄዳል?››...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

[የኢኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪው ቅሬታ የቀረበባቸው አንዳንድ ጉዳዮችን ክቡር ሚኒስትሩ ተመልክተው ምላሽና ውሳኔ እንዲሰጡባቸው ለማድረግ ከክቡር ሚኒስትሩ ጋር እየተወያዩ ነው] 

ክቡር ሚኒስትር ተቋማችን በሚሰጣቸው አንዳንድ አገልግሎቶች ላይ ጥያቄ እየተነሳ በመሆኑ ነው ዛሬ ከእርስዎ ጋር ለመወያየት የፈለግኩት። የምን ጥያቄ? ማነው ጥያቄውን ያቀረበው? ጥያቄውን ያቀረቡት የተቋማችን ተገልጋዮች ናቸው። እሺ፣...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት ጋር በአገራዊ ጉዳዮች ላይ እየመከሩ ነው]

ክቡር ሚኒስትር ባለፈው ሊያወያዩን ሲመጡ ለአገራችን የፖለቲካ ችግር መፍትሔው አንድና አንድ እንደሆነ ነግረንዎት ነበር፣ ያስታውሳሉ? አላስታውስም። ባለፈው የተገናኘን ጊዜ ይህችን አገር ከችግር የሚያወጣው መፍትሔ አንድና አንድ...

[ክቡር ሚኒስትሩ በዕረፍት ቀናቸው በመኖሪያ ቤታቸው ሆነው ከባለቤታቸው ጋር ከውጭ እንዳይገቡ ስለተከለከሉ ምርቶች እያወሩ ነው]

እኔ እምልህ ...ኤል ሲ እንዳይከፈት ተከልክሏል ሲባል አልነበረም እንዴ? ኤል ሲ ደግሞ ምንድነው? ሌተር ኦፍ ክሬዲት ነዋ!? አልገባኝም? አስመጪዎች ከውጭ ለሚያስገቡት ዕቃ የሚያስፈልጋቸውን የውጭ ምንዛሪ ከባንኮች አይደል የሚያገኙት? አዎ። ኤል...