Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርት‹‹አፄዎቹ›› ፕሪሚየር ሊጉን አልመዋል

‹‹አፄዎቹ›› ፕሪሚየር ሊጉን አልመዋል

ቀን:

ከ17ኛው እስከ 19ኛው ምታመት አጋማሽ የኢትዮጵያ መዲና የነበረችው ዕድሜ ጠገቧ ጎንደር ከአፄ ፋሲል እስከ ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ የበርካታ ነገሥታትና መሳፍንት መቀመጫ ነበረች፡፡

ከ19ኛው ምታመት መገባደጃ በኋላ በዳግማዊ ምኒሊክ ዘመን የማዕከላዊው መንግሥት መቀመጫነት አዲስ አበባ ብትወስድም፣ ጥንታዊቷ ጎንደር ከነበራትና ካላት ታሪክና ቅርስ ጋር እየተቆራኘ ስሟ ይነሳል፡፡ የያኔው የታሪክ አሻራዎቿ ዛሬም እንደፈኩ ከአገሪቱም አልፎ የጎንደር ምልክትና መለያ እንደሆኑ አሉ፡፡

አሁን ድረስ ነዋሪዎቿ ከተማቸውን የነገሥታት ከተማነቷን ለማጉላት ‹‹የአፄዎቹ›› ከተማ በማለት ሲጠሯት ራሳቸውንም ቢሆን ‹‹የአፄዎቹ›› ልጆች በማለት ሲገልጹ ይደመጣሉ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ይህንኑ ታሪካዊ ዳራነት ዛሬ ድረስ ለመለያ ስያሜነት በስፖርት እንቅስቃሴ ሳይቀር እየተጠቀሙበት እንደሚገኙ አንዱ ማሳያ የጎንደር ከተማን በመወከል በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ተሳታፊው ፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለባቸውን አቆላምጠው ይጠቀሙበታል፡፡ በከተማዋ ያሉ ወጣቶች ፋሲል ከነማ ከማለት ይልቅ ‹‹አፄዎቹ›› በማለት ክለቡንም ሆነ ተጫዋቾችንና ደጋፊዎችን ለመጥራት ይጠቀሙበታል፡፡ ለዚህ ደግሞ በጎንደር ከተማ መሀል በሚገኘው ብቸኛ ስታዲየም ተፎካካሪውን እንግዳ ክለብን ሲያስተናግድ ‹‹የአፄዎቹ ልጆች›› የተባሉት ደጋፊዎች ፋሲል ከነማን ‹‹አፄዎቹ›› ብለው በመጥራት በዜማ ሲያወድሷቸው፣ በጭፈራና ጭብጨባ ሲያበረቱ ማየት አንዱ ማስረጃ ነው፡፡ ከራሳቸው ሜዳም አልፈው ቡድናቸው በተለየዩ ከተሞች በሚያደርገው ጨዋታ ተከትለው በመሄድ ሲያወድሱና ሲያበረታቱም ይታያሉ፡፡

‹‹የጎንደር ወጣት፣ ሕፃን አዋቂ ሳይል ሁሉም ነዋሪ ቀልቡ በሙሉ ከአፄዎቹ ከፋሲል ከነማ ጋር ሆኗል፡፡ አፄዎቹ በልቡ ውስጥ ያልገቡበት የጎንደር ነዋሪ ፈልጎ የሚገኝ አይመስለኝም፤›› በማለት የክለቡ የደጋፊዎች ማኅበር የአባላት አሰባሰብና አደረጃጀት ተወካዩ አቶ ግዛቸው ወንድይፍራው ለሪፖርተር ይገልጻል፡፡

በአሁኑ ወቅት የክለቡን ደጋፊዎች በቁጥር ለመግለጽ እንደሚቸገር የሚናገረው አቶ ግዛቸው፣ በየሦስት ዓመት የሚመረጠው የደጋፊዎች ማኅበር አመራር ግን ባለፉት ሁለት ዓመታት የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች ለማብዛት ባደረገው ጥረት የተገኘውን ውጤት ‹‹ክለቡን በሁሉም ቤት እንዲገባ ማድረግ ችለናል›› በማለት ያስረዳል፡፡

በአገሪቱ ከጥቂት ክለቦች በስተቀር አብዛኞቹ የደጋፊዎች ምች የመታቸው የሚመስሉ መኖራቸው ይታወቃል፡፡ ከጥቂት ክለቦች ቋሚ አባላት ካላቸው በስተቀር አብዛኞቹ ዘላቂ ደጋፊ የሌላቸው መሆኑ ይታያል፡፡

በደጋፊ ብዛትና ጥንካሬ አንጻር ለብዙ ዓመት ጎልተው በአንፃራዊነት መዝለቅ ስለመቻላቸው ሊጠቀሱ የሚችሉ ሁለቱ የአዲስ አበባ ባላንጣዎች ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና ሲሆኑ፣ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ግን የተሻለ ዕድገት እያስመዘገቡ ነው ሊባሉ የሚችሉ እንደ ሐዋሳ ከነማ፣ ሲዳማ ቡና፣ አርባ ምንጭ ከነማና አዳማ ከነማ ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህም ቢሆን የክለባቸው ደጋፊ ብዛትም ሆነ ጥንካሬ ክለቦቹ በፕሪሚየር ሊጉ ላይ መሳተፍ ከመቻላቸው ጋር የተያያዘ መሆኑ የአገር ውስጥ ተንታኞች ሲናገሩ ይሰማል፡፡

በጎንደር የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች ግን ገና ክለቡ ከታችኛው ሊግ እያለ ከዋናው የፕሪሚየር ሊጉ ተሳታፊ ከሆኑ የክለብ ደጋፊዎች በሚስተካከል መልኩ ክለባቸውን ሲደግፉ ይታያሉ፡፡

በደማቅ ቀይና ነጭ ቀለማት የተዋበ መለያውን ከመልበስ ባሻገር በተመሳሳይ ቀለማት አዘጋጅተው የሚያውለበልቡትን ዓርማ ለሚመለከት፣ ይህ ቡድን በሁለተኛው የከፍተኛው ሊግ የሚጫወት ቡድን ሳይሆን በዋናው የአገሪቱ ሊግ ተሳታፊ ያስመስለዋል፡፡

ተጨዋቾችም ሆኑ ደጋፊዎች በአንገታቸው ላይ የሚያደርጉት ፎጣ (ስካርፍ) የስፔኑን አትሌቲኮ ማድሪድ መለያ ጀርሲ በመመልከት ያዘጋጁት ሊሆን እንደሚችል ግምት ሊያጭር ይችላል፡፡

እነ ግዛቸው ግን መልስ አላቸው፡፡ ‹‹እኛ አትሌቲኮ ማድሪድ አይደለንም ወይም የሌላ ክለብ ደጋፊዎች አይደለንም፡፡ እኛ አፄዎቹ ነን›› በማለት የአፄነታቸውንና የመለያ ቀለማቸውን ትስስር ይገልጻሉ፡፡ ምክንያቱን አስመልክቶም፣ ‹‹ክለባችን ፋሲል ከነማ የተባለው የአፄ ፋሲልና የከተማችንን ትስስር የሚያሳይ በመሆኑና ከአፄ ቴዎድሮስ ጋር የተገናኘ በመሆኑም ጭምር ነው፤›› በማለት የመለያው ቀለም ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ቀይና ነጭ ቀለማት የነበሩትን የጊዜው የንጉሡን አልባሳት በማስታወስ መሆኑን ይገልጻል፡፡

ግዛቸውም ሆነ ሌሎች በከተማዋ የሚገኙ የክለቡ ደጋፊዎች ክለባቸው ወደ ዋናው ፕሪሚየር ሊግ አድጎ በ2009 ዓ.ም. በመሳተፍ የጎንደር ተወካይ ሆኖ ለማየት ፍላጎታቸውን ይገልጻሉ፡፡ በተለይ ክለቡ አሁን ካለበት ወቅታዊ አቋምና ደረጃ አንጻር ህልማቸው ዕውን ሊሆን የተቃረበ ተስፋ እንደሆነላቸውም ያስረዳሉ፡፡

ፋሲል ከነማ አሁን ወደፕሪሚየር ሊጉ ለመግባት ፉክክር እያደረገበት ካለው ምድብ፣ 50 ነጥብ ካለው የወልድያ ከተማ በሁለት ነጥብ ዝቅ ብሎ በሁለተኝነት እየተከተለ ይገኛል፡፡ ቡድኑ ቀድሞ በሙገር፣ ኒያላ፣ ወንጂ ስኳር እንዲሁም ከ20 ዓመት በታች ለብሔራዊ ቡድን በተጫዋችነት ባሳለፉት ዘማሪያም ወልደጊዮርጊስ አሠልጣኝነት ግስጋሴውን በመቀጠል በቅርቡ ወደ ፕሪሚየር ሊግ እንደሚያድግ ተስፋ አላቸው፡፡

‹‹ቡድኔ እንደቡድን በአንድነት በመጫወትና ወጥ በሆነ መንገድ መዋቀር በመቻሉ በጥሩ አቋም ላይ እንገኛለን ብዬ አምናለሁ፤›› ሲል ዋና አሠልጣኝ ዘማሪያም ወልደጊዮርጊስ በተጫዋቾቹ እምነት እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡

ቡድኑ በአብዛኛው በወጣቶች የተገነባ ሲሆን፣ የቡድኑ አማካይ ዕድሜ በ20ዎቹ መጀመሪያ ላይ መሆናቸውን የሚገልጹት አሠልጣኙ፣ ‹‹ያላቸውን ችሎታና ወኔ ስመለከት በትክክልም ለፕሪሚየር ሊጉ የሚመጥኑ ብቻ ሳይሆን ክለቡ ከዓመታት በፊት በዋና ሊግ ሊሳተፍ ይገባው እንደነበር ማየት ይቻላል›› ብለዋል፡፡

በአብዛኛው ደጋፊዎችም እንደ አሠልጣኙ በቡድን የሚሠራውን ሥራ ቢስማሙበትም የደጋፊዎችን ልብ በተናጠል በመግዛት ረገድ ተከላካዩን ከድር ኬሬዲን ያህል ቀድሞ ስሙ የሚነሳ የለም፡፡

እነዚሁ ደጋፊዎች ከድር የተባለውን የቡድናቸውን ተከላካይ በተለየ መልኩ ሊያወድሱት የቻሉበት ደግሞ የተከላካዩ ታጋይነት፣ ችሎታ፣ ወጥ አቋሙንና ከምንም በላይ አመለሸጋነቱ መሆኑን የደጋፊ ማኅበር አመራሩም ሆነ ሌሎች አባላቱ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹በእኔ ከድር ጎበዝ፣ ደፋር፣ ፀባዩ ያማረ ተጫዋች መሆኑን ለመናገር ቃል ያጥረኛል፡፡ የልቤን ደስታ የሚያረካልኝ ተጫዋች ነው›› ሲል አቶ ግዛቸው በተጫዋቹ ላይ ያለውን እምነት ይገልጻል፡፡

አሠልጣኙም ቢሆን ስለ ለተጫዋቹ የተሰጠውን ምስክርነት ይስማማበታል፡፡ በተለይ በወጥ አቋሙና በአመለሸጋነቱ፣ ‹‹ስለችሎታውም ሆነ ስለማይዋዥቅ አቋሙ የማትጠራጠርበት ተጫዋች ነው፡፡ ከሦስት ዓመታት በላይ ሳያርፍ፣ ሳይዋዥቅ ከመጫወቱ በላይ ባለፉት ሁለት ዓመት አንድም ጊዜ ቢጫ ካርድ እንኳ አይቶ አያውቅም፤›› በማለት ለተከላካዩ ያለውን አድናቆት ይገልጻሉ፡፡ በዚህ ብቻ ስለተከላካዩ ‹‹ምርጥነት›› መግለጽ ያልተቆጠበው አሠልጣኝ ዘማሪያም፣ ‹‹በሁለት ዓመት ውስጥ ያሳረፍኩ ሁለት ጨዋታዎችን ብቻ ነው፤›› በማለት የተጫዋቹን ጠንካራነት ይናገራል፡፡

የአፄዎቹ የጥንካሬ ቁልፍ

ፒያሳ ተብሎ በሚጠራው የከተማዋ ዕምብርት በሚገኘው ሴንትራል ካፌ፣ የፋሲል ከነማ ደጋፊ የሆነው አምዴ ምሕረቱ፣ ከጓደኞቹ ጋር የክለቡን ደጋፊዎች በቅፅል ስማቸው እየጠራ ቀደም ብለው የተከናወኑ ጨዋታዎችን ይተነትናል፡፡ የ20 ዓመቱ አምዴ ከተቀመጠበት የፕላስቲክ ወንበር ከጀርባው ወዳለው ግንብ ዞሮና ጣቱን አሹሎ፣ ‹‹እኛማ ስድስቱን ጨዋታ አንጠብቅም›› በማለት ክለቡ በቅርቡ ፕሪሚየር ሊግ የሚያስገባውን ነጥብ እንደማያሳጣ በልበ ሙሉነት ይገልጻል፡፡

ብዙዎቹ የክለቡ ደጋፊዎች እ.ኤ.አ. በ1979 በዩኔስኮ ዓለም አቀፍ ቅርስ ሆኖ የተመዘገበው ይኸው የፋሲል ግንብ ለፋሲል ከነማ ተጫዋቾች እንደ ቅፅል መለያ ስም ይጠቀሙበታል፡፡

ለአፄዎች የእስካሁኑ ጉዞና ስኬት ክለቡን በፋይናንስና በቴክኒክ ድጋፍ በሚያደርጉለት የከተማው አስተዳደር፣ ደጋፊዎቹና ተባባሪዎቹ ባሳዩት ጥረት መሆኑን የክለቡ የደጋፊዎች ማኅበር አመራሮችና አሠልጣኙ ዘማሪያም ያስረዳሉ፡፡ በከተማዋ የሚገኘው የዳሽን ቢራ ፋብሪካ በበኩሉ ከእያንዳንዱ የቢራ ሽያጭ ከሳጥን ከሚገኘው ገንዘብ ሁለት ብር ለፋሲል ከነማ ድጋፍ ያደርጋል፡፡

እንዲሁም የጎንደር ዩኒቨርሲቲም ድጋፍ አልተለየውም፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ለፋሲል ከነማ የፋይናንስ፣ የቁስና የቴክኒክ እገዛ ማድረጉ፣ ተቋሙ ለኅብረተሰቡ ከሚያደርጋቸው አገልግሎቶች አንዱ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

‹‹ዩኒቨርሲቲያችን ለኅብረተሰብ የሚጠቅም የኮርፖሬት ማኅበራዊ ኃላፊነቶች የሚያደርገው እገዛ ወጣቶችን ለማነቃቃት፣ ከአልባሌ ሱሶች ለማራቅና በተሻለ ስፍራ ጊዜያቸውን እንዲያሳልፉ እገዛ ያደርጋል ብሎ በማመኑ ለክለቡ ድጋፍ ለማድረግና ቡድኑ ሕዝባዊነት እንዳለው ለማነቃቃት ጭምር በማሰብ ነው፤›› በማለት የዩኒቨርሲቲውን ድጋፍ አስረድተዋል፡፡

በቅርቡም ከአንድ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር ከ80 በላይ ኳሶች፣ የክለቡን ስም የሚገልጽ መለያ፣ ቁምጣ ገምባሌና የግጭት መከላከያ ከውጪ አገር በማስመጣት ለክለቡ ማስረከባቸውንም ፕሬዚዳንቱ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በተለይ ክለቡ በፕሪሚየር ሊግ ለመጫወት ከቻለ ዩኒቨርሲቲው በራሱ ከሚያደርገው የገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ በራሱ ተነሳሽነት ክለቡን ሊረዳ የሚችልበትን አማራጭ በማስፋት የሀብት ማሰባሰብ፣ ስፖንሰር የማፈላለግና ሌሎች አጋዥ ነገሮች ለማድረግ ቃል መግባቱን ጨምረው ዶ/ር ደሳለኝ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ክለቡ የራሱ የሆኑ ተሽከርካሪዎች የሌሉት በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው በጊዜያዊነት መንቀሳቀሻ የሚሆኑ አንድ አውቶቡስና ፒክአፕ ተሽከርካሪ እንዲጠቀሙበት ማድረጉን ደግሞ የክለቡ አሠልጣኝና የደጋፊዎች ማኅበር ተወካይ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

አሠልጣኙ ዘማሪያምና የደጋፊ ማኅበሩ አመራር አቶ ግዛቸው ለሪፖርተር እንደገለጹት ከሆነ፣ ዩኒቨርሲቲው ለክለቡ እያደረገ ያለው ዕገዛ በቡድኑ ተጫዋቾችም ሆነ በከተማዋ ነዋሪዎች ትልቅ መነቃቃት በመፍጠሩ ለአፄዎቹ የድል ጉልበት ሆኖታል፡፡

ደጋፊዎቹም ቢሆን ይህንን የሚያንፀባረቁት ሲሆን ክለቡ ጨዋታ ሲኖረው  የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ መምህራን፣ ሠራተኞች እንዲሁም ተማሪዎቹ በጨዋታው ሲታደሙ፣ ደጋፊዎች ‹‹መማር ያስከብራል፣ አገርን ያኮራል፤›› በሚሉ ዜማዎች የአድናቆትና የምስጋና መልዕክቶችን ሲያስተላልፉ ተደምጠዋል፡፡

ፋሲል ከነማ 50 ነጥብ ካለው የወልዲያ ከነማ በሁለት ነጥብ ልዩነት እግር በእግር በመከተል ፕሪሚየር ሊጉን ለመቀላቀል ተስፋው እያደገ የመጣ ቢሆንም፣ ገና ስድስት ጨዋታዎች ይቀረዋል፡፡ በተጠናቀቀው የዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ የነበረው ዳሸን ቢራ ክለብ ወደ ከፍተኛው ሊግ መውረዱ ተረጋግጧል፡፡ በሚቀጥለው ዓመት ጎንደር በአዲሱ ቡድን ደጋፊዎቹ ‹‹አፄዎቹ›› በሚሉት ፋሲል ከነማ ትወከል ይሆን? እነ ግዛቸው ተስፋቸውን ይገልጻሉ፣ ‹‹… ምክንያቱም አፄዎቹ እኛ ነን፡፡ በድጋሚ አፄዎች በጎንደር ይነግሣሉ፤›› ሲል ግዛቸው ፊቱን ወደ ታላቁ የፋሲል ግንብ በማዞር እምነቱን ይገልጻል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...