Saturday, June 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአርጀንቲና ኩባንያ አዲስ የጥርስ ሕክምና መስጫ ምርት ለአፍሪካ ለማቅረብ ኢትዮጵያን ማከፋፈያ ማዕከል ማደረጉን አስታወቀ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

– የ50 ሚሊዮን ዶላር ምርት ለማቅርብ ማቀዱን ገልጿል

ዋና መሥሪያ ቤቱን በአርጀንቲና ያደረገውና ቬንዳኖቫ ግሩፕ የተሰኘው ኩባንባ፣ በዓለም ጥቅም ላይ ሲውል ገና አዲስ እንደሆነ የተነገረለትን የጥርስ ሕክምና መስጫ ቴክኖሎጂ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚያመጣ፣ ኢትዮጵያን መነሻ በማድረግም ለሌሎች የአፍሪካ አገሮች የማከፋፈል ዓላማ እንዳለው አስታውቋል፡፡ ኩባንያው በአርጅቲና ማምረት ከጀመረ አራት ዓመታት ያስቆጠረውንና የተጎዳ ወይም የተቦረቦረ የጥርስ ክፍልን ለማከም የሚውለው ቅባት መሰል የጥርስ ሕክምና መስጫ ‹‹ብሪክስ-3000›› ተብሎ የሚጠራውን ምርት ለማምጣት ተዘጋጅቷል፡፡ ይህ ቅባት መሰል የጥርስ ሕክምና መስጫ፣ የታመመ ወይም የተቦረቦረን ጥርስ ያለ ምንም ማደንዘዣና መቦርቦሪያ አማካይነት በደቂቃዎች ውስጥ ለማከም የሚያስችል ቴክኖሎጂ መሆኑን የኩባንያው ኃላፊ፣ ጆርጅ ሌይን ሐምሌ 4 ቀን 2008 ዓ.ም. ምርቱን በማስመልከት ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ አስታውቀዋል፡፡ ጆርጅ ሌይን በአርጀንቲና ከ58 ያላነሱ ኩባንያዎችን በግሩፕ በማቀፍ የሚንቀሳቀሰውን ቬንዳኖቫ ግሩፕ ኩባንያ በምክትል ፕሬዚዳንትነት ይመራሉ፡፡ የጥርስ በሽታን ለማከም፣ በተለይም የተቦረቦሩ ጥርሶችን ለማጠብና ለመሙላት ይውላል የተባለው ይህ ምርት፣ በጥርስ ሕመምና በተምዶ በሚካሄደው የሕክምና ሒደት ሳቢያ የሚደርሰውን ጉዳትና አልፎ አልፎም የሚከሰተውን ሞት ለመቀነስ አስተዋጽኦ እንዳለው የጠቀሱት ሌይን፣ በአንዱ ምርት ብቻ አሥር የተቦረቦሩ ጥርሶችን ለማጠብና ለመሙላት የሚችል ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ምርቱ ሲጀመር ለሕፃናት ተብሎ የተፈበረከ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ተሻሽሎ አዋቂዎችም እንዲጠቀሙበት በሚያስችል መልኩ እየተመረተ ለዓለም በመቅረብ ላይ እንደሚገኝ ተጠቅሷል፡፡ በብዛት በላቲን አሜሪካ አገሮች ዘንድ ሰፊ የገበያ ድርሻ እንዳለው የተገለጸው ብሪክስ-3000 የጥርስ ሕክምና መስጫ፣ በአፍሪካ ካ አገሮች እስካሁን ደቡብ አፍሪካ ምርቱን በሰፊው ስትጠቀም ቆይታለች ያሉት ሌይን፣ በአሁኑ ወቅት ግን ኢትዮጵያ በማዕከልነት ተመርጣ ምርቱን ወደ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ለማከፋፈል ኩባንያቸው ማቀዱን ገልጸዋል፡፡ የኩባንያው ወኪል ጽሕፈት ቤትም በኢትዮጵያ ተከፍቶ ሥራ መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን ሚረር የንግድና አገልግሎት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ፣ የቬንዳ ኖቫ ግሩፕ ኩባንያ ዋና ወኪል በመሆን እንደሚሠራ በተደረገው ስምምነት መሠረት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በጅምላ በማስመጣት ማከፋፈል እንደሚጀምር የሚረር ኩባንያ ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ወንድሙ አስታውቀዋል፡፡ አቶ ተስፋዬ በገለጹት መሠረት፣ ሆስፒታሎች፣ የጥርስ ሕክምና ማዕከሎች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትና ሌሎችም ድርጅቶች በሚሰጡት የምርት ትዕዛዝ መሠረት ምርቱ ወደ አገር ውስጥ እንደሚገባ ይጠበቃል፡፡ ቬንዳኖቫ ለኢትዮጵያ ገበያ ሊያቀርብ ያቀደው የምርት መጠን 50 ሚሊዮን ዶላር እንደሚገመት አስታውቋል፡፡ ሆኖም በዋጋ ረገድ አሥር ጥርሶችን ለመሙላት የሚውለው አንዱ ብሪክስ-3000 ምርት፣ በ50 ዶላር ለገበያ እንደሚቀርብና አንድ ጥርስ ለመሙላት የሚጠይቀው ወጪም አምስት ዶላር ብቻ እንደሚሆን የኩባንዎቹ ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡ አሁን ባለው አሠራር ለአንድ ጥርስ ሙሊት እንደየ ተጨባጭ ሁኔታው እስከ 150 ዶላር እንደሚጠየቅ ሌይን በሰጡት ማብራሪያ ጠቅሰዋል፡፡ የምርቱን የጥራት ደረጃና የብቃት ሁኔታን በሚመለከት ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ የሰጡት የቬዳኖቫ የአትዮጵያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳዊት ወልደ ጻዲቅ፣ የምርቱ ደኅንነት ተፈትሾ፣ የጥራት ደረጃው በመረጋገጡ ፈቃድ ቢትዮጵያ ፈቃድ ማግኘት የሚያስችለውን ሒደት ጨርሶ እየተጠባበቀ እንደሚገን ገልጸዋል፡፡ ሌይን በበኩላቸው ከዓለም የጤና ድርጅትና ከአርጀንቲናው የምግብ፣ መድኃኒትና የህክምና መሣሪያዎች አስተዳደር ተቋምና ከመሰሎቹ የብቃት ማረጋገጫ ማግኘቱን ጠቅሰዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች