Friday, March 1, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ብርሃን ባንክ ከእጥፍ በላይ ጭማሪ ያሳየበትን የ365 ሚሊዮን ብር ትርፍ ማስመዝገቡ ታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ብርሃን ኢንተርናሽናል ባንክ በተገባደደው በጀት ዓመት የ365 ሚሊዮን ብር በማስመዝገብ አምና ካገኘው 139 ሚሊዮን ብር አኳያ ከሁለት እጥፍ በላይ ትርፍ ከታክስ በፊት ማግኘቱ ታወቀ፡፡ ከባንኩ ምንጮች በተገኘው መረጃ መሠረት በተገባደደው በጀት ዓመት ባንኩ ያስዘመገበው ትርፍ ባለፈው ዓመት ከተመዘገበው ይልቅ የ226 ሚሊዮን ብር በላይ ጭማሪ ያለው ትርፍ በማስመዝገቡ ከ162 ከመቶ በላይ ለውጥ ያሳየበትን ውጤት በማስመዝገብ አፈጻጸሙን በጥሩ ውጤት አሟሽቷል፡፡ ምንም እንኳ ከባንኩ ይፋዊ መግለጫዎችን ማግኘት ባይቻልም ባንኩ በአሁኑ ወቅት 103 ያህል ቅርንጫፎችን በመክፈት እ.ኤ.አ. በ2014/15 ከነበረበት ደረጃ ይልቅ በመስፋፋት ላይ እንደሚገኝ የባንኩ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ባንኮች በዓመቱ ያስመዘገቧቸውን የሥራ አፈጻጸሞች በማስመልከት እንዲሁም የፋይናንስ አቅምና ሌሎች እንቅስቃሴያቸውን የሚያመለካክቱ የፋይናንስና ክንውን መረጃዎችን ለባለአክሲዮኖች ይፋ ማድረግ እንደሚጀምሩ በሚጠበቅበት በዚህ ወቅት ያልተጠበቀ ውጤት እያሳዩ ስለሆናቸው ከወዲሁ ከታየው አንዱ የሆነው ብርሃን ባንክ፣ ከሁለት ዓመት በፊት ያስዘመገበው ትርፍ ከዓምናው አኳያ ያሳየው ጭማሪ ከ14 በመቶ ያልበለጠ እንደነበርና ለዚህም በርካታ ቅርንጫፎችን ለመክፈት ያወጣው ወጪ መጨመር አንዱ ምክንያት እንደነበር ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ ባንኩ ባለፈው በጀት ዓመት ሁለት ቢሊዮን የሚጠጋ ገንዘብ ማበደሩና፣ ተቀማጩ ሒሳቡም ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱን ይፋ ማድረጉ አይዘነጋም፡፡ ካለፈው ዓመት የባንኩ የፋይናንስ ሪፖርት ለመረዳት እንደተቻለው፣ የባንኩ ጠቅላላ ሀብት ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ ሲገመት የባንኩ የተከፈለ ካፒታልም ከ570 ሚሊዮን ብር በላይ ማሻቀቡ ተመልክቷል፡፡ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ የግል ባንክ ኢንዱስትሪውን ከተቀላቀሉ ኩባንያዎች አንዱ የሆነው ብርሃን ኢንተርናሽናል ባንክ፣ በፍጥነት እያደጉ ከሚገኙት መካከል የሚመደብ ነው፡፡ በቅርብ የተመሠረቱት ባንኮች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያስቀምጠዋል ተብሎ የሚጠበቀውን የሁለት ቢሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል መጠን የማሟላታቸው አቅም ላይ ሥጋት ቢደቅንም፣ በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ማሟላት እንደሚችሉ በርካቶቹ በመግለጽ ላይ ይገኛሉ፡፡ በአንፃሩ የአንዳንዶችን የተከፈለ ካፒታል መጠን በእጥፍ የሚበልጥ ዓመታዊ ትርፍ በማስመዝገብ ላይ የሚገኙ አንጋፋ የንግድ ባንኮችም በባንክ ኢንዱስትሪው ውስጥ እየታዩ ነው፡፡ በቅርብ እየተፎካከሩ የሚገኙት ዳሸን ባንክና አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ ለዚህ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ባለፈው ዓመት በአገሪቱ ሪከርድ የተባለውን የ980 ሚሊዮን ብር ትርፍ ያስዘመገበው ዳሸን ባንክ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ምንም እንኳ የዘንድሮ የዳሸን ባንክ አፈጻጸም ይፋ ባይደረግም፣ አዋሽ ባንክ ከምን ጊዜውም ሪከርድ የሆነውን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ በማስመዝገብ የግል ባንኮችን በመምራት ላይ ይገኛል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች