Wednesday, September 27, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የዓለም ባንክ በታላቁ ህዳሴ ግድብ አደራዳሪ እንዲሆን በግብፅ መጠየቁ ሥነ ሥርዓት የጣሰ መሆኑ ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ የዓለም ባንክ አደራዳሪ እንዲሆን ግብፅ ያቀረበችው ጥያቄ ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን የተስማሙበትን የውይይት ሥነ ሥርዓት የጣሰ መሆኑ ተገለጸ፡፡

በጉዳዩ ላይ እንደሚሳተፍ ባለሙያ አስተያየታቸውን የሰጡት የኢትዮጵያ ተደራዳሪና የሦስቱ አገሮች የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ ጌድዮን አስፋው (ኢንጂነር)፣ የዓለም ባንክ በአደራዳሪነት እንዲሳተፍ በግብፅ መጠየቁ ችግር ባይሆንም ሦስቱ አገሮች ስምምነት ካደረጉበት የውይይት ቅደም ተከተል የጣሰና በተናጠል የቀረበ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የሦስቱ አገሮች የቴክኒክ ኮሚቴ ሳይንሳዊ መርህን በመከተል በሚያደርጉት ውይይት ስምምነት ያልተደረሰበት ጉዳይ ለሦስቱ አገሮች የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች እንደሚመራ፣ በእነዚህ ሚኒስትሮችም ስምምነት ካልተደረሰበት እንዳስፈላጊነቱ ሦስተኛ ወገን እንዲመለከተው ወስነው የሚስማሙበትን ሦስተኛ ወገን ሊሰይሙ እንደሚችሉ አስታውቀዋል፡፡

በመሆኑም ግብፅ የዓለም ባንክ እንደ ሦስተኛ ወገን አደራዳሪ እንዲሳተፍ ያቀረበችው ጥያቄ፣ ከሥነ ሥርዓቱ ያፈነገጠና በተናጠል የቀረበ በመሆኑ ስህተት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

‹‹የዓለም ባንክ አደራዳሪ እንዲሆን መጠየቁ በእኛ በኩል ችግር አይኖረውም፡፡ ነገር ግን ሥነ ሥርዓትን ያልተከተለ ከአደራዳሪነትም በዘለለ ተቋሙ ዳኛ እንዲሆን የመፈለግ አዝማሚያ የታየበት ነው፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ስምምነት ባልተደረሰባቸው ጉዳዮች አደራዳሪ እንዲገባ መጠየቅ የሚቻለው፣ የተቀጠሩት ሁለት አጥኝ ኩባንያዎች ተግባራቸውን ፈጽመው ምክረ ሐሳብ ካቀረቡ በኋለ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ግብፅ በተደጋጋሚ ከውይይት ሥነ ሥርዓቱ ስታፈነግጥ ይታወቃል፡፡ ጉዳዩን በተመለከተ ግብፅ የምታደርገው ጥረት በሙሉ በኢትዮጵያና በሱዳን ጥቅም ላይ የራሷን ጥቅም ለማስከበር ከሚመነጭ ፍላጎት እንደሆነ፣ ይህም የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ፍትሐዊ አጠቃቀምን ለማስከበር በማድረግ ትግል ውስጥ የሚፈጠር እንደሆነ ያምናሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት ድርድሩ የተስተጓጎለ ቢሆንም በነበረበት ሁኔታ በሦስቱ አገሮች የጋራ የቴክኒክ ኮሚቴ ተመልሶ ይቀጥላል የሚል እምነት እንዳላቸው፣ የጋራ መፍትሔ የሚገኘውም በዚሁ መንገድ ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የግብፅን ሚዲያዎች በመጠቀም ጉዳዩን ፖለቲካዊ የማድረግና የትብብር መንፈስን የሚያደፈርሱ አስተያየቶችን የማራገብ እንቅስቃሴን ወቅሰዋል፡፡ ግብፅ ላቀረበችው ጥያቄ የኢትዮጵያና የሱዳን መንግሥታት በይፋ ምላሽ እንደሚሰጡበት ይጠበቃል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች