ሔፒታይተስን የሚያስከትለው ቫይረስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚከሰት ሞት ቀዳሚው ምክንያት እየሆነ እንዳለ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ የወጣ ሪፖርት አመለከተ፡፡ ከ183 አገሮች የተሰበሰበው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በኢንፌክሽን፣ በሔፒታይተስ ቫይረስ በሚከሰት የጉበት በሽታና ካንሠር የሚመዘገብ ሞት እ.ኤ.አ. በ1990፣ 890,000 የነበረ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. በ2013 63 በመቶ ጭማሪ አሳይቶ 1.45 ሚሊዮን ሆኗል፡፡ በንጽጽር እ.ኤ.አ. በ2013 ላይ በኤድስ የተመዘገበው ሞት 1.3 ሚሊዮን፣ በቲቢ 1.4 ሚሊዮን እንዲሁም በወባ 855,000 ነበር፡፡ ‹‹በቲቢና በወባ የሚመዘገቡ ሞቶች ከ1990 ወዲህ እየቀነሱ ቢሆንም፣ በሔፒታይተስ ቫይረስ የሚከሰተው ሞት ግን በመጨመር ላይ ነው›› ያሉት በለንደን ኢምፔሪያል ኮሌጅ ተመራማሪ የሆኑትና ሪፖርቱን ያዘጋጀው ቡድን መሪ ግራሀም ኩክ ናቸው፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው፣ ሔፒታይተስ አብዛኛውን ጊዜ በቫይረስ የሚመጣ ሲሆን፣ አንዳንድ ጊዜ በእፅ፣ በአልኮል ወይም በሌላ ኢንፌክሽን ሊከሰት ይችላል፡፡ አምስት ዓይነት ሔፒታይተስ (ኤ፣ ቢ፣ ሲ፣ ዲ እና ኢ) ሲኖር ኤ እና ኢ የሚተላለፉት በተበከለ ውሀ ወይም ምግብ ነው፡፡ የተቀሩት ዓይነቶች የሚተላለፉት ደግሞ በኢንፌክሽኑ ከተያዘ ሰው በሚወጡ ፈሳሾች አማካይነት ነው፡፡ ሔፒታይተስ ቢ እና ሲን በሕክምና ወደ ከፋ የጉበት በሽታ እንዳይሸጋገሩ ማድረግ የሚቻል ቢሆንም፣ 95 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች ኢንፌክሽኑ እንዳለባቸው እንኳ አያውቁም፡፡ 96 በመቶ የሚሆነው የሔፒታይተስ ሞት የሚከሰተው ደግሞ በቢ እና ሲ መሆኑን የሚናገሩት ተማራማሪዎቹ፣ በሔፒታይተስ የሚመዘገብ አብዛኛው ሞት የሚደርሰው በምሥራቅና ደቡብ እስያ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡ ተመራማሪው ኩክ እንደሚሉት፣ በሽታውን ለማከም መድሃኒት አለ፡፡ በተለይም ሔፒታይተስ ኤ እና ቢን ማከም ይቻላል፡፡ ክትባት ለሌለው ለሔፒታይተስ ሲም ቢሆን መድሃኒት አለ፡፡ ነገር ግን መድሃኒቱ ለድሀም ሆነ ለሀብታም አገር ውድ በመሆኑ የሚደፈር አይደለም፡፡ ስለዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለጤና የሚደረገው ፈንድ ዳግም እንዲጤን ሆኖ ዝቅተኛም ሆነ መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገሮች ተገቢውን ምላሽ መስጠት እንዲችሉ መደረግ እንዳለበት ሪፖርቱ ይደመድማል፡፡