Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊሕፃናት ላይ ያነጣጠሩ ማስታወቂያዎች

ሕፃናት ላይ ያነጣጠሩ ማስታወቂያዎች

ቀን:

በካፌው የነበሩት ተጠቃሚዎች በየጠረጴዛቸው ጨዋታ ይዘዋል፡፡ በአንዱ ጠረጴዛ ዙሪያ ከልጃቸው ጋር ወደ ካፌው ያመሩ ጥንዶች ይገኛሉ፡፡ ልጁ ካፌው ውስጥ ወዲያ ወዲህ ሲል በዓይናቸው ይከታተላሉ፡፡ ታዳጊው ካፌው ውስጥ ያለውን የአይስክሬም ፍሪጅ ተዘዋውሮ ካየ በኋላ ወደ ወላጆቹ ቀርቦ እንዲገዛለት ጠየቀ፡፡ ቤተሰቦቹ ግን ፈቃደኛ አልነበሩም፡፡ ሕፃኑ ለምኖ ተለማምጦም እንደማይፈቀድለት የገባው ይመስል ተመልሶ ሄደ፡፡ ነገር ግን ትንሽ ቆየት ብሎ እንደገና እንዲሰጡት የቦታውን አስተናጋጅ ይጠይቃል፡፡ ቤተሰቦቹ ሳያዩት ወደ ፍሪጁ ይሄድና የማረከውን ፍሌቨር አስተናጋጆቹም ይሰጡታል፡፡ የልቡ የተሳካለት ሕፃን አይስክሬሙን እየላሰ ወደ ቤተሰቦቹ ጠረጴዛ ሄደ፡፡ በሁኔታው የተበሳጩት ቤተሰቦች ልጃቸውን ተቆጥተው ወዲያው አስተናጋጆቹን ጠርተው ማናገር ጀመሩ፡፡

ወላጆቹ ሕፃናት የሚፈልጉትን ነገር ሲያዙ የቤተሰብ ፈቃድ ሳይጠየቅ መስጠቱ ተገቢ እንዳልሆነ አስተናጋጆቹን ያስረዱ ነበር፡፡ ልጁ አለርጂ፣ ቶንሲል ወይም ሌላ ችግር ቢኖርበት ሊፈጠር የሚችለውን ሁኔታ ሁሉ እየጠቀሱ ለማስረዳት ሞከሩ፡፡ በመጨረሻ ግን ንግግራቸው መግባባት ያመጣ አይመስልም፡፡

ልጆች ዓይናቸው የገባ ምግብም ይሁን ማንኛውም ነገር እንዲገዛላቸው ከመጠየቅ ወደኋላ አይሉም፡፡ በጤናቸው ላይ ሊያስከትል የሚችለው ጉዳት ወይም የቤተሰባቸው የመግዛት አቅም ለእነሱ ጥያቄ አይደለም፡፡ ዕድሜያቸው ብዙ መጠየቅ ያለባቸውን ጥያቄዎች እንዳያነሱ ያደርጋቸዋልና ስለዚህም ለሕፃናት ከሚሸጡ፣ ከሚሰጡና ከሚተዋወቁ ነገሮች ጋር የቤተሰብ ሐሳብና ይሁንታ ያስፈልጋል፡፡

ምርቶቻቸው በየትኛውም መንገድ እንዲሸጡላቸው የሚፈልጉ አምራቾች ወይም አከፋፋዮች ደግሞ የልጆችን ያልተገናዘበ ፍላጐት ሊጠቀሙበት ሲሞክሩ ይስተዋላል፡፡ የሕፃናት ፍላጐት፣ የሻጭ ግብና የቤተሰብ ቁጥጥር በምን መንገድ ሊጣጣሙ ይችላሉ? የሚለውን ጥያቄ እዚህ ጋር ማንሳት ይቻላል፡፡ ምርቶች ገበያ እንዲያገኙ በማስቻል ትልቁን ድርሻ የሚወስደው የማስታወቂያ ሥራም ተመሳሳይ ጥያቄ ውስጥ ይወድቃል፡፡ በመገናኛ ብዙኃን ወይም በመሸጫ ቦታዎች ምርቶች ለሕፃናት ሲተዋወቁና ሲቀርቡ ስለሚከተሉት መንገድ የተለያዩ አስተያየቶች ይሰነዘራሉ፡፡

በማማለል ቤተሰብ ምርቶችን እንዲሸምት ልጆች እንዲጎተጉቱ ማድረግ ከሙያዊ ሥነ ምግባር ያፈነገጠ እንደሆነ የሚናገሩ ወላጆች አሉ፡፡ ምርትን በአግባቡ በማስተዋወቅና በማማለል መካከል ያለው መስመር እንዳልተለየ የሚገልጹም አሉ፡፡ በካፌው ውስጥ የነበሩት አስተናጋጆች ምርታቸውን መሸጥ ስላለባቸው አይስክሬሙን የጠየቃቸው ሕፃንን ዕድሜ ከግምት ሳያስገቡ ሰጥተውታል፡፡ ከቤተሰቦቹ ፈቃድ ያገኘ ወይም የተላከ ቢመስላቸውም ቤተሰቦቹ ደግሞ ጉዳዩን በተቃራኒው ተመልክተውታል፡፡

የሁለት ልጆች እናት የሆነችው ወ/ሮ ሔለን መስፍን ለልጆች የሚዘጋጅ ማንኛውንም ምርት የሚሸጡ ሲያስተዋውቁ ጥንቃቄ መውሰድ አለባቸው ትላለች፡፡ ‹‹መንገድ ላይ ያሉ ሻጮችና የተለያዩ የልጆች መገልገያዎች የሚያቀርቡ መደብሮች ማስታወቂያ ለወላጆች መረጃ የሚሰጥ እንጂ አስገዳጅ መሆን የለበትም፤›› ትላለች፡፡ መንገድ ላይ ፊኛ፣ የፊልምና የሕፃናት መዝሙር ሲዲ ያለፈቃዷ ለልጆቿ የሚሰጡ ነጋዴዎች በየቦታው ገጥመዋታል፡፡ ልጆች ያዩት ስለሚያምራቸው ዕቃዎቹ ባያስፈልጓቸው ወይም የነበራቸው ቢሆንም እንዲገዛላቸው ይወተውታሉ፡፡ በአንድ ቀን ሁለት ፊኛ የገዛችባቸው ቀኖች ብዙ ናቸው፡፡ በሻጮችና ልጆቿ ጉትጐታ የሲንደሬላና ሚኪማውዝ ፊልሞችን በተደጋጋሚ ገዝታለች፡፡ በመገናኛ ብዙኃን የሚተዋወቁ መዝናኛ ቦታዎች ካልሄድን ብለው ልጆቿ ያለቀሱባቸው ጊዜያትንም ታስታውሳለች፡፡

መንገድ ላይ የተለያየ ሸቀጥ የሚሸጡ ግለሰቦች ቦታ እንደማይመርጡ ትናገራለች፡፡ በእምነት ቦታዎች፣ትምህርት ቤቶችና መኖሪያ አካባቢ ይገጥሟታልና ቤተሰብ ያለ ዕቅዱ ለልጆቹ እንዲገዛ የሚገደድባቸው አጋጣሚዎች እንዳሉ ታስረዳለች፡፡ ‹‹በልጆች መዝናኛ ፓርኮች ወይም ገበያ አካባቢ ቢሸጡ ወላጅ ፈልጓቸው ይሄዳል፡፡ በየቦታው ሲሸጡ ግን ልጆቼ ሁሌ እንዲገዛላቸው ይጠይቃሉ፡፡ ስከለክል ልጆቼ ያዝናሉ፡፡ የልጆቼን ስሜት ማሟላት እንደማልችል እንዲሰማኝም ያደርጋል፤›› በማለት ታስረዳለች፡፡

በመገናኛ ብዙኃን የሚተላለፉ ማስታወቂያዎች ወላጆች የሚተዋወቀውን ነገር ካልገዙ ልጆቻቸው እየተጐዱ እንደሆነ ማስመሰል እንደሌለባቸው ታስረዳለች፡፡ በተለይ ከጤና ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያላቸው እንደ ምግብና ዳይፐር ላሉት ጥንቃቄ ሲወሰድ አይታይም ትላለች፡፡ ምርቶች ለልጆች የሚሰጡት ጠቀሜታ ተጋኖ ሲቀርብ ምርቶቹን ከመግዛት ይልቅ ጥርጣሬ ውስጥ ይከቷታልና ማስታወቂያ የበዛባቸውን ምርቶች አትመርጥም፡፡ ወላጅ አዳዲስ ስለመጡ መጫወቻዎች ወይም መዝናኛ ቦታዎች መረጃ እንዲኖረው ማስተዋወቅ ቢያስፈልግም፣ ለቤተሰብ እውቀት ማስጨበጥና ሕፃናትን ማታለል መካከል ያለው ልዩነት መታወቅ አለበት ስትል ትገልጻለች፡፡

አቶ ጌትነት ጥላሁን ግን የተለየ ሐሳብ አላቸው፡፡ የአምስት ልጆች አባት ሲሆኑ፣ ልጆቻቸው የሚጠቀሙባቸውን መገልገያዎች የሚመርጡት ልጆቻቸው ናቸው፡፡ በእሳቸው እምነት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ ላይ፣ በመገናኛ ብዙኃን፣ በትምህርት ቤትና በሠፈር ሱቅም ስለተለያዩ ምርቶች ማስታወቂያ ይሠራል፡፡ እነዚህ በስፋት የሚተዋወቁ ምርቶቹ በቀላሉ ይገኛሉ፡፡ ልጆቻቸው እንዲገዛላቸው የሚፈልጉትም እነዚህን ነው፡፡ ምርቶች መታወቃቸው ደግሞ ስለምርቶቹ ጥሩነት እርግጠኛ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡

ልጆች የሚበሉትና የሚጠጡትን፣ የሚዝናኑበትን ቦታ፣ የሚለብሱትን ልብስ፣ መማሪያ ደብተራቸውንና የምሳ ዕቃ ምርጫዎቻቸውን ከማስታወቂያ ተጽእኖ ለማላቀቅ እንደማይቻል ይሰማቸዋል፡፡ ማስታወቂያዎች በመገናኛ ብዙኃን ሲተላለፉ ወላጆች ለመከላከል ቢሞክሩም፣ ልጆቹ በተለያየ መንገድ መረጃውን ያገኙታል፡፡ ‹‹በማስታወቂያ አይተው ወይም ከሰው ሰምተው የሚመርጧቸውን ምርቶች እገዛለሁ፡፡ ይህ ማለት ፍላጐታቸው ላይ ገደብ አልጥልም ማለት አይደለም፡፡ አያስፈልጓቸውም ብዬ የማምንባቸውን ነገሮች አልገዛም፤›› ይላሉ፡፡ ውሳኔያቸው በልጆቻቸው ቅሬታ ማሳደሩ እንደማይቀር ግን ያክላሉ፡፡  

ልጆች ተኮር ማስታወቂያዎችን በተመለከተ ከቤተሰቦች የተለያዩ አስተያየቶች ሲሰነዘሩ፣ በአገር ደረጃ ማስታወቂያዎቹን መስመር ለማስያዝ የሚደረጉ ጥረቶችም አሉ፡፡ አንዳንድ አገሮች የሕፃናት ተኮር ምርቶችን ማስታወቂያ ሙሉ በሙሉ ሲያግዱ፣ በመገናኛ ብዙኃን የሚተላለፉበትን ሰዓት የሚገድቡና ልጆችን በዕድሜ በመከፋፈል የአንዳንድ ምርቶችን ማስታወቂያ የሚከለክሉ አገሮችም አሉ፡፡ ሕፃናት የአንድን ምርት ጠቀሜታ ወይም የማስታወቂያን ምንነት ሳይገነዘቡ ቤተሰቦቻቸው እንዲገዙ የሚጠይቋቸው ነገሮች የሚያስከትሉት ጉዳት ላይ ጥናት የሠሩ ባለሙያዎችም አሉ፡፡

ለምሳሌ አምና ዘ ጋርዲያን ባወጣው ዘገባ አንድ ልጅ በዓመት ከ16,000 በላይ ማስታወቂያዎች በቴሌቪዥን ከማየቱ ጐን ለጐን መጓጓዣዎች፣ መንገዶችና ትምህርት ቤቶች ለማስታወቂያ ያጋልጡታል፡፡ ምርቶች የሚተዋወቁበት መንገድ ልጆችን የማሳመን ጉልበት ቢኖረውም የአንዳንዶቹ ምርቶች ጥራት ጥያቄ ያስነሳል፡፡ የአኒሜሽን ፊልም ገፀ ባህሪዎችና በሕፃናት የሚወደዱ ሙዚቀኞች በማስታወቂያ ይካተታሉ፡፡ ለሕፃናት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ቢተዋወቁም፣ ማስታወቂያቸው የማይገልጻቸው ምርቶች አይታጡም፡፡ ሕፃናትን ለአደጋ የሚያጋልጡ መዝናኛ ቦታዎች ወይም ለልጆች ጤና የማይስማሙ ምግቦች ሲተዋወቁ የመንግሥት ጣልቃ መግባት አስፈላጊ ይሆናል፡፡

ወ/ሮ ሜሊያ ዮሐንስ እንደምትናገረው፣ ማስታወቂያዎች በአጠቃላይ የሚሠሩት ሰዎችን አሳምኖ እንዲገዙ ለማድረግ በመሆኑ የልጆች ምርቶች ማስታወቂያዎች የተለየ ይሆናሉ ማለት አይቻልም፡፡ የአንድ ልጅ እናት ስትሆን፣ ልጇ በማስታወቂያዎች በመገፋፋት እንድትገዛለት የሚጠይቃት ነገሮች ጥቂት እንደሆኑ ትናገራለች፡፡ የወደዳቸው ምርቶች ማስታወቂያዎች ይዘት ልጆችን የሚያሳምን እንደሆነ ብታስተውልም፣ እሷም በምርቶቹ ስለምታምንባቸው ትገዛለታለች፡፡ መንገድ ላይ ሲሄዱ ያለዕቅዷ እንድትገዛ የሚጠይቀውን ግን አትፈቅድለትም፡፡

እሷ እንደምትለው፣ ወላጆች የማስታወቂያዎችን ተጽእኖ መቀነስ የሚችሉት ልጆቻቸውን ለማሳመን ሲሞክሩ ነው፡፡ ‹‹አንድን ሕፃን ይኼ ይሆንሃል ወይም አይጠቅምህም ብሎ ማስረዳት ከባድ ቢሆንም እንደየዕድሜያቸው በተለያየ መንገድ ስለነገሮች ማስረዳት ይቻላል፤›› ትላለች፡፡

በአገሪቱ ያሉ የጐዳናና የመገናኛ ብዙኃን ልጆች ተኮር ማስታወቂያዎች የሚያስከትሉት ወጪ የአብዛኛውን ማኅበረሰብ አቅም እንደማያገናዝቡ ታምናለች፡፡ ቤተሰቦች ልጆቻቸውን ይዘው መንገድ ላይ ለመሄድ እስኪሳቀቁ ድረስ አላሳልፍ የሚሉ ሻጮች ይገጥማሉ፡፡ የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ጣቢያ በተቀየረ ቁጥር ያለሰዓት ገደብ ማስታወቂያዎች ይለቀቃሉ፡፡ አካሄዱ እንዲስተካከል ቤተሰብና የሚመለከታቸው አካላት መተባበር እንዳለባቸው ትናገራለች፡፡  

ማስታወቂያዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ባለማድረግ ሳቢያ፣ ልጆች ጤናማ ላልሆነ አመጋገብ የተጋለጡባቸው አገሮች አሉ፡፡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ ብዙ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በማስታወቂያ የሕፃናትን ቀልብ ለመግዛት እንዲችሉ የሥነ ልቦና ባለሙያዎችና ተመራማሪዎች ያማክራሉ፡፡ የልጆች መገልገያዎች ማስታወቂያ በሚሊዮኖች የሚወጣበት ሲሆን፣ በእጥፍ ገቢ የሚያገኙበት ድርጅቶች አሉ፡፡ ከጀማሪ እስከ ስኬታማ ነጋዴዎች በዘርፉ ቢጠቀሙም የማስታወቂያዎቻቸው ጉዳይ የብዙ አገሮች መነጋገሪያ ነው፡፡

የ20 ዓመቱ የመንገድ ላይ አዝዋሪ ተፈራ ታሪ ከሆሳዕና ወደ አዲስ አበባ የመጣው የተሻለ ሕይወት ፍለጋ ነው፡፡ ቀላልና ትርፋማ ሆኖ ያገኘው ሥራ የሕፃናት መገልገያዎች መሸጥ ሲሆን፣ ላለፉት አራት ዓመታት ራሱን እያስተዳደረበትም ነው፡፡ ያገኘነው አንበሳ ግቢ አካባቢ ሲሆን፣ ሕፃናት የሚያዘወትሩት አካባቢ በመሆኑ እንደመረጠው ይናገራል፡፡

ተፈራ እንደሚለው፣ እንደእሱ ካሉ ጀማሪ ነጋዴዎች እስከ ትልልቆቹ ምርታቸው እንዲሸጥ የተለያየ መንገድ መጠቀማቸው አይቀሬ ነው፡፡ ‹‹አስፋልት ዳር የቆምኩት ለመሸጥ ነው፡፡ እንጀራዬ ስለሆነ ሕፃናት ሲያልፉ ፊኛ፣ ማክስ፣ ጡሩምባ በመስጠት ወላጆች እንዲገዙ አደርጋለሁ፤›› ይላል፡፡ በሚከተለው መንገድ ከወላጆች ጋር የሚጋጭበት ጊዜ አለ፡፡ ‹‹ልጆች ወላጆቻቸውን እንዲያስቸግሩ ወይም እንዲያለቅሱ ባልፈልግም ትኩረታቸውን የማገኝበት መንገድ ስለሆነ እጠቀመዋለሁ፤›› ይላል፡፡

የማስታወቂያ አዋጅ 759/2004 ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆችን አመለካከት የሚጐዱ ማስታወቂያዎች በብሮድካስት እንዳይተላለፉ ይከለክላል፡፡ በቤተሰብ፣ በማኅበረሰብና በትምህርት ተቋሞች እምነት እንዲያጡ የሚያደርጉ እንዲሁም ቤተሰቦች ምርት እንዲገዙ ተጽእኖ የሚያደርጉና የገዙ ካልገዙት የተሻሉ እንደሆኑ የሚያስመስሉ ማስታወቂያዎች አይፈቀዱም፡፡ ማስታወቂያዎች ላይ ሕፃናት ተዋንያንን መጠቀምም በአዋጁ መሠረት ክልክል ነው፡፡

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት ማስተባበር ኃላፊ አቶ ወርቅነህ ጣሰው እንደሚናገሩት፣ በማስታወቂያ አዋጁ ላይ ያሉትን ሕግጋት ጥሰው የተገኙ ድርጅቶችና መገናኛ ብዙኃን ማስጠንቀቂያ ይሰጣቸዋል፡፡ እስካሁን ሕጉን በመጣሳቸው ፍርድ ቤት የደረሱ ኬዞች የሉም፡፡ ‹‹እስካሁን ሕፃናት ተኮር ማስታወቂያዎች ላይ የጐላ ችግር አልገጠመንም፡፡ በብሮድካስት ሚዲያ ግን አንዳንድ ክፍተቶች አሉ፤›› ይላሉ፡፡

ሕፃናት ተዋናይ የሆኑበት የወተት ማስታወቂያ፣ ታዳጊዎችን ለአልኮል መጠጥ የሚገፋፉ ማስታወቂያዎችና አዋቂዎች የሚገለገሉባቸው ምርቶችን በሕፃናት ተዋንያን ማስተዋወቅ ከገጠሟቸው መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ለእነዚህ ማስጠንቀቂያ እንደሰጡና ማስታወቂያዎቹ መስተካከላቸውን ኃላፊው ይናገራሉ፡፡ መሥሪያ ቤታቸው ከኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ጋር በመተባበር ግንዛቤ ከማስጨበጥ ጀምሮ ችግሮች እንዲታረሙ እንደሚሠራም አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ