Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናለፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን አዲስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተሾመ

ለፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን አዲስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተሾመ

ቀን:

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በ33.144 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላቋቋመው የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን አዲስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተሾመ፡፡ የቀድሞው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ከኃላፊነታቸው ተነስተዋል፡፡

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የተሰየሙት የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትሩ አቶ ዓለማየሁ ተገኑ፣ በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተሞች ሥር የሰደደውን የመኖርያ ቤት ዕጦት እንዲፈታ ኃላፊነት ተሰጥቶት በድጋሚ ለተዋቀረው የፌዴራል ቤቶች ኤጀንሲ አቶ ረሻድ ከማል (ኢንጂነር) ዋና ሥራ አስፈጻሚ አድርገው ሾመዋል፡፡

አዲሱ ተሿሚ አቶ ረሻድ ማክሰኞ ጥር 1 ቀን 2010 ዓ.ም. አቶ ዓለማየሁና የኮርፖሬሽኑ ማኔጅመንት አባላት በተገኙበት ኮርፖሬሽኑን ተረክበዋል፡፡ አቶ ረሻድ ከደቡብ ኮሪያ ያንግናም ዩኒቨርሲቲ በዴቨሎፕመንት ኢኮኖሚክስ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ በሥራው ዓለም ስምንት ዓመት በተለያዩ ሙያዎች፣ 11 ዓመት በወረዳ፣ በዞንና በከተማ አስተዳደር በአመራርነት በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ሠርተዋል፡፡ ከዚያም በኋላ በኦሮሚያ ክልል የከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ በኦሮሚያ ክልል ኮንስትራክሽን ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ፣ ወደ ፌዴራል እስኪመጡ ድረስም የቢሮ ኃላፊ ሆነው መሥራታቸው ታውቋል፡፡

አቶ ረሻድ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን መልካም አጋጣሚዎችና ተግዳሮቶች አሉበት፡፡ ‹‹መልካም አጋጣሚው መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት የሰጠው በመሆኑ የከተማ አስተዳደር አካላት ሊገቡበት የማይቻላቸው ሰፊ የሪል ስቴት ልማት ማካሄድ የሚያስችሉ ሁኔታዎች አሉ፤›› ሲሉ ገልጸው፣ ‹‹በተግዳሮቹ በኩልም ያልተፈቱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች መኖራቸውና የአገልግሎት አሰጣጡ ደካማ መሆን ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ረሻድ እነዚህን ችግሮች በመፍታት የኮርፖሬሽኑን ዓላማዎች ዕውን ለማድረግ እንደሚሠሩ አስታውቀዋል፡፡

አቶ ረሻድ ወደ አዲሱ ኃላፊነታቸው ከመምጣታቸው በፊት የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበሩት አቶ ሀብታሙ ሲሳይ ነበሩ፡፡ አቶ ሀብታሙ ኮርፖሬሽኑ እንደ አዲስ ከመደራጀቱ በፊት፣ የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ በሚባልበት ወቅት ጭምር ዋና ዳይሬክተር ሆነው ሠርተዋል፡፡  

አቶ ዓለማየሁ ኤጀንሲው ኮርፖሬሽን ከሆነ በኋላም አቶ ሀብታሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው እንዲቀጥሉ ሰኔ 2 ቀን 2009 ዓ.ም. ሹመት ሰጥተው ነበር፡፡

በወቅቱ ከአቶ ሀብታሙ በተጨማሪ ለኮርፖሬሽኑ ሦስት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚዎችን መሾማቸው አይዘነጋም፡፡ አቶ ግሩም ብርሃኑ የቤቶች ልማት ዘርፍ፣ አቶ ብርሃኑ ዜና የፋይናንስ ዘርፍ፣ አቶ ይርጋም ኩመሌ ደግሞ የቤቶች አስተዳደር ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች ሆነው ተሹመዋል፡፡

ሦስቱ ምክትል ኃላፊዎች በኃላፊነታቸው የቀጠሉ ሲሆን፣ አቶ ሀብታሙ ይፋ ባልተደረጉ ምክንያቶች ወደ ኦሮሚያ ክልል በመዛወር የኦሕዴድ ጽሕፈት ቤት አማካሪ ሆነው መሾማቸው ታውቋል፡፡

ለአቶ ሀብታሙ መነሳት ምንጮች የተለያዩ ምክንያቶችን ቢያስቀምጡም፣ አቶ ሀብታሙ ለሁለት ወራት ለከፍተኛ ግምገማ ሥልጠና ሲቪል ሰርቪስ በገቡበት ወቅት በርካታ ቅሬታዎች እንደቀረቡባቸው ተሰምቷል፡፡

ከእነዚህ ቅሬታዎች መካከል በመዋቅር ሰበብ በርካታ ሠራተኞችን ከቦታቸው በማፈናቀል የራሳቸውን ሰዎች መመደብ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ የጥበቃና የፅዳት ሠራተኞች ከኮርፖሬሽኑ ጋር ቀጥታ ግንኙነት እንዳይኖራቸውና በኤጀንሲ በኩል እንዲሠሩ ማድረጋቸው የሚሉት ይገኙባቸዋል፡፡

መንግሥት እነዚህን ክሶች ከተመለከተ በኋላ ሠራተኞቹ በሥራቸው እንዲቆዩና ቀደም ሲል ምክትል ሆነው ሲሠሩ የቆዩና በአዲሶቹ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች የተተኩ ሦስት የቀድሞ ኃላፊዎች፣ በኮርፖሬሽኑ አማካሪ ሆነው እንዲሠሩ አዲስ የሥራ መደብ እንደተሰጣቸው ታውቋል፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ኮርፖሬሽኑን ባቋቋሙበት ደንብ ላይ እንደተገለጸው፣ ኮርፖሬሽኑ 33.144,772.136 ብር የተፈቀደ ካፒታልና 11,048,287,378 ብር በጥሬና በዓይነት በተከፈለ ካፒታል ተመሥርቷል፡፡

ኮርፖሬሽኑ በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተሞች የተፈጠረውን የመኖርያ ቤት ቀውስ እንዲፈቱ ኃላፊነት ከተሰጣቸው መንግሥታዊ ተቋማት መካከል አንዱ ሲሆን፣ በቅርቡ በሙሉ አቅሙ ወደ ግንባታ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...