እነሆ መንገድ። ከሳሪስ አቦ ወደ ስታዲየም ልንጓዝ ነው። ተለምዷዊው ታካቹ ጉዞ የወትሮ ምሱን ሊበላ ያጉላላን ጀምሯል። ባሳር የሚረጥበው መሬታችን ዓመት በድርቀት ተንፏቆ ይኼው ሐምሌ ባተለት። ሰማይና ምድር ተኳርፈው ላይኳረፉ፣ ተጣልተው ላይጣሉ ሲጎረባበጡ ቢከርሙ ፍጥረት የምር መስሎት ለመቆራረጥ ይጣደፋል። በየአቅጣጫው ለፍቺ የሚጣደፈው በዝቷል። መንገድና መንገደኛ አልግባባ ብሏል። ወያላና ሾፌር፣ ዙፋንና ባለዙፋን፣ አባወራና እማወራ በአንድ ራስ ሁለት ምላስ ሆነዋል። ጋቢና ከጎኔ የተሰየመ ፀጉረ ጨብራራ ‹‹ጎልማሳ ወይ ፈተና?›› እያለ በረጂሙ ይተነፍሳል። ሾፌሩ ማትሪክ ተፈታኝ አድርጎ ቆጥሮት፣ ‹‹አይዞን ከመጣ ይመጣል፣ ካልመጣ አይመጣም፤›› ይለዋል። ‹‹ምኑ?›› ይጠይቃል ጎልማሳው። ‹‹ውጤቱ ነዋ፤›› ሾፌሩ ዞር ብሎ ዓይቶት በጥርጣሬ ይመለከተዋል። ‹‹ምን ውጤት አለው ብለህ ነው የእኛ ነገር? ከፈተና ወደ ፈተና፣ ደግሞ ወደ ፈተና እያሉ መኖር እንጂ። አሁን እስኪ ማትሪክና ቫይበርን ምን አገናኝቷቸው ነው የዘጉብን?›› አለ ጨብራራው ስልኩን እንደ ቁልፍ መያዣ እየገለባበጠ። ‹‹እኔ እኮ ማትሪክ ተፈታኝ መስለኸኝ ኖሯል። ለካ የረበሸህ የቫይበር ከአገልግሎት ክልል ውጪ መደረግ ነው። አይዞህ። ቅድሚያ ለተተኪው ትውልድ በሚለው ያዘው፤›› ሲለው ሾፌራችን ማርሽ እያጫወተ፣ ‹‹ተተኪው ትውልድማ ከዚህ ወዲያ ምን ደህና ነገር ይማራል ብለህ ነው? ይኼው በየአቅጣጫው ቆረጣና ስርቆት ነው ያስተማርነው። ይልቅ እኔ ያልገባኝ አንዱ ፈተናው ተረጋግቶ እንዲፈተን ሲደረግ ሌላው ለምን ከወዳጅ ዘመድ ተራርቆ በናፍቆትና በሥጋት እንዲፈተን እንደሚደረግ ነው?›› ብሎ ጎልማሳው የናፈቃትን አፍላ ወጣት ፎቶ የስልኩ ስክሪን ላይ በሙላት አውጥቶ ግንባሯን ሳመላት። ይኼኔ ከሾፌሩ ጀርባ የተሰየሙ ወይዘሮ፣ ‹‹አይ ዘመን። አንዱ መንገድ አጠጋግቶ ናፍቆትን ማስረሻ ዘዴ ሲያመጣ፣ ሌላው የተሰረቀ ፈተና ማደያና መደለያ መረብ አዘጋጅቶ አጥማጅና ተጠማጁን ይቀላቅላል። አይ ዘመን!›› ይላሉ። ድፍድፉ ሁሉ ዘመን ላይ እየተደፈደፈ ኑሮ አለ ግን? ጉዟችን ከተጀመረ ቆያይቷል። ‹‹እኔ ምለው?›› አለ ከወይዘሮዋ አጠገብ የተቀመጠ ቀጠን ረዘም የሚል ወጣት። በቀጣዩ ዓመት የአንዳንድ ትምህርት ቤቶች ገበያ ከወዲሁ መቀዝቀዙ ታወቀ ነው የምትሉኝ?›› ሲል፣ ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተሰየመች ቡኒ ቡትስ የተጫማች ጠይም፣ ‹‹ማን ምን አለ? ደግሞ ብላችሁ ብላችሁ አንደበታችንን መስረቅ ጀመራችሁ እንዴ?›› አለችው። ‹‹አባባሌ ያው አለ አይደል አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ማትሪክ ተፈትኖ የወደቀብን ተማሪ የለም እያሉ ይነግዳሉ፡፡ እነሱ ምን ሊሆኑ ነው ለከርሞ?›› ሲል ሁሉም ግራ ተጋብቶ ምንድነው የሚያወራው ዓይነት ተያየ። አንዳንዱ ማውራት የፈለገውን ማውራቱ ብቻ ሳይበቃው ሌላውን የሚያስተባብረው ነገር አለው። ‹‹እና?›› አለችው ጠይሟ። ‹‹በቃ ይኼው ዘንድሮ ኩረጃ የለ ምን የለ። አዳሜ በተናጠል ስትፈተን ጉዱ ሊታይ ነው፤›› ከማለቱ፣ ‹‹ድሮስ ተደራጅተን ኖሯል እንዴ ማትሪክ የምንፈተነው?›› አለው ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተሰየመ አጭር ባለፈር ካፖርት ለባሽ ጎልማሳ። ‹‹በለው። በተለይ ልማታዊው መንግሥታችን የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋፋት የገነባቸውን አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች ለመሙላት ይሁን ለማጉደል ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ማትሪክ ተራ ነገር ሆኖ ነበር፤›› ከማለቱ መለሎው አሳ ጎርጓሪ ወይዘሮዋ ቀበል አድርገው፣ ‹‹ኩረጃን ያስፋፋው መንግሥት ነው እያልከን እንዳይሆን፤›› ሲሉት መግቢያ ጠፋው። ‹‹እንደሱ ለማለት እንኳ ይከብዳል እማማ። ጥናት የሚፈልግ ጉዳይ ነው፤›› ሲላቸው፣ ‹‹አገሩን የኩረጃና የስርቆት ባህል ወሮት ጥናቱን ማን አጠናው ብለን ማንን እናምናለን?›› ሲሉት፣ ምን ችግር አለው? ዘመኑ የዴሞክራሲ ነው። በድምፅ ብልጫ መተማመን ነዋ፤›› ቢላቸው ከት ብለው ሳቁ። እኛም አብረናቸው ሳቅን። ሳቅም በአብላጫ ድምፅ ካልሆነ ያስጠቁራላ! ጉዟችን ቀጥሏል። መጨረሻ ወንበር የተሰየሙ ተሳፋሪዎች ድምፃቸውን ጎላ አድርገው የስላቅ ጨዋታ ይዘዋል። አንዱ ከሾፌሩ ትይዩ ጥጉን ይዞ የተቀመጠ ወጣት፣ ‹‹ጎበዝ ዘንድሮ ለጊዜው ተቋርጧል የሚባለው ነገር አልበዛባችሁም?›› ብሎ ይጠይቃል። ‹‹ኧረ በጣም። ባለፈው ወደ አንድ መሥሪያ ቤት ሥራ አስኪያጁን ላናግር ሄጄ ለጊዜው ማነጋገር አይችሉም አሉኝ። ለምን? ስል ምን ብባል ጥሩ ነው? ጉድ እኮ ነው እናንተ?›› ብሎ ልብ ሲያንጠለጥል፣ ‹‹መብራት ስለጠፋ አሉኝ እንዳትለን ብቻ፤›› ብሎ አጠገቤ የተየሰመው ጎልማሳ በርቀት ወሬ ጀመረ። ‹‹ኦልሞስት እንደዚያ ነው፤›› የተባልኩት። ሙሉ ልብሳቸውን ላውንደሪ እንዳስገቡት በኃይል መቆራረጥ ምክንያት ስላልደረሰላቸው ሥራ አልገቡም ተባልኩ፤›› ሲል ሁሉም ሳቅ ማማጥ ጀመረ። ‹‹እኔ ምለው ለምን አንድ ጊዜ መኖር ራሱ ለጊዜው ተቋርጦ ኔትወርኩ፣ መብራቱ ውኃው መንገዱ፣ ግድቡ ብቻ ሁሉም ነገር ሲያልቅ እንደገና አይጀመርልንም?›› ብትል ባለ ቡትሷ፣ ‹‹ቢችሉ ኖሮ አንቺ እስክትነግሪያቸው መቼ ይጠብቁ ነበር ልጄ? አንዳንዱ ቆጣሪ በፈጣሪ እጅ መሆኑ በጀ እንጂ ዘንድሮስ አጥፍቶ ጠፊው አያተነፍሰንም ነበር፤›› ብለው ወይዘሮዋ ተቀላቀሉ። ‹‹አይምሰላችሁ በሚቀጥለው ዓመት ስንትና ስንት ቢሊዮን ብሮች ከታክስ ለማግኘት ታቅዶ ሳለ እልም ብርት የሚለው ሕልውናችን ባለበት የሚቀጥል ይመስላችኋል?›› ሲል ባለ ካፖርቱ ጎልማሳ፣ ‹‹ቢሊዮን?›› እያለ አዳናቂው ተንጣጣ። ታዲያስ! ፓርላማ አትከታተሉም እንዴ?›› ብሎ ወደ አዳነቁት ወጣቶች ሲዞር አንዱ ቀበል አድርጎ ‹‹ነቁ እንዴ?›› አለ። ‹‹እንዴት አይነቁ? ገንዘብ ለመሰብሰብ ጊዜ ማን የማይነቃ አለ? የሕዝብ ገንዘብና ንብረት ሲበዘብዝና ሲበትንማ እንኳን እነሱ እኛም እንቅልፍ ላይ ነን፤›› አለው። ይኼን ጊዜ ወራጅ አለ በሉ እሺ! ወያላችን የሰበሰበውን ገንዘብ በመሰል በመሰሉ እያደረገ መልስ ያድለን ጀምሯል። መጨረሻ ወንበር ከተሰየሙት ወጣቶች አንዱ አሁንም በስልክ ወሬ ይዟል። ‹‹አጎቴ እኔ እንዴት ብዬ እንደማስረዳህ አላውቅም። ተከራይቼ የምኖረው ሁለት ክፍል ቤት ነው አልኩህ። ሁለት የሆነችውም በመጋረጃ ተጋርዳ ነው። አንተ ብቻህን ብትሆን ግድ የለኝም። ግን ሦስት ልጆች አሉህ። ሚስትህ አለች። በቅርቡ አዲስ አበባ ወርቅ ይታፈሳል ብሎ ከግብርና ሥራው ራሱን በራሱ አፈናቅሎ መጥቶ የተጠለለህ ወንድምህ አለ። እንዴት ብዬ ነው ይኼን ሁሉ ሰው የምችለው?›› ይላል። ተሳፋሪው እርስ በእርሱ በግርታ እየተያየ በተመስጦ ስልከኛውን ያዳምጣል። ‹‹ቆይ እንዴት ምትክ ቤት ሳይሰጡህ ቤትህን ያፈርሱታል? ዝም ትላለህ እንዴ አንተ?›› ሲል ወጣቱ ነገሩ ግልጽ ሆነና ተሳፋሪው ነገር ይጎነጉን ጀመር። ‹‹ወይ መልሶ ማልማትና መልሶ መላልሶ መቆርቆዝ? ድህነት ቅነሳና የገጽታ ግንባታ እኮ ትርጉሙ አልገባን አለ ጎበዝ። ሜዳ እየበተኑ አገር መገንባት የማን አገር ተሞክሮ እንደሆነ ቢነግሩን እኮ አንድያችንን ጠቅልለን እዚያው እንሄድላቸው ነበር፤›› ሲል አንዱ ሌላው ቀበል አድርጎ፣ ‹‹መንገድ ሲኖር እኮ ነው የምትሄደው፤›› አለው። ጎልማሳው ጣልቃ ገብቶ፣ ‹‹ይኼ ሁሉ በብድርና በእልህ የተሠራ መንገድ እያለ እንዴት መንገድ የለም ትላለህ?›› ሲለው ያኛው ፈጠን ብሎ፣ ‹‹አልሰማህም እንዴ? መንገዱም እኮ የመልሶ ማልማቱ አካል ሆኗል። ካላመንከኝ በተመረቀ ሳይቆይ የፈራረሰውን መንገድ ቆጥረህ ካልፈራረሰው ላይ ቀንሰህ ድረስበት፤›› አለው። ‹‹ወይ ጣጣ የማንሰማው የለም እኮ እናንተ?›› ሲሉ ወይዘሮዋ፣ ‹‹መቻል ነው። ያለነው ታዳጊ አገር ውስጥ ነው አላቸው፤›› ወያላው። ግን ሳናድግ ካረጀን የቆየን አንመስልም? ማለት በአንድ ወደፊት ሦስት ወደ ኋላ ሒሳብ ስናየው? ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። የታክሲያችን ተሳፋሪዎች ስለ መንገዱና ባክኖ አባካኝነቱ አንስተው አልጠግብ ብለዋል። ‹‹የእኔ ነገር አለ ዘፋኙ… ሲሉ ወይዘሮዋ፣ ‹‹የእኛ ነገር የሚልማ የለም…›› አሉዋቸው ወጣቶቹ ተባብረው። ‹‹በኅብረት እየተቸገርን በተናጠል እየጮህን እስከየት እንደምንዘልቅ እንጃ?›› ሲል ከጎኔ ጠይሟ ቀዘባ ቀበል አድርጋ፣ ‹‹መቶ ፐርሰንት የወከልናቸው የት ሄደው ነው እኛ ምንጨነቀው? እነሱ እንዲጮሁልን አይደለም እንዴ የወከልናቸው?›› ትላለች። ‹‹ተይ ማነሽ የእኔ እህት በሰው ውክልና ዝም ብለሽ ጣልቃ ገብተሽ እሳት አትጫሪ፤›› አላት ከኋላ። ‹‹ማለት?›› ስትለው፣ ‹‹በቃ! ወካይና ተወካይ አልስማማ ብሎ አይደል እንዴ አንድ ፕላን ወጥቶ ወዲያው የሚሻረው? ወዲያው የሚታጠፈው? ያላሳደጋቸውን መንጋዎች እንደሚያግድ እረኛ ይኼው የሚወጠነውና የሚታቀደው ነገር ሁሉ የጎንዮሽ ጥፋትና ክስረቱን ያላሰላ ሆኗል። በልማት ስም የማኅበረሰብ ሞራልና ህሊናን የሚያደቅ አካሄድ እየበዛ ነው። በፕሮፓጋንዳና በፖለቲካ ታክቲክ የሠለጠነ አለብላቢ አንድን የተፈጠረ ችግር ከሥር ከመሠረቱ አመጣጡን አጢኖ መመለስና ማስታረቅ በሚችለው ባለሙያ ምትክ ተሰይሞ፣ ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ መልስ እየመለሰ ቅራኔያችን እያደር ሰፋ። በአንድ ታክሲ ተሳፍረን መሄዳችንን ብቻ አትዩ። እንደ አንድ አገር ሕዝቦች መኖራችንን የታክሲና የባቡር ወንበር መጋራታችን ብቻ ያረጋግጠዋል?›› እያለ በብዙ አዝኖ አሳዘነን። በአጭሩ ባክኖ ያባከነን መንገድ በዝቷል። ማቋረጥ ሲኖርብን እያረዘምን በረዥሙ መቀባበል ያለብንን ደግሞ በአጭር ቅብብል እየሸወደን ነው። ማቀድ አልሰለቸን ብሏል። አፈጻጸሙን አይቶ እንዳለየ ማለፍ ተጣብቶናል። ሐምሌ ይመጣል ሐምሌ ይሄዳል። ትውልድ ይመጣል ትውልድ ይሄዳል። ወራት ያልፋሉ፣ ትውልዶችና በጀቶች ይባክናሉ። መንገዱ የብክነት ሆኖ ግን እስከ መቼ? አሁን ደግሞ ፈተና እና ጦሱ ብዙ ያነጋግሩናል፡፡ መልካም ጉዞ!