Saturday, January 18, 2025
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ለየት የሚያደርገን ሰሊጥን በብቸኝነት ወደ ደቡብ ኮሪያ መላካችን ነው››

አቶ ይትባረክ ዘገየ፣ የዋርካ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ

ተወልደው ያደጉት በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ ነው፡፡ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርታቸውን በአክሱም ከተማ በመማር ላይ እያሉ በድንገት ታላቅ ወንድማቸውን ፍለጋ በ1966 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ ይመጣሉ፡፡ አቶ ይትባረክ ዘገየ፣ አዲስ አበባ በመጡበት ወቅት አብዮቱ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ላይ የነበረበት፣ ልጅ እንዳልካቸው መኰንን ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በተሾሙበትና ‹‹ጉልቻ ቢለዋወጥ ወጥ አያጣፍጥም›› በማለት ተቃውሞ ቀርቦባቸው፣ እሳቸውን ተክተው ከሁለት ወራት ላልበለጠ ጊዜ ልጅ ሚካኤል እምሩ የተሾሙበት ወቅት መሆኑንም ያስታውሳሉ፡፡ ወንድማቸው ወደ ደሴ ሲሄዱ እሳቸውም ተከትለው በመሄድ ወርቅ ቤት ተቀጥረው መሥራት መጀመራቸውን፣ በደሴ ብዙም ሳይቆዩ ወደ አሰብ በመሄድ ባጠራቀሙት ገንዘብ ወርቅ ቤት ከፍተው ደርግ እስከወደቀበት ጊዜ እዚያው በንግድ መሥራታቸውን ይናገራሉ፡፡ የደርግ መንግሥት ከወደቀ በኋላ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ዋርካ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የሚል ድርጅት መሥርተው በእርሻ ኢንቨስትመንት ላይ በመሰማራት ዛሬ አስመጪና ላኪ በመሆን ከታዋቂ ነጋዴዎች መካከል አንዱ ሆነዋል፡፡ የ56 ዓመቱ ሥራ እንጂ ሚዲያ ላይ መቅረብ አልወድም ቢሉም፣ ባለትዳርና የአራት ልጆች አባት የሆኑትን አቶ ይትባረክ፤ ታምሩ ጽጌ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- አሰብ ብዙ ዓመታትን እንዳሳለፉ ገልጸውልኛል፡፡ በምን ሥራ ላይ ነበር የተሰማሩት?

አቶ ይትባረክ፡- አሰብ ትንሽ ወርቅ ቤት ነበረችኝ፡፡ ደሴ በነበርኩበት ጊዜ ሥራ የጀመርኩት ወርቅ ቤት በመቀጠር ነው፡፡ ለበርካታ ዓመታት አሰብ ላይ ስሠራ ከቆየሁ በኋላ፣ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ምክንያት ወደ አዲስ አበባ መጣሁ፡፡ እዚህም ወርቅ ቤት ነበረኝ፡፡ የወርቅ ንግድ ብዙም አስደሳች ስላልነበርና መንግሥት ለአገር ውስጥና ለውጭ አገር ባለሀብቶች የተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በመስጠቱ፣ እኔም የወርቅ ንግድ ተውኩና ወደ እርሻ ገባሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ እርሻ የገቡት መቼ ነው? የእርሻ ቦታዎትስ የት ነው?

አቶ ይትባረክ፡- ወደ እርሻ የገባሁት በ1986 ዓ.ም. ነው፡፡ መሬት የወሰድኩትም በትግራይ ክልል ሁመራ ነው፡፡ እንግዲህ ላለፉት 24 ዓመታት በእርሻ ልማት ላይ ተሰማርቼ እየሠራሁ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ያህል ሔክታር መሬት ወሰዱ? የሚያመርቱት የሰብል ዓይነት ምንድነው?

አቶ ይትባረክ፡- የወሰድኩት የእርሻ ቦታ አንድ ሺሕ ሔክታር ነው፡፡ የማመርተው የቅባት እህሎችንና አንዳንዴም ሌሎች አዝዕርትን ነው፡፡ ሰሊጥና ሱፍ በዋናነት የምናመርታቸው የቅባት እህሎች ሲሆኑ፣ ማሽላ፣ ማሾ (ምስርን የሚተካ ነው) እናመርታለን፡፡

ሪፖርተር፡- የሚያመርቷቸውን የቅባት እህሎችና ሌሎች ምርቶችን የሚሸጡት ለአገር ውስጥ ነጋዴዎች ነው ወይስ ወደ ውጪ ይልካሉ?

አቶ ይትባረክ፡- መጀመርያ የማመርታቸውንና ከአካባቢው አምራቾችም የምገዛውን ለአዲስ አበባ ነጋዴዎች አቀርብ ነበር፡፡ ነገር ግን አሁን አሠራሬን ቀይሬያለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ምንድነው የቀየሩት? ወደ ሌላ የሥራ ዘርፍ ተሰማርተዋል ማለት ነው?

አቶ ይትባረክ፡- አዎ ወደ ሌላ የሥራ ዘርፍም ገብቻለሁ፡፡ አሁን ዋና ሥራዬ ላኪነት ነው፡፡ ይህ ማለት ግን የእርሻ ሥራዬን ትቻለሁ ማለት አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- በዋናነት ወደ ውጭ የሚልኩት ምንድነው?

አቶ ይትባረክ፡- የቅባት እህሎችን ነው፡፡ ሰሊጥ፣ ኑግና ጥራጥሬዎችን በብዛት እንልካለን፡፡

ሪፖርተር፡- የት የት አገር ይልካሉ?

አቶ ይትባረክ፡- እንደሚታወቀው በዓለም ላይ በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ ግዢ የሚፈጽም አገር ቻይና ነው፡፡ በአብዛኛው የምንልከው ቻይና ነው፡፡ እኔ በብቸኝነት የምልከው ደቡብ ኮሪያ ነው፡፡ ሌሎች ላኪዎች ወደሚልኩበት አገሮች ቻይና፣ ጃፓንና ሌሎችን አገሮችን ጨምሮ በብቸኝነት እንልካለን፡፡ ዓረብ አገሮችም እንዲሁ፡፡ አልፎ አልፎ አሜካም እንልካለን፡፡

ሪፖርተር፡- በዓመት ምን ያህል ቶን ይልካሉ?

አቶ ይትባረክ፡- በዓመት ከ30 ሺሕ እስከ 40 ሺሕ ቶን ድረስ እንልካለን፡፡

ሪፖርተር፡- ከላኪነት በተጨማሪ በአስመጪነት ሥራ ላይም እንደተሰማሩ ሰምቻለሁ፡-

አቶ ይትባረክ፡- ትክክል ነው፡፡ በዋናነትና ትኩረት ያደረግነው በላኪነት ሥራ ላይ ስለተሰማራን እንጂ፣ የአስመጪነት ሥራም እየሠራን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ምንድነው የሚያስመጡት?

አቶ ይትባረክ፡- የምናስመጣው ሞተር ሳይክሎችን ነው፡፡ ሞተር ሳይክሎቹን ዝም ብሎ ማስመጣት ሳይሆን የሞተር ሳይክል ክፍሎችን በማስመጣት እዚሁ እንገጣጥማለን፡፡ ማከፋፈልም ጀምረናል፡፡ በቀጣይም ሌላ ዕቅድ አለን፡፡ እዚሁ አገራችን ውስጥ ሁሉንም ነገር በማምረት ሙሉ በሙሉ የአገር ውስጥ ምርት ለማድረግም እየሠራን ነው፡፡ አሁን ለጊዜው እየገጣጠምን ለአገር ውስጥ ነጋዴዎች እያከፋፈልን ነው፡፡ ገጣጥመን ለመላክ ከሱዳንና ሌሎች ጎረቤት አገሮች ጋር ስምምነት እየፈጸምን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከወርቅ ንግድ ወደ እርሻ፣ ወደ ላኪነትና አስመጪነት ሥራ ተሰማርተው እየሠሩ ነው፡፡ መነሻ ካፒታልዎ ስንትና ከየት የተገኘ ነው?

አቶ ይትባረክ፡- መነሻ ካፒታሌ ዜሮ ነበር፡፡ ሥራ ከመጀመሬ በፊት ምንም አልነበረኝም፡፡ አንድ ሰው መጀመርያ ጥሮ፣ ግሮና ሠርቶ እንደሚያገኝ እንደሚያድግና ወስኖ ከተነሳ ከዜሮ ተነስቶ ትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ እንደሚችል አምናለሁ፡፡ ዋናው ዓላማና ግብ ነው፡፡ አርቆ ማለም ውጤታማ ያደርጋል፡፡ እኔ አሁን ደረጃ ላይ የደረስኩት ትልቅ ካፒታል ኖሮኝ ሳይሆን ዓላማና ግብ ይዤ በመነሳቴ ነው ቀስ በቀስ ነው እዚህ የደረስኩት፡፡ እንደነገርኩህ መጀመርያ የአንድ ወርቅ ቤት ተላላኪ ነበርኩ፡፡ ያገኘኋትን ሳንቲም በመቆጠብ የራሴን ወርቅ ቤት ከፈትኩኝ፡፡ በራሴ ወርቅ ቤት ሠርቼ ያገኘኋትን ይዤ ወደ እርሻ ገባሁ፡፡ አሁን እርሻውንም ሳላቆም፣ መላክ፣ ማስመጣት ሥራ ላይ ደረስኩ ማለት ነው፡፡ አሁን ላይ ግን ጥሩ ደረጃ ላይ ነኝ ብዬ አስባለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- በተሰማሩበት የእርሻ፣ ላኪነትና አስመጪነት ሥራ ላይ ለአገሪቱም የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ላይ ነዎት፡፡ ከመንግሥት የሚደረግልዎት ድጋፍ አለ?

አቶ ይትባረክ፡- መንግሥት በኤክስፖርት ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ድጋፍ ያደርጋል፡፡ አንዳንድ የቢሮክራሲ ችግሮች የሚያጋጥሙ ቢሆንም፣ ጥሩ ድጋፍ አለ፡፡ በሁሉም ባንኮች በኩል ኤክስፖርትን ለማበረታታት ብድር ይሰጣል፡፡ የምንፈልገውን ያህል ይሰጡናል፡፡ ይህ በጣም አበረታች ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሁሉም ነገር አልጋ ባልጋ ሊሆን ስለማይችል፣ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ቢነግሩን?

አቶ ይትባረክ፡- ሥራ ሊያደናቅፉ የሚችሉ የቢሮክራሲ ችግሮች አሉ፡፡ ባንክ በምንፈልገው መጠን ብድር የሚፈቅድ ቢሆንም ችግሮች የሉም ማለት አይደለም፡፡ ጥቃቅን ነገር ግን በቀላሉ ሊፈቱ የሚችሉ የቢሮክራሲ ችግሮች አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩም ሆኑ መንግሥት የተሻለ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲኖር ምን ማድረግ አለባቸው?

አቶ ይትባረክ፡- የንግድ የሥራ ዘርፍ የራሱ የሆነ አሠራር፣ ሥርዓትና አፈጻጸም አለው፡፡ ማንም ዝም ብሎ ዘው ብሎ የሚገባበት አይደለም፡፡ ዝም ብሎ በስሜት ቢገባም ውጤታማ አይሆንም፡፡ አንድ ሰው ወደ ንግድ ዓለም ከመሰማራቱ በፊት፣ ግቡ ምን መሆን እንዳለበት አርቆ ማሰብ አለበት፡፡ ግብ ማስቀመጥ አለበት፡፡ ግቡን ለማሳካት ቆርጦ ከተነሳና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት አስፈላጊውን ትብብርና እገዛ ካደረጉለት ውጤታማ የማይሆንበት ምክንያት የለም፡፡ ዋናው በዕቅድና በግብ መነሳት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ መንግሥት በየዘርፉ ለተሰማሩና ውጤታማ ለሆኑ ነጋዴዎች በተለይም በላኪነትና አስመጪነት የሥራ ዘርፍ ለተሰማሩ ባለሀብቶች የሚያዘጋጃቸውን የዋንጫና የሠርተፊኬት ሽልማቶች በተከታታይ ዓመታት ከሚወስዱ ባለሀብቶች አንዱ ነዎት፡፡ ለዚህ ተደጋጋሚ ሽልማት መብቃትዎ የተለየ ሚስጥር ይኖረው ይሆን?

አቶ ይትባረክ፡- አዎ ተሸላሚዎች ነን፡፡ እስካሁን በዘርፉ ከተሰማራንበት ጊዜ አንስቶ ከአንደኛ እስከ አራተኛ እየወጣን እየተሸለምን ነው፡፡ በተለይም የምንወስደውን ብድር በአግባቡ በመጠቀምና በመመለስ ታማኝነትን በማትረፋችን መንግሥት በየዓመቱ ይሸልመናል፡፡ የአገሪቱ ፕሬዚዳንቶችና ጠቅላይ ሚኒስትሮችን ጨምሮ በትላልቅ ተቋማት ተሸልመናል፡፡ የተለየ ሚስጥር ኖሮት ሳይሆን ሥራችንን በአግባቡና በጥረት ሠርተን የሚፈለግብንን አስተዋጽኦ ለአገራችን በማበርከታችንና ሌሎች እኛን እያዩ ተመሳሳይ እንቅስቃሴ በማድረጋቸው አርአያ ስለሆንን ይመስለኛል፡፡ ከመንግሥት ተቋማት በዋናነት ሸላሚያችን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው፡፡ ባንኩ ከፍተኛ የሆነ ድጋፍ ያደርግልናል፡፡ እንዲያውም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባይኖር ኖሮ ኤክስፖርት ማድረግም የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለተለያዩ ድርጅቶችም ያበድራል፣ ያማክራል፣ ችግር በሚያጋጥምበት ጊዜ በመወያየትና በመነጋገር የሚፈታ ትልቅ ባንክ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሌሎች በላኪነት የተሰማሩ ነጋዴዎች በማይልኩበት አገር ደቡብ ኮሪያ ብቸኛ ላኪ መሆንዎን ነግረውኛል፡፡ ለምንድነው ሌሎች የማይልኩት?

አቶ ይትባረክ፡- ይህንን ነገር ከመጀመርያው ጀምሮ ልነግርህ እፈልጋሁ፡፡ ወደ ጃፓን የሚላከው የቅባት እህል ችግር ገጥሞት ነበር፡፡ ችግሩ የተከሰተው በቅባት እህል እርሻ ላይ አርሶ አደሩ ዲዲቲ በመጠቀሙ ነው፡፡ ጃፓኖች ደግሞ እንኳን ዲዲቲን ተጠቅመህ ቀርቶ ከዲዲቲ በታች የሆኑና ጉዳት የሌላቸውን ኬሚካሎች ስትጠቀም መቀበልና መጠቀም አይፈልጉም፡፡ በዚህ ምክንያት (ሰሊጥ አንገዛም) ብለው ነበር፡፡ በወቅቱ እኛ ያደረግነው፣ አርሶ አደሩ ዲዲቲን እንዳይጠቀም መመካከር ነበር፡፡ ይህንን ያደረገው የእኛ ድርጅት ዋርካ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ብቻ ነው፡፡ አርሶ አደሩ ዲዲቲን ትቶ ሌሎች ጉዳት የሌላቸውን አረምና ተባይ ማጥፊያ እንዲጠቀም ዘመናዊ መርጫ ገዝተን የቅባት እህል ማምረት ላይ ለተሰማሩ አርሶ አደሮች በነፃ ሰጠን፡፡ በመርጫ መሣሪያው ላይ ዲዲቲ አንጠቀምም ብለን በመለጠፍ እንዳይጠቀሙ አደረግን፡፡ ከዛ በኋላ ምርታችንን የሚቀበሉ የጃፓን ነጋዴዎችን ወደ ኢትዮጵያ አምጥተን ዲዲቲ የሚባል ኬሚካል እንደማንጠቀም አሳይተናቸው እንዲቀበሉን አድርገናል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በጃፓን ከፍተኛ የቅባት እህል ገበያ አለን፡፡ በተሻለ ዋጋ ይገዙናል፡፡ እምነትም አላቸው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ እኛ ብቸኛ ላኪ የሆንበት ደቡብ ኮሪያ ነው፡፡ ደቡብ ኮሪያዎች ሰሊጥ በከፍተኛ ደረጃ ይገዛሉ፡፡ ከእኛ ድርጅት በስተቀር ሌሎች አይልኩም፡፡ በአውሮፓውያን ነጋዴዎች በኩል የኢትዮጵያን ምርት ወደ ደቡብ ኮሪያ መላክ ይቻላል፡፡ ከኢትዮጵያ ወደ ደቡብ ኮሪያ ለመላክ ግን ከፍተኛ የሆነ ሥራ ይጠይቃል፡፡ ምክንያቱም አሉ ከተባሉ ትልልቅ የዓለም አቅራቢዎች ጋር ነው የምንወዳደረው፡፡ ከፓኪስታን፣ ከህንድና ሌሎች አገሮች ጋር ነው የምንወዳደረው፡፡ አስቸጋሪ ስለሆነ ከእኛ በስተቀር ወደ ደቡብ ኮሪያ ሌላ የሚልክ የለም፡፡ በነገራችን ላይ በየጊዜው የየአገሮቹን ተቀባይ ነጋዴዎች ወደ ኢትዮጽያ እያመጣን የምርታችንን ሁኔታ እናስጎበኛለን፡፡ ይህንን በማድረጋችን በድርጅታችን ላይ ትልቅ አመኔታ አላቸው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ማለት ይቻላል ድርጅታችን ተዓማኒ ነው፡፡ በሌሎች አገሮች የኤክስፖርት ሥራ ላይ እኛን ጨምሮ ብዙ ነጋዴዎች የሚሳተፉ ቢሆንም፣ በደቡብ ኮሪያ ግን ከኢትዮጵያ እኛ ብቸኛ ላኪ ነን፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ደቡብ ኮሪያ ምን ያህል ቶን ሰሊጥ ትልካላችሁ?

አቶ ይትባረክ፡- በዓመት አምስት ሺሕ ቶን እንልካለን፡፡ አልፎ አልፎ ኑግ ቢኖርም በብዛት የምንልከው ሰሊጥ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የእርሻ መሬት የወሰዱት በትግራይ ክልል ሁመራ ላይ መሆኑን ነግረውኛል፡፡ በአካባቢው ማኅበረሰብ ያለው ተቀባይነትና የሥራ ዕድል ፈጠራ ምን ይመስላል?

አቶ ይትባረክ፡- መጀመርያ መሬቱን በሚመለከት ላስረዳህ፡፡ በአንድ መሬት ላይ በተደጋጋሚ አንድ ዓይነት ዘር መጠቀም ምርታማነቱን ይቀንሰዋል፡፡ በአካባቢው አልፎ አልፎ ጥጥ ይበቅላል እንጂ አብዛኛው ምርት ሰሊጥና ማሽላ ነው፡፡ እኛ ግን ሌላ ዘር መዘራት መቻል አለመቻሉን አጥንተን፣ ማሾ (ምስርን የሚተካ) የህንድ ሰብል ዘርተን እንዲበቅል አድርገናል፡፡ የሚገርመው ነገር ከማሾ በኋላ ሰሊጥ ስንዘራ በእጥፍ ደረጃ ምርቱ ይጨምራል፡፡ ይህ የሚያሳየው መሬት አንድ ዘር ዘርተህበት ሌላ ስትቀይርለት እንደሚታደስ ነው፡፡ ማሾ ልክ እኛ አገር ምስርን እንደምንጠቀምበት ህንድ፣ ፓኪስታንና ሌሎች የእስያ አገሮችም የሚጠቀሙበት የጥራጥሬ ዘር ነው፡፡ በነገራችን ላይ ማሾ ምስር የሚሰጠውን ጥቅም ይሰጣል፡፡ ከህንድ የተገኘ የጥራጥሬ ዘር ቢሆንም፣ በአሁኑ ጊዜ በብዙ አገሮች ተለምዷል፡፡ እየበቀለም ነው፡፡ በአገራችንም በተለያዩ አካባቢዎች እየበቀለ በመሆኑ ወደፊት ወደ ውጭ ይላካል የሚል እምነት አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- በሁመራ እርሻችሁ ላይ ለምን ያህል የአካባቢው ተወላጆች የሥራ ዕድል ፈጥራችኋል?

አቶ ይትባረክ፡- እርሻው ተጀምሮ ምርቱ እስከሚደርስ ድረስ ብዙ ሰው በሥራው ላይ ይሰማራል፡፡ ማረስ አለ፣ አረም አለ፣ አጨዳና መሰብሰብን ጨምረህ በአንድ ጊዜ እስከ 500 ሰው የሥራ ዕድል ያገኛል፡፡ በመተማ፣ አዲስ አበባ፣ ሁመራ፣ ደሴና በሌሎችም ቦታዎች ማበጠሪያ ስላለን ለብዙ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥረናል፡፡

ሪፖርተር፡- ከውጭ የሚገጣጠሙ ክፍሎችን በማምጣት ሞተር ሳይክል እየገጣጠማችሁ ታከፋፍላላችሁ፡፡ ወደ ጎረቤት አገርም ኤክስፖርት ለማድረግ ውል እየፈጸማችሁ መሆኑን ነግረውኛል፡፡ የምትገጣጥሙት የት ነው?

አቶ ይትባረክ፡- በኦሮሚያ ልዩ ዞን ገላን የኢንዱስትሪ ቦታ አለን፡፡ በዛ ቦታ ላይ ዘመናዊ ማበጠሪያ ማሽን ተክለናል፡፡ ጎን ለጎን በገነባነው ሕንፃ ሥር ሰፊና ዘመናዊ የመገጣጠሚያ ማሽኖችን ተክለናል፡፡ የውጭ ዜጎችን ከህንድ አስመጥተን የእኛን ዜጎች እያሠለጠንን ነው፡፡ ከትንሽ ጊዜ በኋላ የራሳችን ዜጎች የመገጣጠም ሥራውን ይረከባሉ፡፡ አሁን 100 ባለሙያዎችን ቀጥረን እያሠለጠንን ነው፡፡ በራስ ኃይል ሙሉ በሙሉ ለመተካት ጠንክረን እየሠራን ነው፡፡ አገር ውስጥ ብቻ ለማከፋፈል ሳይሆን በቀጣይ የሞተር ሳይክልን ምርት ሙሉ በሙሉ በአገራችን አምርተን ኤክስፖርት ለማድረግ እየተጋን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የሞተር ክፍሎችን ከየት አገር ነው የምታመጡት?

አቶ ይትባረክ፡- የምናስመጣው ከህንድ ነው፡፡ ባጃጅ የሚባል በዓለም የተመሰከረለት ሞተር ሳይክል ነው፡፡ በዋጋም ሆነ በጥንካሬያቸው የተመሰከረለት ሞተር ሳይክል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የተለያዩ የንግድ ዕቃዎችን ከተለያዩ አገሮች ለማስመጣት ትልቁ ተግዳሮት የውጭ ምንዛሪ መሆኑ ይነገራል፡፡ እናንተ ይህ ተግዳሮት አልገጠማችሁም?

አቶ ይትባረክ፡- የውጭ ምንዛሪ የአንድ ወይም የጥቂቶች ችግር ብቻ ሳይሆን የሁሉም ችግር ነው፡፡ ይህ ችግር ቢኖርም መፍታት ያለብን እኛ ነን፡፡ ማለትም ወደ ውጪ የምንልከውን ምርት በብዛትና በጥራት በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት አለብን፡፡ እስካሁን ችግሩ አለ፡፡ ግን ያው ያለውን እያብቃቃን እየተጠቀምን እንጂ በበቂ ሁኔታ አናገኝም፡፡ ምናልባት ወደፊት ይፈታል የሚል ግምት አለን፡፡ በነገራችን ላይ ለስኬታችን ትልቁ ሚስጥር የዋርካ ሠራተኞች ብቃት ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ሠራተኞቼን ላመሰግን እወዳለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ዋርካ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ስንት ሠራተኞች አሉት?

አቶ ይትባረክ፡- በአጠቃላይ 300 ቋሚ ሠራተኞች አሉት፡፡ በጊዜያዊ ደግሞ ከ250 በላይ አሉት፡፡ ይህ በአዲስ አበባ ብቻ ነው፡፡ በእርሻና በማበጠሪያዎች አካባቢ ቋሚ ባይሆኑም ከዓመት ዓመት ሥራ ላይ የሚገኙ ከ500 በላይ ሠራተኞች አሉት፡፡

ሪፖርተር፡- በቀጣይ አሁን ከምትሠሩት በተጨማሪ ምን ለመሥራት አቅዳችኋል?

አቶ ይትባረክ፡- በቀጣይ በምግብ ማቀነባበር ሥራ ላይ የመግባት ዕቅድ አለን፡፡ የቅባት እህሎችንና ጥራጥሬን ማቀነባበር ሥራ ላይ ለመሰማራት እንፈልጋለን፡፡ በተለይ መንግሥት በአሁኑ ጊዜ በገነባቸውና በሚገነባቸው የኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ገብተን መሥራት እንፈልጋለን፡፡ ልነግርህ የምፈልገው ነገር ቢኖር፣ የመንግሥት ፍላጎት ነጋዴው በኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ገብቶ እንዲሠራ ነው፡፡ አንድን ምርት በጥሬው ከማቅረብ ይልቅ ተቀነባብሮና ጣጣውን ጨርሶ እንዲቀርብ ይፈለጋል፡፡ የተሻለ ዋጋም ያስገኛል፡፡ ነገር ግን ለውጭ አገሮች ጣጣውን የጨረሰና የተቀነባበረ ምርት መላክ አስቸጋሪ ነው፡፡ ምክንያቱም በውጭ የሚገኙ ተቀባይ ነጋዴዎችና አገሮች ትልልቅ ፋብሪካዎች ገንብተውና የራሳቸውን የሰው ኃይል በማደራጀት የሚቀበሉትን ጥሬ ዕቃ አቀነባብረውና ጣጣውን ጨርሰው የሚሸጡ ናቸው፡፡ እኛም ተወዳዳሪ ለመሆን ቀድመን መሥራት ያለብን ነገር አለ፡፡ ይህንን ፈርተን ግን አንተወውም፡፡ ቀስ በቀስ ወደዛ መግባት አለብን፡፡ ከዛ በፊት ግን መንግሥት ከተቀባይ አገሮች መንግሥታት ጋር የስምምነት ውል መፈጸም አለበት፡፡ ለእኛ ምርቶች የተለያዩ ጥቅሞችን ወይም ማበረታቻዎችን የሚያገኙበት መንገድ መፈጠር አለበት፡፡ ከታክስ ነፃ ማስገባት የሚቻልበትን ሁኔታዎች ማመቻቸትና በአገሮቹ ገብተውና ተወዳድረው እንዲሸጡ የሚቻልበት ስምምነት መፈጸም አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ ከተደረገ የታሰበውን የተቀነባበረ ምርት ይዞ ተወዳዳሪ ሆኖ መሸጥ ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ከሁለትና ሦስት ዓመታት ወዲህ በተለያዩ አካባቢዎች ሁከቶችና ተቃውሞዎች እየታዩ ነው፡፡ በንግድ እንቅስቃሴ ላይ የሚፈጥረውን ተፅዕኖ እንዴት ያዩታል?

አቶ ይትባረክ፡- ትክክል ነው፡፡ በአገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚታዩ አለመረጋጋቶችና ችግሮች አሉ፡፡ በእርግጥ ጊዜያዊ ናቸው፡፡ የሚያልፉ እንጂ ዘላቂ ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ ሕዝብ ነው፡፡ የሚለያይበት ምክንያት የለም፤ ተለያይቶም አያውቅም፡፡ ወደድንም ጠላንም መጓዝ ያለብን አንድ ላይ ሆነን ነው፡፡ ችግሮቻችንን ራሳችን ፈትተን በአንድነት እንድንኖር በአንድነት መቀጠል ብቸኛው አማራጫችን ነው፡፡ እስካሁን ግን በሥራችን ላይ የተፈጠረ ተፅዕኖ የለም፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የብድርና ቁጠባ ኅብረት ሥራ ማኅበራትን ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ ማጠናከር ያስፈልጋል›› አቶ ፍፁም አብርሃ፣ የአሚጎስ ብድርና ቁጠባ ኅብረት ሥራ ማኅበር መሥራችና ሥራ አስኪያጅ

አሚጎስ የብድርና ቁጠባ ኅብረት ሥራ ማኅበር ከተመሠረተ አሥራ ሁለት ዓመታት ሆኖታል፡፡ በእነዚህ ዓመታት 8,500 አባላትን ማፍራት ችሏል፡፡ አሚጎስ ስለተመሠረተበት ዓላማ፣ እያከናወናቸው ስለሚገኙ ተግባራት፣ የብድርና...

ከደብረ ብርሃን የሚጣራው ሀበሻ የአረጋውያንና የምስኪኖች መርጃ

ሀበሻ የአረጋውያንና የምስኪኖች መርጃ ልማት ድርጅት መቀመጫውን ደብረብርሃን በማድረግ ጧሪ የሌላቸውን ችግረኞች እየረዳ ይገኛል፡፡ በነፍሰሄር አርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም እና በአቶ ዮርዳኖስ ፍቃዱ ተክለማርያም በ2008...

ለጡት ካንሰር ሕሙማን የቆሙት ነርስ

ዘውድነሽ ወልዴ (ሲስተር) የጽናት የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሕክምና ኮሌጅ የካንሰር ታካሚዎች ድጋፍ ማኅበር መሥራችና ፕሬዚዳንት እንዲሁም የሕክምና ኮሌጁ የሕፃናት ሕክምና ክፍል ነርስ ናቸው፡፡ የአንደኛ...