Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርክቡር ከንቲባው የቤት ጉዳይ ላይ መፍትሔ ይስጡን

ክቡር ከንቲባው የቤት ጉዳይ ላይ መፍትሔ ይስጡን

ቀን:

የጨረቃ ቤቶችን ግማሹን ሕጋዊ እያደረጉ ግማሹን ማፍረሱ አነጋጋሪም አስስገራሚም ሆኗል፡፡ ቀድመው በያዙት ቤት ተጨማሪ የቤት ኪራይ ገቢ የነበራቸውንና ለዓመታት ከቤት ኪራይ ጫና ያመለጡትን ሰዎች ሕጋዊ አድርጐ በአንፃሩ አዲስ የሠሩትን ማፍረሱ እንዲሁም በአዲስ አበባ የመሬት ጥበት አለብን በማለት ለልማት ተነሺዎች የገዛ ይዞታቸው የሆነ 700 እና 800 ካሬ ሜትር ቦታ በመንግሥት መወሰዱ ሳያንስ በምትኩ ከ500 ካሬ ሜትር በላይ አንሰጥም እየተባለ፣ ሕጋዊ ለተደረጉ አካላት በሊዝ መነሻ ሒሳብ ከ75 እስከ 150 ካሬ ሜትር ብቻ እንዲሆን መደረጉ በጠቅላላው አሠራሩን አድሎአዊ አድርጐታል፡፡

ሕገወጥ የሆነ ሁሉ በመሆኑ እኩል መታየት ሲገባው በጊዜ ገደብ ከፋፍሎ ከዚህ ጀምሮ ያለው ሕጋዊ ነው ማለቱ፣ ሕግ አክብረው ሕገወጥ ላለመሆን ዋጋ ሲወደድባቸውም ሠፈር እየቀያየሩ ቅናሽ የቤት ኪራይ ፍለጋ ቤተሰብ ይዘው የሚንከራተቱ፣ በቤት ኪራይ የሚጠበሱ፣ ሕገወጥ ከሚባሉት ሰዎች ሳይቀር ቤቶችን ተከራይተው የሚኖሩ ዜጐችን ሞራል አይነካም ወይ? ሕግን ማክበር ለድህነትና ችግር የሚያጋልጥ ዋጋ ቢስ ሰብዕና እንደሆነ በመቁጠር እኛም የዕድሉ ተጠቃሚ እንሆናለን በማለት እኔ በምኖርበት ሠፈር የገበሬ ቦታ በመንደር ውል እየተዋዋሉ የ1994፣ የ1995 እና የ1996 ይዞታ እንደሆነ አድርገው በመስማማት ቦታ የሚገዙ፣ ከደንብ ማስከበርና ከቀበሌ ሰዎች ጋር በመመሳጠር በአንድ ሌሊት ቤት እየሠሩ መኖር የጀመሩ ወገኖች አሉ፡፡ የከተማ አስተዳደሩ የውሳኔና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ዜጐች በአገራቸው ሀብት እኩል ተጠቃሚ እንዳይሆኑ እያደረገ ነው፡፡

ከዚህ ባሻገር መንግሥት በኮንዶሚኒየም ቤት ዕጣ አወጣጥ ላይ በከተማዋ ከ15 እስከ 30 ዓመታት የኖሩና ቤተሰብ ይዘው በቤት ኪራይ የሚንከራተቱ፣ ኢኮኖሚያቸው ለረጅም ዓመታት የተጐዳ ነዋሪዎች ከሁለት ዓመት ያነሰ ጊዜ በአዲስ አበባ የኖሩትንም እኩል ዕጣ ውስጥ ማስገባቱ ኢፍትሐዊ ሆኖ የሚታይ ነው፡፡

በሌላ ጐኑ መንግሥት ቀጥሮ ለሚያሠራቸው ሠራተኞች ተገቢ የደመወዝ ማሻሻያና ጭማሪ ማድረግ ሲገባው በርካታ ችግረኞች ተስፋ አድርገው ከሚጠብቁት የኮንዶሚኒየም ቤት ዕጣ ቅድሚያውን ለመንግሥት ሠራተኞች፣ ለመምህራን፣ ለሐኪሞች ወዘተ እየተባለ መቀናነሱ፣ ከእነዚህ ወገኖች ያነሰ ኑሮ የሚኖሩና ለከተማዋ ዕድገት የሚለፉ ብዙኃን የከተማዋ ነዋሪዎች፣ የግል ድርጅት ተቀጣሪዎች፣ የግል ሥራ ተወዳዳሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ እየፈጠረ ነው፡፡ ከልማት ተነሺዎች ከፍተኛ ቁጥር ጋር ተዳምሮ የኮንዶሚኒየም ቤት ‹‹ላም አለኝ በሰማይ ወተቷን አላይ›› የሚያስብል አሠራር እንደሆነ በማሰብ፣ የቤት ቁጠባቸውን እንዲያቋርጡ ምክንያት በመምጣቱ የአዲስ አበባ ነዋሪን እያሳዘነ ያለ ተግባር ነው፡፡

በመጨረሻም በአዲስ አበባ ዙሪያ ያለ በቂ ካሳ የተፈናቀሉ ገበሬዎችን የሚያቋቁም ኤጀንሲ ማዋቀሩ መንግሥትን ቢያስመሰግነውም፣ በከተማዋ የጣራና የግድግዳ ካሳ እየተባለ የሚሰጠው ድርጐ አጥር ለማያሳጥር እንኳ የማይበቃ መሆኑ ሳያንስ፣ ከከተማ ውጪ መሬት ተሰጥቷቸው ከብሎኬትና ጭቃ ቤት ወደ ቆርቆሮና ላስቲክ ቤት የወረዱ፣ ኑሯቸው የተመሰቃቀለባቸው ዜጐችም ተመልካች ቢኖራቸው እንዴት ጥሩ ይሆን ነበር፡፡ ስለዚህ ከንቲባ ድሪባ ኩማ ለጠቃቀስኳቸው መሠረታዊ ችግሮችና ማኅበራዊ ቀውሶች ዕልባት ይፈልጉ ዘንድ እጠይቃለሁ፡፡

(በከተማ አስተዳደሩ ከተከፉ ዜጐች አንዱ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...