በሽታው ከተከሰተ አምስት አሥርታት ያለፈ ቢሆንም እስካሁን ድረስ ፈውስ ሊገኝለት አልቻለም፡፡ ለታማሚዎችና ለተመራማሪዎች ትልቅ ተስፋ የሆነው ፀረ ኤችአይቪ መድኃኒት እስኪገኝ ድረስ ኤድስ ሚሊዮኖችን ቀጥፏል፣ እስካሁንም 70 ሚሊዮኖችን ደርሷል፡፡ ሥርጭቱ ከፍተኛ በሆነበት ወቅት እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ከሰሃራ በታች የሚገኙ አገሮችን የሞት ቀጣና እስከማድረግ ደርሶም ነበር፡፡
በሽታው በየመንደሩና በየቤቱ ገብቶ ሕፃናትን ወላጅ አልባ አድርጓል፡፡ ከቫይረሱ ጋር የሚወለዱ ጨቅላ ሕፃናትም የበሽታው ሌላኛው አስከፊ ገጽታ ነበሩ፡፡ በአጠቃላይ ኤችአይቪ እንደማንኛውም ዓይነት በሽታ ሳይሆን በአስፈሪ የሞት መንፈስ እንዲመሰል አድርጎት ነበር፡፡
ይኽም ሰዎች እርስ በርስ እንዳይተማመኑ፣ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ዜጎች ከሌላው ማኅበረሰብ ተገለው እንዲኖሩ አድርጓል፡፡ የሚያስታምማቸው አጥተው በየጎዳናው የወደቁ ዜጎች ብዙ ነበሩ፡፡ ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸውን የሚያሳይ ሰርተፍኬት ማቅረብም የጋብቻ ቅድመ ሁኔታ የነበረበት ወቅት ሩቅ አይደለም፡፡ በአጠቃላይ ኤችአይቪ የማኅበረሰቡን የአኗኗር ዘይቤ የቀየረ በታሪክ የማይዘነጋ አሁንም ያለ ክስተት ነው፡፡
ሚሊዮኖችን እንደ ቅጠል ያረገፈው በሽታው የዓለም የመገናኛ ብዙኃን አጀንዳ ሆኖ ብዙ ቆይቷል፡፡ በኢትዮጵያ የቫይረሱ ሥርጭት ከፍተኛ በሆነበት ወቅት ሥርጭቱ እስከ 16 በመቶ፣ በአንዳንድ የኅብረተሰቡ ክፍሎች ደግሞ እስከ 23 በመቶ ደርሶ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ በየትምህርት ቤቱ፣ በየቀበሌውና በየጎጡ በተሠሩ የተለያዩ የዘመቻ ሥራዎች፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞች ሥርጭቱ በከፍተኛ መጠን ቀንሶ ወደ 1.2 እንዲወርድ ተደርጎም ነበር፡፡ ይህ ትልቅ እምርታ የሚባል ቢሆንም ወረርሽኙ የማገርሸት አዝማሚያ ማሳየቱ ድንጋጤን ፈጥሯል፡፡
በፌዴራል ኤችአይቪ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽሕፈት ቤት (ሃብኮ) የዘርፈ ብዙ ምላሾች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ክፍሌ ምትኩ፣ ኤችአይቪ አሁንም በኢትዮጵያ ትልቅ ችግር እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ‹‹እ.ኤ.አ. ከ1980 እስከ 1990 የድንጋጤና የጨለማ ዘመን ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. 2000 ላይ ደግሞ የቫይረሱ ሥርጭት በጣም ከፍተኛ የነበረበት ነበር፡፡ ነገር ግን በተሠሩ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እ.ኤ.አ. በ2010 ሥርጭቱ በጣም ሊቀንስ የቻለበት ወቅት ነበር፤›› የሚሉት አቶ ክፍሌ፣ በወቅቱ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎችን ቁጥር በ90 በመቶ፣ የሚሞቱትን ደግሞ በ70 በመቶ መቀነስ መቻሉን ይናገራሉ፡፡
ለዚህም የተለያዩ ዓለም አቀፍና አገር በቀል ተቋማት ኤችአይቪን ቀዳሚ አጀንዳቸው አድርገው መሥራታቸው ትልቁን ሚና መጫወቱ፤ ሥርጭቱን ከመቆጣጠር ባለፈ ኤችአይቪ በኅብረተሰቡ ዘንድ የሞት ፍርድ መሆኑ ቀርቶ ከማንኛውም በሽታ የተለየ እንዳልሆነ ተደርጎ እንዲታሰብ አድርጎታል፡፡
እ.ኤ.አ. በ2030 ኤችአይቪን ከዓለም ጨርሶ ለማጥፋት ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ ባለበት በአሁኑ ወቅት ግን በኢትዮጵያ ኤችአይቪ የማገርሸቱ ዜና ይሰማል፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ ማኅበረሰቡ ስለበሽታው ያለው ግንዛቤ ማሽቆልቆሉ የጉዳዩን አሳሳቢነት ከፍ አድርጎታል፡፡ በተሠሩ የዳሰሳ ጥናቶች ስለ በሽታው ግንዛቤ ያላቸው ሴቶች 18 በመቶ፣ ወንዶች ደግሞ 31 በመቶ ብቻ መሆናቸው ይፋ የተደረገው ከዓመት በፊት ነበር፡፡
በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ከ722,248 ሺሕ በላይ ዜጎች ከቫይረሱ ጋር አብረው ይኖራሉ፡፡ ከነዚህ መካከል ተመርምረው ራሳቸውን ያወቁት 62 በመቶ ብቻ ሲሆኑ፣ መድኃኒቱን እየወሰዱ የሚገኙት ከእነዚህ 64 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው፡፡ በየዓመቱ ደግሞ 27,000 አዲስ ኬዞች ይመዘገባሉ፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ያለው የበሽታው ሥርጭትም ከነበረው አሻቅቧል፡፡ በብዛት የሚጠቁትም ከ15 እስከ 24 የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች መሆናቸው ጉዳዩን ይበልጥ አሳሳቢ እንደሚያደርገው አቶ ክፍሌ ይናገራሉ፡፡
የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በቅርቡ ይፋ ባደረገው ሪፖርት፣ እ.ኤ.አ. ከ2015 እስከ 2021 ድረስ ባሉት ዓመታት በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በቤንሻንጉል ጉምዝ፣ በትግራይ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች፣ በአፋር ክልሎችና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የቫይረሱ ሥርጭት መጠን እየቀነሰ ይሄዳል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ በሐረር፣ በጋምቤላ፣ በሶማሌ ክልሎችና በአዲስ አበባ የሥርጭት መጠኑ እየጨመረ እንደሚሄድ ሪፖርቱ ያትታል፡፡ ከፍተኛ የሥርጭት መጠን በተመዘገበባት በአዲስ አበባ እ.ኤ.አ. በ2015 ሥርጭቱ 4.9 በመቶ የነበረ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. በ2021 ወደ 5.2 ከፍ እንደሚል ተገምቷል፡፡
ጉዳዩን ውስብስብ እንዲሆን ካደረጉ አጋጣሚዎች መካከልም መድኃኒቱን ጀምረው የሚያቋርጡ ሰዎች መኖር ዋነኛው ነው፡፡ ጀምሮ ማቋረጡ መድኃኒት የተላመደ ቫይረስ እንዲስፋፋ መንገድ እየከፈተ እንደሚገኝ ጉዳዩም አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ከቀናት በፊት በፌዴራል ሀብኮና በኤኤችኤፍ አማካይነት በሳፋየር ሆቴል ተዘጋጅቶ በነበረው የውይይት መድረክ ላይ ተነስቷል፡፡
በአሁኑ ወቅት መሠረታዊ መዘናጋት ይታያል፡፡ ጉዳዩ እንደ ቀድሞ የዘመቻ ሥራ የሚጠይቅ ቢሆንም ለአንድ ሴክተር ብቻ ተትቷል፡፡ በዚህ ሁኔታ ኤችአይቪን እ.ኤ.አ. በ2030 ለማጥፋት የተያዘው ዕድቅ የሚሳካበት ዕድል ጠባብ ይሆናል፡፡ ዕቅዱን ለማሳካት በንቃት ሊሠራበት እንደሚገባ፣ ኤችአይቪ መደበኛ የሥራ አካል ሆኖ ሊወጣ እንደሚገባው አቶ ክፍሌ ይናገራሉ፡፡ ዓለም አቀፍ ተቋማት ዕርዳታን ከመጠበቅም በአገር ውስጥ ያሉ አማራጮችን መጠቀም ዘላቂ መፍትሔ እንደሚሆንም አክለዋል፡፡ ለዚህም የተለያዩ ሴክተሮች ከሚመደብላቸው በጀት የተወሰነውን ለኤችአይቪ እንዲያውሉ በሚል መንግሥት ያስቀመጠውን አቅጣጫ መከተል አማራጭ የሌለው አካሄድ እንደሚሆን አቶ ክፍሌ እምነታቸው ነው፡፡
‹‹ሦስተኛ ደረጃ መድኃኒት የሚወስዱ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው፡፡ መድኃኒቱን የተቋቋመ የቫይረሱ ሥርጭት በየክልሉ እየበዛ ነው፡፡ ለዚህም መድኃኒቱን ማቋረጥና መልሶ የመጀመር ነገር መለመዱ ዋናው ምክንያት ነው፤›› ያሉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውስጥ ደዌና የተላላፊ በሽታዎች ስፔሻሊስቱ ዶ/ር ወንድወሰን አሞኘ ናቸው፡፡ መድኃኒቱን የተላመደ ቫይረስ ላለባቸው ታካሚዎች መድኃኒት ለመስጠት ባለው እጥረት እንደሚቸገሩም ተናግረዋል፡፡
‹‹የቫይረሱን ሥርጭት መግታት የሚቻለው ማኅበረሰባዊ የባህሪ ለውጥ በማምጣት ነው፤›› የሚሉት ዳይሬክተሩ፣ በየትምህርት ቤቱ ተወርዶ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን መሥራት እንደሚያስፈልግ፣ የሃይማኖት አባቶችም ቀድሞ የነበራቸውን ሚና እንዲጫወቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ጉዳዩ ትኩረት ተደርጎ ካልተሠራበት የአገሪቱን ኢኮኖሚ የሚያዳክም መሆኑን ‹‹በአሁኑ ወቅት 64 በመቶ ብቻ የሚሆኑ የቫይረሱ ተጠቂዎች ናቸው ፀረ ኤችአይቪ መድኃኒቱን የሚጠቀሙት፡፡ ለእነሱ በየዓመቱ 2.4 ቢሊዮን ብር ይወጣል፡፡ ሁሉም ራሳቸውን አውቀው የመድኃኒቱ ተጠቃሚ ቢሆኑ ደግሞ በዓመት ለመድኃኒቱ የሚወጣው ወጪ ወደ 5.4 ቢሊዮን ብር ያድጋል፡፡ ሥርጭቱ በዚህ መጠን እያደገ የሚሄድ ከሆነ የአገሪቱ በጀት ወዴት ሊዞር እንደሚችል ግልጽ ነው፤›› በማለት አቶ ክፍሌ ከወዲሁ ርብርብ ተደርጎ ሊሠራበት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡