የጥጥ ምርት መጥንና ጥራት በአገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ማሽቆልቆሉን ለማሻሻልናየምርቱን አቅርቦት መጠን ከፍላጎት ጋር ለማጣጣም እንዲቻል ለማድረግ ስትራቴጂ እየተቀረጸ ሲሆን፣ ጥጥ በአሁኑ ወቅት የሚገኝበትን በመመልከት የወደፊትን አቅጣጫ የሚያስቀምጥ ጥናት ይፋ ተደርጓል፡፡ የጥጥ ምርት በኢትዮጵያ በሚል ርዕስ ሐምሌ 5 ቀን 2008 ዓ.ም. ለሚመለከታቸው አካላት ይፋ የተደረገው ጥናት፣ የቅድመ ስትራቴጂክ ዕቅድ አካል ሲሆን፣ ጥናቱ በጥጥ ዘርፍ ውስጥ የሚታዩትን ልዩ ልዩ ችግሮች፣ የአመራረትና የምርታማነት ክፍተቶች እንዲሁም መፍትሄዎች ላይ ያተኮረ ጥናት የተካሄደበት መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ ለመጪዎቹ አሥር ዓመታት የሚያገልግል ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ለመንደፍ መነሻ የተደረገው ይህ ጥናት፣ በጥጥ ምርት ላይ በአሁኑ ወቅት እየታዩ ካሉት ችግሮች ውስጥ፣ በአሁኑ ወቅት ያለው የጥጥ ምርት ቀደም ብሎ ከነበረው ጋር ሲተያይ እየቀነሰ መምጣቱ ተገልጿል፡፡ በዚህ መሠረት አሁን ላይ ያለው የጥጥ ምርት መጠን ከ100 እስከ 150 ሺሕ ቶን የሚገመት ሲሆን፣ በአንጻሩ የአገሪቱ የጥት ምርት ፍላጎት ከ220 ሺሕ ቶን በላይ ሆኖ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ከ70 ሺሕ በላይ የአቅርቦት ክፍተት እንደሚታይ አስተያየት ሰጪዎች ይጠቅሳሉ፡፡ ለጥጥ ምርት ማሽቆልቆል የጥራት፣ የግብአት አጠቃቀም ችግር፣ የዋጋ፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዲሁም ለጥጥ ምርት ይውሉ የነበሩ የእርሻ መሬቶች ለስኳር ማሳነት መዋላቸው ዋነኛ መንስዔዎች ተብለው ከሚጠቀሱት ውስጥ መሆናቸው ተነስቷል፡፡ የግብኣት ዕቃዎች ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመር የጥጥ ጥራት ደረጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየወደቀ መምጣት ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ ያስገደዱት የኢትዮጵያ የጥጥ ዘርፍ፣ በአሁኑ ወቅት የጨርቃ ጨርቅ አምራቾች በብዛት እየገቡ መሆናቸው ታክሎበት አስፈላጊውን የጥጥ ምርት በአገር ውስጥ አምርቶ ለማቅረብ እንዳልተቻለ አስተያየት ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚመረተውን ጥጥ ቀደም ብሎ ከነበረው መጠን አኳያ ዝቅተኛ እየሆነ እንዲመጣ አስገድደዋል ከተባሉት ሌሎች ምክንያቶች መካከል የጥጥ መዳመጫ መሣሪያዎች በቂ አለመሆን፣ የእርሻ ዘዴዎች ዘመናዊ አለመሆን እንዲሁም የተሻሻሉ ግብርና ዘዴዎች እንደልብ አለመገኘታቸው፣ ለችግሩ መንስዔ ከሆኑት ውስጥ ይመደባሉ፡፡ በጥናቱ እንዲህ ያሉት ችግሮች ስለመበራከታቸው ተንጸባርቋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የጥጥ ምርትን በመስኖና ወቅቱን በጠበቀ የእርሻ ሥራ በመታገዝ፣ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ በአማካይ በጥጥ መሸፈን የተቻለው መሬት 80 ሺሕ ሄክታር እንደሚደርስ ጥናቱ ይጠቅሳል፡፡ ከዚህ ውስጥ ሁለት ሦስትኛው ድርሻ የሰፋፊ ጥጥ እርሻዎች መሆኑም በጥናቱ ቀርቧል፡፡ በአንጻሩ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ የለማው የጥጥ መጠን በአማካይ 135 ሺሕ ቶን ይገመታል፡፡ አሁንም ከዚህ ውስጥ ሦስት አራተኛው ድርሻ የሰፋፊ እርሻዎች መሆኑ ተመልክቷል፡፡ አቶ ፍስሐ ተክሌ፣ የሮው አግሮ ኢንዱስትሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ አቶ ፍስሐ በሰጡት አስተያየት መሠረት፣ የኢትዮጵያ የጥጥ ምርታማነት ከ100 ሺሕ እስከ 150 ሺሕ ቶን ድረስ ያህል የሚገመት ሲሆን ይህም ውጤት ቢሆን ቀደም ባሉት ጊዜያት ሲመዘገብ የቆየ ነው፡፡ ለስትራቴጂክ ዕቅዱ አጋዥ በሆነው ጥናት መሠረት፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ የጥጥ ምርት ምርታማነት መጠን ከ77.5 ወደ 66.2 ከመቶ ማሽቆልቆሉ ተገልጿል፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ የጥጥ ምርት እየተጠቀመ ያለው የጥጥ ዘር ከ30 ዓመት በላይ ያስቆጠረ መሆኑና አዲስና ዘመናዊ ዘር ሲመጣ በተገቢው መንገድ አለመጠቀም፣ ዝቅተኛ የግብርናና የእርሻ አሠራር ጥናት መኖሩ፣ የሠራተኞች እጥረት፣ የመስኖ ተፋሰስ አለመዳበር፣ የፋይናንስ አቅርቦት አለመኖር፣ የውጭ ምንዛሪ ማጣት ተደጋግመው በጥጥ ዘርፍ ውስጥ ዋነኛ ችግሮች ተደርገው የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በአገሪቱ በጠቅላላ ያለውን የጥጥ ፍላጎት ለማሟላትና ከ30 በመቶ በላይ የሚሆነውን የምርት ጉድለቱን ለማሟላት የአገሪቱን የጥጥ ምርት ፖሊሲ ማስተካከል ላይ ትኩረት መስጠት ወሳኝ እንደሆነ አቶ ታደሰ ኃይሌ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ገልጸዋል፡፡ ሦስት ክልሎች ማለትም አማራ፣ አፋርና ትግራይ በጠቅላላው ከአገሪቱ የጥጥ ምርት ውስጥ 70 ከመቶውን የሚሸፍኑ ሲሆን፣ ከ60 ሺሕ እስከ 70 ሺሕ ቶን ድረስ የሚገመት ምርት ሲያመርቱም ቆይተዋል፡፡ ይሁንና አሁን ላይ እየታየ ላለው የምርቱ ማሽቆልቆል አንዱ ምክንያት በአፋር ክልል የሚገኘው የጥጥ ምርት መሬት በስኳር ማሳ መሸፈኑ አንዱ ስጋት ነው፡፡ በትግራይ ክልል ዝቅተኛ የዝናብ መጠን መከሰቱና በአማራ ክልልም ቢሆን በየጊዜው እየታየ ባለው ከፍተኛ የአየር ንብረት መዋዥቅ ሳቢያ የጥጥ ከምንጊዜውም ይልቅ እየቀነሰ በመምጣት ላይ ይገኛል ተብሏል፡፡ ኢትዮጵያ በጥጥ ምርት ከምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ውስጥ የ50 ከመቶ የሚሆነውን ድርሻ የመሸፈን አቅም ቢኖራትም፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየታየ ያለው የጥጥ የምርት መቀነስን ለማሻሻል በስትራቴጂው መሠረት እንዲሁም ጥናቱ የሚያነሳቸወው ችግሮችን መነሻ በማድረግ የሚጠቆሙ ችግሮች ላይ መፍትሔዎች ተብለው የቀረቡ፣ የጥጥ ምርቱን ለማሻሻል ግብዓት ይሆናሉ የተባሉ አቅጣጫዎችም ተቃኝተዋል፡፡ በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ውስጥ እየተመረተ የሚቀርበው ጥጥ በዓለም ገበያ ከሚቀርበው ጥጥ አኳያ ጥራቱ የወረደ ቢሆንም የሚሸጥበት ዋጋ ከፍተኛ መሆኑ ግን በዘርፉ የበለጠ ስተሬቴጂካዊ አቅጣጫ አስቀምጦ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ አመላክቷል፡፡ በሁለት ወራት ውስጥ ይፋ የሚደረገው የአገሪቱ የጥጥ ምርትና ምርታማነት ስትራቴጂ ተጠናቆ ወደ ተግባር ሲገባ፣ በምርቱ ላይ ክፍተት ካልተፈጠረ በስተቀር ከውጭ የሚገባውን ምርት ሊያስቀር የሚችል የምርት መጠን በአገር ውስጥ እንዲኖር ለማድረግ የሚያስችል መሆኑ ተገልጾ፣ የጥጥ ምርትን በመስኖ ጭምር በመታገዝ የአገር ውስጥ የውጭ ባለሀብቶችን በብዛት ተሳታፊ እንደሚያደርግ አቶ ታደሰ አስረድተዋል፡፡ የውጭ ባለሀብቶችን በተመለከተም ሲገለጽም በደቡብ ኦሞ ዞን ዙሪያ ኤልሲ የተባለ ኩባንያ በ500 ሔክታር መሬት ላይ እያደረገ ያለው የማልት እንቅስቃሴ ሌሎችም ኢንቨስተሮች ወደ ዘርፉ ሊመጡ የሚችሉበትን ፍንጭ ይሰጣል በማለት አክለዋል፡፡ አቶ አብርሃ ኃይለሥላሴ ብሌን ጸጋዬ ቢዝነስና ኢንዱስትሪ ለተባለው ድርጅት የምርት መምሪያ ኃላፊ ሲሆኑ፣ በአፋር ክልል በጥጥ ምርት ላይ የሚሳትፍ ድርጅት ቢሆንም፣ በዘርፉ ላይ እየታየ ያለው ችግር በተለይ የግብዓት ወጪዎችን ለመሸፈን የገንዘብ እጥረት ድርጅቱ እያጋጠመው በመሆኑና የብድር ሊመቻችለት አለመቻሉ ኩባንያው የሚገጥመው የምርት ሒደት ችግር እንዲባባስ አድርጎታል ብለዋል፡፡ እስካሁን በተበጣጠሰ መንገድ ይካሄድ የነበረውን የጥጥ ምርት ለማሳደግ እየተደረጉ ያሉ ጥናቶችን በአንድ ስትራቴጂ ማዕቀፍ ውስጥ አዋቅሮ ለማስኬድ መነሳት፣ ወደፊትም ምርትን ከመጨመር፣ ግብርናውን ዘመናዊ ከማድረግ፣ ፋይናንሱንና የግብዓት ችግሮችን ከመፍታት አኳያ የሚሠሩ ሥራዎች ከውጭ የሚገቡትን የጥጥ ምርቶች ለመቀነስ እንደሚረዱ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ምርት አቅረብን ገዥ ጠፋ›› በማለት ጥጥ አምራቾች ለሚያቀርቡት ጥያቄ ምላሹ፣ በጥራት አምርቶ ማቅረብ መሆኑንና በጥራት ማቅረብ ከተቻለም ገዢ እንደማይጠፋ አቶ ታደሰ ገልጸዋል፡፡ ምርቱን ለገበያ ለማቅረብ የገበያ ትስስር መፍጠር ላይ ያለውን ችግር ለመቅረፍ ስትራቴጂክ ዕቅዱ ጠቃሚ እንደሆነ፣ በተጨማሪም በጥጥ ምርት ገበሬው የተሻለ ገቢ እንዲኖረውና ተመጣጣኝ ዋጋ ያለው ምርት እንዲገኝ ያደርጋል ብለዋል፡፡ በትልልቅ ገበያዎች ላይም ምርት ማቅረብ እንዲቻልና የውጭና የአገር ውስጥ ነጋዴዎች እንዲሳተፉ ማድረግም በግብይት ሰንሰለት ውስጥ የሚታዩ ማነቆችዎችን ለመፍታት ከሚረዱ መፍትሄዎች መካከል እንደሚመደብ ተብራርቷል፡፡