Wednesday, March 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊሞተር ሳይክል አምቡላንሶች ሥራ ሊጀምሩ ነው

ሞተር ሳይክል አምቡላንሶች ሥራ ሊጀምሩ ነው

ቀን:

ጠብታ አምቡላንስ ሕይወት የማዳኑን ሥራ ለማቀላጠፍ ሞተር ሳይክል አምቡላንሶችን ሊጠቀም ነው፡፡ ባለው የትራፊክ መጨናነቅ አምቡላንሶች የተጠሩበት ቦታ ለመድረስ በአማካይ 30 ደቂቃዎች እንደሚወስድባቸው፣ ይህም ብዙዎች የመጀመርያ ዕርዳታ ሳያገኙ ሕይወታቸው እንዲያልፍ ማድረጉን፣ በዚህ ወር መጨረሻ ሥራ የሚጀምሩት የሞተር ሳይክል አምቡላንሶች በመጠኑም ቢሆን ችግሩን እንደሚቀንሱ ድርጅቱ ሰኞ ሐምሌ 4 ቀን 2008 ዓ.ም. በቢሮው በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ክብረት አበበ እንደገለጹት፣ ሞተር ሳይክል አምቡላንሶቹ ከመጀመርያ ዕርዳታ ሳጥን ከፍ ያለ ትራውማ ባግ የሚይዙ ሲሆን፣ የትንፋሽ መስጫ፣ ልብ ማስነሳት የሚችሉና ደም ማቆሚያ መሣሪያዎች ተገጥሞላቸዋል፡፡ በሚቀጥለው አንድ ወር ውስጥም የሙከራ አገልግሎት መስጠት ይጀምራሉ፡፡ በሙከራ ጊዜው መልካም ውጤት ከተገኘ በየክፍለ ከተማዎቹ ብሎም ከአዲስ አበባ ውጪ ባሉ አካባቢዎች ሞተር ሳይክል አምቡላንሶቹ ይሰማራሉ፡፡ ለሞተረኞቹም የመጀመርያ የሕይወት ዕርዳታ ላይ ያተኮረ በቂ ሥልጠና መስጠት መቻሉ ተገልጿል፡፡ ካለው የትራፊክ መጨናነቅ አንፃር በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ አደጋው በተከሰተበት ቦታ መድረስ ሲገባቸው አምቡላንሶች በሰዓቱ አይደርሱም፡፡ ለምሳሌ የትንፋሽ መቆም አደጋ ያጋጠመው ሰው በፍጥነት ካልተደረሰለት በአምስት ደቂቃ ውስጥ ሕይወቱ ያልፋል፡፡ በዚህ ምክንያት በርካቶች የሚታደጋቸው አጥተው ሕይወታቸውን ማጣታቸው ይገለጻል፡፡ ‹‹አደጋ ሲፈጠር አምቡላንስ ሳይሆን ሕዝቡ ነው ሕይወት ማትረፍ የሚችለው፡፡ ነገር ግን የመጀመርያ የሕይወት ዕርዳታ ክህሎት ያላቸው በጣም ጥቂት ናቸው፡፡ ስለዚህም የመጀመርያ ዕርዳታ አደጋ በብዛት በሚከሰትባቸው አካባቢዎችና ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ግለሰቦችና ሰዎች በሚበዙባቸው አካባቢዎች የሚውሉ እንደ ሾፌሮች፣ ፖሊሶችና አስተማሪዎች ሥልጠና መስጠት ያስፈልጋል፡፡ እኛም ግፊት እናደርጋለን፤›› ያሉት አቶ ክብረት ከአንድ የውጭ ድርጅት ጋር በመተባበር የመጀመርያ ዕርዳታ ሥልጠና በዚሁ ሳምንት እንደሚያዘጋጁ ገልጸዋል፡፡ ለማኅበረሰቡ በቂ የመጀመርያ ዕርዳታ ሥልጠና እስኪዳረስ ድረስ እነዚህ ሞተር አምቡላንሶች ችግሩን በተወሰነ መጠን እንደሚቀንሱ አሠራሩም በሌሎች አገሮች ተሞክሮ ውጤታማ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ድርጅቱ እንደሚገልጸው፣ በ2001 ዓ.ም. የተቋቋመው ጠብታ አምቡላንስ ባሉት 11 አምቡላንሶች እስካሁን 40,000 ለሚሆኑ ሰዎች አገልግሎት ሰጥቷል፡፡ የአገልግሎት ክፍያውም ወደ 400 ብር ገዳማ ነው፡፡ ከ25,000 ለሚበልጡ ዜጎችም አደጋ መከላከል ላይ ያተኮረ ሥልጠና ጠቁመዋል፡፡ እንደ አቶ ክብረት ገለጻ፣ መንግሥት ለመጀመርያ የሕይወት ዕርዳታ በቂ ትኩረት አልሰጠም፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ የተሠሩ ጥናቶች አለመኖርም የችግሩን ጥልቀት ለማወቅና መፍትሔ ለማቅረብ አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የአዲስ አበባ የጤፍ ገበያ

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤፍ የተከሰተውን የዋጋ ንረት...