Friday, September 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናማዕከላዊ ወንጀል ምርመራን በወፍ በረር ዕይታ

ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራን በወፍ በረር ዕይታ

ቀን:

ከዳግማዊ ምኒልክ አደባባይ ወደ ሰሜን ማዘጋጃ በሚወስደው በላይ ዘለቀ ጎዳና ጥቂት እንደተጓዙ በስተቀኝ በኩል አንድ ደሴት ላይ ሁለት ዓይነት ፖሊሶች ይገኛሉ፡፡

መጀመርያ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን (ሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ) ቀጥሎ ደግሞ የብዙ ኢትዮጵያውያን እንባና ደም የፈሰሰበት የፌዴራል ወንጀል ምርመራ መምሪያ ማዕከል (ማዕከላዊ) ይገኛል፡፡

በኢትዮጵያ ከ40 ለሚበልጡ ዓመታት የሰቆቃ ማዕከል ሆኖ የቆየው ማዕከላዊ በመጨረሻ ሰሞኑን ሙዚየም እንደሚሆን ተነግሯል፡፡

የኢሕአዴግ ሊቀመንበር አቶ ኃይለ ማርያም ዳሳለኝ ከኢሕአዴግ ብሔራዊ ድርጅቶች ሊቃነ መናበርት ጋር በጋራ ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ፣ ማዕከላዊ ከዚህ በኋላ የምርመራ ማቆያ ሥፍራ ሆኖ እንደማይቀጥልና ሙዚየም ሆኖ እንደሚያገለግል ተናግረዋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ኮማንደር መብራቱ ተስፋ ሚካኤል ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ማዕከላዊ ሙዚየም እንደሚሆን በይፋ ሲነገር ቢሰማም ነገር ግን እስካሁን የወረደ መመርያ የለም፡፡ አሁንም የተጠርጣሪዎች ማቆያ ሆኖ እያገለገለ ነው ብለዋል፡፡

‹‹የቢሮ ጥበት ስላጋጠመው የወንጀል ምርመራ ክፍል ባምቢስ አባባቢ፣ የፎረንሲክ ክፍሉ ደግሞ ኢምግሬሽን አካባቢ ቢሮ ተከፍቶላቸው እየሠሩ ነው፡፡ ማዕከላዊ ግን አሁንም ማቆያ ሆኖ እያገለገለ ነው፤›› ሲሉ ኮማንደር መብራቱ ገልጸዋል፡፡

በሁለተኛው የጣሊያን ወረራ ወቅት በጣሊያን ዲዛይነሮችና ኮንትራክተሮች የተገነባው ማዕከላዊ፣ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ‹‹የፖሊስ ሠራዊት ልዩ ምርመራ›› ተብሎ ይጠራ እንደነበር መዛግብት ይገልጻሉ፡፡

ማዕከላዊ ገብተው በሚደረግባቸው ምርመራ ስቃይ በቀመሱ የመሬት ሥሪት ባለሙያዎች ግምት፣ የማዕከላዊ ጠቅላላ የቦታ ስፋት ስምንት ሺሕ ካሬ ሜትር ይጠጋል፡፡

በማዕከላዊ የተካሄደው ግንባታ በተለይ በጣሊያን ዘመን የተካሄደው ድንጋይ በድንጋይ ሲሆን፣ በውስጡ የምርመራና የማጎሪያ ክፍሎችን ያጨቀ ነው፡፡ አቶ ግርማይ አብርሃ ሐምሌ 2002 ዓ.ም. ‹‹የሚያነቡ እግሮች›› በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጽሐፍ ላይ እንደገለጹት፣ እስረኞች ወዳሉበት ግቢ ለመድረስ ሦስት ቢሮዎችን ማለፍ ግድ ይላል፡፡ ሦስተኛውን በር አቋርጦ የገባ ሰው ሁለት የተከለሉ ግቢዎች መኖራቸውን ይመለከታል፡፡ የላይኛውና የታችኛው ግቢ እየተባሉ የሚጠሩት እነዚህ እስር ቤቶች በድምሩ 21 ክፍሎች የያዙ ናቸው፡፡

የላይኛው ግቢ ከ800 በላይ እስረኞች ይታጎሩበት የነበረ ባለ 12 ክፍሎች ግቢ ነው፡፡ በአንድ ጊዜ ስምንት ሰዎች ብቻ የሚያስተናግዱ አራት መፀዳጃ ቤቶችና ሁለት ሰዎች የሚይዝ መታጠቢያ ቤት ያለው እስር ቤት ነው፡፡

የታችኛው ግቢ ደግሞ በ1971 ዓ.ም. በላይኛው ግቢ ቅርፅ የተሠራና በ1973 ዓ.ም. ከላዩ ላይ ተጨማሪ ቤት የተገነባለት ዘጠኝ ክፍሎች ያሉት ድፍን ግቢ ነው፡፡

በማዕከላዊ እያንዳንዱ የእስረኛ ክፍል ባለብረት መዝጊያና ባለወንፊት የብረት መስኮት እንዲኖው ሆኖ የተሠራ ነው፡፡ በላይኛው ግቢ የእንጨት ንጣፍ ካላቸው ከአንድ እስከ ስድስት ቁጥር በስቀተር ሌሎቹ የሲሚንቶ ወለል ያላቸው መሆኑን አቶ ግርማይ በመጽሐፋቸው አስፍረዋል፡፡

በተለይ በ1970ዎቹ መጨረሻ አካባቢ በወታደራዊው መንግሥት ትዕዛዝ የመንግሥት ኮንትራክተሮች የነበሩት ለአብነት ሕንፃ ኮንስትራክሽን፣ ባቱ ኮንስትራክሽን፣ ኪቤአድና የመሳሰሉት ተቋማት በጋራ ተጨማሪ ክፍሎችን እንደገነቡ ሪፖርተር ያሰባሰበው መረጃ ይጠቁማል፡፡

ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው በማዕከላዊ ምርመራ እየተደረገበት አራት ወራት ከ26 ቀናት ቆይቷል፡፡ ጋዜጠኛ ጌታቸው ያየውን ለሪፖርተር ሲገልጽ፣ ማዕከላዊ በዋናነት ሦስት ክፍሎች አሉት፡፡ የመጀመርያው ሳይቤሪያ ይባላል፡፡ ሳይቤሪያ በምርመራ ወቅት የሚቆይበት ሥፍራ ሲሆን፣ ከመሬት በታች ዝቅ ያሉ ክፍሎች አሉት፡፡ ሳይቤሪያ የተባለበት ምክንያት ተጠርጣሪዎች በብዛት ሲገቡ የሚሞቅ፣ የተመርማሪዎች ቁጥር ሲያንስ ደግሞ እጅግ የሚቀዘቅዝ ሥፍራ በመሆኑ ነው፡፡  

ሳይቤሪያ ዘጠኝ ክፍሎች ሲኖሩት፣ ክፍል ቁጥር ስምንት በአራት ተከፍሎ አንድ ሰው ለብቻው የሚታሰርበት ጨለማ ቤት ነው፡፡

‹‹ሳይቤሪያ ዘግናኙ ክፍል ሲሆን፣ ቁጥር ስምንት ደግሞ ለሕይወት አደገኛ ነው፤›› ሲል ጋዜጠኛ ጌታቸው ይገልጸዋል፡፡

ጋዜጠኛ ጌታቸው እንደሚለው ማዕከላዊ ሰው በሕይወት እወጣለሁ ብሎ የማያስብበት እጅግ አደገኛ ሥፍራ ነው፡፡

ይህ ነው እንግዲህ በስምንት ሺሕ ካሬ ሜትር ያህል ቦታ ላይ አርፎ፣ በጣሊያን ኮንትራክተሮች መሠረቱ ተጥሎ፣ በወታደራዊ መንግሥትና በኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ማሻሻያ ተደርጎበት የበርካታ ኢትዮጵያውያንን ሕይወት የበላው፣ አሰቃቂ አካል ጉዳት ያደረሰው፣ በአሰቃቂ ድብደባና ማሰቃያ ዘዴዎች የኢትዮጵያውያንን ልብ የሰበረ የሰቆቃ ማዕከል፡፡

አቶ ግርማይ አብረሃ በመጋቢት 2006 ዓ.ም. ‹‹ከደርግ ማኅደር›› በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጽሐፍ ላይ ደግሞ የማሰቃያ ዘዴዎችን ተንትነዋል፡፡

በተለይ በአለንጋ፣ በኤሌክትሪክ ሽቦ፣ በአጠና፣ የውስጥ እግር እስከሚበጣጠቅ ድረስ መግረፍ፣ በተበከለ ውኃ መድፈቅ፣ አስሮና አንጠልጥሎ ማቆየት፣ እግር በጩቤ እየቆራረጡ እንዲነፈርቅ ማድረግ፣ እንቅልፍ መከልከል፣ በወንድ ብልት ውኃ ወይም አሸዋ የተሞላ ጠርሙስ ማንጠልጠል፣ በሴቶችም ላይ እጅግ አሰቃቂ ኢሰብዓዊ ጉዳት ማድረስ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ክፍሎቹ በተለያዩ ተውሳኮች ከመሞላታቸው በላይ ብርሃንና  ንፋስ የማይገባባቸው በመሆኑ ሞትን እንደሚያስናፍቅ ይናገራሉ፡፡

በእነዚህ ዘግናኝ ማሰቃያዎች በወታደራዊውም ሆነ በኢሕአዴግ የሥልጣን ዘመን በርካታ ሰቆቃ መድረሱ በተለያዩ መዛግብቶች ከመመዝገቡ ባሻገር ቋሚ በርካታ ምስክርነት ሰጪዎችም አሉ፡፡

ይህ ማዕከላዊ ተቋም በመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎች እንዲዘጋና ወደ ሙዚየምነት እንዲዛወር መወሰኑ ብዙኃኑን ያስደሰተ ቢሆንም፣ ይህንኑ አሰቃቂ የምርመራ ዘይቤ በሌሎች ነባርና አዳዲስ ምርመራ ቦታዎች ላለመካሄዱ መንግሥት በይፋ ዋስትና እንዲሰጥ የሚጠይቁም በርካታ ናቸው፡፡

ጋዜጠኛ ጌታቸው እንደሚያሳስበው ይህ አደገኛ ቦታ በንጉሡ፣ በወታደራዊውና በኢሕአዴግ ዘመን የዜጎች የሰቆቃ ቦታ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ሌላው ትውልድ እንዲያየው መደረጉ መልካም ነው፡፡ ነገር ግን ድብደባና ስቃይ በሌሎችም እስር ቤቶች የሚታይ በመሆኑ እንደሚያሳስበው ይናገራል፡፡ በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ታሪካዊ ዳራውንና የዲዛይኑን ሁኔታ ለመረዳት በርካታ የታሪክ ምሁራንና አርክቴክቶችን ለማነጋገር ቢሞከርም፣ የተሟላ መረጃ አልተገኝም፡፡ አስፈሪውና ዘግናኙ ማዕከላዊ እንደ ታላቅ ወንድሙ የአዲስ አበባ ወህኒ ቤት መዘጋቱ መልካም ሆኖ በሌሎች ቦታዎች እንዳያቆጠቁጥ የሚሠጉ በርካቶች ናቸው፡፡

በአዲስ አበባ የማዕከላዊን ያህል አሰቃቂ የነበረው፣ የማዕከላዊ ታላቅ የሚባለው የአዲስ አበባ ወህኒ ቤት (ከርቸሌ) ነው፡፡

ከርቸሌ ከጣሊያን ወረራ በፊት የተገነባ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመርያው መደበኛ እስር ቤት ነው፡፡ አቶ ግርማይ በመጽሐፋቸው እንዳብራሩት፣ ከርቸሌ ለመጀመርያ ጊዜ ሕጋዊ መሠረት ይዞ እንዲሠራና ተጠሪነቱ ለአገር ግዛት ሚኒስቴር እንዲሆን የተደረገው በ1936 ዓ.ም. ነው፡፡

ከርቸሌ በአጠቃላይ 400 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ስፋት የነበረው ሲሆን፣ በውስጡ የብዙ ኢትዮጵያውያንን ልብ የሰበረው ‹‹ዓለም በቃኝ›› ጎልቶ ይነሳል፡፡ ከዓለም በቃኝ በተጨማሪ የቀጠሮ ክልል፣ የፍርደኛ ክልል፣ የፍትሐ ብሔር ክልልና የሴቶች ክልል  ይገኛሉ፡፡ እስረኞች ከሚገኙባቸው ከእነዚህ ክልሎች በተጨማሪ የቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን፣ የሙስሊሞች መስጊድና የተለያዩ አገልግሎት መስጫዎች አሉ፡፡

ከእነዚህ ሁሉ ዘግናኙ ዓለም በቃኝ የተሰኘው ማሰቃያ ሲሆን፣ በዚህ ቦታ በርካታ ተስፈኞች ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ የአካልና የመንፈስ ስብራትም የደረሰባቸው በርካቶች ናቸው፡፡

ይህ አዲስ አበባ ወህኒ ቤት ያለበት ቦታ ለአፍሪካ ኅብረት ማስፋፊያ ያስፈልጋል ተብሎ እስር ቤቱ ሙሉ ለሙሉ ተነስቷል፡፡ በውስጡ የነበሩት እስረኞችም ወደ ተለያዩ ማረሚያ ቤቶች ተዘዋውረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በምርመራ ስም የሚደረግ ኢሰብዓዊ የምርመራ ዘዴ እንዲቀር፣ ዕውቀትን መሠረት ያደረገ ለሰብዓዊ መብቶች ትኩረት የሚሰጥ ሥልት ተግባራዊ እንዲደረግ የሚጠይቁ በርካቶች እንደ መሆናቸው፣ መንግሥት ሌሎች ማሰቃያዎችን ይዝጋ፣ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ምርመራ ይጀመር ይላሉ፡፡

እርግጥ ሆኖ ማዕከላዊ ከሦስት መንግሥታት በኋላ ሙዚየም የሚሆን ከሆነ ማን ያስተዳድረዋል? የሚለው ጥያቄ ለአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ገብረ ፃዲቅ ሐሰሳ በሪፖርተር ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር፡፡

እሳቸውም ሙዚየም የመሆኑን ዜና ከሚዲያ እንደሰሙ፣ ሙዚየሙ በፌዴራል ይተዳደር? ወይስ በአዲስ አበባ? የሚለው ጉዳይ በቀጣይ የሚታይ እንደሚሆን በመግለጽ ዝርዝሩን ለመናገር እንደሚቸገሩ ገልጸዋል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...