Wednesday, March 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትካፍ ኢትዮጵያን ቀጣ

ካፍ ኢትዮጵያን ቀጣ

ቀን:

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ሰኔ 26 ቀን 2008 ዓ.ም. ካይሮ ላይ ባደረገው ስብሰባ ኢትዮጵያን በገንዘብና በዲሲፕሊን ጥሰት እንድትቀጣ መወሰኑ ይፋ አድርጓል፡፡ ብሔራዊ ፌደሬሸኑ በበኩሉ ውሳኔው የደረሰው ዘግይቶ በመሆኑ ጉዳዩን በማጣራት ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡ አህጉራዊ ውድድሮችን በመምራት የሚታወቀው ካፍ ከሚያከናውናቸው መርሐ ግብሮች መካከል ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች የአፍሪካ ወጣቶች የእግር ኳስ ዋንጫ ይጠቀሳል፡፡ በዚሁ መሠረት በሚቀጥለው ዓመት በዛምቢያ አስተናጋጅነት ለሚያካሂደው ለዚሁ የአፍሪካ ወጣቶች የእግር ኳስ ዋንጫ የማጣሪያ ውድድሮችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ በመርሐ ግብሩ መሠረት የሶማሊያ አቻውን በደርሶ መልስ ጨዋታ አሸንፎ ወደ ቀጣዩ ማጣሪያ የገባው የኢትዮጵያ ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በጋና አቻው በድምር ውጤት 5 ለ2 ተሸንፎ ዛምቢያ ከምታስተናግደው የአፍሪካ ወጣቶች እግር ኳስ ዋንጫ ውጪ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ይሁንና ቡድኑ ከአህጉራዊው ሻምፒዮና ውጪ በሆነበት ማለትም ሰኔ 7 ቀን 2008 ዓ.ም. በጋና አቻው 4 ለ0 በተሸነፈበት ጨዋታ ቡድኑን በመሪነት ይዘው የተጓዙት የፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ኢንጂነር ቾል ቤልና የቡድኑ ሐኪም ዶ/ር ዘገነ ታዬ ሜዳ ውስጥ በፈጠሩት የዲሲፕሊን ግድፈት የካፍ የዲሲፕሊን ኮሚቴ ሰኔ 26 ቀን 2008 ዓ.ም. ካይሮ ላይ ባደረገው ስብሰባ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ 10,000 ዶላር፣ የቡድኑን መሪና ሐኪም ደግሞ እያንዳንዳቸው አምስት ሺሕ ዶላርና በተጨማሪ ካፍ የሚመራቸውን አራት ውድድሮች ተሳትፎ እንዳያደርጉ መወሰኑ ታውቋል፡፡ ይሁንና ለፌዴሬሽኑ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለሪፖርተር እንደገለጹት ከሆነ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ላይ የተላለፈው አሥር ሺሕ ዶላር የቅጣት ውሳኔ ለፌዴሬሽኑ አልደረሰውም፡፡ የቡድን መሪውና የሐኪሙ የቅጣት ውሳኔ ግን ለፌዴሬሽኑ ደርሷል፡፡ ውሳኔውን አስመልክቶ ሪፖርተር በስልክ ያነጋገራቸው የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ በበኩላቸው፣ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን (ካፍ) የዲሲፕሊን ኮሚቴ የጨዋታ ዳኞችን ሪፖርት መነሻ አድርጎ ያስተላለፈው የገንዘብና የዲሲፕሊን ውሳኔ ለተቋሙ የደረሰው ሐምሌ 4 ቀን 2008 ዓ.ም. ነው፡፡ በመሆኑም ፌዴሬሽኑ ካፍ በይቅርታም ሆነ በሌላ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ቅጣቱ የሚነሳበት ሁኔታ ካለ ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸው፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ እንደ ተቋም ጥፋተኛ በተባሉት አመራሮች ላይ ስለሚወስደው ዕርምጃ ግን በቀጣይ የሚታይ ጉዳይ መሆኑን ጭምር ተናግረዋል፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ፣ ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን (ሉሲዎች) በአፍሪካ ዋንጫ ምድብ ማጣሪያ እንዲሳተፉ ካፍ ለብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ተደጋጋሚ ደብዳቤ ጽፎ መልስ ባለማግኘቱ ምክንያት፣ ቡድኑ ከምድብ ማጣሪያ ውጭ እንዲሆን መደረጉ አይዘነጋም፡፡ በወቅቱ ጥፋተኛ ተደርገው ከተወሰዱት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ፣ እንዲሁም የፌደሬሽኑ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ በነበሩት አቶ ዘሪሁን ቢያድግልኝና በሌሎችም የፌዴሬሽኑ ሠራተኞች ላይ የዕገዳ ውሳኔ ማስተላለፉ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም አሁን ደግሞ ለዚህ የዲሲፕሊን ግድፈት በምክንያትነት በተጠቀሱ አመራሮች ላይ የሚወሰደው የዲሲፕሊን ዕርምጃ ይጠበቃል፡፡ ምክንያቱም ለካፍ የዲሲፕሊን ውሳኔ ምክንያት የሆነውና ሰኔ 7 ቀን 2008 ዓ.ም. የጋናና የኢትዮጵያ ወጣት ብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ በተደረገበት ዕለት የተከሰተውን ሁኔታ አስመልክቶ ለፌዴሬሽኑ የደረሰው ምንም ዓይነት ሪፖርት ከልዑካን ቡድኑ አለመቅረቡ እየተነገረ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የአዲስ አበባ የጤፍ ገበያ

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤፍ የተከሰተውን የዋጋ ንረት...