Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህል‹‹ቶስትማስተርስ›› በአዲስ አበባ ዓውድ

‹‹ቶስትማስተርስ›› በአዲስ አበባ ዓውድ

ቀን:

ወቅቱ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎቻቸውን የሚያስመርቁበት በመሆኑ ምርቃት ነክ ክንውኖች በየቦታው ይስተዋላሉ፡፡ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት የያዘ የአበባ እቅፍና ፖስትካርድ ገበያ ደርቷል፡፡ ተመራቂዎች ሙሉ ልብስ አልያም የምርቃት ጋዋን ለብሰው ወዲያ ወዲህ ይላሉ፡፡ ይህ የምርቃት ድባብ በብሉናይል ቶስትማስተርስ ክለብ አባላትም የተጋባ ይመስላል፡፡ አመሻሽ ላይ ቦሌ በሚገኘው አምባሳደር ሆቴል የክለቡ አባላት ተሰባስበዋል፡፡ ሐምሌ 4 ቀን 2008 ዓ.ም. ቶስት ለማድረግ (ጽዋቸውን ለማንሳት) የመረጡት ዘንድሮ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋሞች ለተመረቁ ተማሪዎች ነው፡፡ የክለቡ አባላት በየሁለት ሳምንቱ ሰኞ ቀን ሲገናኙ ቶስት የሚያደርጉበት ጉዳይ ይኖራል፡፡ በዕለቱም አባላቱ በአጠቃላይ ከመቀመጫቸው ተነስተው የሚጠጡትን ውኃ መያዣ ፕላስቲክ ከፍ በማድረግ ‹‹ለተመራቂዎች መልካሙን ሁሉ እንመኛለን›› ብለዋል፡፡ ብሉናይል ቶስትማስተርስ ክለብ አዲስ አበባ ካሉ ስድስት የቶስትማስትርስ ክለቦች አንዱ ነው፡፡ ቶስትማስተር አጋፋሪ እንደማለት ሲሆን፣ በዓለም ላይ በርካታ የቶስትማስተርስ ክለቦች ይገኛሉ፡፡ በአገራችንም በ1950ዎቹ ብሉናይል ቶስትማስተርስ የተሰኘ ክለብ ነበር፡፡ በክለቡ እንደ ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ፣ ወ/ሮ ሒሩት በፍቃዱና ክቡር ገና ያሉ ታላላቅ ሙያተኞች ነበሩበት፡፡ ክለቡ ለዓመታት ዘልቆ ቢቋረጥም፣ ከአራት ዓመት በፊት ዳግም ተጀምሯል፡፡ በኢትዮጵያ ግንባር ቀደም የቶስትማስተርስ ክለብ እንደሆነ የሚነገርለትን ብሉናይል ቶስትማስተርስ ክለብ ስያሜ ለራሳቸው በመስጠት እንቅስቃሴ ከጀመሩት ወጣቶች በተጨማሪ፣ ጁፒተር ቶስትማስተርስ ክለብ፣ አዲስ አበባ ቶስትማስተርስ ክለብና ኢምፔሪያል ቶስትማስተርስ ክለብ በሚል የሚታወቁ ክለቦችም ይገኛሉ፡፡ ከስምንት አሠርታት በላይ በዓለም ላይ የሚታወቀው የቶስትማስትርስ ክለብ ዋነኛ ትኩረቱን ያደረገው የንግግርና አመራር ችሎታን ማዳበር ላይ ነው፡፡ በየክለቡ ያሉ አባላት የሚከተሉት ዓለም አቀፍ መመርያ አለ፡፡ የየክለቡ አባላት በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ንግግር ያደርጋሉ፡፡ ከሃይማኖትና ፖለቲካ ውጪ ሁሉም ርዕሰ ጉዳዮች ይዳስሳሉ፡፡ የብሉናይል ቶስትማስተርስ ክለብን በጐበኘንበት ዕለት፣ ለተመራቂ ተማሪዎች ቶስት ከተደረገ በኋላ፣ የክለቡ አባላት በአንድ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ድንገት ንግግር እንዲያደርጉ የተጋበዙበት ክንውን ነበር፡፡ ከአባላቱ አንዱ ለንግግር ይሆናሉ ያላቸውን ጉዳዮች መዝግቦ ተናጋሪዎችን ወደ መድረክ ይጋብዛል፡፡ ተናጋሪዎቹ ለመዘጋጀት ያላቸው ጊዜ ስማቸው ተጠርቶ መድረክ ላይ እስኪወጡ ያሉት ሰከንዶች ብቻ ናቸው፡፡ ‹‹አንድ ሰው ከፎቅ ጫፍ ላይ ሆኖ ራሱን ለማጥፋት ሲዘጋጅ ብትደርስ ምን ትለዋለህ?›› ለንግግር ከቀረቡት ነጥቦች አንዱ ነው፡፡ ይህ ክንውን ‹‹ቴብል ቶፒክ›› (የወግ ገበታ) በመባል ይታወቃል፡፡ በቶስትማስተርስ ክለቦች በአንድ ርዕሰ ጉዳይ ንግግር ለማድረግ ተዘጋጅተው የሚገኙ አባሎችም ይስተናገዳሉ፡፡ ንግግሮቹ የሚቀርቡበት መንገድ የዓለም አቀፍ ቶስትማስተርስ ክለብ መመርያን ይከተላል፡፡ መግቢያ፣ ሐተታና መደምደሚያ እንዴት ይቀርባሉ፣ የተናጋሪዎች የሰውነት እንቅስቃሴ ምን መምሰል አለበት የሚሉ ርዕሰ ጉዳዮችና መሰል የንግግር ሥርዓት መርሆች በመመርያው ይገኛሉ፡፡ አንድ ሰው መመርያውን በመከተል የሚያደርጋቸው ንግግሮች ከአንድ ደረጃ ወደ ሌላው ያሸጋግሩታል፡፡ ለምሳሌ አንድ የክለቡ አባል አሥር ንግግሮች እስኪያደርግ ቶስትማስተር (ቲኤም) ተብሎ ይጠራል፡፡ ከአሥረኛ ንግግሩ በኋላ ኮምፒተንት ኮምዩኒኬተር – ሲሲ (ብቁ ተናጋሪ) ይባላል፡፡ በአመራር ችሎታ ኮምፒተንት ሊደር-ሲኤል (ብቁ መሪ) ደረጃ ላይ ይደርሳል፡፡ ይህ ደረጃ የክለቡ አባላት በሚያደርጉት ንግግር መጠን የሚጨምር ሲሆን፣ በዓለም አቀፉ የቶስትማስተርስ መርሕ መሠረት የመጨረሻውን የላቀ ደረጃ ዲስቲንጉሽድ ቶስትማስተር – ዲቲኤም ነው፡፡ ሪፖርተር በታደመው መርሐ ግብር፣ የክለቡ አባል ሚስተር ራዥንድራ ሲንጋህ ስለቀና አመለካከት ንግግር አድርገዋል፡፡ ኮምፒተንት ኮምዩኒኬተር (ሲሲ) ደረጃ የደረሱ ሲሆን፣ ሰዎች ስለሕይወት ቀና አመለካከት እንዲኖራቸው የሚያሳስብ ንግግር አቅርበዋል፡፡ በክለቡ በተለያየ ሙያ መስክ የተሰማሩ ከታዳጊዎች እስከ አዛውንቶች ይገኙበታል፡፡ እነዚህ አባላትም በመርሐግብሩ መጨረሻ በንግግርና የአመራር ብቃታቸው ይመዘናሉ፡፡ የንግግራቸው ድምፀት፣ ይዘት፣ የሰውነት እንቅስቃሴ፣ ሰዓት አጠቃቀምና ሰዋስው ከመመዘኛዎቹ መካከል ይገኙበታል፡፡ የብሉናይል ቶስትማስተርስ ክለብ ፕሬዚዳንት በሱፈቃድ መኩሪያ እንደሚናገረው፣ የቶስትማስተርስ ክለቦች ንግግር የማድረግና የመሪነት ሚናን በብቃት የመወጣት ችሎታ ለማዳበር ሁነኛ መንገድ ናቸው፡፡ ‹‹በአገራችን በ1950ዎቹ የነበረው የቶስትማስተርስ ክለብ ብዙ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች የነበሩበት ነው፡፡ አሁን ባሉት ክለቦችም አባላት ንግግር ሲያደርጉ በመገምገምና ገንቢ አስተያየት በመስጠት የአባላቱ ችሎታ እንዲዳብር ይደረጋል፡፡ በተለያየ የአመራር ዘርፍ በመሰማራት በራስ የመተማመን ብቃትን ለማሳደግም ያግዛሉ፤›› ይላል፡፡ ዓለም አቀፉ የቶስትማስተርስ መመርያ የቶስትማስተርስ ክለብ መቀመጫ ከሆነችው አሜሪካ የአመራርና የንግግር መርሆች ይዞ ለአባላት ይላካል፡፡ እሱ እንደሚለው፣ በመመርያው መሠረት ለአባላት ራስን ከማስተዋወቅ ጀምሮ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ንግግር የማድረግ ዕድል ይሰጣል፡፡ ከክለብ ክለብ የተለያዩ አካሄዶች ቢኖሩም፣ አብዛኞቹን የሚያመሳስሏቸው ክንውኖች አሉ፡፡ ለምሳሌ ለመልካም መንስኤ ጽዋ ማንሳት (ቶስት) እና በተለያዩ ሰዎች የተባሉ አነሳሽ ንግግሮችን መጠቀም ይጠቀሳሉ፡፡ ክለቡ በዓለም ላይ ለዓመታት የብዙዎችን አኗኗር ዘዬ በመለወጥ እንደዘለቀ የሚናገረው ፕሬዚዳንቱ፣ ዘጠነኛ የንግግር ደረጃው ላይ ይገኛል፡፡ ንግግር ለማድረግ ከመረጣቸው ርዕሰ ጉዳዮች ሰልፊ (ራስን በራስ ፎቶ ማንሳትና) የኢትዮጵያ ባህላዊ እሴቶች ይገኙበታል፡፡ የሳይበር ሰኪዩሪቲ ኢንጂነሩ በሱፈቃድ፣ ክለቡ የንግግር ችሎታውን ያዳበረበት እንደሆነ ይገልጻል፡፡ በሥራ ቦታና በማኅበራዊ ሕይወቱም ስለምን ጉዳይ በምን ሁኔታ መናገር እንዳለበት መማሩን ያስረዳል፡፡ ‹‹ሐሳቤን ከመግለጽ የምታቀብ ሰው ነበርኩ፡፡ ክለቡን ከተቀላቀልኩ በኋላ ያመንኩበትን እናገራለሁ፤›› ሲል ይገልጻል፡፡ ብሉናይል ቶስትማስተርስ 20 ቋሚ አባላት ያሉት ሲሆን፣ በየ15 ቀኑ ወደ 50 ታዳሚዎች ይገኛሉ፡፡ ከአባላቱ አንዱ ኮርፖሬት ትሬነርና ኮንሰልታንት ኤባ ተስፋዬ ነው፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች፣ ኢንጂነሮች፣ ዲፕሎማቶች፣ የሕክምና ባለሙያዎችና በሌላ ሙያ የተሰማሩም ከየተሞክሯቸው የሚያደርጉት ንግግር አስተማሪ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ‹‹ሥራዬ ከንግግር ጋር በቀጥታ ስለሚገናኝ ሥራዬን በተሻለ ብቃት ለመወጣት ያግዘኛል፡፡ እያንዳንዱ አባል ለሚያደርገው ንግግር ከሱ ከፍ ባለ ደረጃ በሚገኝ ሰው ተገምግሞ ገንቢ አስተያየት ይሰጠዋል፤›› ይላል፡፡ በተለያየ የአመራር ደረጃ ያሉ አባላት እንቅስቃሴም ይገመገማል፡፡ ከፕሬዚዳንቱ በመቀጠል የአባላትን ብቃት የመከታተልና የሕዝብ ግንኙነትን የመቆጣጠር ኃላፊነት የሚጣልባቸው አባላት አሉ፡፡ አመራር ላይ ያሉ አባላት በየወቅቱ ይለዋወጣሉ፡፡ አንድ ሰው የየትኛውም የቶስትማስተር ክለብ አባል ሲሆን በዓለም አቀፉ ክለብ መዝገብ ይሰፍራል፡፡ የንግግርና አመራር ደረጃዎች መመርያ መጻሕፍት ላይ ያለውን መርህ ተከትሎ በማለፍ ዓለም አቀፍ ሰርተፊኬት ማግኘት ይቻላል፡፡ ኤባ እንደሚለው፣ የንግግርና አመራር ትምህርት በተዋቀረ መልኩ ለማግኘት ከባድ በመሆኑ የቶስትማስተርስ ክለቦች ያስፈልጋሉ፡፡ በቀድሞና በአሁኑ የቶስትማስተርስ ክለብ አባል የሆኑና እንደ ወ/ሮ ሒሩት በፍቃዱ ያሉ ሰዎች ልምዳቸውን የሚያካፍሉበት መድረክ መዘጋጀቱም ጠቀሜታ አለው ይላል፡፡ አሁን በአዲስ አበባ ያሉ የቶስትማስተር ክለቦች በእንግሊዝኛና በአማርኛ መድረኮች ያዘጋጃሉ፡፡ መሰል ክለብ ሐዋሳ ውስጥ እየተቋቋመ እንደሆነም ይነገራል፡፡ ‹‹ቃላት ትልቅ ኃይል አላቸው፡፡ ቃላትን እንዴት መጠቀም እንደሚቻል ማወቁ ለአንድ ሰው ጉልበት ይሰጠዋል፤›› የሚለው ኤባ፣ ሰዎች በቶስትማስተርስ ክለቦች ንግግራቸውን አቃንተው ለበጐ ነገር ማዋል የሚችሉበትን መንገድ እንደሚማሩ ይናገራል፡፡ በተጨማሪም ሰዓት ማክበር ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል፡፡ እያንዳንዱ እንቅስቃሴያቸው ይጀመራል ከተባለበት ሰዓትና ደቂቃ ዝንፍ እንዳይል የተቻለውን ሁሉ ያደርጋሉ፡፡ ‹‹ሶ ዩ ቲንክ፣ ዩ ካን ስፒክ›› (የንግግር ክህሎት ያለዎት ይመስልዎታልን) ዓመታዊ የንግግር ውድድር ነው፡፡ በቅርቡ የውድድሩ ሦስተኛ ዙር የሚካሄድ ሲሆን፣ የቶስትማስትርስ ክለብ አባሎችና ሌሎች ግለሰቦችም ይሳተፋሉ፡፡ የቶስትማስተርስ ክለቦች አባሎች ከውድድሩ በተጨማሪ በየክለቦቻቸው በሚኖራቸው መርሐ ግብርም እርስ በርስ ይገናኛሉ፡፡ ከአንዱ ክለብ ወደሌላው ሄዶ ንግግር ማድረግ የተለመደ ነው፡፡ የጁፒተር ቶስትማስተርስ ክለብ አባል የሆነችው ጽኑ ዐምደሥላሴን ያገኘናት በብሉናይል ቶስትማስተርስ መርሐ ግብር ላይ ነበር፡፡ በ2001 ዓ.ም. ክለቡን የተቀላቀለችው ጽኑ ጠበቃ ስትሆን፣ የዓመታዊው የንግግር ውድድር አዘጋጅ ኮሚቴ አባልም ናት፡፡ የጁፒተር ቶስትማስተርስ ክለብ አባሎች በየ15 ቀኑ እሑድ በጁፒተር ሆቴል ይገናኛሉ፡፡ ጽኑ ‹‹ክለቡ ብዙ ሰዎችን ያወቅኩበትና ጓደኞችም ያፈራሁበት ነው፤›› ስትል ትገልጻለች፡፡ የተለያዩ ኃላፊነቶችን በመውሰድ ስለአመራር ሒደት መማሯን ትናገራለች፡፡ በክለቦቹ መካከል ያለው እርስ በርስ መደጋገፍ እንደሚያስደስትም ታክላለች፡፡ ‹‹ክለቦቹ የሥራ ትስስር ለመፍጠር ይጠቅማሉ፡፡ አባላቱ ለመተባበር ፈቃደኛ ስለሆኑ ብዙ ነገር እንማማራለን፡፡ የዓለም አቀፉ ቶስትማስተርስ ክለብ አባል መሆንም ጠቀሜታው የጐላ ነው፤›› ትላለች፡፡ በቶስትማስተርስ ክለብ የሚገኙ የንግግርና አመራር ደረጃዎችን በገጸ ታሪካቸው (ካሪኩለም ቪቴ) የሚያሰፍሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ በአገራችን በተለያየ ሙያ ዕውቅና ያላቸው ግለሰቦች በ1950ዎቹ ገደማ ንግግር ከሚያደርጉባቸው ቦታዎች ወጣቶች ወንዶች ክርስቲያን ማኅበር (ወወክማ) እና ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍትና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ (ወመዘክር) ይጠቀሳሉ፡፡ ዶ/ር እጓለ ገብረዮሐንስ፣ ዶ/ር የማነ ገብረማርያም፣ ሊቀ ሥልጣናት አባ ሀብተማርያም ወርቅነህና አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ተሳታፊ ከነበሩ ቀደምቶች ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡ የመጀመሪያው የቶስትማስተርስ ክለብ እ.ኤ.አ. በ1924 ራልፍ ሲ ስሜድሊ በተባለ አሜሪካዊ ካሊፎርኒያ ውስጥ ከተቋቋመ በኋላ፣ በ135 አገሮች ወደ 332,000 አባሎችና ወደ 15,400 ክለቦች አፍርቷል፡፡ ከመጀመሪያው ክለብ ጀምሮ በንግግርና አመራር ሒደት እርስ በርስ የመገማገም ልማድ አለ፡፡ ዓለም አቀፉ የቶስትማስተርስ ክለብ የሚመራበት ሕግጋት የወጡት በመሥራቹ ሲሆን፣ በመላው ዓለም በወጥነት ይሠራባቸዋል፡፡ ዓለም ላይ ወደ 40 የሚጠጉ ንግግሮች ካደረጉ በኋላ ትልቁን የቶስትማስተርስ ማዕረግ (ዲስቲንጉሽድ ቶስትማስተር) ያገኙ ወደ 20,000 ይጠጋሉ፡፡ ከእነዚህ አንዱ ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ መሆናቸውም ይነገራል፡፡ የቶስትማስተርስ ክለቦች ኮምዩኒቲ ቤዝድ (ሁሉንም ሰው የሚያሳትፍ)፣ ኮሌጅ ቤዝድ (ተማሪዎችን የሚያሳትፍ) እና ኮርፖሬት ቤዝድ (በድርጅት የሚዋቀሩ) ናቸው፡፡ ብሉናይል ቶስስትማስተርስ ክለብና ጁፒተር ቶስትማስተርስ ክለብ ማኅበረሰብ ተኮር (ኮምዩኒቲ ቤዝድ) ናቸው፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኤአይቲ ቶስትማስተርስ ክለብ ደግሞ ከኮሌጅ ቤዝድ ይመደባል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...