Thursday, December 1, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  የአገር ችግር የሚፈታው በኢሕአዴግ ብቻ አይደለም!

  ኢትዮጵያ ለገጠማት ችግር የማያዳግም መፍትሔ ያለው ሕዝቧ ዘንድ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጠረፍ እስከ ጠረፍ በአገሩ ጉዳይ ተሳታፊ ሆኖ ሐሳቡን በነፃነት መግለጽ ሲችል፣ አሁን ላጋጠመው አገራዊ የጋራ ችግር ሁነኛ መፍትሔ ያመነጫል፡፡ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ለመግለጽ እንደተሞከረው ከአገር ህልውና በላይ ምንም ነገር የለም፡፡ ግለሰብም ሆነ ቡድን ከአገር በላይ መሆን አይችሉም፡፡ ሰሞኑን በአገር አቀፍም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ መነጋሪያ ሆኖ የሰነበተው የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ሊቃነ መናብርት መግለጫ፣ አገሪቱ ለገጠማት ፈተና መልሱ ኢሕአዴግ ዘንድ ብቻ እንዳልሆነ የጠቆመው ነገር አለ፡፡ አገሪቱን የገጠማት ችግር በጣም አሳሳቢና ህልውናዋን የሚፈታተን መሆኑ ግልጽ ከመደረጉም በላይ፣ ለዚህ አሳሳቢ ችግር ዋነኛ ተጠያቂው ከፍተኛ አመራሩ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ጉዳዩ በጥልቅ ሲታይ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ሕዝብን በአግባቡ ባለማዳመጡ ምክንያት አገሪቱን ችግር ውስጥ መክተቱ ግልጽ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የአገሪቱን ችግር መፍታት የሚቻለው በኢሕአዴግ ብቻ አይሆንም ማለት ነው፡፡

  ከ100 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ እንዳላት በሚገመትባት ኢትዮጵያ የተለያዩ ፍላጎቶች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ የእነዚህን ፍላጎቶች ልዩነት አጥብቦ አንድ የጋራ አማካይ መፈለግ ካልተቻለ አገር ችግር እንደሚገጥማት ግልጽ ነው፡፡ የተለያዩ ፍላጎቶችን ማስተናገድና ችግርን ለመቅረፍ ሲቻል ደግሞ አገር በሰላምና በሥርዓት ትመራለች፡፡ ከዚህ ውጪ ኢሕአዴግም ሆነ ሌላ ኃይል ካለ እኔ አይሆንም የሚሉ ከሆነ ተቀባይነት የላቸውም፡፡ ስለዚህ ኢሕአዴግ እንዳሁን ቀደሙ በለመደበት ሁኔታ ትዕዛዛትን ከላይ አንቆረቁራለሁ የማይልበት ደረጃ ላይ ስለሚገኝ፣ ሕዝብን ከዳር እስከ ዳር ማነጋገር አለበት፡፡ የአገሪቱ ችግር በአንድ ፓርቲ ወይም 36 አባላት ባሉት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ይፈታል ብሎ መጠበቅ በዚህ ዘመን አይሠራም፡፡ ከዚህ በፊት ግራ የሚያጋቡ መግለጫዎች እየወጡ የፈየዱት ስላልነበረ፣ ሕዝብ ካሁን በኋላ ግራ መጋባት አይፈልግም፡፡ ይልቁንም በቃል የተነገረው ተግባራዊ መሆን የሚችለው የራሱ ጉልህ ተሳትፎ ሲታከልበት ብቻ እንደሆነ ነው የሚያምነው፡፡

  ኢሕአዴግ ባለፉት 26 ዓመታት በላይ አገሪቱን ሲያስተዳድር በርካታ ጠቃሚ ተግባራት የማከናወኑን ያህል፣ ሕዝብን እጅግ ያስቆጡ አሳዛኝ ድርጊቶችን ፈጽሟል፡፡ በአገሪቱ ግልጽነትና ተጠያቂነት ጠፍተው ግለሰቦችና ቡድኖች እንዳሻቸው እየሆኑ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፡፡ ከአገር ሀብት ዘረፋ እስከ ንፁኃን ሕይወት መቀጠፍ ድረስ የወንጀል ድርጊቶች ተፈጽመዋል፡፡ በቅርቡ በተሰጠው መግለጫ በእስር ላይ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎችና ግለሰቦች በይቅርታና ክሳቸው ተቋርጦ በምሕረት እንደሚፈቱ ተገልጿል፡፡ ከዚህ ውሳኔ ጎን ለጎንም በአገርና በሕዝብ ላይ በደል ያደረሱ ሹማምንትም በሕግ ሊጠየቁ ይገባል፡፡ በአገሪቱ ላይ ችግርና መከራ እንዲደርስ ያደረጉ በሕግ መጠየቅ ያለባቸው፣ ካሁን በኋላ ተጠያቂነት መስፈን እንደሚኖርበት ማረጋገጫ ለመስጠት ጭምር ነው፡፡ ከእስር መለቀቅ ያለባቸውን ያህል ታስረው በሕግ የሚጠየቁ መኖራቸው ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር ጠቃሚ ነው፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት ሲኖር የሕግ የበላይነት ይኖራል፡፡ ሕገወጥነት አደብ ይገዛል፡፡ የአገር ሀብት መዝረፍና ከሕግ በላይ መሆን ይቆማል፡፡ ሕዝብም የሚፈልገው ይህንን ዓይነቱን ተጠያቂነት ያለበት አሠራር ነው፡፡ ከዚህ በኋላ በሥልጣን መባለግ ቦታ እንደሌለው ለማሳያነትም ይጠቅማል፡፡ የአገርን ችግር ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የሕዝብን ተሳትፎ ያጎለብታል፡፡

  ሕዝብ የአገሩ ባለቤት ነው ሲባል የመጨረሻው የሥልጣን ባለቤት ነው ማለት ነው፡፡ ኢሕአዴግ ሕዝብን ‹ጥፋቴን በግልጽ ንገረኝ፣ ውቀሰኝ፣ ምን ማድረግ እንዳለብኝ በዝርዝር አስረዳኝ፣ ፍላጎትህን ምንም ሳታጎድል ንገረኝ. . .› በማለት ለወቅቱ አሳሳቢ ጉዳይ ሕዝቡን በስፋት ማነጋገር አለበት፡፡ ይህ ይሆን ዘንድ ደግሞ እንደተለመደው በወትሮው ‹አደረጃጀት› እና ‹ጥርነፋ› ሳይሆን ግልጽ የውይይት መድረኮች መክፈት አለበት፡፡ አርሶ አደሮች፣ የከተማ ነዋሪዎች፣ ምሁራን፣ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የተለያዩ ማኅበረሰቦች ተወካዮች፣ ወዘተ. በነፃነት የሚወያዩባቸው መድረኮች ይዘጋጁ፡፡ የኢሕአዴግ አመራሮች ‹ከሰማይ በታች ምንም ያልተነጋገርንበት ጉዳይ የለም› እንዳሉት፣ ሕዝቡም ምንም ነገር ሳያስቀር የውስጡን የሚናገርበት ዕድል ይመቻች፡፡ ለዓመታት የታመቁ ብሶትና ቁጭት ይውጡ፡፡ እልህና ንዴት ይተንፍሱ፡፡ መወቃቀሱ በሥርዓት ከተከናወነ በኋላ ምን ይደረግ ለሚለው በሠለጠነ መንገድ ምክክር ይደረግ፡፡ በዚህ ላይ በመመሥረት ለሰላምና ለዴሞክራሲ የሚሆን ፍኖተ ካርታ ይነደፍ፡፡ የአገር ችግር የሚፈታው በዚህ መንገድ ብቻ መሆኑን መተማመን ይገባል፡፡

  እንደሚታቀው ከዚህ በፊት የነበሩ ‹ውኃ ቅዳ ውኃ መልስ› ዓይነት እሰጥ አገባዎችና ንትርኮች አገሪቱንም ሆነ ሕዝቧን አልጠቀሙም፡፡ ኢሕአዴግ የሁሉም ነገር ተቆጣጣሪና የበላይ ካልሆንኩ የሚለው ትርክቱም አላዋጣም፡፡ አሁን ወቅቱ እየተናበቡ በጋራ ከችግር መውጫ መፈለግ እንጂ በነበረው ሁኔታ መቀጠል የማይቻልበት ነው፡፡ የኢሕአዴግ አመራሮች እንዳሉት የአገሪቱ ችግር በጣም አሳሳቢና ለህልውናዋም አሥጊ መሆኑ መተማመን ከተፈጠረ፣ ካሁን በኋላ የሚጠበቀው ለተግባራዊነቱ በአጭር ታጥቆ መነሳት ብቻ ነው፡፡ ይህ መነሳት ደግሞ የአጠቃላይ ሕዝቡን ድርጊታዊ ተሳትፎ ማካተት አለበት፡፡ እኔ ብቻ ነኝ የማውቅልህ በማለት የደረሰው አደጋ መደገም የለበትም፡፡ የበርካታ ንፁኃንን ደም ያፈሰሱ ግጭቶችና ትርምሶች ዳግም እንዳይመለሱ ከልብ የሚፈለግ ከሆነ ማዳመጥ የሚገባው ሕዝብን ብቻ ነው፡፡ ሕዝብ በፌዴራል ሥርዓቱ ላይ ጭምር ጥያቄ ሲያነሳ ችግር የለም ብሎ ማድበስበስ ሳይሆን፣ የችግሩ ምንጭ ምንድነው ብሎ በግልጽ መነጋገር ተገቢ ነው፡፡ ሕዝብ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት እየጠፋ ብሔርተኝነት አገሪቱን ችግር ውስጥ እየከተታት ነው እያለ፣ እንዳላዩ ተሸፋፍኖ ለማለፍ መሞከር አደገኛ ነው፡፡ ሕዝብ ብሔራዊ ማንነት እየደበዘዘ በየጎጡ ሥርቻ ውስጥ እንዲገባ መደገደዱ ሲሰማው የአገሩ ህልውና ያሳስበዋል፡፡ ለዚህም ነው ሕዝብ በአገሩ ጉዳይ ዋነኛ ተዋናይ መሆን ያለበት፡፡

  የኢትዮጵያ ሕዝብ የአገሩ ደኅንነትና ህልውና ያሳስበዋል፡፡ ከዚህ የወቅቱ ችግር ለመላቀቅ ደግሞ ቁልፉ በእጁ ላይ እንደሚገኝ መጠራጠር አይገባም፡፡ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ብልፅግና ዕውን የሚሆኑት ሕዝብ የአገሩ ባለቤት መሆኑ በተግባር ሲረጋገጥ ብቻ ነው፡፡ ገዥውን ፓርቲን ጨምሮ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ለሕዝብ ፍላጎት ተገዥ መሆን አለባቸው፡፡ በተለይ ኢሕአዴግ ሕዝብ የአገሪቱ ሥልጣን የመጨረሻው ባለቤት መሆኑን በማመን፣ በዚህች ታሪካዊት አገር ዴሞክራሲ እንዲሰፍንና ሕዝብን ማዕከል ያደረገ ልማት እንዲከናወን ለሕግ የበላይነት ትኩረት መስጠት አለበት፡፡ ሥልጣን የሚያዘውም ሆነ የሚለቀቀው በነፃ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ በሚከናወን ምርጫ እንዲሆን ለሕግ የበላይነት መገዛት ያስፈልጋል፡፡ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚከበሩት የሕግ የበላይነት ሲኖር ነው፡፡ ዜጎች የፈለጉትን በነፃነት የሚደግፉትና የማይፈልጉትን የሚቃወሙት በሕግ የበላይነት ሥር ነው፡፡ ሥልጡን ዴሞክራሲያዊ ውይይቶችና ክርክሮች የሚኖሩት ለሕግ የበላይነት ክብር ሲሰጥ ነው፡፡ በሥልጣን መባለግ የማይቻለው በሕግ የበላይነት ነው፡፡ ሕዝብም የሚከበረውና የሚደመጠው በዚህ መሠረት ነው፡፡ ኢሕአዴግ አዲስ ምዕራፍ እንዲጀመር ከልቡ ከፈለገ መጀመርያ ከራሱ ጋር ይታረቅ፡፡ ከዚያም ለሕዝብ ፍላጎት ይገዛ፡፡ መሠረታዊ ለውጥ የሚኖረው የሕዝብ ወሳኝነት ሲረጋገጥ ነው፡፡ የአገር ችግር የሚፈታው በኢሕአዴግ ብቻ አይደለም የሚባለው ለዚህ ነው!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  ባንኮች እንዲዋሀዱ እስከ ማስገደድ ሊገባ እንደሚችል ብሔራዊ ባንክ ጠቆመ

  በአሁኑ ወቅት የባንኮች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ችግር የሚሆንና የውጭ...

  የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅን የሚተካ ረቂቅ ተዘጋጀ

  ከቫት ነፃ የነበረው የኤሌክትሪክ ኃይል ገደብ ተቀመጠለት የገንዘብ ሚኒስቴር ከሃያ...

  የአገር ውስጥ የፍራፍሬ ገበያን ፍላጎት ይሸፍናል የተባለለት የብላቴው እርሻ ልማት

  መንግሥት የግብርና ምርታማነትና የፍራፍሬ ምርትን ለማሳደግ በ‹‹አረንጓዴ አሻራ›› በሚል...

  ‹‹ከገበሬው እስከ ሸማቹ ያለውን የንግድ ቅብብሎሽ አመቻቻለሁ›› ያለው ፐርፐዝ ብላክ ውጥኑ ከምን ደረሰ?

  ከመቼውም ጊዜ በላይ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የሚሰማ አንድ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  [በተቋሙ ሠራተኞች የተወከሉ አንድ ባልደረባ ሚኒስትሩን ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘው ወደ ቢሯቸው ገቡ]

  ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም ሰላም ... ተቀመጥ! አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር!...

  የጉራጌ ዞን ጥያቄና የክላስተር አደረጃጀት የገጠመው ተቃውሞ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አካል የነበሩ ዞኖችንና...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው?

  ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው አዋሽ ባንክ የ43 ቢሊዮን...

  አቢሲኒያ ባንክ ካለፈው ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ በማግኘት አዲስ ታሪክ አስመዘገበ

  አቢሲኒያ ባንክ ከቀደሚ የሒሳብ ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው...

  የጉድለታችን ብዛቱ!

  ከፒያሳ ወደ ሜክሲኮ ልንጓዝ ነው። ጎዳናውን ትውስታ እየናጠው ሁለትና...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ለዘመኑ የማይመጥን አስተሳሰብ ዋጋ ያስከፍላል!

  በኳታር እየተከናወነ ያለው የዓለም ዋንጫ በእግር ኳስ ጨዋታ ውስጥ ያልተጠበቁ ማራኪ ቴክኒኮችንና ታክቲኮችን ከአስገራሚ ውጤቶች ጋር እያስኮመኮመ፣ ከዚህ ቀደም በነበረ ችሎታና ዝና ላይ ተመሥርቶ...

  መንግሥት ለአገር የሚጠቅሙ ምክረ ሐሳቦችን ያዳምጥ!

  በሕዝብ ድምፅ የተመረጠ መንግሥት ለሕዝብ የሚጠቅሙ ሐሳቦችን የማዳመጥ ኃላፊነት አለበት፡፡ ሥራውን ሲያከናውንም በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በኃላፊነት መርህ መመራት ይኖርበታል፡፡ እያንዳንዱ ዕርምጃው በሕግ ከተሰጠው ኃላፊነት አኳያ...

  የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ ይደረግ!

  የሰላም ስምምነቱ ‹‹ታጥቦ ጭቃ›› ሊሆን የሚችልባቸው ምልክቶች እየተስተዋሉ ነው፡፡ ሚሊዮኖችን ለዕልቂት፣ ለመፈናቀል፣ ለከፍተኛ ሰብዓዊ መብት ጥሰትና መሰል ሰቆቃዎች የዳረገው አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት...