Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ስፖርትስሜት የሚመራው የክለቦች መዋቅር

ስሜት የሚመራው የክለቦች መዋቅር

ቀን:

የእግር ኳስ ክለቦች ቁጥር ጭማሪም፣ ቅናሸም እየታየበት አንዳንዶቹ እየከሰሙ ጥቂቶቹ እየበቀሉ ቢመጡም፣ ስሜታዊነት በታከለበት የግለሰቦች ውሳኔ የፈረሱ ክለቦች አልታጡም፡፡ በተለይ በድርጅት ወይም በኩባንያ ባለቤትነት የተቋቋሙ ክለቦች አንድ እክል በገጠማቸው ቁጥር ለማፍረስ በሚሽቀዳደሙ አመራሮች ህልውናቸው ያከተመ ክለቦችን መቁጠር የአደባባይ ሚስጢር ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡

ከሰሞኑን የመፍረስ አደጋ የተጋረጠበት የኢትዮጵያ መድን ድርጅት እግር ኳስ ክለብ ለዚህ ማሳያ መሆኑ አይቀርም፡፡ የክለቡ አመራሮች ለአንድ ዓመት ሲንከባለል በቆየው የአሠልጣኝ አሥራት ኃይሌ ስንብት ጉዳይ ላይ ባደረባቸው ቅሬታ ምክንያት የመጨረሻ ዕርምጃቸው ቡድኑ በሥሩ የሚተዳደሩ፣ ማለትም ዋናውን ቡድን፣ ዕድሜያቸው ከ20 እና ከ17 ዓመት በታች ቡድኖችን ማፍረስ እንደሆነ ይፋ አድርገዋል፡፡

የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በሦስቱ ቡድኖች አማካይነት ከ100 በላይ በስፖርቱ የታቀፉ ስፖርተኞችንና ባለሙያዎችን እንደሚያስተዳድር ጠቅሶ፣ በብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ተፈጸመብኝ ያለው በደል ካልተፈታና የተጣለበት ዕገዳ ካልተነሳለት በቀር ለዚህ ሁሉ ደመወዝ እየከፈለ ያለውድድር የሚቆይበት ምክንያት እንደማይኖር፣ በዚህም ክለቦቹን እንደሚያፈርስ አመራሩ አስታውቋል፡፡

- Advertisement -

አመራሩ ታኅሣሥ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. በድርጅቱ ዋና መሥሪያ ቤት በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ውሳኔ የሕግ አካሄድን ያልጠበቀና የሕግ መሠረት የሌለው፣ ከአገሪቱ የእግር ኳስ ዕድገት ይልቅ ለግለሰቦች ጥቅም ያደላ፣ ስፖርቱ የሚመራበትን ደንብና መመርያ የደፈጠጠ መሆኑን በመጥቀስ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አስረድቷል፡፡

መግለጫውን የሰጡት የክለቡ ፕሬዚዳንት አቶ ተምትም ቶላ እንደሚናገሩት ከሆነ፣ አሠልጣኝ አሥራት ኃይሌን በተመለከተ የቡድኑ ቴክኒክ ኮሚቴ መጋቢት 3 ቀን 2006 ዓ.ም. ባደረገው ግምገማ ቡድኑ በሚሰጠው ሥልጠና ደረጃውን የጠበቀ ካለመሆኑም በላይ ውጤታማ እያደረገው አይደለም፡፡ ይህንኑ መነሻ ያደረገው የክለቡ አመራር አሠልጣኙና ክለቡ በስምምነት መለያየት የሚችሉትን ሁኔታ ለማመቻቸት ጥረት አድርጎ የነበረ ቢሆንም፣ ጉዳዩ በአሠልጣኙ በኩል ተቀባይነት ሊያገኝ አለመቻሉን ጭምር በመግለጫው ተካቷል፡፡

እንደ ክለቡ ፕሬዚዳንት፣ አመራሩ ሰኔ 5 ቀን 2006 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ የቡድኑ ውጤት እንዲሻሻልና የተፎካካሪነቱም አቅም እንዲጨምር በሚል ለአሠልጣኙ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያዎች ተሰጥተዋል፡፡ በዚህም የቡድኑ ውጤትም ሆነ የተፎካካሪነት አቅሙ ሊለወጥ ባለመቻሉ ውሉ እንዲቋረጥ አድርጎ ውሳኔው በአምስት ቀን ውስጥ ለአሠልጣኙ እንዲደርስ መደረጉን ይናገራሉ፡፡

መግለጫው ሲቀጥል፣ በክለቡ ውሳኔ ያልተስማሙት አሠልጣኝ አሥራት፣ ጉዳዩን ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዲሲፕሊን ኮሚቴ ክስ መመሥረታቸው፣ ይኼው የሁለቱ ወገኖች ክርክር ከዲሲፕሊን ኮሚቴው ወደ ፌዴሬሽኑ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ደርሶ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴውም ከዲሲፕሊን ኮሚቴው ውሳኔ በተቃራኒ አሠልጣኙ ወደ ሥራ ገበታቸው ተመልሰው፣ ያልተከፈላቸው ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም እንዲከፈላቸው ስለመወሰኑ ጭምር ያብራራል፡፡ ክለቡ የፌዴሬሽኑ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ያሳለፈው ውሳኔ በፌዴሬሽኑ የዲሲፕሊን መመርያ አንቀጽ 20 ቁጥር አንድ መሠረት ይግባኝ መቅረብ ያለበት ቀደም ሲል በተጠቀሰው ውሳኔ ቅሬታ ያለው ወገን ውሳኔው በተሰጠበት በሦስት የሥራ ቀናት ውስጥ ነው፣ የሚለውን በመጣስ፣ ከ20 ቀናት በኋላ መሆኑን በመጥቀስ እንዳልተቀበለው በመግለጫው አስረድቷል፡፡ ይሁንና ፌዴሬሽኑ ጥቅምት 22 ቀን 2008 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ መድን እግር ኳስ ክለብ በጻፈው ደብዳቤ ዕግድ መጣሉ አይዘነጋም፡፡

ድርጅቱ ጥቅምት 26 ቀን 2008 ዓ.ም. ቅሬታው ለወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር እንዳቀረበ፣ ሚኒስቴሩም የክለቡንና የፌዴሬሽኑን አመራሮች በመጥራት ካነጋገረ በኋላ የፌዴሬሽኑ ውሳኔ ትክክል እንዳልሆነ ስምምነት ላይ ተደርሶ ዕገዳው እንዲነሳ መደረጉን የክለቡ አመራር በመግለጫው ይፋ አድርጓል፡፡

በውሳኔው ያልተስማሙት የቡድኑ አሠልጣኝ ጉዳዩን እስከ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አድርሰውት ውድቅ ሆኗል፡፡ ይሁንና ጉዳዩ እንደገና ለሁለተኛ ጊዜ አገርሽቶ ከታኅሣሥ 12 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ታኅሣሥ 9 ቀን ፌዴሬሽኑ በቁጥር ኢ.እ.አ9/1718 በተጻፈ ደብዳቤ ክለቡ እንደታገደ የተገለጸለት መሆኑን አስታውቋል፡፡ በክለቡ በኩል ቀደም ሲል በጉዳዩ ዙሪያ የተደረሰበት ስምምነቶችንና ከጉዳዩ ጋር የተያየዙ ደብዳቤዎችን በማካተት ጭምር ለፌዴሬሽኑ በማሳወቅ ውሳኔውን እንደገና እንዲያጤን መጠየቁን ጭምር የክለቡ አመራር በመግለጫው ይፋ አድርጓል፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መድን ድርጅት እግር ኳስ ክለብ አመራሮችም ሆኑ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ለስፖርቱ ሲባል ካላስፈላጊ ንትርክና እሰጣ ገባ ወጥተው በእግር ኳሱ ሕግና ደንብ ሊመሩ እንደሚገባ የሚመክሩ በርካታ ናቸው፡፡

  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...